ኢራን ግጭቱ የሚቆመው “በድርድር ብቻ” እንደሆነ ገለጸች

የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ከአሜሪካ ጋር ያለው ግጭት የሚገታው “በድርድር መፍትሔ ላይ ሲደረስ ብቻ” መሆኑን ተናገሩ። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢራን በኩል የሆርሙዝ ወሽመጥን ለመክፈት የቀረበውን ዕቅድ ውድቅ አድርገዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. የሰሜን ኢትዮጵያው ግጭት መቀስቀሱ በተገለፀ ማግስት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ጂቡቲ አቀኑ

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከአውሮፕላን ሲወርዱ የጅቡቲው ፕሬዝደንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌ ተቀብለዋቸው በቀይ ምንጣፍ ላይ ሲራመዱ
    የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን የጂቡቲው ፕሬዝደንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌ ተቀብለዋቸዋል

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ወደ ጂቡቲ ማምራታቸውን ጽሕፈት ቤታቸው አስታወቀ።

    የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት በማኅበራዊ የትስስር ገፁ ከፎቶግራፎች ጋር ባጋራው አጭር መረጃ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ጅቡቲ ያመሩት ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት እንደሆነ ነው የገለፀው።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ጂቡቲ መሄዳቸው የተገለፀው በኢትዮጵያ መንግሥት ኃይሎች እና በትግራይ ታጣቂዎች መካከል ግጭት እንደ አዲስ መቀስቀሱ በይፋ በተገለፀ ማግስት ነው።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጂቡቲ ሲደርሱ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌ አቀባበል እንዳደረጉላቸው የጽሕፈት ቤታቸው መረጃ ያመለክታል።

    ሁለቱ መሪዎች በኢትዮጵያ እና በጅቡቲ መካከል ያለውን ኢኮኖሚያዊ ትስስር “ይበልጥ ለማጠናከር ያለመ የጋራ ፕሮጀክት ይፋ የሚሆንበትን መድረክ ይታደማሉ” ከማለት ውጭ ጽሕፈት ቤቱ ስለ ጉብኝቱ በዝርዝር አልገለፀም።

    ትናንት ረቡዕ መስከረም 13/2019 ዓ. ም. ማለዳ የትግራይ ኃይሎች መቀለ የሚገኘውን አውሮፕላን ማረፊያ መቆጣጠራቸው ከተገለጸ በኋላ በአፋር እና በአማራ ክልሎች በሚገኙ ቦታዎች ውጊያዎች መካሄዳቸው ተዘግቧል።

    ይሁን እንጂ ዳግም ስለተቀሰቀሰው ግጭት የፌዴራሉ መንግሥት እስካሁን በይፋ ያለው ነገር የለም።

  2. በትግራይ በረራ የተቋረጠባቸው አውሮፕላን ማረፊያዎች

    ካርታ

    ለወራት በውጥረት ውስጥ የነበረው የፌደራል መንግሥቱ እና የህወሓት መሪዎች ግንኙነት ወደ ይፋዊ ጦርነት ማምራቱ ተዘግቧል።

    ከማክሰኞ ሌሊት ጀምሮ በተያዩ ቦታዎች ላይ በተወሰዱ እርምጃዎች እና ግጭቶች የተቀሰቀሰው ጦርነት እንዳሳሰባቸው የተለያዩ አገራት፣ አህጉራዊ ድርጅቶች እና ተቋማት እየገለጹ ነው።

    ትግራይ ክልል ከአማራ እና ከአፋር ክልሎች ጋር በሚዋሰንባቸው አካባቢዎች ግጭቶች መቀስቀሳቸውን የህወሓት መሪዎች፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ እና የአፋር ክልል አረጋግጠዋል።

    በተጨማሪም የትግራይ ኃይሎች በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ዋነኛ የአውሮፕላን ማረፊያዎችን ተቆጣጥረዋል። በዚህም የመቀለ፣ የአክሱም እና የሽረ አውሮፕላን ማረፊያዎች ተዘግተው በረራዎች ተቋርጠዋል።

    እስካሁን የኢትዮጵያ መንግሥት ስለክስተቱ በይፋ ያለው ነገር ባይኖርም፣ ግጭቱ ዳግም ወደ ደም አፋሳሽ ጦርነት ሊሸጋገር ይችላል የሚል ስጋት ተፈጥሯል።

  3. ኦነግ የተመሠረተው ጥምረት ኦሮሚያን የጦር ሜዳ የሚያደርግ ነው አለ

    የኦነግ ሊቀ መንበር ዳውድ ኢብሳ
    የምስሉ መግለጫ, የኦነግ ሊቀ መንበር ዳውድ ኢብሳ

    የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በሰባት ታጣቂ ቡድኖች በቅርቡ መመሥረቱ የተገለጸው ጥምረት ኦሮሚያን የጦርነት ሜዳ የሚያደርግ ነው በማለት ተሳታፊዎች ውሳኔያቸውን እንዲያጤኑ ጥሪ አቅርቧል።

    በዳውድ ኢብሳ የሚመራው እና መቀመጫውን አዲስ አበባ ያደረገው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ባወጣው መገልጫ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (ኦነሠ) ተሳታፊ የሆነበትን ጥምረት ከመቃወሙ በተጨማሪ በዋናነት መንግሥት ኦሮሚያ ውስጥ ሀቀኛ ድርድር እንዲጀምር ጥሪ አቅርቧል።

    ኦነግ በመግለጫው "ጽምዶ" እና "ሰሜናዊ ጥምረት" በማለት የጠራው እንቅስቃሴ ዓላማው "ኦሮሚያን የጦርነት ሜዳ ማድረግ እና ኦሮሚያን በመቆጣጠር ሀብቷን ለመቀራመት ነው" በማለት ከስሷል።

    ኦነግ በመግለጫው የጠቀሰው በቅርቡ የተመሠረተውን የታጣቂ ቡድኖችን ጥምረት ስለመሆኑ በግልጽ ባያስቀምጥም ያቀረበው ክስ እና ጥሪ ትኩረቱ ጥምረቱ ላይ መሆኑን ያመለክታል።

    ጥምረቱን ከፈጠሩት ታጣቂ ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነው እና በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የትጥቅ እንቅስቃሴ እያደረገ ላለው ኦነሠ የሚመስል ጥሪም አቅርቧል።

    "ለኦሮሞ ሕዝብ እታገላለሁ እያሉ ከታሪካዊ ወራሪዎቻችን እና ጨቋኞች ጋር የቆሙ ታሪክ ፈጽሞ የማይረሳው ስህተት እየፈጸሙ በመሆናቸው መንገዳቸውን መለስ ብለው እንዲቃኙ" አሳስቧል።

    ጨምሮም ኦነግ የኦሮሞ ሕዝብ የፖለቲካ ልዩነት ሳያግደው የሌሎችን መብቶች ሳይጥስ ግዛቱን ለመከላከል በአንድነት እንዲቆምም ጥሪ አድርጓል።

    እንዲሁም የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እና የኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች የሕዝቡን መብት አደጋ ላይ በማይጥል ሁኔታ በአንድነት እንዲቆሙ አሳስቧል።

    በማጠቃለያው ላይም ጦርነት እና ወታደራዊ እርምጃ ዘላቂ መፍትሄ እንደማያመጣ በመጥቀስ ብቸኛው መፍትሄ ድርድር መሆኑን አመልክቷል።

  4. የአውሮፓ ኅብረት በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ውጥረት በአስቸኳይ እንዲረግብ ጥሪ አቀረበ

    የአውሮፓ ኅብረት

    በሰሜን ኢትዮጵያ በፍጥነት እየተባባሰ ያለው ሁኔታ እና ይህ ሁኔታ በሕዝቡ ላይ እያሳደረ ያለው ተጽዕኖ በጥልቅ እንደሚያሳስበው የአውሮፓ ኅብረት ገለፀ።

    በበርካታ አካባቢዎች ወታደራዊ እንቅስቃሴ ስለመኖራቸው የሚወጡ ዘገባዎች፣ እንዲሁም በትግራይ የሚገኙትን የመቀለ፣ የአክሱም እና የሽረ አየር ማረፊያዎች የህወሓት ኃይሎች መቆጣጠራቸውም አሳስቦኛል ሲል ኅብረቱ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

    ባለፉት ሳምንታትም በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የተፈጸሙ በርካታ የድሮን ጥቃቶችን በስጋት ሲከታተል እንደቆየም ጠቅሷል።

    “ውጥረቱን በአስቸኳይ ማርገብ ያስፈልጋል” ያለው የአውሮፓ ኅብረት፣ ሁለቱም አካላት ግጭትን በዘላቂነት ለማቆም ለተደረሰው ስምምነት ዳግም ቁርጠኝነታቸውን እንዲያሳዩ ጠይቋል። ለዚህም “ጊዜው አልረፈደም” ብሏል።

    ልዩነቶች ሊፈቱ የሚችሉት በውይይት ብቻ እንጂ በወታደራዊ እርምጃ እንዳልሆነም ገልጿል።

    የሲቪሎችን ደኅንነት መጠበቅን እና የሰብዓዊ ድጋፍ ሥራዎችን ገለልተኝነትና ነፃነት ማክበርን ጨምሮ የግጭቱ ተሳታፊዎች ዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግን እንዲያከብሩ ኅብረቱ አሳስቧል።

    የአውሮፓ ኅብረት በዚሁ መግለጫው፣ በሰብዓዊ ድጋፍ መኪኖች ላይ የሚደርሱጥቃቶችን እና የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽነትን የሚከለክል ማንኛውንም እርምጃ በጽኑ እንደሚያወግዝ አስታውቋል።

    ኅብረቱ ውጥረትን ለማርገብ የሚደረጉ ጥረቶችን፣ በአፍሪካ ኅብረት የሚመራውን የሽምግልና ሂደት እና ትርጉም ያለው ውይይትን ለመደገፍ ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጧል።

  5. ኢጋድ በሰሜን ኢትዮጵያ የተነሳው ግጭት እንዲገታ አሳሰበ

    የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ

    የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ውጥረት መባባሱ “እጅግ እንዳሳሰበው” አስታወቀ።

    እንደ አዲስ የተቀሰቀሰው ግጭት፣ የአውሮፕላን ማረፊያዎች በቁጥጥር ሥር መዋል እና የአየር ትራንስፖርት አግልግሎት መቋረጥ እንዳሰጋው ኢጋድ በድረ ገጹ ባወጣው መግለጫ አትቷል።

    ሁሉም ወገኖች “ግጭቱን እንዲያቆሙ እንዲሁም ውጥረቱን ከሚያባብሱ፣ የንጹኃንን ሕይወት ለአደጋ ከሚያጋልጡ እና የሰላም ጥረትን ከሚያሰናክሉ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ” ጠይቋል።

    የፕሪቶሪያ ስምምነት “ችግሮችን ለመፍታት እንዲውል” እና በስምምነቱ የተቀመጡት ግዴታዎች “ሙሉ በሙሉ እንዲከበሩ” ኢጋድ በመግለጫው አሳስቧል።

    ተዋጊዎቹ ሳይዘገይ ወደ ቀጥተኛ ውይይት እንዲመለሱ እና ጎረቤት አገራትም ግጭቱን ከማባባስ እንዲቆጠቡ ጠይቋል።

    በአፍሪካ ኅብረት አሸማጋይነት የተደረሰው የፕሪቶሪያ ስምምነት እንዲከበር የጠየቀው ኢጋድ “መጠነ ሰፊ ግጭት በኢትዮጵያ እና በቀጣናው የከፋ መዘዝ ያስከትላል” ሲልም አሳስቧል።

  6. የኢራን ፕሬዝዳንት አገራችው “እንደማትንበረከክ” በተመድ ጉባዔ ላይ ተናገሩ

    ማሱድ ፔዤሽኪያን

    የኢራኑ ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዤሽኪያን በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር አገራቸው “እንደማትንበረከክ” ተናገሩ።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በጉባዔው ላይ ባደረጉት ንግግር ኢራንን “ለማጥፋት” መዛታቸውን ተከትሎ የኢራኑ ፕሬዝዳንት በሰጡት ምላሽ ነው ይህንን የተናገሩት።

    አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጦርነት ከከፈቱ ሰባት ወራት ተቆጥረዋል።

    የኢራኑ ፕሬዝዳንት አገራቸው አሁንም ለዲፕሎማሲያዊ ንግግር ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል።

    ለትራምፕ ዛቻ በሰጡት ምላሽም “ማዕቀቦች ሲጣሉ፣ ጫናው ሲበረታ እና ግብዝነቱ ሲባባስ ኢራናውያን የበለጠ ራሳቸውን ይከላከላሉ” ብለዋል።

    አሜሪካ በባሕረ ሰላጤው የሚያልፉ የኢራን መርከቦች ላይ የጣለችውን ክልከላ ስታነሳ ቴህራን ከስምምነት እንደምትደርስ ፕሬዝዳንቱ ጨምረው ገልጸዋል።

    “ሁሉም አካል ከሆርሙዝ ወሽመጥ እየተጠቀመ እኛ ብቻ ክልከላ ሊጣልብን አይችልም” ብለዋል።

    የኢራን ፕሬዝዳንት በተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ንግግር ማድረግ ሲጀምሩ የአሜሪካ ልዑካን አዳራሹን ጥለው ወጥተዋል። እስካሁን ድረስ በፕሬዝዳንቱ ንግግር ላይ ከአሜሪካ በኩል አስተያየት አልተሰጠም።

    በኒው ዮርኩ ጉባዔ ላይ የኢራን ፕሬዝዳንት “የአሜሪካው ፕሬዝዳንት አሸባሪ ብሎናል፤ እኛ የሽብር ሰለባ ነን” ብለዋል።

  7. የኢራን ፕሬዝዳንት “ወራሪዎች እንዲጸጸቱ እናደርጋለን” ሲሉ በተመድ ጉባዔ ተናገሩ

    ማሱድ ፔዤሽኪያን

    በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዤሽኪያን የአገራቸው ፍላጎት የኒውክሌር የጦር መሣሪያ መገንባት እንዳልሆነ ገልጸው፤ የኒውክሌር ሳይንስ እና ሰላማዊ ቴክኖሎጂ የማበልጸግ እንቅስቃሴ ግን እንደማይገታ አስታውቀዋል።

    “ኢራን የኒውክሌር እውቀት በጥቂት አገራት ቁጥጥር ሥር መሆኑን አትቀበልም” ብለዋል።

    ኢራን የባሕር ላይ ደኅንነት ጥበቃን “ማንም እንዲነጥቃት እንደማትፈቅድም” በንግግራቸው ጠቅሰዋል።

    ጨምረውም “ራሳችንን ለመከላከል ከሆነ ጦርነት አንፈራም። የሰላም ድርድርም ገሸሽ አናደርግም” ብለዋል።

    ፕሬዝዳንቱ “ኃይል የምንፈልገው ራሳችንን ለመከላከል እንጂ ሌሎች አገራትን ለመውረር አይደለም” ሲሉም ተናግረዋል።

    “አቶሚክ ቦምቡ ያለው እስራኤል ነው፤ መርማሪዎቹ ግን ኢራን መጥተዋል” በማለትም በጉባዔው ላይ ንግግራቸውን አሰምተዋል።

    አክለውም “እስራኤል ትገድላለች፤ ማዕቀብ የሚጣለው ግን በኢራን ላይ ነው” ሲሉ ተችተዋል።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በጉባዔው ላይ ኢራንን “ለማጥፋት” መዛታቸው ይታወሳል።

    የኢራኑ ፕሬዝዳንት “ይሄ በኃይል ጫና የማሳደር ምልክት ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

    አገራቸው ላይ ጫና ለማሳደር ቢሞከርም “ኢራን ወራሪዎቿ እንዲጸጸቱ ታደርጋለች” በማለት ዝተዋል።

    በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን ሁኔታ በተመለከተም “የትኛውም አገር ብቻውን ደኅንነቱ የተጠበቀ አይሆንም። ደኅንነት የምንገነቫው በጋራ ነው፤ ደኅንነት ስናጣ የምንጋፈጠውም አብረን ነው” ብለዋል።

  8. በደቡብ አፍሪካ በመኖሪያ ቤት ላይ በተከፈተ ተኩስ 11 ሰዎች ተገደሉ

    ጥቃቱ የተፈፀመበት አካባቢ የቆሙ የፖሊስ መኪኖች

    በደቡብ አፍሪካ ደርባን ከተማ አቅራቢያ በመኖሪያ ሕንፃ ላይ በተከፈተ ተኩስ ቢያንስ 11 ሰዎች ተገደሉ።

    ማክሰኞ ምሽት ላይ መሣሪያ የታጠቁ ሰዎች በመኖሪያ ሕንጻው ላይ ከበባ በመፈፀም ነበር በ14 ሰዎች ላይ ተኩስ የከፈቱት። በዚህም 10 ሰዎች ወዲያውኑ ሲሞቱ አራቱ ወደ ሆስፒታል ከተወሰዱ በኋላ ሕይወታቸው ማለፉን ፖሊስ ገልጿል።

    ከሟቾቹ መካከል ነፍሰ ጡር ሴት እንደምትገኝበት ተገልጿል።

    የጥቃቱ ዓላማ ምን እንደሆነ እስካሁን አልታወቀም።

    አሁን ላይ ባለው መረጃ 13 ወንዶች እና ነፍሰ ጡር እንደሆነች የተገለጸ አንዲት ሴት በቤቱ ውስጥ በዝግጅት ላይ እየተዝናኑ ባሉበት ወቅት ሦስት ግለሰቦች ቦታው በመድረስ ተኩስ መክፈታቸውን ፖሊስ በመግለጫው አመልክቷል።

    በቦታው የነበረ የአካባቢው የቴሌቪዥን ጣቢያ የሆነው ኢኤንሲኤ ዘጋቢ ታጣቂዎቹ ከአካባቢው ከመሸሻቸው አስቀድሞ የተጎጂዎቹ ንብረት የሆነ ተሽከርካሪን በእሳት ማያያዛቸው ገልጿል።

    ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹን እያደንኩ ነው ብሏል።

    ደቡብ አፍሪካ በዓለም ላይ ከፍተኛ ግድያ ከሚፈፀምባቸው አገራት አንዷ ነች። የፖሊስ መረጃ እንደሚያሳየውም በቀን ከ60 በላይ ሰዎች ይገደላሉ።

  9. አሜሪካ እና ኢራን ከወራት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ “ ተስፋ ሰጭ” ውይይት ማድረጋቸው ተገለጸ

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር  አባስ አራግቺ

    የኢራን እና የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በኒው ዮርክ እየተካሄደ ባለው ጉባዔ ጎን ለጎን ተገናኝተው መወያየታቸው ተገለጸ።

    አገራቱ ከወራት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ንግግር ያደረጉት ፕሬዚደንት ትራምፕ ግጭቱ ካልተፈታ እስላማዊ ሪፐብሊኳን "እንደሚያጠፉ" በዛቱበት ተመሳሳይ ቀን ነው።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ የተኩስ አቁሙ ከፈረሰ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፉበት እና በኳታር አሸማጋይነት በተደረገው ድርድር የተደረሰ ስምምነት ስለመኖሩ አልተገለጸም።

    ዊትኮፍ የተለያዩ ውይይቶች ማድረጋቸውን እና የተደረጉትም ንግግሮች “ገንቢ እና ተስፋ ሰጭ” እንደሆኑ ተናግረዋል።

    “በውይይቶቹ ወቅት አደራዳሪዎቹ በሁለቱ ተወካዮች መካከል ያሉ ሃሳቦችን ወደኋላ እና ወደፊት እየተመላለሱ ሲያነሱ ነበር” በማለት ውይይቶቹ “ ተስፋ ሰጭ፣ ገንቢ እና ስኬታማ” እንደነበሩ ገልጸዋል።

    ፕሬዚደንት ትራምፕም በኋላ ላይ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ከኢራን ልዑካን ጋር “ለሦስት ሰዓታት የዘለቀ ውጤታማ ውይይት” ማድረጋቸውን ለጋዜጠኖች ተናግረዋል።

    የኢራን የመንግሥት ቴሌቪዥንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አባስ አራግቺ ከዊትኮፍ ጋር መነጋገራቸውን ዘግቧል።

    ኢርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጋይን ጠቅሶ እንደዘገበው ድርድሩ የተደረገው በኳታር አደራዳሪዎች አማካኝነት እንደሆነ ገልጿል።

    ኢራን አሜሪካ "የእብሪት ድርጊቷን እንድታቆም እንደምትፈልግ" ገልጻለች።

    አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ አየር ጥቃት የከፈቱት የካቲት ወር መጨረሻ ላይ ነበር። ይህንንም ተከትሎ ኢራን በገልፍ እና በአረብ ባሕረ ሰላጠጤው የአሜሪካ አጋራት የጦር ሰፈሮች ላይ ጥቃት በመፈፀም ምላሽ የሰጠች ሲሆን 20 በመቶው የዓለም ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ የሚተላለፍበትን ወሳኙን የሆርሙዝ ወሽመጥ ዘግታለች።

    ወሽመጡ መዘጋቱም የነዳጅ አቅርቦት ላይ መስተጓጎል የፈጠረ ሲሆን ዋጋ እንዲዋዥቅ አድርጓል።

  10. የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ ከፍተኛ ባለሥልጣን በወሲባዊ ትንኮሳ ክስ ተመሰረተባቸው

    ሌተናል ጄነራል ሻድራክ ሲቢያ
    የምስሉ መግለጫ, ሌተናል ጄነራል ሻድራክ ሲቢያ

    በደቡብ አፍሪካ ካሉት ከፍተኛ የፖሊስ መኮንኖች አንዱ ወሲባዊ ትንኮሳ በመፈጸም ተከስሰው በጆሃንስበርግ ሰሜን ምዕራብ በሚገኝ ፍርድ ቤት ቀረቡ።

    ክሶቹ ሌተናል ጄኔራል ሻድራክ ሲቢያ የ16 ዓመት ልጅን ለጾታዊ ግንኙነት በማባበል እንዲሁም የ18 ዓመት ልጅን አስገድደው ደፍረዋል የሚሉ ናቸው።

    በተጨማሪም ጄነራሉ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ክስ የቀረበባቸው ሲሆን ይህም ሌሎች ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ሊታሰሩ እንደሚችሉ ይጠቁማል።

    ሰኞ ዕለት የታሰሩት እና ከኃላፊነታቸው የታገዱት ምክትል የፖሊስ ኮሚሽነር ምንም አስተያየት አልሰጡም።

    የ59 ዓመቱ አዛውንት መስከረም 29 የዋስትና ጥያቄ ለማቅረብ ዳግም ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

    አቃቤ ሕግ ሲቢያ ከታሰሩበት እስር ቤት ለማስመለጥ የተዘጋጀ ዕቅድ መኖሩን ፍንጮች አሉ በማለት ወደ ሌላ ማረሚያ ቤት እንዲቀይሩ ጠይቋል።

    በከፍተኛ የፖሊስ መኮንኑ ላይ ክስ የተመሰረተው ፖሊስ በሙስና እና ከወንጀለኞች ጋር በመተባበር ተወንጅሎ የሕዝብ ተወካዮች ምርመራ እያካሄዱ ባለበት ወቅት ነው።

    የማድላንጋ ኮሚሽን በመባል የሚታወቀው ይህ ምርመራ ባለፉት ሳምንታት የተጀመረ ሲሆን ሲቢያ ፖሊስ ከለላ እንዲሰጥ በመስማማት '20 ኢምፓላዎች' ከተባለ የወንጀል መሪ ስጦታዎች ተቀብሏል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።

    የአገሪቱ ፖሊስ ግን ክሱን ውድቅ አድርጎታል።

  11. ትራምፕ በመንግሥታቱ ድርጅት ላይ ባደረጉት ንግግር ኢራንን “ለማጥፋት” ዛቱ

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለተባበሩት መንግሥታት ጉባዔ ተሰብሰቢዎች ኢራንን ዳግም ማጥቃት ወይም የሰላም ድርድሩን መቀጠል የሚሉ “ትልቅ ውሳኔዎችን” መጋፈጣቸውን ተናገሩ።

    ማክሰኞ ዕለት በኒው ዮርክ በተጀመረው የመንግሥታቱ ድርጅት ጉባዔ ላይ የተገኙት የኢራን ልዑክ አንድ ብቻ ናቸው።

    ትራምፕ ለጉባዔው ባደረጉት ንግግር ከኢራን ጋር የገቡበት ግጭት የማይፈታ ከሆነ እስላማዊ ሪፐብሊኳን “ሊያጠፏት” እንደሚችሉ ዝተዋል።

    ትራምፕ በመንግሥታቱ ድርጅት አዳራሽ ለተሰበሰቡት የዓለም መንግሥታት ንግግር ሲያደርጉ “የዓለም አቀፉ መንግሥታት” የሚለውን ሃሳብ ውድቅ አድርገው በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ሰላምን ለማምጣት እንደሚያሸማግሉ እንዲሁም አሜሪካ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ፉክክሩን በበላይነት እንደምታጠናቅቅ ተናግረዋል።

    ፕሬዚዳንቱ ይህንን የተናገሩት ከፍተኛ የአሜሪካ እና የኢራን ዲፕሎማቶች ከተወያዩ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።

    በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት እያካሄዱ ያሉት ትራምፕ ከጉባዔው ጎን ለጎን በርካታ የዓለም መሪዎችን አግኝተው አነጋግረዋል።

    ፕሬዚዳንት ትራምፕ ንግግራቸውን የጀመሩት በምጣኔ ሃብት፣ በስደተኞች፣ በድንበር እና ወንጀልን በመቆጣጠር ረገድ ያስመዘገቧቸውን ስኬቶች በመዘርዘር ነው።

    ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው ባለፈው ዓመት በየካቲት ወር ከእስራኤል ጋር በመሆን የጀመሩትን እና የዓለም ነዳጅ ዋጋ ማሻቀብ ያስከተለውን የኢራን ጦርነት ትክክለኛነት ለማስረዳት ጥረዋል።

    የፕሬዚዳንቱ ንግግር የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸኃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የዓለም ሕዝብ “እርስ በእርሱ የተሳሰረ” መሆኑን፤ ነገር ግን ዓለም አቀፍ መንግሥታት ልዩነታቸው እየሰፋ መሆኑን መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩትን የተቃረነ ነው።

    የትራምፕ ንግግር ጦርነቱ ቴህራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንዳይኖራት ማድረግ የቻለ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።

    "ከኢራን ጋር፣ አገራቸውን ዳግም እንዲገነቡና ከምንጊዜውም በበለጠ ታላቅ አገር እንዲፈጥሩ የሚያስችላቸው ስምምነት ይደረግ ይሆን?" ሲሉ የተናገሩት ትራምፕ ቀጥለውም "ወይስ ይህን የእስላማዊ ሪፐብሊክ መንግሥት በፍጥነት አጥፍቼ ሰዎችንና አገራትን እንደገና የመግደልና የማውደም ዕድል ፈጽሞ እንዳያገኙ አደርጋለሁ? ወደ ገሃነምስ እወረውራቸዋለሁ?" ሲሉ በንግግራቸው ላይ ጥያቄ አቅርበዋል።

    ትራምፕ እስካሁን ሳይሳካ የቆየው ከኢራን ጋር የሚደረገው የሰላም ድርድር ከኅዳሩ ምርጫ በኋላ ይሳካል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

    ይህ አስተያየታቸው ድርድሮችን ክፍት እያደረጉ ከፍተኛ ወታደራዊ ኃይልን በመጠቀም ማስፈራራትን የሚያካትተውን የእርሳቸውን የውጭ ፖሊሲ ስትራቴጂ የሚያንፀባርቅ ነው።

    ትራምፕ ከንግግራቸው በኋላ ለጋዜጠኞች የአሜሪካ ባለሥልጣናት ከተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን ከኢራን ልዑክ ጋር "እጅግ ውጤታማ" የሆነ ሦስት ሰዓት የፈጀ ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

    የኢራን መገናኛ ብዙኃን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ በመካከለኛው ምሥራቅ የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ከሆኑት ስቲቨ ዊትኮፍ ጋር መገናኘታቸውን ዘግበዋል።

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስተር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጋይ ንግግሩ በአደራዳሪዋ ኳታር በኩል መደረጉን መናገራቸውን ኢርና ዘግቧል።

    ቴህራን የቀረቡት ቅድመ ሁኔታዎች አሜሪካ በሁሉም ግንባሮች የምታካሄደውን ጦርነት ማቆም ጨምሮ የሚጠይቅ መሆኑን የመገናኛ ብዙኃኑ ዘግቧል።

    ቢቢሲ ዊትኮፍን ስለ ስብሰባው ጠይቆ በአውራ ጣታቸውን በጥሩ ሁኔታ ሄዷል የሚል ምልክት በመስጠት መልሰዋል።

    ዊትኮፍ በኋላ ላይ በኤክስ ገጻቸው ላይ ንግግሩ “ቀኑን በሙሉ በሁለቱ ወገኖች መካከል መልዕክቶችን ሲያለዋውጡ በነበሩ አደራዳሪዎች” በኩል መካሄዱን አስታውቀዋል።

    ዊትኮፍ አከለውም "ገንቢ እና ተስፋ ሰጪ ይሆናሉ ብለን ተስፋ ያደረግነውን የአንድ ዙር ውይይት በተሳካ ሁኔታ አጠናቀናል" ሲሉ ተናግረው "አደራዳሪዎቹም ሥራቸውን ይቀጥላሉ" ብለዋል።

  12. ትራምፕ የተመድ በጀት በ15 በመቶ መቀነሱን እና በሺዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞቹ መሰናበታቸውን ተናገሩ

    ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ንግግር ሲያደርጉ

    የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ መንግሥታቸው ከሌሎች በርካታ አገራት ጋር በመተባበር በመንግሥታቱ ድርጅት ታሪክ እጅግ ሰፊ የሆነ ማሻሻያ ማድረጉን አስታወቁ።

    ትራምፕ ዛሬ በተጀመረው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር የድርጅቱ በጀት በዘንድሮው የአውሮፓውያኑ ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ 15 በመቶ መቀነሱን እና ከ4000 በላይ ሰራተኞቹም እንደተሰናበቱ ተናግረዋል።

    ድርጅቱ "አስደናቂ አቅም" እንዳለው የጠቀሱት ፕሬዚደንቱ፣ ነገር ግን የግራ ዘመሞችን "አጀንዳ መሸከም" ማቆም አለበት ብለዋል።

    ትራምፕ በሁለተኛው የሥልጣን ዘመናቸው ትላልቅ እርምጃዎችን የወሰዱ ሲሆን ከእነዚህ መካከል አሜሪካን ከበርካታ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አባልነት ማስወጣት ይገኝበታል።

    የፕሬዚደንቱ እርምጃ ካረፈባቸው 66 ተቋማት መካከል ግማሽ ያህሉ ከመንግሥታቱ ድርጅት ጋር የተገናኙ ናቸው።

    በወቅቱ ዋይት ሃውስ በሰጠው መግለጫ እርምጃው የተወሰደው ተቋማቱ "ለአሜሪካ ጥቅም የሚሰሩ" ባለመሆናቸው እና "ውጤታማ ያልሆኑ ወይም ድብቅ አጀንዳዎችን ስለሚያራምዱ" እንደሆነ ገልጿል።

  13. አፍሪካ በተመድ የጸጥታ ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት ዋና ጸሐፊው ጠየቁ

    የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ

    የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ አፍሪካ በመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤት ውስጥ ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት ጠየቁ።

    ዋና ፀሐፊው ይህን ያሉት ዛሬ በተጀመረው የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የመክፈቻ ንግግር ባደረጉበት ወቅት ነው።

    ጉቴሬዝ በንግግራቸው አፍሪካ ቢያንስ አንድ ቋሚ መቀመጫ ሊሰጣት እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።

    “ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የፀጥታው ምክር ቤት የአፍሪካ ቋሚ ውክልና አለመኖር ኢ ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ ያልሆነ ነው” ሲሉ መቀየር እንዳለበት አሳስበዋል።

    ዋና ፀሐፊው ባለፈው ዓመትም “ከ1945 በኋላ ብዙ የዓለም እውነታ ተቀይሯል፤ ይሁን እንጂ የፀጥታው ምክር ቤት ስብጥር ጉልህ ለውጥ ሳያሳይ እንደቀጠለ ነው” ሲሉ ተመሳሳይ ጥሪ አቅርበው ነበር።

    የፀጥታው ምክር ቤት አራት ቋሚ አባላት ያሉት ሲሆን እነዚህም ቻይና፣ ፈረንሳይ፣ ሩሲያ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና አሜሪካ ናቸው።

    በዚህም የአፍሪካ ክፍል በቅኝ ግዛት ሥር በነበረበት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የነበረውን እውነታ አሁንም ያንፀባርቃል በሚል ምክር ቤቱ ለረዥም ጊዜ ሲተች ቆይቷል።

    ምክር ቤቱ የተለያዩ የዓለም ቀጣናዎችን የሚወክሉ አስር ቋሚ ያልሆኑ አባላት ቢኖሩትም እንደ አምስቱ ቋሚ መቀመጫ እንዳላቸው አገራት ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት የላቸውም።

    የአፍሪካ ሕብረት በምክር ቤቱ ውስጥ ሁለት ቋሚ ተወካዮች እና ተጨማሪ ሁለት ቋሚ ያልሆኑ ተወካዮች እንዲኖሩት ለረዥም ጊዜ ግፊት ሲያደርግ ቆይቷል።

    የፀጥታው ምክር ቤት አገራት፣ ተቋማት እና ግለሰቦች ላይ ዓለም አቀፍ ማዕቀቦችን መጣል፣ የሰላም ማስከበር ስምሪቶችን መፍቀድ፣ እንዲሁም ለግጭቶች ተመድ ምን ዓይነት ምላሽ መስጠት አለበት የሚለውን የመወሰን ሥልጣን አለው።

  14. ሳዑዲ በየመን በፈፀመችው ጥቃት ከ20 በላይ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው እና መቁሰላቸው ተገለጸ

    መሣሪያ ይዞ ጀልባ ላይ የተቀመጠ የሁቲ ታጣቂ
    የምስሉ መግለጫ, ከቅርብ ቀናት ወዲህ ሁቲዎች ሳዑዲ በየመን በርካታ የአየር ድብደባዎችን ፈጽማለች ሲሉ ይከስሳሉ

    ሳዑዲ አረቢያ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ በየመን በፈፀመችው ጥቃት ከ20 በላይ ሰላማዊ ሰዎች እንደተገደሉ እና ጉዳት እንደደረሰባቸው የየመን ሁቲዎች እና ከቡድኑ ጋር ግንኙነት ያለው ሚዲያ አስታወቁ።

    የሁቲ ጦር ቃል አቀባይ ሳዑዲ አረቢያ ግጭቱ ከተባባሰ ወዲህ ከ900 በላይ የአየር እና የሚሳዔል ጥቃቶችን በይዞታቸው ላይ መፈፀሟን ተናግረዋል።

    በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ዘንድ እውቅና ያለው የየመን መንግሥት በበኩሉ ቡድኑ ለተፈፀመበት ጥቃት አፀፋ ለመስጠት በላህጂ ግዛት በገበያ ሥፍራ ላይ በፈፀመው ጥቃት ሰላማዊ ሰዎች ተጎድተዋል ሲል ከስሷል።

    ሁቲዎች ግን የሳዑዲ ጥቃት የየመን ሰላማዊ ሰዎችን ዒላማ ያደረገ እንደሆነ ጠቅሰው፣ ግጭቱ ከተቀሰቀሰ ወዲህ የሚፈፀመው ጥቃት መባባሱን ገልጸዋል።

    ታጣቂ ቡድኑን የምትደግፈው ኢራንም ሳዑዲ አረቢያ በሁቲ ግዛቶች ላይ የምትፈፅማቸውን ጥቃቶች እንድትታቆም አሳስባለች።

  15. አሜሪካ ከኢራን ጋር ለመነጋገር ዝግጁ መሆኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ተናገሩ

    የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ

    የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በኒው ዮርክ በሚካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ ጎን ለጎን ከኢራን ባለሥልጣናት ጋር ለመነጋገር ዝግጁ መሆናቸውን ገለጹ።

    ሩቢዮ "አሁን ላይ ምንም ነገር የታቀደ አይመስለኝም ፤ ነገር ግን ለእንዲህ ዓይነት ውይይት በእርግጠኝነት ዝግጁ ነን። በተለይ ተገናኝቶ መነጋገሩ አዎንታዊ ውጤት ካመጣ እና በመጨረሻም ዋናውን ዓላማ የማሳካት ተስፋ ካለ” ብለዋል።

    ሚኒስትሩ ዋና ዓላማ ሲሉ የገለጹት ኢራን የኒውክሌር የጦር መሣሪያ መታጠቅ እንዳትችል ማረድግን ነው።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራቅቺ ሰኞ ዕለት ጀመርው በኒው ዮርክ የሚገኙ ሲሆን ማስዑድ ፔዝሽኪያንም ለጠቅላላ ጉባኤው ወደ ኒውዮርክ ተጉዘዋል።

    ከሁለት ቀናት በፊት ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራኑ ፕሬዚደንት ማስዑድ ፔዝሽኪያን ጋር ለመገናኘት ዝግጁ መሆናቸውን ለፎክስ ኒውስ ተናግረው ነበር።

    ጠቅላላ ጉባኤው ዛሬ የተጀመረ ሲሆን የኢራን ተወካዮች ንግግር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

  16. በቱርክ በትምህርት ቤት አቅራቢያ በተፈፀመ ጥቃት 11 ሰዎች ተጎዱ

    ክስተቱ ያጋጠመበት አካባቢ የቆመ የፖሊስ መኪና

    በቱርክ በትምህርት ቤት አቅራቢያ በተከፈተ ተኩስ 11 ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ፖሊስ አስታወቀ።

    ማክሰኞ ጠዋት ላይ አንድ መሣሪያ የታጠቀ ግለሰብ በከፈተው ተኩስ ከተጎዱት መካከል ሁለቱ በአስጊ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸው ተገልጿል።

    ጥቃቱ የተፈፀመው በምዕራባዊ ማኒሳ ግዛት በሚገኝ ኢንሲ ኡዝሜዝ በተባለ የሙያ እና የቴክኒክ ትምህርት ቤት አቅራቢያ ሲሆን ጉዳት የደረሰባቸው ሁሉም ተማሪዎች ናቸው ተብሏል።

    ጥቃቱን በመፈፀም የተጠረጠረው የ15 ዓመት ታዳጊ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ፖሊስ ገልጿል።

    ተጠርጣሪው የጦር መሣሪያ ይዞ ጭር ባለ መንገድ ወደ ትምህርት ቤቱ ሲራመድ እና ተመልሶ በሩጫ ሲያመልጥ ከደኅንነት ካሜራ የተገኙ ተንቃሰቃሽ ምሥሎች አሳተይዋል።

    የተጠርጣሪው እናት፣ አባት እና የመሣሪያው ባለቤት እንደሆኑ የተገለፁት አያትም ከክስተቱ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የአገሪቷ የፍትሕ ሚኒስትር አኪን ጉርሌክ ተናግረዋል።

    የጥቃቱ ዓላማ ምን እንደሆነ እስካሁን ግልጽ አይደለም።

    የአገሪቷ የትምህርት ሚኒስቴር “ክስተቱ አገራችንን በተለይም የትምህርት ማኅበረሰቡን እጅግ ያሳዘነ ነው” ብሏል።

    ሚኒስቴሩ ጨምሮም ሦስት ብሔራዊ መርማሪዎች ወደ ማኒሳ ግዛት መላካቸውን ገልጿል።

    በቱርክ በዚህ ዓመት ብቻ በትምህርት ቤት ላይ ጥቃት ሲፈፀም ይህ ሦስተኛው ነው።

    የአሁኑ ጥቃት የተፈፀመው መንግሥት እየጨመረ የመጣውን መሰል ጥቃት ለማስቆም እየታገለ ባለበት ወቅት ነው።

  17. የአሜሪካ ዋነኛ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ለትራምፕ እንቅስቃሴ ሽፋን መስጠታቸውን አቋረጡ

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሲኤንኤን፣ ፖለቲኮ እና ኤምኤስ ናው መገናኛ ብዙኃን ዋይት ሐውስ ገብተው እንዳይዘግቡ የጣሉትን ዕገዳ በመቃወም ዋነኛ የአሜሪካ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ለፕሬዝዳንቱ የሚሰጡትን ሽፋን አቋረጡ።

    ትራምፕ አርብ ዕለት እገዳውን ሲያሳውቁ፣ መገናኛ ብዙኃኑ ስለ አስተዳደራቸው “የፈጠራ ወይም የውሸት” ዘገባዎችን እያቀረቡ ነው ሲሉ ከስሰዋል። የዜና ተቋማቱ በበኩላቸው፣ ዘጋቢዎቻቸው ቅዳሜ ዕለት ወደ ዋይት ሐውስ እንዳይገቡ መከልከላቸውን ገልጸዋል።

    ሦስቱ የአሜሪካ የዜና ተቋማት በመቀጠል፣ “መንግሥት ፕሬሱ ምን እንደሚዘግብ አይወስንም የሚለውን መርኅ ለማስከበር” በትራምፕ አስተዳደር ላይ ክስ እንደሚመሠርቱ አስታውቀዋል።

    ዋነኞቹ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ለትራምፕ ሽፋን ላለመስጠት መወሰናቸውን ተከትሎ የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት “ትራምፕ ቲቪ” የተባለ የራሱን በኢንተርኔት የሚተላለፍ ቻናል ጀምሯል፤ ይህም ስለ ፕሬዝዳንቱ ያለማቋረጥ ለ24 ሰዓታት ቪዲዮዎችን የሚያስተላልፍ ነው።

    ሌሎችም በርካታ የአሜሪካ የዜና ተቋማት በጋራ በሚደረጉ የፕሬዝዳንቱ ዘገባዎች ላይ እንደማይሳተፉ አስታውቀዋል። ከእነዚህ መካከል ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ እና ዘ ዋሽንግተን ፖስት ከትራምፕ ዝግጅቶች የሚገኙ ፎቶዎችን እንደማያጋሩ አሳውቀዋል።

    በዚህ ምክንያት ትራምፕ በፕሬዝዳንታዊ አውሮፕላናቸው ሲሳፈሩ ወይም በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ለመሳተፍ ኒው ዮርክ ሲደርሱ የሚያሳይ ምንም ቪዲዮ በቴሌቪዥን ጣቢያዎች አልቀረበም።

    ትራምፕ በዋይት ሐውስ ደቡባዊ መስክ ላይ በተገነባው አዲስ ሄሊኮፕተር ማረፊያ ምረቃ ላይ የተገኙ ሲሆን፣ ዝግጅቱ በአዲሱ የዋይት ሐውስ ድረ-ገጽ ላይ በቀጥታ ተላልፏል፣ ሆኖም የፕሬዝዳንቱ ንግግር በግልጽ አልተሰማም።

  18. የግንባታ ሠራተኞች በቆረጡት ኬብል ምክንያት በአሜሪካ ውስጥ በረራዎች ተስተጓጎሉ

    አውሮፕላኖች

    በአሜሪካ ውስጥ የግንባታ ሠራተኞች ለአየር ትራፊክ ቁጥጥር አስፈላጊ የሆነ ኬብል በስህተት በመቁረጣቸው በአገሪቱ በሚገኙ ዋና ዋና አየር ማረፊያዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ በረራዎች እንዲዘገዩ ምክንያት ሆነ።

    በዚህም የተነሳ ሰኞ ከሰዓት በኋላ በኒው ዮርክ፣ ፔንስልቬኒያ፣ ኒው ጀርሲ እና ማሳቹሴትስ በሚገኙ አየር ማረፊያዎች ውስጥ የሚካሄዱ በረራዎች ዘግይተዋል።

    የአሜሪካ ትራንስፖርት ሚኒስትር ሴን ዳፊ ኬብሉ መጠገኑን እና አየር ማረፊያዎቹ ወደ መደበኛ ሥራቸውን እንደሚመለሱ የገለጹ ቢሆንም፣ አሁንም መዘግየቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።

    ይህ በአሜሪካ ምሥራቃዊ ክፍል የተፈጠረው ከፍተኛ የበረራ መስተጓጎል ዛሬ ማክሰኞ በኒው ዮርክ ከሚካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ አስቀድሞ የተፈጠረ ሲሆን፣ ለጉባኤው በርካታ የዓለም መሪዎች በከተማዋ አካባቢ ወዳሉ አየር ማረፊያዎች ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።

    የአሜሪካ የትራንስፖርት ባለሥልጣናት እንዳሉት፣ የተቆረጠረው ኬብል የበረራ መቆጣጠሪያ ሥርዓትን ጎድቶታል። ይህ ሥርዓት አውሮፕላኖችን በሚነሱበት እና በሚያርፉበት ጊዜ ደኅንነታቸው በተጠበቀ ሁኔታ ለመምራት ይጠቅማል።

    የኒው ጀርሲ የሕዝብ ማመላለሻ ተቋም የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ ኒውስ እንደገለጸው፣ በቁፋሮ ቦታው የነበሩ ምልክቶች በተሳሳተ ሁኔታ ተቀምጠው ስለነበረ የግንባታ ሠራተኞቹ መስመሩን በስህተት ቆርጠውታል።

  19. ዩኬ ለሳዑዲ አረቢያ “ወታደራዊ ድጋፍ” እንደምትሰጥ አስታወቀች

    የዩኬ አውሮፕላን

    የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር አንዲ ቡርንሀም አገራቸው ለሳዑዲ አረቢያ ወታደራዊ ድጋፍ እንደምትሰጥ አስታወቁ።

    በኢራን በሚደገፉት የሁቲ አማጽያን ጥቃት የተሰነዘረባትን ሳዑዲ ለመርዳት በበረራ ላይ ላሉ አውሮፕላኖች ነዳጅ የመሙላት አገልግሎት እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

    ወታደራዊ ድጋፉ በቀጣይ ቀናት እንደሚጀመር ተገልጿል። በቆጵሮስ በሚገኘው ራፍ የዩኬ የጦር ሰፈር የሚገኝ አንድ የእንግሊዝ አውሮፕላን በወታደራዊ ድጋፉ እንደሚካተትም ተመልክቷል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት ሳዑዲ አረቢያ ወታደራዊ ድጋፍ እንዲደረግላት ጠይቃለች። ከመከላከያ ሚኒስትሩ ዌስ ስተርሊንግ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኤድ ሚሊባንድ በተሰጣቸው ምክር መሠረት ጥያቄውን ለመቀበል መወሰናቸውን ተናግረዋል።

    ወታደራዊ ድጋፉ “ለሳምንታት” ሊዘልቅ እንደሚችል ተገልጿል።

  20. ኢራን ሁቲዎችን “ማስታጠቅ እና መደገፍ” እንድታቆም የቡድን ሰባት አገራት አሳሰቡ

    ሁቲዎች

    ኢራን ሁቲዎችን “ማስታጠቅ እና መደገፍ” ማቆም አለባት ሲሉ የቡድን ሰባት አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በጋራ ባወጡት መግለጫ አሳሰቡ።

    በየመን ሁቲ ታጣቂዎች በሳዑዲ አረቢያ ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶችን “እጅግ እናወግዛለን” ሲሉም በመግለጫው አቋማቸውን አስታውቀዋል።

    በየመን በሳዑዲ ከሚደገፉ የመንግሥት ኃይሎች ጋር በቅርቡ እየተባባሰ የመጣው ውጊያ ለቀጣናው እንዲሁም ለዓለም አቀፍ የኃይል አቅርቦት ዘርፍም አስጊ እንደሆነ ገልጸዋል።

    በኢራን የሚደገፉት ሁቲዎች በቀይ ባሕር አቅራቢያ ግዛቶችን መያዛቸውን ተከትሎ ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ በሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ከየመን ሸሽተው ወጥተዋል።

    የቡድን ሰባት አገራት መግለጫውን ያወጡት በኒው ዮርክ ከሚካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ አስቀድሞ ነው። በጉባዔው የኢራን ተወካዮች ንግግር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

    የዩናይትድ ኪንግደም፣ ካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ጣልያን፣ ጃፓን እና አሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በጋራ ባወጡት መግለጫ “ሁቲዎች በአፋጣኝ ሁሉንም ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንዲያቆሙ እንጠይቃለን” ብለዋል።

    “የመርከብ ጉዞዎች ላይ የሚደርስ ጥቃት እና ዛቻ እንዲገታ እና ወደ ፖለቲካዊ የንግግር ሒደት መመለስ እንዲቻል” ሲሉም አሳስበዋል።