በኦሮሚያ ክልል ሽርካ ወረዳ በተፈጸመ ጥቃት ሕጻናትን ጨምሮ "ከ40 በላይ ሰዎች" መገደላቸውን የዐይን እማኞች ተናገሩ

ታጣቂ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

በኦሮሚያ ክልል ሽርካ ወረዳ በሳምንት ልዩነት ውስጥ በተፈጸመ አዲስ ጥቃት ቢያንስ አምስት ሕጻናትን ጨምሮ ከ40 በላይ ሰዎች መገደላቸው ሦስት የዐይን እማኞች ለቢቢሲ ተናገሩ።

ትናንት ቅዳሜ ጥቅምት 14/2018 ዓ.ም. በተፈጸመው ጥቃት የተገደሉ "46 ሰዎች" በአካባቢው በሚገኘው ቤተ ክርስቲያን "በአንድ ጉድጓድ" መቀበራቸውን ሁለት ነዋሪዎች፣ ቀብሩ የተፈጸመበት ቤተ ክርስቲያን እና የወረዳው የቤተ ክርስቲያን ምንጮች ገልጸዋል።

"20 ገደማ" የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን አንድ ምንጭ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ስለ ጥቃቱ "መረጃው እንዳለው" እና "ክትትል እየተደረገበት ያለ ጉዳይ" መሆኑን አስታውቋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ምንጮች እንደሚናገሩት፤ በቀድሞው የኦሮሚያ ክልል አደረጃጀት በአርሲ ዞን ሥር በነበረው ሽርካ ወረዳ፣ ቢርቦና ጮሌ ቀበሌ ጥቃት የተከፈተው ከንጋት 11 ሰዓት ገደማ ጀምሮ ነው።

በትናንቱ ጥቃት የ75 ዓመት አዛውንት የሆኑ አባቱ የተገደሉበት አንድ ነዋሪ፣ "ሌሊት 11 ሰዓት ነው በአራት ማዕዘን ከበባ የተደረገብን። ምንም ባልተዘጋጀንበት እና በማናውቀው ሁኔታ ነው በአራቱም ማዕዘን ከበባ [ውስጥ] የጨመሩን" ሲል ሁኔታውን ገልጾታል።

የአካባቢው ነዋሪዎች "ሮንድ ጥበቃ" ያደርጉ እንደነበር የገለጹ ሌላ ነዋሪ ደግሞ፣ ሕዝቡ "ትንሽ በተዘናጋበት ሁኔታ ጠዋት ላይ፣ ከሮንድ ገብቶ ግማሹ እረፍት ባደረገበት ሰዓት ገብቶ ከባድ አደጋ ነው ያደረሰው" በማለት በድንገት ጥቃት መከፈቱን አስረድተዋል።

ጥቃቱ በተፈጸመበት ሰዓት ሚሊሻ ከነበሩት አባቱ ጋር "ሲከላከል" እንደነበር የገለጸ ሌላ የቀበሌው ነዋሪ በበኩሉ፣ "የመጀመሪያ የተኩስ ድምፅ የሰማሁት ተኝቼ ነው። በአቅማችን የያዝናትን ትጥቅ ሁላችንም ይዘን ተነሳን። ግን የእኛ እና የእነሱ አቅም የሚመጣጠን አልሆነም። በስናይፐር እና በብሬን ነው ሲታገሉን የቆዩት" ብሏል።

Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በዚህ ጥቃት የቀበሌ ሚሊሻ አባል የነበሩት አባቱ መገደላቸውን ተናግሯል። አዛውንት አባት ያጣው ሌላኛው ነዋሪ ደግሞ፣ የተገደሉት ከቤት ሸሽተው በአካባቢው ወደሚገኝ ቤተ ክርስቲያን ከደረሱ በኋላ መሆኑን ገልጿል።

ታጣቂዎቹ ጥይት እና ስለታማ መሣሪያዎችን መጠቀማቸውን የሚናገሩ አንድ የአካባቢው ነዋሪ፣ "ቤት ውስጥ እንዳሉ፣ ሸሽተው ቤት ውስጥ ሲያመልጡ፣ ቤት ውስጥ ነው ፍጅት ያደረጓቸው። ቤት ውስጥ በር ዘግተው [ያሉትን] በር እየሰበሩ [ጥቃት ፈጽመውባቸዋል]" ብለዋል።

ሦስት የቀበሌው ነዋሪዎች ለቢቢሲ እንደገለጹት፤ ንጋት ላይ በጀመረው ጥቃት በአጠቃላይ "46 ሰዎች" ተገድለዋል።

የሽርካ ወረዳ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ የሆኑ ምንጭ ደግሞ "በጮሌ ቀበሌ 43 ሰዎች ተገድለዋል" ብለዋል።

አንድ የአካባቢው ነዋሪ እንደተናገሩት "የአምስት፣ ሰባት እና አሥር ዓመት" ሕጻናትን ጨምሮ "ቢያንስ ሰባት አካባቢ" ልጆች ተገድለዋል። ሌላ ነዋሪ በበኩሉ የተገደሉት ሕጻናት ብዛት "ቢያንስ አምስት እንደሚሆን" ገልጿል።

ሕይወታቸው ካለፉት ነዋሪዎች ውስጥ አዛውንቶች እና ሴቶች እንደሚገኙበትም ነዋሪዎቹ አክለዋል።

በተጨማሪም "ከ20 በላይ ሰዎች ቆስለው ሆስፒታል" ውስጥ እንዳሉ በሽርካ ወረዳ የሚገኙ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ አስረድተዋል።

ሆስፒታል የገቡት ሰዎች "በጣም በከባዱ የተጎዱ ናቸው" ያሉት ምንጩ፤ ከእነዚህም መካከል ትናንት እንዲሁም ዛሬ ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎች እንደሚገኙበት አክለዋል። የተገደሉት ሰዎች ቁጥር "ሊጨምር እንደሚችልም" ስጋታቸውን ገልጸዋል።

አባቶቻቸው የተገደሉባቸው ሁለት ምንጮች እንደሚናገሩት፤ የተገደሉት ሰዎች በሙሉ ትናንት ቅዳሜ በቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን "በአንድ ጉድጓድ በጅምላ" ተቀብረዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የቤተ ክርስቲያን ምንጮችም ይህንኑ አረጋግጠዋል።

አንድ የቤተ ክርስቲያን ምንጭ እንዳሉት፤ በጅምላ ቀብር እንዲፈጸም የተደረገው "በእያንዳንዱ ተቆፍሮ ስለማይቻል፣ ጊዜም ስለሌለ፣ ጠላትም ደግሞ ላያስቀብረን ስለሚችል፣ ስጋቱ ቅርብ ላይ ስላለ" ነው።

የሽርካ ወረዳ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ የሆኑት የቢቢሲ ምንጭም የተገደሉት ሰዎች ትናንት "በአንድ መቃብር በጅምላ መቀበራቸውን" ተናግረዋል።

"ትናንት ነው የተቀበሩት፤ በጥይት ተፈረካክሶ [አስከሬናቸው] እንዴት ያድራል?" ብለዋል።

የተፈጸመውን ጥቃት "ጅምላ ፍጅት ነው" ሲሉ የገለጹት የቤተ ክርስቲያን አገልጋዩ፣ በአካባቢው በቅርብ ርቀት ያሉ የፀጥታ ኃይሎች በሥፍራው ቢደርሱም "ያገዱት ነገር የለም" ሲሉ ጥቃቱን ማስቆም አለመቻሉን ገልጸዋል።

"በቦታው ደርሰው ነበር፤ ምንም ማስጣል አልቻሉም፤ ሕዝቡ ከማለቅ አልዳነም" ብለዋል።

በሰዎች ላይ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ ዲገሉ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን "በከባድ መሣሪያ ተመትቷል" ያሉት አገልጋዩ፤ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ የሸሹ ሰዎች ላይም "ጥቃት መፈጸሙን" ገልጸዋል። "ቤተ ክርስቲያኑ ተዘርፏል፤ በሮቹ ተበሳስተዋል" ሲሉም ተናግረዋል።

ዛሬ ያለውን ሁኔታ ሲገልጹም "አሁንም ከባድ ነው ያለው። የተጨመረ ኃይል የለም። ያለው ነው ያለው። ለጊዜው ተረጋግቷል። ከሰዓት ምን ይሆናል፣ ነገር ምን ይሆናል? የሚለው የሚታወቅ ነገር የለም" ብለዋል። ጥቃቱን ተከትሎ በርካታ ነዋሪዎች ከአካባቢው መሸሻቸውንም አክለዋል።

ቢቢሲ ክስተቱን በተመለከተ ከኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ አስተያየት ለማግኘት ያደረገው የስልክ ጥሪ እና በመልዕክት ያቀረበው ጥያቄ ወዲያውኑ ምላሽ አላገኘም።

የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት፤ የኦሮሚያ ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ፣ ለደረሰው ጥቃት "ፅምዶን" ተጠያቂ አድርገዋል።

ይህ ቡድን "በሰሜን ኢትዮጵያ የደረሰበትን ከባድ ኪሳራ አቅጣጫ ለማስቀየር የብሔር እና የሃይማኖት ግጭት ለመፍጠር ያደረገው እንቅስቃሴ ከሽፏል" ማለታቸውም ተዘግቧል።

በሽርካ ወረዳ፣ ጮሌ እና ቢርቦ ቀበሌዎች በንጹኃን ዜጎች ላይ ላደረሰው የሕይወት እና የንብረት ጉዳት የክልሉ መንግሥት "የተሰማውን ሐዘን" ገልጸውም፤ "ክልሉ ይህንን ጥፋት በፈጸሙ አካላት ላይ የጀመረውን እርምጃ" እንደሚቀጥል አክለዋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጉዳዩ ክትትል እየተደረገበት መሆኑን ገልጿል።

በኮሚሽኑ የሰብአዊ መብቶች ክትትል እና ምርመራ ከፍተኛ ዳይሬክተር የሆኑት ሜቲ አቶምሳ "መረጃው አለን፤ ክትትል የምናደርግበት ጉዳይ ነው" ሲሉ ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል።

"ክትትል እየተደረገበት ያለ ጉዳይ ነው። አሁን እጃችን ላይ ያለ፣ የተጨበጠ ምንም ነገር የለም" ሲሉም አክለዋል።

የሽርካ ወረዳ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ የሆኑት የቢቢሲ ምንጭ የትናንቱን ጥቃት "እስካሁን ከተደረጉት ድርጊቶች ትልቁን ቁጥር የያዘ ነው" ሲሉ ገልጸውታል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መገናኛ ብዙኃን ትናንት በፌስቡክ ገጹ ላይ ትናንት ባወጣው መግለጫ፤ በሽርካ ወረዳ "በርካታ ክርስቲያኖች እየተገደሉ፣ ከቀዬአቸውና ከንብረታቸው እየተፈናቀሉ ይገኛሉ" ሲል የአርሲ አገረ ስብከት ማስታወቁን ጠቅሷል።

መግለጫው ጥቃቱ የተፈጸመባቸውን ቀበሌዎች፣ መቼ ጥቃቱ እንደተፈጸመ እንዲሁም ምን ያህል ሰዎች እንደተገደሉ እና እንደተጎዱ በዝርዝር ባይጠቅስም የአርሲ አገረ ስብከት "በአርሲ ሽርካ ክርስቲያኖች ላይ በታጠቁ ሃይሎች እየተፈጸመ ያለው ግድያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰ መጥቷል። ይህም ትልቅ ሀዘን ፈጥሮብናል" ማለቱን አትቷል።

መፍትሔ ለማግኘት በሚል ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ የአርሲ እና የሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል "ከሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ጋር በመሆን በተደጋጋሚ ውይይቶችን ሲያደርጉ" መቆየታቸውን የጠቀሰው መግለጫው፤ ሆኖም ግን ችግሩ "ሊቆም እንዳልቻለ" አመልክቷል።

"ከታች ካሉት የመንግሥት አካላት እስከ ሰላም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ጉዳዩን በተደጋጋሚ እያሳወቁ ይገኛሉ፤ እስካሁን ድረስ ግን የተሰጠ መፍትሔ የለም" ሲልም የአርሲ አገር ስብከት መግለጹን አክሏል።

በሽርካ ወረዳ የትናንቱ ዓይነት ጥቃት ሲፈጸም ይህ በአንድ ሳምንት ልዩነት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

ከጥቅምት 2 እስከ 7/2019 ዓ .ም. ባሉት ቀናት በሽርካ እና ሆንቆሎ ዋቤ ወረዳዎች በተፈጸሙ ተከታታይ ጥቃቶች ቢያንስ ስድስት ሰዎች መገደላቸውን እና ቢያንስ አምስት ሰዎች መታገታቸውን ነዋሪዎች ተናግረው ነበር።

ማክሰኞ ለረቡዕ አጥቢያ ላይ ደግሞ አጎራባች በሆነው መርቲ ወረዳ ጎራ ሲሊንጎ ቀበሌ ከ15 በላይ ሰዎች መገደላቸውን አንድ የወረዳው ምንጭ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) ሐምሌ 19/2018 ዓ. ም. ባወጣው የምርመራ ሪፖርት በአርሲ ዞን ውስጥ በአራት ዓመታት በተፈጸሙ ጥቃቶች "458 ሰዎች" ሲገደሉ፤ "38 ነዋሪዎች ያሉበት ሁኔታ አይታወቅም" ብሎ ነበር።

ከ2014 እስከ ግንቦት 24/2018 ዓ.ም. በዞኑ "የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን" የዳሰሰበት ሪፖርት "በአካባቢው የሚገኙ የታጠቁ ቡድኖች የአካባቢው ማኅበረሰብ ላይ ሃይማኖትን መሠረት ባደረገ መልኩ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ላይ" ጉዳት ማድረሳቸውን ያትታል።

የኢሰመጉ ባለሙያዎች ምርመራ ካካሄዱባቸው ዘጠኝ ወረዳዎች መካከል ሽርካ፣ መርቲ፣ ሆንቆሎ ዋቤ እና አሰኮ ይገኙበታል።

ያለፈው ዓመት ብሔራዊ ምርጫ በተካሄደበት ወቅት የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ‎ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባደረጉት ንግግር "ንጹኃንን እና የሃይማኖት ተቋማትን ዒላማ በማድረግ የተፈጸሙ ጥቃቶች ዓላማቸው አገሪቱ እንዳትረጋጋ እና ምርጫውን ለማደናቀፍ የተደረገ ዕቅድ ተከታይ ነው" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን ለጥቃቶቹ ተጠያቂ አድርገዋል። ታጣቂ ቡድኑ በተደጋጋሚ በሚፈጸሙ ግድያዎች፣ እገታዎች፣ ማፈናቀሎች እና የንብረት ውድመቶች ቢወነጀልም ክሶቹን ያስተባብላል።

በአርሲ ዞን ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታዩች በተጨማሪ ሙስሊሞች ላይም ጥቃቶች መድረሳቸው ከዚህ በፊት ተሰምቷል።

ቢቢሲ በተለያየ ጊዜ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ጥቃቶች "የሃይማኖት እና የብሔር" መልክ እንዳላቸው ገልጸዋል።

ከሰሞኑ ከተፈጸሙ ግድያዎች ጋር በተያያዘ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ፤ ጥቃቶቹ "ሃይማኖት ተኮር" መሆናቸውን ያምናሉ።