የሁቲ አማፂያን በሳዑዲ አረቢያ ሪያድ የሚገኝ የነዳጅ ማከማቻ ማጥቃታቸውን አስታወቁ

የሁቲ አማፂያን በሳዑዲ አረቢያ ዋና ከተማ ሪያድ የሚገኘውን የነዳጅ ማከማቻ በተወንጫፊ ሚሳዔል እና ድሮኖች ማጥቃታቸውን አስታወቁ። ሳዑዲ አረቢያ ጥቃቱ ስለመፈጸሙ ወዲያውኑ ማረጋገጫ አልሰጠችም። የሁቲ ታጣቂዎች ጥቃቱን የፈጸሙት ሳዑዲ በሰነዓ እና ሌሎች የየመን ግዛቶች ላይ ለፈጸመቻቸው የአየር ድብደባዎች ምላሽ መሆኑን ተናግረዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ወደ እስራኤል እየተጓዘ በነበረው አውሮፕላን ላይ ፓይለቱን በስለት የወጋው አብራሪ መታሰሩ ተገለጸ

    ከዱባይ ወደ ቴል አቪቭ እየተጓዘ የነበረው አውሮፕላን

    ከዱባይ ወደ ቴል አቪቭ እየተጓዘ በነበረ አውሮፕላን ላይ ፓይለቶች በመጣላታቸው በረራው ወደ ሳዑዲ አረቢያ እንዲለወጥ ተደርጓል።

    ዋና አብራሪው እና ምክትል አብራሪው ተጣልተው ጉዳት እንደደረሰባቸው እና ወደ ሆስፒታል እንደተወሰዱ ተገልጿል።

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ “የስለት ጥቃት የፈጸመው ፓይለት በቁጥጥር ሥር ውሎ በሳዑዲ ባለሥልጣናት ጥያቄ እየቀረበለት ነው” ብለዋል።

    አውሮፕላኑ ወደ እስራኤል ሲቃረብ አንደኛው ፓይለት ሌላኛውን ፓይለት በስለት እንደወጋው እና አውሮፕላኑን ለመከስከስ እንደሞከረ ተገልጿል።

    ከዱባይ የተነሳው የፍላይዱባይ አውሮፕላን በረራውን በጀመረ በሁለት ሰዓታት ውስጥ የድንገተኛ ጊዜ ምልክት ማሳየቱን በረራዎችን የሚከታተለው ፍላይትራዳር24 ድረ ገጽ ጠቁሟል።

    ከሁለት ደቂቃ በኋላ ደግሞ አውሮፕላን ሲጠለፍ የሚሰጠውን ምልክት አውሮፕላኑ ማሳየት ጀምሯል።

    ዋና አብራሪው እና ምክትሉ “መጋጨታቸውን” የእስራኤል መከላከያን ጠቅሰው መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

    በኤፍዜድ1073 በረራ ላይ 150 ተሳፋሪዎች የነበሩ ሲሆን አብዛኞቹ እስራኤላውያን ናቸው።

    ሁሉም ተሳፋሪዎች ደኅና እንደሆኑ እና አውሮፕላኑም በታቡክ አየር ማረፊያ እንደደረሰ ተገልጿል።

    ልጇ ሚርያም በረራው ላይ እንደነበረች የተናገረችው ያስሚን አቡካሲስ፣ ስለት የያዘ ግለሰብ ከፓይለቶቹ አንዱ መሬት ላይ እንዲወርድ እንዳስገደደው ገልጻለች። አውሮፕላኑ ውስጥ ደም ይታይ እንደነበርም ተናግራለች።

    ጀሩሳሌም ፖስት ያነጋገረው ተጓዥ እንዳለው አንደኛው ፓይለት ሌላኛውን በስለት ወግቶታል። አውሮፕላኑ ፊት ወንበር ላይ ተቀምጠው የነበሩ ተሳፋሪዎች ጥቃት አድራሹን ከጀርባው እንዳነቁትም ተናግረዋል።

    አውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩ ሌሎች ሁለት ፓይለቶች አውሮፕላኑን በማሳረፍ እንደተባበሩ ተገልጿል።

    ሁለቱም ፓይለቶች ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገልጿል።

  2. “ለቀናት የጥይት እና ከባድ መሣሪያ ድምጽ ይሰማናል”- ከላሊበላ መውጣት ያልቻሉት ቱሪስቶች

    የላሊበላ አውሮፕላን ማረፊ

    የአውሮፕላን በረራ በመቋረጡ ምክንያት ከላሊበላ ለመውጣት ያልቻሉ ቱሪስቶች 33 እንደሚደርሱ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ቱሪስቶች ተናገሩ።

    በታሪካዊቷ ከተማ ዙሪያ ግጭት እየተባባሰ በመሄዱ ለቀናት የጥይት እና ከባድ መሣሪያ ድምጽ እየሰሙ እንደሆነ ገልጸዋል።

    ጎብኚዎቹ በረራ እስከሚጀመር ድረስ በጭንቀት እየተጠባበቁ እንደሚገኙ ለቢቢሲ ኒውስደይ አስረድተዋል።

    እንግሊዛዊ ቱሪስት ትናንት ማክሰኞ እንደተናገረው 33 ቱሪስቶች ከላሊበላ መውጣት አልቻሉም።

    14 እስራኤላውያን ቱሪስቶች በወታደራዊ ሄሊኮፕተር፣ ሌሎች አምስት ቱሪስቶች እና አንድ የእርዳታ ሠራተኛ ደግሞ በተራድኦ ድርጅት ተሽከርካሪ ከከተማዋ ወጥተዋል።

    ሁለት እንግሊዛውያንን ጨምሮ አሜሪካውያን፣ እስራኤላውያን፣ ደቡብ ኮሪያውያን፣ ደቡብ አፍሪካውያን፣ ሜክሲኳውያን እና የሌሎችም አገራት ቱሪስቶች አሁንም በከተማዋ ይገኛሉ።

    በላሊበላ ዙርያ ውጊያ ቢኖርም ከተማዋ ሰላም መሆኗን እንግሊዛውያኑ ቱሪስቶች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

    ከአስጎብኚዎች፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት፣ ከአየር መንገድ፣ ከኤምባሲዎች እና ከቀይ መስቀል መረጃ እንደሚጠባበቁም ተናግረዋል።

    ቢቢሲ ያነጋገረው እንግሊዛዊ ቱሪስት “ውጊያ ይሰማናል፤ ሙሉ ሳምንቱን ጥይት እና ከባድ መሣሪያ ሲተኮስ እንሰማለን” ሲል ገልጿል።

    ከትናንት በስትያ በነበሩት 48 ሰዓታት ውስጥ ውጊያው ጋብ በማለቱ በረራ ሊጀመር ይችላል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉም አክሏል።

    መስከረም 21/2019 ዓ. ም. በረራ ሊጀመር ይችላል የሚል መረጃ ቢደርሳቸውም “እርግጠኛ እንዳልሆነ” ጎብኚዎቹ ገልጸዋል።

    ባለፈው ሳምንት በፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል እንደ አዲስ ጦርነት መነሳቱን ተከትሎ የላሊበላ አውሮፕላን ማረፊያ በረራ አቋርጧል።

  3. ዓለሚቱ ኡሞድ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ተሾሙ

    ዓለሚቱ ኡሞድ

    የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት ዛሬ መስከረም 20/ 2019 ዓ. ም. 7ኛ የሥራ ዘመን፣ 1ኛ ዓመት፣ 1ኛ መደበኛ ጉባዔውን ያካሄደ ሲሆን፤ ዓለሚቱ ኡሞድ ​በድጋሚ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ተሹመዋል።

    የክልሉ የማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ሆነው ያገለግሉ የነበሩት ዓለሚቱ፤ ነሐሴ 2016 ዓ. ም. ላይ ኡመድ ኡጁሉን ተክተው ርዕሰ መስተዳደር መሆናቸው ይታወሳል።

    ከዚያ ቀደም የክልሉን ሴቶች እና ሕጻናት ቢሮም በኃላፊነት መርተዋል።

  4. አዳነች አቤቤ የአዲስ አበባ ከንቲባ ሆነው ተሾሙ

    ወ/ሮ አዳነች አቤቤ

    የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የከተማ አስተዳደር መንግሥት ምሥረታ እና 4ኛ ዙር የመክፈቻ ጉባዔውን ዛሬ መስከረም 20፣ 2019 ዓ. ም. ያደረገ ሲሆን፤ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የከተማዋ ከንቲባ ሆነው በድጋሚ ተሹመዋል።

    የደሴ ከተማ ከንቲባ የነበሩት አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የፕላን ልማት ቢሮ ኃላፊ ሆነው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ተሹመዋል።

    የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ከንቲባዋ “በቀጣዩ ምዕራፍ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችን ኑሮ ለማሻሻል በትኩረት ይሠራል” ብለዋል።

    ከንቲባዋ ባደረጉት ንግግር “የኑሮ ውድነት እና የዋጋ ግሽበትን በመቀነስ የከተማውን ነዋሪ የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል በትኩረት ይሠራል” ማለታቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

  5. ኢራን በአደራዳሪዋ ኳታር በኩል የአሜሪካን ምላሽ መቀበሏን ገለጸች

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ የሆርሙዝ ወሽመጥን ለመክፈት ያስችላል በሚል በኳታር በኩል ላቀረቡት ዕቅድ የአሜሪካን ምላሽ መቀበላቸውን የመንግሥት ቃል አቀባይ ፋጢመህ ሞሃጄራኒ ረቡዕ ዕለት መግለጻቸውን የመንግሥት የዜና አገልግሎት ኢሪብ ዘገበ።

    ሞሃጄራኒ የዋሽንግተንን ምላሽ ይዘት ወዲያውኑ ይፋ ያላደረጉ ሲሆን የቴህራን ቀጣይ እርምጃ ምን እንደሚሆንም አልገለጹም።

    አራግቺ ረቡዕ ዕለት በቴህራን በአሜሪካ ምላሽ ዙሪያ እንደሚወያዩ ይጠበቃል ሲሉ ባለሥልጣኑ ተናግረዋል።

    ኢራን ባለፈው ሳምንት በሰባት ቀናት ውስጥ የሆርሙዝ ወሽመጥን መክፈት ያስችላል ያለችውን ዕቅድ አቅርባ ነበር። በዚህም መሰረት አስፈላጊዎቹ ሁኔታዎች ከተሟሉ የሆርሙዝ ባሕር ወሽመጥ እንደገና ሊከፈት እና መርከቦች በነጻነት መንቀሳቀስ እንደሚችሉ አራግቺ ገልጸው ነበር።

    ሆኖም የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዕቅዱን ውድቅ በማድረጋቸው፣ ጉዳዩን በድርድር ለመፍታት ኳታር ተጨማሪ ጥረት እያደረገች መሆኑ ተገልጿል።

    በሌላ በኩል፣ የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን ቴህራን የኢዝላማባዱን የመግባቢያ ስምምነት ስኬታማ ለማድረግ የሚቻላትን ሁሉ ጥረት እያደረገች መሆኑን ኢስና የዜና ወኪል ዘግቧል።

    ፕሬዚዳንቱ ከድርድሩ ስለተገኙት ጥቅሞች እና ውጤቶች ማብራራት እንደ እጅ መስጠት ወይም ለኢራን ተቃዋሚዎች መገዛት ተደርጎ መወሰድ የለበትም፤ ይልቁንም እንደ ግልጽነት መገለጫ ሊታይ ይገባል ብለዋል።

    ፔዜሽኪያን በተጨማሪም ኢራን በኢዝላማባድ የመግባቢያ ሰነድ ውስጥ በተካተተ በማንኛውም ድንጋጌ ላይ ከመሠረታዊ መርሆቿ አለማፈግፈጓን ገልጸዋል።

    ይህንን ስምምነት በኢራን ታሪክ ውስጥ “የኩራት ምንጭ” እንዲሁም “ወሳኝ እና ከፍተኛ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰነድ” ሲሉ ገልጸውታል።

    ይህ የተከሰተው የሆርሙዝ ባሕር ወሽመጥን እንደገና ለመክፈት ኢራን ያስቀመጠቻቸውን ቅድመ ሁኔታዎች የኳታር አደራዳሪዎች ለዋሽንግተን እንደሚያቀርቡ አራግቺ ሰኞ ዕለት ከተናገሩ በኋላ ነው።

    ከአደራዳሪዎቹ ጋር ከተደረጉት ውይይቶች በኋላ የአሜሪካ ምላሽ ለኢራን እንደሚደርስ እንደሚጠብቁም ገልጸው ነበር።

    ኢራን፤ የአሜሪካን ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ለማስቆም፣ የታገዱ የኢራን ንብረቶችን መልቀቅ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ የመርከብ መተላለፊያ መስመር ላይ ስምምነት መድረስ የሚሉ ነጥቦችን በቅድመ ሁኔታነት አስቀምጣለች።

    ቴህራን እነዚህን አቋሞቿን ለዋሽንግተን ያቀረበችው ባለፈው ሳምንት ከተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን በተደረገ የሁለት ሰዓት ውይይት ወቅት በኳታር በኩል ነው።

  6. በሶማሊያ የባሕር ላይ ወንበዴዎች አምስት የነዳጅ ጫኝ መርከብ ሰራተኞች ተገደሉ

    ባሕር ላይ ያለች ጀልባ

    በሶማሊያ የባሕር ዳርቻ አምስት የመርከብ ሰራተኞች መገደላቸውን አንድ ከፍተኛ የክልሉ ባለሥልጣን ለቢቢሲ ተናገሩ።

    የፑንትላንድ ምክትል የማስታወቂያ ሚኒስትር ቢል ቃቦውሳድ እንዳሉት አምስቱ ባሕረተኞች የተገደሉት በባሕር ላይ ወንበዴዎች ነው።

    ተጠልፋ የቆየችው እና 'ኤምቲ ሆርነር 25 የተሰኘችው' ነዳጅ ጫኝ መርከብ በአካባቢው የጸጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር መዋሏን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ባሕረተኞቹ የተገደሉት መርከቧ በጸጥታ ኃይሎች እጅ ከመግባቷ አስቀድሞ እንደሆነ ገልጸዋል ።

    ሟቾቹ ሦስት ፓኪስታናዊ፣ ሕንዳዊ እና ምያንማራዊ መሆናቸውንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል። ሦስት ፓኪስታናዊ እና አንድ ሕንዳዊ እንዲሁም ሌሎች አራት ባሕረተኞች ላይም ጉዳት ደርሷል።

    ነዳጅ ጫኝ መርከቧ ወደ 18 ሺህ 500 በርሜል ነዳጅ ጭና ወደ ሶማሊያ መዲና ሞቃዲሹ እየተጓዘች ሳለ ነበር ሚያዚያ ላይ በስድስት ታጣቂዎች የተጠለፈችው። አስራ ስድስት ተጠርጣሪ ወንበዴዎች በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሲሆን ሌሎች ማምለጣቸውን እና ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑን ባለሥልጣናት ገልጸዋል።

    የተወሰኑ ወንበዴዎች እንዲያመልጡ ከፊል ራስ ገዝ የሆነችው ፑንትላንድ ረድታላች በሚል የቀረቡ ክሶችን የማስታወቂያ ሚኒስትሩ አጣጥለዋል።

    ባለሥልጣናት ወንበዴዎቹ መርከቧን እንዴት እንደተቆጣጠሩ እና አምስቱ ባሕረተኞች እንዴት እንደተገደሉ ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።

    ሆኖም ሚያዝያ ወር ላይ መርከቧ ስትጠለፍ 17 ባሕረተኞችን ይዛ እንደነበር ባለሥልጣናት ገልጸዋል። እነዚህም 10 ፓኪስታናዊ፣ አራት ኢንዶኔዥያውያን ፣ አንድ ሕንዳዊ፣ አንድ ስሪላንካዊ እና የምያንማር ዜጋ ናቸው።

    ከአውሮፓውኑ 2011 ዓለም አቀፍ የባሕር ላይ ዘመቻዎች በኋላ የወንበዴዎች እንቅስቃሴ ቢቀንስም ጥቃቶች እና ጠለፋዎች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እንደገና ጨምረዋል።

  7. በፈረንሳይ ከተባባሰው የተማሪዎች ተቃውሞ ጋር በተያያዘ ከ400 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

    በእሳት የተያያዘ የቆሻሻ ቅርጫት

    በመላው ፈረንሳይ በተቀሰቀሰው የተማሪዎች ተቃውሞ ጋር በተያያዘ ታዳጊዎችን ጨምሮ ከ400 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሯ ተናገሩ።

    በፓሪስ የተጀመረው እና ታዳጊዎች ለቀናት ትምህርት የዘጉበት የተቃውሞ ሰልፍ የተነሳው የክፍለ ጊዜዎች መጨናነቅ እና የመምህራን እጥረትን ጨምሮ ከተነሱ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ነው።

    ማክሰኞ ዕለት በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍም ቢያንስ 10 መምህራን፣ በርካታ ተማሪዎች እንዲሁም 48 ሕግ አስፈፃሚ አካላት ላይ ጉዳት መድረሱ ተገልጿል። እንደ ትምህርት ሚኒስቴር ከሆነ በተቃውሞ ሰልፉ ቢያንስ 400 የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ተስተጓጉለዋል።

    ቪዲዮ እና ምስሎችም በተቃዋሚዎች የወደሙ የአውቶብስ መቆሚያዎች እና በእሳት የተያያዙ የቆሻሻ ቅርጫቶችን አሳይተዋል።

    ተማሪዎች በዱላ እና አስለቃሽ ጭስ በመተኮስ ምላሽ በሰጡት የጸጥታ ኃይሎች ላይ የተለያዩ ቁሳቁሶችን መወርወራቸውንም የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

    የትምህርት ሚኒስትሩ ኤዶርድ ጂፍሬይ፣ ተማሪዎች ተቃውሞ የማካሄድ መብት እንዳላቸው ገልጸው፤ ነገር ግን የሚፈፅሙትን ጥቃት " ስህተት" ሲሉ አውግዘዋል።

    የውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ላውረንት ኑንዝ በበኩላቸው ከተቃውሞው ጋር በተያያዘ 440 ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ጠቅሰው፤ ከእነዚህ መካከል ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት እስር ላይ መሆናቸው እንደተነገራቸው ገልጸዋል።

    የተማሪዎቹ ተወካይ እና የማኅበሩ ፕሬዚደንት የሆነው ሪያድ ራኒ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል “በአፈና” እና "ፖሊስ ያልተመጣጠነ ኃይል ተጠቅሟል” ሲል መንግሥትን ከስሷል።

    ፖሊስ የሰጠው ምላሽ በበርካታ የአገሪቱ ፖለቲከኞችም የተተቸ ሲሆን የውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ግን ክሱን አስተባብለዋል።

  8. አሜሪካ ከቴህራን የጦር መሣሪያ ግዢ ጋር ንክኪ አላቸው ያለቻቸው የሩሲያ ኩባንያዎች ላይ ማዕቀብ ጣለች

    የኢራኑ እና የሩሲያው ፕሬዚዳንቶች ስምምነት ሲፈራረሙ

    አሜሪካ ከኢራን ጦር መሣሪያ ግዢ ጋር ግንኙነት አላቸው ያለቻቸው በርካታ ግለሰቦች፣ ድርጅቶች እና ሁለት የሩሲያ ኩባንያዎች ላይ ማዕቀብ ጣለች።

    የአሜሪካ ግምጃ ቤት በትናንትናው ዕለት የጣለው አዲስ ማዕቀብ የሩሲያ ኩባንያዎችን ጨምሮ በሆንግ ኮንግ፣ ቻይና እና ፓኪስታን የሚገኙ 13 ግለሰቦችን ዒላማ ያደረገ ነው።

    አሜሪካ በቴህራን ላይ የምጣኔ ሃብት ጫና ለመፍጠር በማሰብ የምታካሄደውን ዘመቻ መቀጠሏን ተናግራለች።

    ማዕቀቡ ከተጣለባቸው የሩሲያ ኩባንያዎች መካከል ለአገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር የጦር መሣሪያዎችን የሚያጓጉዘው እና የሩሲያ አውሮፕላን አምራች ኩባንያዎች እንደሚገኙበት ሮይተርስ ዘግቧል።

    ከዚህ ቀደም ሩሲያ ለቴህራን የድሮን መለዋወጫዎችን እና የጦር መሣሪያዎችን መስጠቷን የሚያሳዩ ሪፖርቶች ወጥተዋል።

    ከዚህ በተጨማሪም ሞስኮ፣ ቴህራን በባሕረ ሰላጤው የሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሠፈሮችን ማጥቃት እንድትችል ድጋፍ ማድረጓ ተገልጿል።

    ሩሲያ በዩክሬን ላይ ሙሉ ወታደራዊ ጥቃት መክፈቷን ተከትሎ የቴህራን እና የሞስኮ ግንኙነት በከፍተኛ ሁኔታ እየተጠናከረ መጥቷል።

    በጦርነቱ የመጀመሪያ ዓመት ኢራን በወታደራዊ እና በሲቪል ዒላማዎች ላይ በስፋት ጥቅም ላይ የሚውሉትን 'ሻሄድ' ድሮኖች ለሩሲያ አቅርባ ነበር።

    በምላሹም የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን፤ ኢራን በሆርሙዝ ባሕረ ሰላጤ አካባቢ ከአሜሪካ ጋር በምታደርገው ግጭት ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ እና "አስፈላጊ ቁሳቁሶችን" እንደሚያቀርቡላት ተናግረዋል።

    የካቲት 28/2018 ዓ.ም. አሜሪካ ኢራን ላይ ጦርነት የከፈተች ሲሆን ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ውጊያው እንደቀጠለ ነው።

    ኢራን ለሩሲያ በምታደርገው ድጋፍ ምክንያት በኪየቭ እና በቴህራን መካከል ውጥረት በነገሰበት በዚህ ወቅት ኪየቭ ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ በካስፒያን ባሕር ወታደራዊ ቁሳቁሶችን እያጓጓዘ በነበረ የኢራን መርከብ ላይ ጥቃት ፈጽማለች።

  9. የኳታር አደራዳሪዎች በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የሰላም ስምምነት እንዲደረስ ግፊት እያደረጉ ነው

    የኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼክ መሐመድ ቢን አብዱልራህማን አል ታኒ
    የምስሉ መግለጫ, የኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼክ መሐመድ ቢን አብዱልራህማን አል ታኒ

    ኳታር ማክሰኞ ዕለት በኢራን እና በአሜሪካ መካከል የሰላም ስምምነት ለማምጣት የዲፕሎማሲ ሥራዎችን እየሰራች መሆኑን አስታወቀች።

    የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማጂድ አል አንሳሪ "ከሁለቱም ወገኖች ጋር መልዕክቶችን እየተለዋወጥን ሲሆን ሁላችንንም ከግጭቱ ጦስ የሚታደግ ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚያስችል የጋራ መግባባት ለመፍጠር እየሠራን ነው" ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

    አሜሪካ እና ኢራን ስምንተኛ ወሩን ከያዘው ጦርነቱ ለመውጣት በሚያስችላቸው ጉዳዮች ላይ እስካሁን ድረስ መግባባት አልቻሉም።

    ባለፈው ሳምንት በኒው ዮርክ በተካሄደው የመንግሥታቱ ድርጅት ጉባዔ ወቅት የዲፕሎማሲ ጥረቶች ተጠናክረው የቀጠሉ ቢሆንም የዓለም አንድ አምስተኛ ነዳጅ የሚንቀሳቀስበትን የሆርሙዝ ወሽመጥን ሊያስከፈት የሚያስችል ስምምነት ላይ ግን መድረስ ሳይቻል ቀርቷል።

    ኳታር ለአጭር ጊዜም ቢሆን የተኩስ አቁም እንዲኖር ያስቻለውን የሰኔውን የመግባቢያ ሰነድ እንዲፈረም በማድረግ ረገድ ቁልፍ ሚና የተጫወተች ሲሆን አሁንም የሰላም ስምምነት ላይ እንዲደረስ ብርቱ ጥረት እያደረገች ነው።

    ሰኞ ዕለት የአሜሪካ እና ኢራን ባለሥልጣናት በተናጠል የኳታር አደራዳሪዎችን ማነጋገራቸውን አስታውቀዋል።

    ነገር ግን ማክሰኞ ዕለት ቀጣይ ንግግር ስለመካሄዱ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።

    ትራምፕ በተደጋጋሚ ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ መታጠቅ እንደማትችል እና ጦርነቱ በቅርቡ እንደሚያበቃ ሲናገሩ ተደምጠዋል።

    ጦርነቱ የኢራንን መከላከያ ኃይል በከፍተኛ ሁኔታ የጎዳ ሲሆን ቀድሞውንም የተዳከመ የነበረው የአገሪቱ ምጣኔ ሃብት የበለጠ እንዲንኮታኮት አድርጎታል።

    ነገር ግን ቴህራን ጦርነት ከተከፈተባት በኋላ በባሕረ ሰላጤው በሚገኙ የአሜሪካ አጋሮች እና ጦር ሠፈሮች ላይ ሚሳዔሎችን እና ድሮኖችን እያስወነጨፈች ነው።

    የሆርሙዝ ወሽመጥንም በመዝጋት ዓለም የነዳጅ ዋጋ እንዲያሻቅብ አድርጋለች።

    ትራምፕ ማክሰኞ ዕል “እስካሁን ተስፋ ስላለመቁረጣቸው የማውቀው ነገር የለም፤ ነገር ግን ተስፋ መቁረጣቸው አይቀርም” ሲሉ ማክሰኞ ዕለት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

    አክለውም “በጣም ደካማ ጥረት ነው እያደረጉ ያሉት” ብለዋል።

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ከኢራን ጋር የገቡትን ጦርነት ለማቆም የማዕቀብ እፎይታ ለመስጠት ቃል ገብተዋል ሲሉ የዘገቡትን አስተባብለዋል።

    የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ጠቅሰው ዘገባቸውን ያቀረቡ የመገናኛ ብዙኃን ትራምፕ ኢራን በኒውክሌር ፕሮግራሟ ላይ “ተጨባጭ” እርምጃ የምትወስድ ከሆነ የተጣለባትን ማዕቀብ ለማርገብ እና እንዳይንቀሳቀሱ የታገዱ ሃብቶችን ለመልቀቅ ተስማምተዋል ብለዋል።

    ትራምፕ ሰኞ ዕለት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ “ይህ ውሸት ነው። ምንም ነገር ለመስጠት ቃል አልገባሁም” ብለዋል።

    ባለፈው ሳምንት በመንግሥታቱ ድርጅት ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ ወደ ኒው ዮርክ ያቀናው የኢራን ልዑካን ቡድን የሆርሙዝ ወሽመጥን በሰባት ቀን ውስጥ መክፈት ያስችላል ያለውን የሰላም ዕቅድ ቢያቀርብም ትራምፕ ውድቅ አድርገውታል።

  10. ኔታንያሁ አገሪቱ በጥቅምት ወር ከምታደርገው ምርጫ አስቀድሞ ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል መረጃ እንዳላቸው ተናገሩ

    የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ

    የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በጥቅምት ወር አጋማሽ ላይ ከሚደረገው ምርጫ በፊት አገሪቱ ላይ ጥቃት ለመፈጸም የሚፈልጉ ኃይሎች ስለመኖራቸው ተናገሩ።

    "ከምርጫው በፊት ጠላቶቻችን ጥቃት ሊሰነዝሩብን እንደሚሞክሩ የሚያሳዩ ምልክቶች አሉ" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከቴል አቪቭ በስተደቡብ በሚገኘው የቴል ኖፍ የአየር ኃይል ሆነው ባስተላለፉት የቪዲዮ መልእክት ተናግረዋል።

    እንዲህ ዓይነቱን ጥቃት ሊፈጽሙ ስለሚችሉ አካላት ወይም ስለተገኘው የደህንነት መረጃ ዝርዝር መግለጫ አልሰጡም።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው "እኛን አትነካኩን፤ ረዥም ክንዳችን በማንኛውም ቦታና ጊዜ ይደርስባችኋል" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

    ኔታንያሁ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ጥቅምት 27 ለሚካሄደው ምርጫ ቅስቀሳ እያደረጉ ነው።

    እስራኤል ጋዛ እና ሊባኖስን ጨምሮ በተለያዩ ግንባሮች ወታደራዊ ዘመቻዎቿን እንደቀጠለች፣ እንዲሁም በቅርብ ሳምንታት ውስጥ በጋዛ ከ100 በላይ "አሸባሪዎችን" መግደሏን ገልጸዋል።

    በተጨማሪም ማክሰኞ ዕለት፣ በምዕራብ ጋዛ ከተማ በሚገኘው አል-ናስር ሰፈር ውስጥ በሚገኝ የመኖሪያ ሕንፃ ላይ በፈጸመችው ጥቃት ሁለት ፍልስጤማውያን ተገድለዋል።

  11. ትራምፕ ለኢራን የማዕቀብ እፎይታ ለመስጠት ቃል አለመግባታቸውን ተናገሩ

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ከኢራን ጋር የገቡትን ጦርነት ለማቆም የማዕቀብ እፎይታ ለመስጠት ቃል ገብተዋል ሲሉ የዘገቡትን አስተባበሉ።

    የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ጠቅሰው ዘገባቸውን ያቀረቡ የመገናኛ ብዙኃን ትራምፕ ኢራን በኒውክሌር ፕሮግራሟ ላይ “ተጨባጭ” እርምጃ የምትወስድ ከሆነ የተጣለባትን ማዕቀብ ለማርገብ እና እንዳይንቀሳቀሱ የታገዱ ሃብቶችን ለመልቀቅ ተስማምተዋል ብለዋል።

    ትራምፕ ሰኞ ዕለት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ “ይህ ውሸት ነው። ምንም ነገር ለመስጠት ቃል አልገባሁም” ብለዋል።

    አክሲዮስ እና ሲኤንኤን ማንነታቸው ያልጠቀሷቸውን የአሜሪካ ባለሥልጣናት በመጠቀም ትራምፕ ኢራን በኒውክሌር ጉዳይ ላይ “ተጨባጭ እርምጃ” ለመውሰድ የምትስማማ ከሆነ የማዕቀብ እፎይታ ለመስጠት እና የታገዱ ሃብቶቿን ለመልቀቅ ፈቃደኛ ናቸው ብለዋል።

    ትራምፕ ከኢራን ጋር የሚያደርጉት ጦርነት የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንዳይኖራት ለመከላከል፣ ጎረቤቶቿን የማጥቃት አቅሟን ለማስቀረት እንዲሁም ኢራናውያን አመራሮቻቸውን ከሥልጣን እንዲያወረዱ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት መሆኑን ተናግረዋል።

    ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንደሌላት ነገር ግን የኒውክሌር ኃይል ለሰላማዊ ግልጋሎት የማበልጸግ መብት እንዳላት ትከራከራለች።

    የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን ከሲቢኤስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ቴህራን በኒውክሌር ፕሮግራሟ እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ዝግጁ መሆኗን ቢናገሩም “ማስገደድን” ግን እንደማይቀበሉ ተናግረዋል።

    “ኢራን ጦርነት አትፈልግም፣ ነገር ግን ራሷን ከጫና፣ ዛቻ እና ጥቃቶች ትከላከላለች” ሲሉ ፔዜሽኪያን ተናግረዋል። ቀደም ሲል “የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ማምረት እንደሌለብን” ስምምነት ላይ መድረሳቸውንም አስታውሰዋል።

    የአሜሪካ እና የኢራን ባለሥልጣናት ሰኞ ዕለት ከአደራዳሪዎች ጋር ለየብቻቸው መነጋገራቸውን ይህም ለሰባት ወር የተካሄደውን ጦርነት ለማስቆም በሚደረገው ጥረት አካል መሆኑን የሁለቱም አገራት ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

    ኢራን እሁድ ዕለት ከዩናይትድ ስቴትስ እና ከእስራኤል ጋር ያላትን ግጭት መፍታት የምትችለው በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ብቻ እንደሆነ ገልጻለች።

  12. የአሜሪካ ወታደሮች ከሁለት አስር ዓመታት በኋላ ኢራቅን ለቅቀው ሊወጡ ነው

    የአሜሪካ ጦር ኢራቅን በይፋ የወረረው እና ሳዳም ሁሴንን ከሥልጣን ያወረደው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር መጋቢት 2003 ነበር።

    የአሜሪካ ወታደሮች እስከ ነገ ረቡዕ ድረስ በኢራቅ ከሚገኙት የመጨረሻዎቹ የጦር ሠፈሮቻቸው ለመውጣት መዘጋጀታቸው ተሰማ። የወታደሮቹ የጦር ሠፈሮቹን ለቅቆ መውጣት በኢራን እና አጋሮቿ ዘንድ እንደ ድል ተቆጥሯል።

    ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በኢራቅ ውስጥ የቆየው የአሜሪካ ጦር ከ4,500 ወታደሮቹ ሕይወታቸውን አጥተዋል።

    የኢራቅ የደህንነት ባለሙያዎች እንደሚናገሩት፣ በፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ዘመን ከስምምነት የተደረሰው እና ከኢራን ጋር ጦርነት እየተካሄደ ባለበት ወቅት በዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የተፈጸመው ይህ ወታደሮቹን የማስወጣት እርምጃ፤ ለቴህራን እና ለአጋሮቿ ሰፊ የመንቀሳቀስ ነፃነትን ሊሰጥ፣ እንዲሁም እንደ እስላማዊ መንግሥት ያሉ ሌሎች የአሜሪካ ጠላቶች እንደገና እንዲጠናከሩ ሊያደርግ ይችላል።

    ከኢራን ጋር ግንኙነት ያላቸውን የታጠቁ ቡድኖችን በማጥናት ላይ ያተኮሩት የኢራቅ የደህንነት ጉዳዮች ተንታኝ ጃሲም አል-ባሃድሊ፣ “ለዓመታት በኢራቅ ውስጥ የቴህራን ተጽዕኖ መገዳደሪያ ሆኖ ያገለግል የነበረውን ጦርን ስለሚያስወግድ፣ የጥምረት ኃይሉ መውጣት ለኢራን ስትራቴጂካዊ ጥቅም ያስገኛል” ብለዋል።

    ከኢራን ጋር ወገንተኛ የሆኑት የታጣቂ ቡድኖች፣ የአሜሪካ ጦር መውጣትን ለእንቅስቃሴያቸው እንደ ድል ከመቁጠር ባለፈ፣ ያንን ሁኔታ በመጠቀም “በደህንነት እና በፖለቲካዊ ውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ላይ የበለጠ ተጽዕኖ ለመፍጠር” እንደሚሞክሩ ተንብየዋል።

    በኢራን የሚደገፉ የታጠቁ ቡድኖች ጥምረት የሆነው ‘ኢስላሚክ ሪዚስስታንስ ኢን ኢራቅ’ አዛዥ አቡ ሞጅታባ አል-ያሲሪ፣ የአሜሪካ ኃይሎች መውጣት “ለኢስላሚክ ሪዚስስታንስ ኢን ኢራቅ እና ለታላቁ የኢራቅ ሕዝብ ታሪካዊ ድል፣ እንዲሁም ለአሜሪካ ፕሮጀክት ደግሞ ከባድ ሽንፈት” ሲሉ ገልጸውታል።

    “እአአ መስከረም 30፣ በኢራቅ ታሪክ ውስጥ ያለውን አንድ ጥቁር ምዕራፍ የሚዘጋበት እና ወረራው በአገራችን ላይ የራሱን ፍላጎት ለመጫን ያደረገው ሙከራ የከሸፈበት በመሆኑ እንዘክረዋለን” ሲሉ ለሮይተርስ ተናግረዋል።

    “ኢራቅ፣ ሉዓላዊነቷ ሊረጋገጥ የሚችለው በውጭ ኃይሎች ሳይሆን በሕዝቧ ትግል እና ቁርጠኝነት እንደሆነ አስመስክራለች” ሲሉም አክለዋል።

    የአሜሪካ ጦር ኢራቅን በይፋ የወረረው እና ሳዳም ሁሴንን ከሥልጣን ያወረደው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር መጋቢት 2003 ነበር።

  13. “ኢራን ነዳጅ መሸጥ የማትችል ከሆነ ማንም ነዳጅ አይሸጥም”- የቴህራን ባለሥልጣን

    የኢራን አፈ ጉባዔ መሐመድ ባጋር ጋባሊፍ ቢቢሲ አማርኛ

    የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባዔ መሐመድ ባጋር ጋባሊፍ፣ ቴህራን ነዳጅ መሸጥ የማትችል ከሆነ “ማንም ነዳጅ አይሸጥም” ሲሉ አስጠነቀቁ።

    “ደኅንነታችን የማይረጋገጥ ከሆነ የትኛውም መሠረተ ልማት ደኅንነቱ አይጠበቅም” ብለዋል።

    አፈ ጉባዔው ዛሬ በበይነ መረብ አማካኝነት በምክር ቤት ባደረጉት ንግግር፣ የኢራን ሕዝብ “በከበባ እና ዛቻ” ፍርሃት ውስጥ መግባት የለበትም ብለዋል።

    “የአሜሪካው ጠላት ኃይል ይሄንን መሠረታዊ እውነታ አልተረዳም፤ በኢራን ከፍተኛ ጥቃት እየደረሰበት በአዙሪት ውስጥ ይቀጥላል” ሲሉም አክለዋል።

    በሌላ በኩል የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ፣ አገራቸው ሰባት ነጥብ ያለው ዕቅድ፣ በኳታር አደራዳሪዎች አማካኝነት ለአሜሪካ ልካ ምላሽ እየጠበቀች እንደሆነ አስታውቀዋል።

    ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን በሰባት ቀናት ውስጥ ለመክፈት ያቀረበችውን ሐሳብ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ውድቅ ማድረጋቸው ይታወሳል።

  14. የቡርኪና ፋሶ መሪ የማዕድን ሽያጭ ትርፍን አገር ውስጥ ለማስቀረት የወርቅ ማቀነባበሪያ ከፈቱ

    ወታደራዊ መሪው ኢብራሒም ትራዎሬ

    የቡርኪና ፋሶ ወታደራዊ መንግሥት የመጀመሪያውን የወርቅ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ከፈተ።

    የአገሪቱን ዕምቅ ሃብት በአገር ውስጥ ጥቅም ላይ ለማዋል እና ቁልፍ ማዕድናትን ለመቆጣጠር የተወሰደ እርምጃ ነው ተብሏል።

    ወታደራዊ መሪው ኢብራሒም ትራዎሬ እንዳሉት፤ አገራቸው ጥሬ ማዕድናትን ለማቀነባበር በውጭ አገራት ላይ ጥገኛ እንዳትሆን በሚል ፋብሪካው ተከፍቷል።

    “ሁሉንም ማዕድናችንን እዚሁ እናቀነባብራለን። የገበያ ሰንሰለቱ በአጠቃላይ የእኛ እንዲሆን እንፈልጋለን” ሲሉ በፋብሪካው ምርቃት ላይ ተናግረዋል።

    ቡርኪና ፋሶ ከአፍሪካ ትልቋ ወርቅ አምራች አገር ናት። ነገር ግን የአገሪቱ መንግሥት ኢ-መደበኛ የሆነውን የማዕድን ዘርፍ ለመቆጣጠር ፈተና ገጥሞታል።

    የማዕድን ዘርፉ ከጂሃዲስቶች ነውጥ ጋር በተያያዘ መሰናክሎች በዝተውበታል።

    ወታደራዊው መንግሥት ቡርኪና ፋሶን የወርቅ ማቀነባበሪያ ማዕከል የማድረግ ዕቅድ አለው።

    የወርቅ ምርት ከመጨመሩ ጋር በተያያዘ የኢብራሒም ትራዎሬ አስተዳደር በመንግሥት የሚመራ የማዕድን ተቋም የመሠረተው ከሁለት ዓመት በፊት ነበር።

    የውጭ አገር የማዕድን ድርጅቶች ለመንግሥት 15% ድርሻ መስጠት የሚጠበቅባቸው ሲሆን፤ የአገር ውስጥ ሠራተኞችን ማሠልጠንም ግዴታቸው ነው።

  15. አሜሪካ በዩኬ አየር ኃይል በተቃጣው ጥቃት “የውጭ ኃይሎች” እጅ አለበት አለች

    የፀረ ሽብር ፖሊስ

    የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ፣ በዩናይትድ ኪንግደም አየር ኃይል የጦር ሰፈር ላይ የቦምብ ጥቃት ለመፈጸም የነበረው ውጥን ውስጥ “የውጭ አካላት” እጃቸው እንዳለበት ተናገሩ።

    በአየር ኃይሉ አቅራቢያ የሽብር ጥቃት ለማድረስ እየተዘጋጁ ነበር በሚል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ውለው የነበሩ አምስት ግለሰቦች በዋስ መለቀቃቸውን የፀረ ሽብር ፖሊስ ገልጿል።

    ሩቢዮ ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “በዩናይትድ ኪንግደም ሊፈጠር ይችል የነበረው ክስተት እጅግ አደገኛ ነው” ብለዋል።

    “የውጭ አካላት ተሳትፎ እንዳለበት ግልጽ ነው” ቢሉም ማስረጃ አላቀረቡም።

    የዩኬ የፀረ ሽብር ፖሊስ ለውጭ አገራት መንግሥታት ተቀጥረው የሚሠሩ ሰዎች ከክስተቱ ጀርባ ይኖሩ እንደሆነ ለማወቅ ምርመራ እንደሚደረግ አስታውቋል።

    ማርኮ ሩቢዮ

    አምስቱም ተጠርጣሪዎች የዩኬ ዜጎች ሲሆኑ በ20ዎቹ ዕድሜ ክልል ውስጥ ይገኛሉ።

    ኢራን ከክስተቱ ጋር በተያያዘ ምንም ዓይነት ተሳትፎ እንደሌላት ገልጻለች።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባደረጉት ንግግር ተጠርጣሪዎቹ በዋስ መለቀቃቸውን ተቃውመዋል።

    “መልቀቃቸው አስገርሞኛል፤ እኔ አልለቃቸውም ነበር” ብለዋል።

    ዩኬ ከአሜሪካ ጋር በቅርበት እየሠራች እንደሆነ አክለዋል።

    ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር ውለው የነበረው ሦስት “አጠራጣሪ ተሽከርካሪዎች” ወደ ዩኬ አየር ኃይል፣ ራፍ የጦር ሠፈር አቅጣጫ ካመሩ በኋላ መሆኑን ፖሊስ ገልጿል።

    አንድ የአካባቢው ነዋሪ በጦር ሠፈሩ አጠራጣሪ ነገር ካየች በኋላ ለፖሊስ ማሳወቋን ለቢቢሲ ተናግራለች።

    በኢራን ጦርነት ወቅት የጦር ሰፈሩ ለአሜሪካ የጦር አውሮፕላኖች ማረፊያ ሆኖ አገልግሏል።

  16. ሦስት የግብፅ የፀጥታ ኃላፊዎች ከ10 ዓመት በፊት ጣልያናዊ ተማሪን በማገት እስራት ተፈረደባቸው

    የ28 ዓመቱ ጊልዮ ራጄኒ

    ሦስት የግብፅ የፀጥታ ኃላፊዎች ከ10 ዓመት በፊት ጣልያናዊ ተማሪን በማገት በሮም ፍርድ ቤት ተፈረደባቸው።

    ተማሪው ስቅይት ከደረሰበት በኋላ ተገድሎ አስከሬኑ በካይሮ ተገኝቷል።

    በሌሉበት ክስ የቀረበባቸው ሦስቱ የፀጥታ ኃላፊዎች ድርጊቱን እንዳልፈጸሙ ተናግረዋል።

    ፍርድ ቤቱ የ10 ዓመት እስራት ፈርዶባቸዋል። አራተኛ ግብፃዊ ተከሳሽ ደግሞ በነጻ ተሰናብቷል።

    የ28 ዓመቱ ጊልዮ ራጄኒ በኬምብሪጅ ዩኒቨርስቲ የዶክትሬት ዲግሪ ለማግኘት እየተማረ ነበር።

    በአውሮፓውያኑ 2016 ግብፅ ለጎብኝት በሄደበት ጠፍቷል። ከቀናት በኋላ ሰውነቱ ተቆራርጦ አስከሬኑ በካይሮ አቅራቢያ ጉድጓድ ውስጥ ተጥሎ ተገኝቷል።

    መጀመሪያ ላይ የግብፅ እና ጣልያን ዐቃቢ ሕጎች በጋራ ምርመራ እያደረጉ ነበር። ነገር ግን ተቃራኒ ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል።

    የግብፅ ባለሥልጣናት ወንጀለኛ ቡድኖችን ለግድያው ተጠያቂ አድርገዋል። በተጨማሪም የመኪና አደጋ፣ አደንዛዥ ዕፅ ለመግዛት የተደረገ ሙከራ ከሽፎ ወይም ከዝርፊያ ጋር የተያያዘ ግድያ ሊሆን ይችላል ብለዋል።

    የግብፅ መንግሥት በተማሪው መጥፋት እጁ እንደሌለበት ገልጸዋል።

    የሮም ዐቃቤ ሕግ ግን የግብፅ ብሔራዊ ደኅንነት ተቋም በወንጀሉ መሳተፉን አስታውቋል።

  17. በዩኬ በሽብር ጥቃት ተጠርጥረው የታሰሩ አምስት ግለሰቦች በዋስ ተለቀቁ

    የፀረ ሽብር ፖሊስ

    በዩናይትድ ኪንግደም አየር ኃይል አቅራቢያ የሽብር ጥቃት ለማድረስ እየተዘጋጁ ነበር በሚል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ውለው የነበሩ አምስት ግለሰቦች በዋስ መለቀቃቸውን የፀረ ሽብር ፖሊስ አስታወቀ።

    እሑድ በአየር ኃይሉ አቅራቢያ ሦስት “አጠራጣሪ ተሽከርካሪዎች” መታየታቸው ለፖሊስ ጥቆማ ደርሶታል። ይህንን ተከትሎም ነዋሪዎች ከአካባቢው እንዲወጡ ተደርጓል።

    የዩኬ የፀረ ሽብር ፖሊስ ምርመራ መጀመሩን አስታውቋል። ለውጭ አገራት መንግሥታት ተቀጥረው የሚሠሩ ሰዎች ከክስተቱ ጀርባ ይኖሩ እንደሆነ ለማወቅ ምርመራ እንደሚደረግ ተገልጿል።

    አምስቱ ተጠርጣሪዎች የዩኬ ዜጎች ሲሆኑ በ20ዎቹ ዕድሜ ክልል ይገኛሉ። ነዋሪነታቸውም በለንደን እንደሆነ ተገልጿል።

    የፀረ ሽብር ፖሊስ እንዳለው ተጠርጣሪዎቹ ላይ የሚደረገው ምርመራ ይቀጥላል። በዋስ ቢለቀቁም “እንቅስቃሴያቸው እና ከሌሎች ጋር የሚያደርጉት ግንኙነት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚደረግ” አስታውቋል።

  18. ኢራን የድርድር ዕቅዷን ለአሜሪካ ልካ ምላሽ እየጠበቀች እንደሆነ አስታወቀች

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ፣ አገራቸው ሰባት ነጥብ ያለው ዕቅድ፣ በኳታር አደራዳሪዎች አማካኝነት ለአሜሪካ ልካ ምላሽ እየጠበቀች እንደሆነ አስታወቁ።

    በኒው ዮርክ በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ተገኝተው ሳለ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፤ የቴህራን ሰባት ነጥቦች ለዋሽንግተን ደርሰዋል። የዋይት ሀውስ ምላሽ በአሸማጋዮች በኩል እንደሚሰጣቸው እየጠበቁ ይገኛሉ።

    “ዓላማችን አሜሪካ ቅድመ ሁኔታዎቻችንን እንድታውቅ ማድረግ ነው። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ኢራን ዕቅድ እንዳላትም ማወቅ አለበት። ቅድመ ሁኔታዎቹ ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ ናቸው። አሜሪካ ሰላማዊ መፍትሔ እፈልጋለሁ ትላለች፤ እኛም ይሄንን መፍትሔ አቅርበናል” ብለዋል።

    ኢራን በኒውክሌር መርሃ ግብሯ ላይ “መለሳለስ አሳይታለች” በሚል የወጡ ሪፖርቶችን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ውድቅ አድርገዋል።

    “ባለፉት ሰዓታት ፕሮፓጋንዳዎች ሲሰሙ ነበር። የኢራን አቋም እንዳልተቀየረ ለመግለጽ እፈልጋለሁ። የሆርሙዝ ወሽመጥን የመክፈት ዕቅዳችንም ግልጽ ነው” ሲሉም አክለዋል።

  19. ከ12 ዓመት በፊት 116 ሰዎች በሞቱበት የአውሮፕላን አደጋ የስፔኑ አየር መንገድ ጥፋተኛ ተባለ

    በ2014 የደረሰው የአውሮፕላን አደጋ

    በአውሮፓውያኑ 2014 በደረሰው የአውሮፕላን አደጋ የስፔኑ አየር መንገድ ስዊፍትኤር ጥፋተኛ ተባለ።

    በፓሪስ ፍርድ ቤት ዛሬ በተላለፈው ውሳኔ አየር መንገዱ 256,000 ዶላር እንዲከፍል ታዝዟል። ይህም ከፍተኛው የቅጣት መጠን ነው።

    ከቡርኪና ፋሶ መዲና ኦጋዶጉ ወደ አልጄርያ፣ አልጀርስ ሲጓዝ የነበረው አውሮፕላን ላይ በደረሰው አደጋ 116 ሰዎች ሞተዋል።

    በኤር አልጄር በደረሰው የአውሮፕላን አደጋ የስፔኑ አየር መንገድ ሆነ ተብሎ ባልተፈጸመ ግድያ ጥፋተኛ ተብሏል።

    ባለቤቷ ፍሬድሪክ ትሪኮትን በአደጋው ያጣችው ሳንድሪ ትሪኮት “ለ4,449 ቀናት ያህል የሟቾች ቤተሰቦች ስንጠብቅ ነበር” ስትል በፍርድ ቤቱ ውሳኔ ደስተኛ መሆኗን ገልጻለች።

    ስዊፍትኤር በፈረንሳይ የተደረገውን ምርመራ “የተመሰቃቀለ ሥራ” ሲል ውድቅ አድርጓል።

    ከዚህ ቀደም በስፔን ዐቃቤ ሕግ የተደረገው ምርመራ ክስ ሳይመሠረት ተጠናቅቋል።

    አየር መንገዱ በ10 ቀናት ውስጥ ይግባኝ ማለት ይችላል።

  20. የኢራን እና አሜሪካ አደራዳሪዎች ውይይቱ ይቀጥላል ብለው እንደሚጠብቁ ተዘገበ

    የኢራን እና አሜሪካ ሰንደቅ አላማ

    የኢራን እና አሜሪካ አደራዳሪዎች ዛሬ ወይም ነገ ከሁለቱ አገራት ጋር በተናጠል ውይይት ይካሄዳል ብለው እንደሚጠብቁ ሮይተርስ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮችን ጠቅሶ ዘገበ።

    የኳታር አሸማጋዮች እና የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ለተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ ኒው ዮርክ ይገኛሉ።

    የኢራኑ ኢርና የዜና ወኪል ኒው ዮርክ ለሚገኘው የልዑካን ቡድን ቅርብ የሆኑ ምንጮችን ጠቅሶ ከዚህ ቀደም እንደዘገበው ከሆነ ከአሜሪካ ጋር ድርድር ለማድረግ ፍላጎት የላቸውም። አራግቺ ነገ ወደ ኢራን እንደሚመለሱን ተዘግቧል።

    “የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ዕይታ እና አቋም በኳታር አሸማጋዮች በኩል ለአሜሪካ በግልጽ ቀርቧል። ኢራን ምላሹን እየጠበቀች ነው” ሲሉም ምንጩ ተናግረዋል።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ከኢራን በኩል የቀረበውን በሰባት ቀናት ውስጥ የሆርሙዝ ወሽመጥን የመክፈት ዕቅድን ውድቅ ቢያደርጉም፤ ድርድር በቅርቡ ይቀጥላል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ትናንት ተናግረዋል።