አሜሪካ የኢራንን ቅድመ ሁኔታዎች ከተቀበለች የሆርሙዝ ባሕረ ሰላጤ በሁለት ቀናት ውስጥ ሊከፈት ይችላል- አራግቺ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ አሜሪካ በቴህራን የቀረቡትን ቅድመ ሁኔታዎች ከተቀበለች ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ ያለው የሆርሙዝ ወሽመጥ በሁለት ቀናት ውስጥ እንደገና ሊከፈት ይችላል አሉ።
አራግቺ እንደገለፁት፣ ከኳታር አደራዳሪዎች ጋር የተደረጉ ውይይቶች የእቅዱን ማስፈጸሚያ ጊዜ ከአምስት ቀናት ወደ ሁለት ቀናት አሳጥረውታል።
ሚኒስትሩ አክለውም ቴህራን ከኢዝላማባድ ስምምነት በኋላ የተጣሉ ማዕቀቦች እንዲነሱ፣ በቀጠናው የሚገኙ የአሜሪካ ወታደራዊ ኃይሎች እንዲቀነሱ፣ ለነዳጅ ሽያጭ የተቀመጡ ገደቦች እንደገና እንዲከለሱ እና በኳታር የሚገኙትን ጨምሮ የታገዱ የኢራን ንብረቶች እንዲለቀቁ ትጠይቃለች።
ኢራን ከኦማን ጋር በተወያየችባቸው የመርከብ መጓጓዣ መስመሮች ላይ ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲሰጥላትም ትፈልጋለች።
አራግቺ እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ከተሟሉ በዋሽንግተንና በቴህራን መካከል በሌሎች እስካሁን ያልተፈቱ ጉዳዮች ላይ አዲስ ድርድር ለመጀመር መንገድ ይከፍታል ብለዋል።
ይህ ሃሳብ የቀረበው በባሕር ማጓጓዣና በኤነርጂ ገበያዎች ላይ ተጽእኖ ያሳደረውን ውጥረት ለመቀነስ የዲፕሎማሲ ጥረቶች በቀጠሉበት ወቅት ነው። የዓለም የነዳጅ ንግድ አንድ አምስተኛ የሚተላለፍበት የሆርሙዝ ወሽመጥ አሁንም ለዓለም አቀፍ የኃይል አቅርቦት ወሳኝ መተላለፊያ ሆኖ እያገለገለ ነው።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር የሚደረገው ድርድር “በጥሩ ሁኔታ እየሄደ” መሆኑን መናገራቸው ይታወሳል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በቅርቡ ባደረጉት ንግግር ደግሞ ትራምፕ ኢራን ላይ ጥቃት ለማድረስ ገና እንዳልወሰኑ ጠቁመዋል።
የኢራን ባለሥልጣናት በበኩላቸው አሜሪካ ጥቃት ከፈጸመች የከፋ የአጸፋ ምላሽ እንደሚሰጡ አስጠንቅቀዋል።


