የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በኦሮሚያ ክልል በምዕመናን ላይ የተፈጸመውን ግድያ አወገዘ

የፎቶው ባለመብት, EOTC TV
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፤ በቀድሞው የኦሮሚያ ክልል አደረጃጀት በአርሲ ዞን ሥር በሚገኙ ወረዳዎች የደረሰውን ጥቃት “በጽኑ እንደሚያወግዝ” አስታወቀ።
ጥቅምት 10 እና 14 ቀን 2019 ዓ. ም.፤ በመርቲ ወረዳ፣ አንጋዳ ቀበሌ፣ ጎራ ሲሊንጎ 14 ምዕመናን እና በሸርካ ወረዳ፣ ጠሬታ ጮሌ ቢርቦ 46 ምዕመናን “ግፍን በተሞላ ጭካኔ” መገደላቸውን ገልጿል።
ቅዳሜ ጥቅምት 14/2019 ዓ. ም. በሽርካ ወረዳ በተፈጸመው ጥቃት የተገደሉት "46 ሰዎች" በአካባቢው በሚገኘው ቤተ ክርስቲያን "በአንድ ጉድጓድ" መቀበራቸውን ሁለት ነዋሪዎች፣ ቀብሩ የተፈጸመበት ቤተ ክርስቲያን እና የወረዳው የቤተ ክርስቲያን ምንጮች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መገናኛ ብዙኃን በፌስቡክ ገጹ ላይ ዛሬ ሰኞ ጥቅምት 16 ቀን 2019 ዓ. ም. ባወጣው መግለጫ፤ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤን ጠቅሶ፤ የ20 ምዕመናን መኖሪያ ቤቶች ሙሉ በሙሉ መቃጠላቸውን አስታውቋል።
ከ20 በላይ የሚሆኑ ሰዎች “ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው” ሆስፒታል መግባታቸውን ከአካባቢው አገረ ስብከት ጽሕፈት ቤት ሪፖርት እንደደረሰው አመልክቷል። በዚህም የተሰማውን “ከፍተኛ ሐዘን” ገልጿል።
በአርሲ አገረ ስብከት እና በሌሎችም አካባቢዎች “ኦርቶዶክሳውያን ንጹኃን ልጆቻችን ላይ የሚፈጸመው እጅግ አሰቃቂና ዘግናኝ ጭፍጨፋ፣ መፈናቀል፣ የአካልና የንብረት ጉዳት ተከታታይነት ባለው ሁኔታ፣ ያለማቋረጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ” መጥቷል ሲልም አትቷል።
የንጹኃን ግድያ እንዲቆምም ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት “ኢ-ሰብዓዊ የሆነውን ተግባር በይፋ እንዲያወግዙ” ጠይቋል።
አክሎም “በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠውን በሕይወት የመኖርና በነጻነት የማምለክ መብትን እንዲያስከብሩልን” ሲል ጠይቋል።
ድርጊቱን የፈጸሙትን “ወንጀለኞች ለሕግ በማቅረብ የሕግ የበላይነትን ከማረጋገጥ በተጨማሪ እንዲህ ዓይነቱ አረመኔያዊ ተግባር ከእንግዲህ በኋላ እንዳይደገም አስፈላጊውን የሕግ ከለላ” እንዲሰጥ ሲኖዶሱ አሳስቧል።
ድርጊቱን “በሰብአዊ መብት ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው፣ የሃይማኖት ነፃነትና በሕይወት የመኖር ሕገ መንግሥታዊ መብትን የጣሰ፣ ከሃይማኖትም ሆነ ከተፈጥሮ ሕገ ሰብእና የወጣ፣ ተከባብሮ የመኖር ሀገራዊ ዕሴቶቻችንን የሚያጠፋ፣ ሊወገዝ የሚገባው ኢ-ሰብአዊ ድርጊት” ሲልም አውግዞታል።
በተጨማሪም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ከሚመለከታቸው የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን ጋር “እንዲወያይ” መወሰኑም ተገልጿል።
ችግሩን በዛላቂነት ለመፍታትም “ጥናት የሚያደርጉ አባቶችን፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እና የሕግ ባለሙያዎችን ያካተተ ኮሚቴ እንዲሰየም” መመሪያ መሰጠቱም ተመልክቷል።
የፀጥታ አካላት ችግሩ እስከሚፈታ ድረስ “አስፈላጊውን ጥበቃ እንዲያደርጉ” እንዲሁም “አደጋዎችን ማስቀረት የሚያስችል ሥራ እንዲሠሩ” የቅዱስ ሲኖዶሱ ምልአተ ጉባኤ አሳስቧል።







