ሌተናንት ጄነራል ታደሰ ወረደ እንዴት እና በማን እገዛ ከእስር አመለጡ?

 የቀድሞው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሌተናንት ጄነራል ታደሰ ወረደ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ለ15 ቀናት እስር ላይ የቆዩት የቀድሞው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሌተናንት ጄነራል ታደሰ ወረደ በህወሓት በሚመራው "የአካባቢው አስተዳደር ባለሥልጣናት እገዛ" ማምለጣቸውን ተናገሩ።

ሌተናንት ጄነራል ታደሰ ከቢቢሲ ትግርኛ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ስለ እስር ቆይታቸው እና እንዴት እንዳመለጡ አስረድተዋል።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት የክልሉን አስተዳደር ተቆጣጥሮ በነበረው ህወሓት ተይዘው ከመቀለ ሲወሰዱ 'ወደ ኤርትራ እንሻገራለን' የሚል ሀሳብ እንዳልነበራቸው ገልፀዋል።

"ጦርነቱን ድል አድርገው፣ ወይ አዲስ አበባ ይዘው አልያም ግማሽ አካባቢ ተጉዘው ሊያሳዩን ነበር ያቀዱት የመሰለኝ" ብለዋል።

በሁለት ሣምታት የእስር ቆይታቸው ከመቀለ አክሱም ከዚያም የኤርትራ ድንበር አቅራቢያ ወደምትገኘው ራማ እንደተወሰዱ አስተድተዋል። ራማ ሲወሰዱ ወደ ኤርትራ ተላልፈው ሊሰጡ እንደሚችሉ መጠራጠራቸውንም ገልፀዋል።

"እነሱ የፈለጉት ነገር እኛን ወደ ኤርትራ ማሻገር ነበር፡፡ ከመቀለ ጀምሮ በየአካባቢው ያየነው ነገር፣ እንደዛ ሊሆን እንደማይችል፣ የሆነ ጊዜ ነፃ እንደምንወጣ እገምት ነበር፣ እሱንም እጠብቅ ነበር፣ በመጨረሻም የሆነው እንደዛ ነው፣ ነፃ ወጥተናል" ብለዋል።

በራማ በፖሊስ ጥበቃ ሲደረግላቸው እንደነበር የተናገሩት ሌተናንት ጄነራሉ፣ የተፈጠረው "የፖለቲካ መከፋፈል" ነፃ ለመውጣታቸው ቁልፍ ምክንያት እንደሆነ ጠቅሰዋል።

ከእስር ያመለጡት በራማ ወረዳ አስተዳዳሪዎች እገዛ እንደሆነ ገልፀዋል። የወረዳው አስተዳዳሪ በቀድሞው የጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ቤተሰቦች አማካኝነት ከመከላከያ ሠራዊት ጋር ግንኙነት መፍጠሩ ለባለሥልጣናቱ መለቀቅ "ትልቅ እርምጃ" እንደሆነ ገልፀዋል።

ታሳሪዎቹን ወደ ኤርትራ የማሻገሩን ሀሳብ "የሚቀበለው ሰራዊት አልነበረም። በየአካባቢው የነበሩት አስተዳዳሪዎችም አልተቀበሉትም። የራሳችንም ጥበቃዎች አልተቀበሉትም" ሲሉ ነጻ የሚወጡበትን መንገድ በተመለከተ ራማ ከሚገኙ ባለሥልጣናት ጋር "መነጋገራቸውን" አስረድተዋል።

ሌተናንት ጄነራል ታደሰ፣ "የሻዕቢያ ሰዎች ወደ መረብ መጥተው እንዲጠብቁን አድርገው ነበር" ሲሉ ወደ ኤርትራ ሊወሰዱ ስለነበሩበት ቅፅበት ገልጸዋል። ነገር ግን በስም ያልጠቀሱት የወረዳው አስተዳዳሪ "አዘናግቶ" ከራማ እንዳስወጣቸው ገልፀዋል።

"ወደ ኤርትራ እንደሚያሻግሩን ጥርጣሬው እየበረታ ሲመጣ፣ መከላከያ ዓድዋ ደረሰ፡፡ ሽረ ከተማም ተያዘ፣ ከዛም የራሳቸው [የህውሓት] አደረጃጀትም መፍረስ ጀመረ፣ ራሳቸውም እዛው እያለን ወደ ኤርትራ መሻገር ጀምረው ስለነበር፣ ሌላ አማራጭ አልነበራቸውም" ሲሉ ሁኔታውን አስታውሰዋል።

"[የራማ ወረዳ አስተዳዳሪ] ከኤርትራ እኛን ለመውሰድ የመጡ የሻዕቢያ የፀጥታ ኃይሎች መረብ ላይ እንዲጠብቁ አደረጋቸው። 'ይዤላችሁ እመጣለሁ፣ እዛው ጠብቁ' ብሎ ነገራቸው።

ጥበቃዎቻችንንም ቦታ ቦታ አስያዛቸው። ከዛ በራሱ መኪና ይዞን ወጣ። ከራማ እንደወጣን ዳዕሮ ተክሊ የሚባል አካባቢ ስንደርስ ከመከላከያ ሰራዊት ጋር ተገናኘን" በማለት ያመለጡበትን መንገድ አብራርተዋል።

የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ከእስር ሲያመልጡ ከእርሳቸው እና ከሌሎች የቀድሞ ባለሥልጣናት በተጨማሪ ነጻ እንዲወጡ አመቻችተዋል የተባሉት አስተዳዳሪ ከእነ ሹፌራቸው አብረው ማምለጣቸውን ተናግረዋል።

 የቀድሞው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሌተናንት ጄነራል ታደሰ ወረደ
Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቢቢሲ የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ቃል በሌሎች ምንጮች አላረጋገጠም። ይሁን እንጂ አብረዋቸው ታስረው የነበሩት ኮሎኔል ተወልደ ገብረትንሳኤ ባለፈው ሳምንት ከቢቢሲ በነበራቸው ቆይታ "በፈቃዳቸው አልለቀቁንም" በማለት አምልጠው መውጣታቸውን ተናግረው ነበር።

ታደሰ ወረደን ጨምሮ አራት የቀድሞ ባለሥልጣናት ከህውሓት መሪዎች ለየቅል የሆነ አቋም በማንፀባረቃቸው በቁጥጥር ሥር ውለናል ብለው እንደሚያምኑ ገልፀዋል።

ሌ/ጄነራል ታደሰ ትግራይ ክልልን ለሁለተኛ ዘመን እንዲያስተዳድሩ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወዲያው እንደተሾሙ ነበር ከህውሓት ተቃውሞ የገጠማቸው።

ቀጥሎም ህወሓት ከሁለት ዓመቱ የትግራይ ጦርነት በፊት በተደረገው እና የፌደራል መንግሥት እውቅና በነሳው ምርጫ የተቋቋመው ምክር ቤት ወደ ሥራ እንዲመለስ ወስኗል።

ምክር ቤቱም የህወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤልን በፕሬዝዳንትነት የሾመ ሲሆን ይህንን ውሳኔ ተከትሎም ታደሰ ወረደ የክልሉ መሪነት ሥልጣናቸውን ተነጥቀዋል።

"የፕሬዝዳንትነቱን ሥልጣን በኃይል ከተቆጣጠሩት በኋላ ቤት ነበር የምቀመጠው። ከቤት ሁኜ ብዙ ሥራ እሰራ ነበር። ከቤት ውጪ እንዳልንቀሰቀስ ባይደረግም ሰላይ ያሰማራሉ፤ በአካባቢውም የደህንነት ሰዎች እንዲንቀሳቀሱ ያደርጋሉ፣ በጫና ውስጥ እንደቆየሁ አውቃለሁ" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ታደሰ ወረደ በሥልጣን ቆይታቸው አሁን ከመንግሥት ጋር ውጊያ ላይ ያሉት የትግራይ ኃይሎች እንዲጠናከሩ የሚያደርግ ተግባር ሲያከናውኑ ነበር የሚል ክስ ከሰሞኑ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ሲሰራጭ ነበር።

ስለዚህ ውንጀላ ከቢቢሲ ጥያቄ የቀረበላቸው ሌተናንት ጄነራል ታደሰ፣ ክሱን ውድቅ አድርገዋል።

"ከመጀመሪያው ጀምሮ ሠራዊት ማዘጋጃት ይቅርና፣ ጦርነቱን ለማስቀረት ነው የነበረው ጥረቴ ሁሉ። እንዴት ነው ሠራዊት የማዘጋጀው? ሲሉ ግልፅ አቋም እንደነበራቸው ገልፀዋል።

"ጦርነቱ ሊጀመር እንደሚችል የቆየ ግምት ነበረኝ። ዛሬ ነው ነገ የሚጀመረው ከሚለው በስተቀር፣ ጦርነት ሊቀሰቀስ እንደሚችል እገምት ነበር" ብለዋል።