ቀጥታ , ትራምፕ የኢራን ጦርነት “በወታደራዊ ደረጃ በስኬት እንደተገባደደ” እና ተጨማሪ ጥቃት እንደማይፈጸም ተናገሩ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኢራን ጦርነት “በወታደራዊ ደረጃ በስኬት እንደተገባደደ” ተናገሩ። ጦርነቱን ለመቋጨት እየተደረጉ ያሉ ድርድሮች “አወንታዊ ውጤት” እያመጡ መሆኑን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ ተጨማሪ ጥቃት ሊፈጸም የሚችልበት ዕድል እንደሌለም አክለዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ዴሞክራቲክ ኮንጎ “ፈሪ” ያለቻቸው 66 ወታደሮች በሞት እንዲቀጡ ወሰነች

    ወታደሮች

    ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ “ፈሪ” ያለቻቸው ቢያንስ 66 ወታደሮች በሞት እንዲቀጡ ወሰነች።

    ወታደሮቹ አገር በመክዳት እና ትዕዛዝ ባለመፈጸም መከሰሳቸውን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

    በሰሜን ኪቭዩ ግዛት በዋሊኬል በሚገኝ ወታደራዊ ፍርድ ቤት 71 ወታደሮች ቀርበው አራቱ ከክስ ነጻ ተብለዋል። ሌሎቹ ወታደሮች ደግሞ የ10 ዓመት እስራት ተፈርዶባቸዋል።

    የአገሪቱ ጦር እንዳለው ወታደሮቹ ፍርድ ቤት የቀረቡት በምሥራቅ ዴሞክራቲክ ኮንጎ ከታጣቂዎች ጋር እየተካሄደ ካለው ውጊያ ጋር በተያያዘ የወታደሮችን ሥነ ምግባርን ለማሻሻል ነው።

    አካባቢው ለዓመታት በግጭት እና በውጊያ ሲናጥ ቆይቷል። የመንግሥት ኃይሎች ከታጣቂው ኤፍአርኤን እና የአማጺያን ጥምረት ከሆነው ኤም23 ጋር እየተዋጉ ይገኛሉ።

    ወታደሮቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ከኤፍአርኤን ጋር ውጊያ ሲካሄድ የተመደቡበትን ሥምሪት ጥለው ሄደዋል በሚል በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 20 ነበር።

    የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጦር ከኤም23 ጋር የሚያደርገው ውጊያ በሠራዊቱ ውስጥ ባለው የሥነ ምግባር ጉድለት ምክንያት ፈተና እንደገጠመው ተገልጿል።

    ጎረቤት አገር ሩዋንዳ አማጺ ቡድኑን በመደገፍ ብትወነጀልም ክሱን አስተባብላለች።

  2. አውስትራሊያ ከቁጥጥር በሚወጣ ኤአይ ጉዳይ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችን ልትከስስ ነው

    አንቶኒ አልባኔዝ

    አውስትራሊያ አዲስ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) መቆጣጠሪያ ልትዘረጋ መሆኑን አስታወቀች።

    ከቁጥጥር ውጭ የሚሆን ኤአይን በተመለከተም የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ላይ ክስ እንደሚመሠረት ተገልጿል።

    የኦፕንኤአይ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ኤጀንቶች የአውስትራሊያ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን መጥለፋቸው (ሀክ ማድረጋቸው) ከተሰማ አንድ ወር ይሆነዋል።

    መስከረም ላይ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኔዝ እንደተናገሩት፤ ከቁጥጥር የወጡ የኦፕንኤአይ ኤጀንቶች የአገሪቱን የጤና ድረ ገጽ ጨምሮ ሌሎችም ድረ ገጾችን ጥሰው ገብተዋል።

    ኦፕንኤአይ ስለ ክስተቱ ለአውስትራሊያ መንግሥት መረጃ ባለመስጠቱም ወቅሰዋል።

    ክስተቱ ላይ ምርመራ ከተደረገ በኋላ 18 ነጥቦች ያሉት ምክረ ሐሳብ ቀርቧል። ይህም አዲስ የኤአይ ደኅንነት መቆጣጠሪያ መንገድን ያካትታል።

    የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በዚህ መቆጣጠሪያ መርሕ መመራት ይጠበቅባቸዋል። ኤአይ ድረ ገጾችን ሀክ ሲያደርግ ጥቆማ የመስጠት ግዴታ ተጥሎባቸዋል።

    “ሕጉ በፍጥነት እየተለወጠ ካለው ዓለም ጋር አብሮ መሄድ መቻል አለበት” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

    • ተጨማሪ ዜናዎች
  3. ሩሲያ እና ዩክሬን “መለሳለስ በታየበት ሁኔታ” ወደ ሰላም ንግግር መመለሳቸው ተገለጸ

    የዩክሬን ወታደር

    ጦርነቱ ከተጠናቀቀ በኋላ የዩክሬንን ምሥራቃዊ ክፍል የሚቆጣጠረውን አካል በተመለከተ “የተለሳለሰ አቋም ያሳዩት” ሞስኮ እና ኪቭ ወደ ሰላም ንግግር መመለሳቸውን የአሜሪካ ባለሥልጣናት አስታወቁ።

    አሜሪካ፣ ሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነቱን ለማስቆም ከጥር ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የሦስትዮሽ ውይይት አድርገዋል።

    የሦስቱ አገራት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በአቡ ዳቢ የተገናኙት ጦርነቱ አምስተኛ ዓመቱን በያዘበት ወቅት ነው።

    የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አማች ጃሬድ ኩሽነር እና የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ስቲቭ ዊትኮፍ እንደገለጹት፤ ከጦርነቱ በኋላ ስለሚኖረው የደኅንነት ሁኔታ ውይይት ተደርጓል።

    ኩሽነር በኤክስ ገጻቸው “ዋናው ነገር ሁሉም ወገኖች ከጦርነቱ በኋላ ምን እንደሚመጣ እንዲያስቡ ማበረታታት ነው” ብለዋል።

    ሆኖም ግን ሞስኮ እና ኪቭ በቅድሚያ ጦርነቱን ማስቆምን በተመለከተ አንዳች ስምምነት ላይ አልደረሱም።

    በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ዋነኛ ልዩነት የዶንባስክ ግዛት አስተዳደር ጉዳይ ነው። በምሥራቅ ዩክሬን የሚገኘው ዶንባስክ አሁን ላይ በአብዛኛው በሩሲያ ቁጥጥር ሥር ይገኛል።

    በኪቭ ቁጥጥር ሥር ያለውን የዶንባስክ ክፍል ሩሲያ መያዝ ትፈልጋለች። ዩክሬን በበኩሏ ይህ አካባቢ ደኅንነቷን ለመጠበቅ ቁልፍ መሆኑን ትገልጻለች።

  4. ትራምፕ የኢራን ጦርነት “በወታደራዊ ደረጃ በስኬት እንደተገባደደ” እና ተጨማሪ ጥቃት እንደማይፈጸም ተናገሩ

    ትራምፕ

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኢራን ጦርነት “በወታደራዊ ደረጃ በስኬት እንደተገባደደ” ተናገሩ።

    ጦርነቱን ለመቋጨት እየተደረጉ ያሉ ድርድሮች “አወንታዊ ውጤት” እያመጡ መሆኑን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ ተጨማሪ ጥቃት ሊፈጸም የሚችልበት ዕድል እንደሌለም አክለዋል።

    “ነባሩን ሁኔታ እያስጠበቅን ነው። ይሄንን የምናደርገውም የጎረቤት አገራት ፍላጎት ስለሆነ ነው” ብለዋል።

    በዋይት ሀውስ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ ኢራን ላይ አዲስ ጥቃት ሊከፈት የሚችልበት ዕድል “በጣም ጠባብ” መሆኑን ቢናገሩም፤ ሁኔታዎች ከተለወጡ “ታጥቀው በተጠንቀቅ እንደሚጠብቁ” ገልጸዋል።

    ትራምፕ ከዚህ ቀደምም ጦርነቱን ስለመግታት ቢናገሩም የኢራን ባለሥልጣናት ጥርጣሬ እንዳላቸው አስታውቀዋል።

    ጦርነቱ አክትሟል ብለው በይፋ የማያውጁበትን ምክንያት የተጠየቁት ትራምፕ “ኢራን ለአንዳንድ የባሕረ ሰላጤው አገራት አሁንም ስጋት ናት” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

    አሜሪካ በኢራን ወደቦች ላይ የጣለችው የእንቅስቃሴ ገደብ የቀጣናውን ደኅንነት ለማስጠበቅ ያለመ መሆኑን ጠቅሰውም፤ “በአካባቢው ታላቅ አጋሮች አሉን። እንዳይጎዱ መጠበቅ አለብን” ብለዋል።

    ፕሬዝዳንቱ ትናንት ሰኞ ከኳታሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ሼኽ መሐመድ ቢል አብዱል ራሕማን አል ታሒኒ ጋር በዋይት ሀውስ ተወያይተዋል።

    ጦርነቱን ለማቆም “ድንቅ ንግግር” አድርገናል ሲሉም ገልጸውታል።

    የኳታሩ ጠቅላይ ሚኒስትርም በኤክስ ገጻቸው “አወንታዊ ውይይት” መከናወኑን አስታውቀዋል።

  5. የአውሮፓውያኑ 2026 ከመቼውም ጊዜ በላይ ሞቃታማው ዓመት እንደሚሆን ሳይንቲስቶች ተነበዩ

    ሰደድ እሳት

    የዓለም የሙቀት መጠን ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍ ያለበት ዓመት የአውሮፓውያኑ 2026 ሊሆን እንደሚችል ሳይንቲስቶች አስጠንቅቀዋል።

    የአየር ንብረት ለውጥ እና የኤል-ኒኖ ክስተት ለሙቀት መጨመሩ እንደ ምክንያት ተጠቅሰዋል።

    ይህ ማስጠንቀቂያ የተሰጠው የተባበሩት መንግሥታት 31ኛው የአየር ንብረት ጉባኤ (COP31) በቱርክ በተጀመረበት ወቅት ነው።

    ትንበያውን ይፋ ያደረገው በአሜሪካ የሚገኘው ገለልተኛው የበርክሌይ ኧርዝ የምርምር ተቋም፣ ዓመቱ ሊያበቃ ሁለት ወራት ቢቀሩትም 2026 እ.ኤ.አ. በ2024 የተመዘገበውን የሙቀት መጠን ክብረወሰን በመስበር ከመቼውም ጊዜ በላይ ሞቃታማው ዓመት እንደሚሆን 95 በመቶ እርግጠኛ መሆኑን ገልጿል።

    የሙቀት መጨመሩ ተፅዕኖ በቅርብ ወራት በኮፕ ጉባኤው በሚሳተፉ አገራት ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ታይቷል።

    በአውሮፓ ሰፊ የደን ቃጠሎዎች፣ በኔፓል ድንገተኛ የበረዶ ግግር በመደርመሱ ከ1,000 በላይ ሰዎችን ለሞት መዳረጉን ጨምሮ ከባድ ተፅዕኖዎችን አሳይቷል።

    የተባበሩት መንግሥታት የዓለም የሚቲዮሮሎጂ ድርጅት በበኩሉ ባለፈው ሰኞ ይፋ ባደረገው ሪፖርት፣ ከበርክሌይ ኧርዝ ትንበያ የበለጠ ጥንቃቄ የተሞላበት ግምት ቢያቀርብም፣ 2026 ከመቼውም ጊዜ በሙቀት ከፍተኛ ከተመዘገቡት አራት ዓመታት መካከል እንደሚሆን ተንብዮአል።

    ድርጅቱ እ.ኤ.አ. በ2027ም የሙቀት መጨመሩ እንደማይቀንስ ገልጿል። ከወትሮው በበለጠ ኃይለኛ የሆነው የኤል-ኒኖ ክስተት ወደሚቀጥለው ዓመት የሚዘልቅ በመሆኑ የዓለም ሙቀት የበለጠ እንደሚጨምር አመልክቷል።

  6. ትራምፕ በሚቀጥለው ሳምንት ከቻይና እና ሩሲያ ፕሬዝዳንቶች ጋር እንደሚወያዩ ተናገሩ

    ትራምፕ

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ በሚቀጥለው ሳምንት በቻይና በሚካሄደው የኤዥያ እና ፓስፊክ የኢኮኖሚ ትብብር (APEC) ጉባኤ ጎን ለጎን፣ ከቻይናው እና ከሩሲያው አቻዎቻቸው ጋር እንደሚወያዩ ተናገሩ።

    ከፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ እና ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር የሦስትዮሽ ስብሰባ እንደሚያደርጉ እንደሚጠብቁ ትራምፕ ገልጸዋል።

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፣ በስብሰባው ከኢራን ጋር ያለውን ጦርነት ማስቆም እና የኒውክሌር መሣሪያ ትጥቅ ቅነሳን ጨምሮ የተለያዩ ጉዳዮች ይነሳሉ።

    ዎል ስትሪት ጆርናል ከዚህ ቀደም ባወጣው ዘገባ፣ ቭላድሚር ፑቲን ከዶናልድ ትራምፕ እና ዢ ጂንፒንግ ጋር በመገናኘት በዩክሬን ሰላም ማስፈን ላይ ለመወያየት ፍላጎት እንዳሳዩ ገልጾ ነበር።

    በሌላ በኩል፣ የቻይና መንግሥት ለመካከለኛው ምሥራቅ ጉዳዮች ልዩ መልዕክተኛ ዣይ ጁን ወደ ቴህራን በመጓዝ፣ ከኢራን ጠቅላይ ብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ምክትል ጸሐፊ አሊ ባገሪ ጋር ተገናኝተው ውይይት አድርገዋል።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እስማኤል ባጋኢ እንደገለጹት፣ የቻይናው ልዩ መልዕክተኛ ጉብኝት በቴህራን እና ቤጂንግ መካከል በሁለትዮሽ ጉዳዮች፣ በቀጠናዊ ደኅንነት እና በዓለም አቀፍ ሁኔታዎች ዙሪያ የሚደረገው ቀጣይ የቅርብ ምክክር አካል ነው።

  7. በዩክሬን ጦርነት ለመሳተፍ ከደቡብ አፍሪካ ሊወጡ የነበሩ ግለሰቦች ታሰሩ

    ወታደር

    ዘጠኝ የውጭ አገር ዜጎች በዩክሬን ጦርነት ለመሳተፍ ከደቡብ አፍሪካ ሊወጡ ሲሉ መያዛቸውን ፖሊስ አስታወቀ።

    በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሰዎች ዕድሜያቸው ከ20 እስከ 26 ይደርሳል። የተያዙት ትናንት እሑድ ጠዋት በጆሀንስበርግ መሆኑም ተገልጿል።

    ከደቡብ አፍሪካ የሚወጣ አውሮፕላን ለመሳፈር እየተዘጋጁ ሳለ መያዛቸውን የአገሪቱ ባለሥልጣናት ተናግረዋል። መዳረሻቸው የት እንደሆነ ግን ግልጽ አልነበረም።

    ያለ መንግሥት ፈቃድ ቅጥረኛ ተዋጊ መሆን የተከለከለ በመሆኑ ዘጠኙ ግለሰቦች የአገሪቱን ሕግ በመጣስ ተከስሰዋል።

    በደቡብ አፍሪካ ትልቁ በሆነው አውሮፕላን ማረፊያ እንዲሁም በርማ በሚባል ሆቴል ውስጥ በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

    ግለሰቦቹን በመያዝ ሒደት ውስጥ ኢንተርፖልም መሳተፉ ተገልጿል።

    የተያዙት ሰዎች በየአገራቸው ያሉ ሕግጋትን በመጣሳቸው ኢንተርፖልን ማሳተፍ እንዳስፈለገ ፖሊስ አስታውቋል።

    ዘጠኙ ግለሰቦች ከየትኞቹ አገራት እንደመጡ ፖሊስ ይፋ ለማድረግ አልፈቀደም። ሊዋጉ ያቀዱት በዩክሬን ወይም በሩሲያ በኩል ስለመሆኑም አልተገለጸም።

    ጉዟቸውን ስላመቻቸው ተቋም ግልጽ መረጃ አልተሰጠም።

  8. በኬንያ 454 ኪሎ ግራም ሜታምፌታሚን የተሰኘ አደንዛዥ ዕጽ ተያዘ

    የኬንያ ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ያዋለው አደንዛዥ ዕጽ

    የኬንያ ፖሊስ ዓለም አቀፍ የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር መረብን ለማክሸፍ በተካሄደ ዘመቻ 454 ኪሎ ግራም ሜታምፌታሚን መያዙን አስታወቀ። የተያዘው ዕፅ ዋጋ 27 ሚሊዮን ዶላር ያህል እንደሚገመት ተገልጿል።

    በኬንያ የባሕር ዳርቻ አካባቢ በተካሄደ በመረጃ ላይ የተመሠረተ ዘመቻ፣ ሁለት ታንዛኒያውያንና አንድ ኡጋንዳዊን ጨምሮ ሦስት ተጠርጣሪዎች ተይዘዋል። ዘመቻው የተካሄደው በኬንያ ፀረ-አደንዛዥ ዕፅ ኃላፊዎችና በታንዛኒያ አቻዎቻቸው ትብብር ነው።

    ፖሊስ እንዳስታወቀው ምርመራው የተጀመረው ታንዛኒያ ውስጥ አንድ ቁልፍ ተጠርጣሪ ተይዞ ለኬንያ ባለሥልጣናት ተላልፎ ከተሰጠ በኋላ ነው።

    ሜታምፌታሚን ወይም “ሜት” በመባል የሚታወቀው በጣም ከፍተኛ ሱስ አስያዥ ሰው ሠራሽ ዕፅ ሲሆን፣ ለከባድ የአእምሮ መታወክ፣ ለልብ ድካም እና ለድንገተኛ የአንጎል ደም መፍሰስ ሊዳርግ ይችላል።

    ባለሥልጣናት እንዳሉት ተጠርጣሪው በታንዛኒያ ከተያዘው 250 ኪሎ ግራም የሚጠጋ ሜታምፌታሚን እና ኮኬይን ጋር ግንኙነት አለው ተብሏል። ግለሰቡ መርማሪዎችን በኬንያ የባሕር ዳርቻ በሚገኘው ምሳምቤኒ ወደሚገኝ ስፍራ በመምራት ዕፁ በቁጥጥር ሥር ሊውል ችሏል።

    በቦታው ተጨማሪ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ሲውሉ፣ ሁለት መኪኖች እና አንድ ሞተር ሳይክል ተወርሰዋል።

    ተጠርጣሪዎቹ በአሁኑ ጊዜ በእስር ላይ የሚገኙ ሲሆን በቅርቡ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

    ፖሊስ ዘመቻው አሁንም እንደቀጠለ በመግለጽ ነዋሪዎች የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውርን ለመታገል የሚያግዝ መረጃ በማቅረብ የጸጥታ አካላትን እንዲያግዙ ጥሪ አቅርቧል።

    ተያያዥ ዜናዎች፡

  9. በሴኔጋል ባሕር ዳርቻ ላይ የስደተኞች ጀልባ ተገልብጦ ቢያንስ 39 ሰዎች ሞቱ

    ስደተኞች የተሳፈሩባት መናኛ ጀልባ በነፍስ አድን ሰራተኞች ጀልባ ስትጎተት

    አውሮፓ ለመግባት ያለሙ ስደተኞችን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረ ጀልባ በሰሜን ሴኔጋል በምትገኘው ክብመር የባሕር ዳርቻ ላይ ተገልብጦ ቢያንስ 39 ሰዎች መሞታቸውን ባለሥልጣናትን ጠቅሶ የአገሪቷ መገናኛ ብዙኃን ዘገበ።

    በመንግሥት የሚተዳደረው ሴኔጋል ፕረስ ኤጄንሲ እንደዘገበው እስካሁን የ34 ሰዎች አስክሬን ተገኝቷል።

    የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴርም ከትናንት በስቲያ ጥቅምት 28፣ 2019 ዓ.ም በደረሰው የጀልባ አደጋ የ39 ሰዎችን አስክሬን ማውጣቱን እና የአንድ ስደተኛን ሕይወት ማትረፍ እንደተቻለ ገልጿል።

    ሚኒስቴሩ የፍለጋ እና የነፍስ አድን ሥራው መቀጠሉንም ጠቅሶ፣ ደብዛቸው የጠፋ ሰዎች ቁጥር አይታወቅም ብሏል።

    ከእንጨት የተሰራው መናኛ ጀልባ አደጋው የደረሰበት በሴኔጋል ዋና ከተማ ዳካር እና በሰሜናዊቷ ከተማ ሴንት ሉዊስ መካከል በሚገኝ ሥፍራ ሲሆን ወደ ስፔን ካናሪ ደሴቶች እያመራ ነበር።

    የሴኔጋል የውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሙሃማዱ ማክታር ሲሴ ዛሬ የአደጋውን ሥፍራ እንደሚጎበኙ ይጠበቃል። የአገሪቱ ፕሬዚደንት ባሲሮ ዲኦማየ ፋየ በአደጋው ለሞቱት ቤተሰቦች የተሰማቸውን ሃዘን ገልጸዋል።

    አደጋው ያጋጠመው ስደተኞች ወደ ካናሪ ደሴቶች ለመግባት አዲስ ሙከራዎችን እያደረጉ ባለበት ወቅት ነው።

    የስፔን ባለሥልጣናት ወደ ደሴቶቹ የሚገቡ ስደተኞች እየጨመረ በመምጣቱ ቅዳሜ ዕለት አስቸኳይ ጊዜ አውጀዋል።

    በአትላንቲክ ውቅያኖስ ወጀብ ይከሰታል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ይህም አሁንም ባሕር ላይ ላሉ ስደተኞች አስቸጋሪ ያደርግባቸዋል ተብሎ ተሰግቷል።

    እንደ ባለሥልጣናቱ ከሆነ ባለፉት ሰባት ቀናት ብቻ ከ3 ሺህ 300 በላይ ስደተኞች በ30 ጀልባዎች ደሴቷ ደርሰዋል።

    የስፔን የውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደገለጸው ከአውሮፓውያኑ ጥር እስከ ጥቅምት 2026 ባሉት ጊዜያት 13 ሺህ 327 ስደተኞች ባሕር አቋርጠው ወደ ደሴቶቹ ገብተዋል።

    ተያያዥ ዜና፡

  10. በፖላንድ ስድስት ሰዎችን ገድሏል የተባለው ተጠርጣሪ በሆስፒታል ውስጥ ሕይወቱ አለፈ

    የፖላንድ ፖሊስ

    የፖላንድ ሁለተኛዋ ከተማ በሆነችው ክራኮው ስድስት ሰዎችን በመግደል የተጠረጠረው ግለሰብ በሆስፒታል ውስጥ ሕይወቱ አለፈ።

    በክራኮው ጽንፈኛ የፖለቲካ አመለካከት እንዳለው በሚጠረጠር በዚህ ግለሰብ በተፈጸመ ጥቃት 6 ሰዎችን ሲገደሉ 16 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸው ተገልጿል።

    ከተገደሉት መካከል አራት ሴቶች እና ሁለት ወንዶች ይገኙበታል። ሦስቱ የፖላንድ ዜጎች ሲሆኑ፣ አንዱ የብሪታንያ ዜጋ ነው ተብሏል።

    ከ16ቱ ቁስለኞች መካከል ሁለት ፖሊሶች እና ከኦስትሪያ፣ ጀርመን፣ ፖርቹጋል፣ ሩሲያ እና ብሪታንያ የመጡ የውጭ ዜጎች ይገኙበታል። ከፖሊሶቹ አንዱ ከባድ ጉዳት እንደደረሰበት ተገልጿል።

    የ24 ዓመት ዕድሜ ያለው ፖላንዳዊው ተጠርጣሪ ከፖሊስ ጋር የተኩስ ልውውጥ ካደረገ ቆስሎ ተይዞ ወደ ሆስፒታል የተወሰደ ቢሆንም ሕይወቱ ግን እዚያው አልፏል።

    የአገሪቱ ባለሥልጣናት ግለሰቡ ስለሞተበት ምክንያት ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ ባይሰጡም፣ በግድያዎቹ ላይ የተጀመረው ምርመራ እንደቀጠለ መሆኑን አረጋግጠዋል።

    በተኩስ ጥቃቱ ስድስት ሰዎች ሲገደሉ፣ በርካታ ሌሎች ደግሞ ቆስለዋል። ጥቃቱም ባለሥልጣናት የአደጋውን መነሻ ለማወቅ ሰፊ የጸጥታ ዘመቻ እንዲያካሂዱ አስገድዷል። የፖላንድ ባለሥልጣናት ክስተቱን በቅርብ ዓመታት ከታዩት በከባድ የጦር መሣሪያ ከታገዙ ጥቃቶች ሁሉ ከባዱ በማለት ገልጸውታል።

    መርማሪዎች በወንጀል ቦታውና ከተጠርጣሪው ጋር ተያይዘው በተለያዩ ቦታዎች የተሰበሰቡ ማስረጃዎችን መመርመራቸውን ቀጥለዋል።

    ዓቃቤ ሕግ ቢሮም ተጠርጣሪው ድርጊቱን ብቻውን ፈጽሟል ወይስ ሌሎች ተባባሪዎች ነበሩት የሚለውን እንዲሁም ወደ ጥቃቱ ያደረሱትን ምክንያቶች ለማጣራት እየሠራ ነው።

    የአገሪቱ የፖለቲካ መሪዎችና የማኅበረሰብ አባላት ለሟቾች ቤተሰቦች የሐዘን መልዕክት በመላክ ለተጎጂዎች ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።

    ተያያዥ ዜናዎች፡

  11. ከኢራን ጋር የሚደረገው ድርድር እንቅፋት በገጠመበት ወቅት ትራምፕ ከኳታሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር በዝግ ሊነጋገሩ ነው

    የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ እና የኳታሩ ጠቅላይ ሚኒስትር አል ታኒ

    የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ከኳታሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ሞሐመድ ቢን አብዱልራህማን አል ታኒ ጋር በዋሽንግተን በዝግ ሊነጋገሩ እንደሆነ ዋይት ሐውስ አስታወቀ።

    ትራምፕ የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርም በመሆን እያገለገሉ ካሉት አል ታኒ ጋር ዛሬ ሰኞ በዝግ እንደሚነጋገሩ አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣንን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል።

    እንደ ባለሥልጣኑ ከሆነ የአሜሪካው ምክትል ፕሬዚደንት ጄዲ ቫንስም ከኳታሩ መሪ ጋር ይገናኛሉ።

    መሪዎቹ ውይይቱን የሚያካሂዱት የኢራንን ጦርነት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመቋጨት የሚደረገው ጥረት እንቅፋት በገጠመው ወቅት ነው።

    ዋይት ሐውስ መሪዎቹ የሚወያዩባቸው አጀንዳዎች ምን እንደሆኑ አልጠቀሰም። ውይይቱ ቀድሞ ከተገለጸው የጉዞ እገዳ ጋር የተያያዘም አይመስልም።

    ኳታር ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በቴህራን እና በዋሽንግተን መካከል ዋነኛ አደራዳሪ ሆናለች።

    የስምምነት እቅዶችን በማስተላለፍ እና በኢራን የኑክሌር ፕሮግራም ላይ ያሉ ልዩነቶችን ለመፍታት እና ግጭቱን ለማቆም እንደ ድልድይ በመሆን እያገለገለች ነው።

    የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ እሁድ ዕለት ከኢራን ጋር የሚደረገው ድርድር "ትንሽ ለውጥ" እንዳሳየ ገልጸዋል።

    ሩቢዮ በፓሪስ ለሚካሄደው የቡድን ሰባት አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ለማቅናት ከፍሎሪዳ ሲነሱ "ትራምፕ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ እንደሚመርጡ" ተናግረዋል።

    ሆኖም ኢራን "ተቀባይነት የሌለው" እና በአንዳንድ ሁኔታዎች "አስቂኝ እና የሚያስቆጡ እንዲሁም ተጨባጭ ያልሆኑ ፍላጎቶች" አሏት ብለዋል።

    ተያያዥ ዜና፡

  12. ትራምፕ ድርድሩ እስከቀጠለ ድረስ በኢራን ላይ አዲስ ጥቃት የማዘዝ ዕድሉ እጅግ ዝቅተኛ ነው አሉ

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር የሚደረገው ድርድር እስከ ቀጠለ ድረስ አዲስ ጥቃት እዲፈጸም የማዘዝ ዕድላቸው አነስተኛ መሆኑን ተናገሩ።

    ትራምፕ እሁድ ዕለት እንደተናገሩት፣ ግጭቱን ለማስቆም የሚደረገው ውይይት መሻሻል እያሳየ ከሆነ በኢራን ላይ አዲስ ወታደራዊ ጥቃቶችን የማዘዝ ዕድላቸው “እጅግ ዝቅተኛ” መሆኑን ገልጸዋል።

    ትራምፕ ለሲኤንኤን በስልክ በሰጡት ቃለ ምልልስ፣ “ጉዳዩ በጣም ጠንካራ ስምምነት ይፈርሙ አይፈርሙ በሚለው ላይ የተመሠረተ ነው። መልሱ ግን ያ አስፈላጊ የሚሆንበት ዕድል እጅግ ዝቅተኛ ነው” ብለዋል።

    ሲኤንኤን ትራምፕን በትክክል ምን እንደጠየቀ ባይገልጽም፣ ፕሬዚዳንቱ ጥቃቶች እንደገና ከተጀመሩ አሜሪካ ልትመታቸው የምትችላቸውን የመሠረተ ልማት ዒላማዎች አስቀድማ ለይታለች ብለዋል። "38 ድልድዮችን ጨምሮ በአንድ ሰዓት ውስጥ ልናፈርሳቸው እንችላለን” ሲሉም ተናግረዋል።

    በኋላ በትሩዝ ሶሻል የማኅበራዊ ገጻቸው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ “አይረን ጌት የተባለው ግብረ ኃይል” በኢራን ላይ ሙሉ በሙሉ ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል።

    ሮይተርስ ዘመቻው ኢራን የጦር መሣሪያና ሌሎች ማዕቀብ የተጣለባቸውን ቁሳቁሶችን በየብስ ድንበሮቿ እና በካስፒያን ባሕር በኩል እንዳታጓጉዝ ለማገድ ያለመ ነው።

    ትራምፕ ከአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ በኋላ በሰጡት ቃለ ምልልስ የኢራን ጦርነት ሪፐብሊካኖች በምርጫው እንዲሸነፉ ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ ነው ሲሉ ምክትል ፕሬዚዳንት ጄዲ ቫንስ ግን “የተሸነፍንበት ምክንያት ጦርነቱ ነው” በማለት ግልጽ አቋም ወስደዋል።

    ትራምፕ እሁድ ዕለት ለጋዜጠኞች “ብዙ ሰዎች ቫንስ ስለ ኢራን የሰጡትን አስተያየት አልወደዱትም” ብለዋል።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በበኩላቸው፣ በጦርነቱና በምርጫ ውጤቱ መካከል ግንኙነት ስለመኖሩ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።

    ሩቢዮ “መናገር የምችለው አንድ ነገር ቢኖር፣ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ለረዥም ጊዜ የነበረን እውነተኛ ስጋት ለይተው ተገቢውን እርምጃ ወስደዋል” ሲሉ ተናግረዋል።

    ጦርነቱን ለማስቆም እየተገደረጉ ስላሉ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች በተመለከተም፣ ወዲያውኑ መፍትሄ ይገኛል ብለው እንደማያምኑ ገልጸዋል።

    “ፕሬዚዳንቱ ሁልጊዜ ይህንና ሌሎች ችግሮችን በዲፕሎማሲ መፍታትን ይመርጣሉ። አንዳንድ ጊዜ ግን ይህ አይቻልም። ዕድሉ ካለ እንመረምረዋለን። ነገር ግን እስካሁን ሂደቱ ፍሬያማ አልሆነም፤ ምክንያቱም የኢራን ጥያቄዎች ተቀባይነት የሌላቸው ብቻ ሳይሆኑ፣ በአንዳንድ ሁኔታዎች የተጋነኑ፣ የማይጨበጡ እና ከእውነታው የራቁ ናቸው” ብለዋል።

    ትራምፕ ምርጫው ካለፈ በኋላ በኢራን ላይ ሰፊ ጥቃት እንደሚጀምሩ ፍንጭ ሲሰጡ ቢቆዩም፣ እስካሁን ትልቅ የአሜሪካ ወታደራዊ ዘመቻ የሚጀመረበት ምልክት አልታየም።

    ኢራን በበኩሏ ውጊያው ከቀጠለ በአሜሪካ እና በእስራኤል ዒላማዎች ላይ ጥቃት እንደምትፈጽም አስጠንቅቃለች።

    በተጨማሪም፣የኢራን ሚዲያዎች ቅዳሜ በደቡባዊ ኢራን የተሰሙት ፍንዳታዎች ከአሜሪካ ጥቃት ሳይሆን ከኢራን ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ጋር የተያያዙ እንደነበሩ ዘግበዋል።

    ተያያዥ ዜናዎች፡

  13. ኢራቅ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ነዳጅ ለመላክ ከአሜሪካ ጋር ተስማማች

    የጭነት መርከብ

    የኢራቅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፉአድ ሁሴን አገራቸው በኦማን አቅራቢያ በሚገኘው የሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ነዳጅ መላኳን እንድትቀጥል ከአሜሪካ ጋር መስማማቷን ገለጹ።

    ሁሴን እንደተናገሩት በኢራን ጦርነት የተነሳ ነዳጅ ለውጭ ገበያ ማቅረብ ላይ በተፈጠሩ መስተጓጎሎች የተነሳ ኢራቅ 60 ቢሊዮን ዶላር ከስራለች።

    ኢራቅ ለውጭ ገበያ የምታቀርበው ነዳጅ በጥቅምት ወር መሻሻል ማሳየቱንም ሚኒስትሩ ጨምረው ገልጸዋል።

    የኢራቅ የኢነርጂ ዘርፍ ኃላፊዎች እንዳሉት በመስከረም ወር አገሪቱ በቀን ትልክ ከነበረው 2.65 ሚሊዮን በርሜል በጥቅምት ወር ወደ 3.5 ሚሊዮን በርሜል አድጓል።

    ሚኒስትሩ በተጨማሪም የአሜሪካ ገንዘብ ሚኒስቴር በቴህራን ላይ የሚደረገውን የኢኮኖሚ ጫና ለማሳደግ ኢራቅ ከኢራን ጋር ያላትን ሁሉንም የድንበር መሻገሪያዎች እንድትዘጋ ተጠይቃለች ብለዋል።

    ሁለት ክፍት ሆነው እንዲቆዩ ከተፈቀደላቸው የድንበር መሻገሪያዎች አንዱ በኩርዲስታን ክልል የሚገኝ መሆኑንም ገልጸዋል።

    ተያያዥ ዘገባዎች፡

  14. ሶሪያ ወታደሮቿን ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለመላክ እየተዘጋጀች ነው

    የሶሪያ እና የሳዑዲ አረቢያ ባለሥልጣናት

    ሶሪያ ወታደሮቿን ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለመላክ እና በየመን ድንበር አካባቢ በማሰማራት አገሪቱ ከሁቲ አማፂያን ጋር በምታደርገው ውጊያ ድጋፍ ለመስጠት መስማማቷን ዕቅዱን በቅርበት የሚያውቁ ሦስት ባለሥልጣናት ለአሶሼትድ ፕሬስ ተናገሩ።

    የፈረንሳይ የዜና ወኪል አንድ የቀጣናው ባለሥልጣን እና ሁለት የሶሪያ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ እንደዘገበው የሶሪያ ወታደራዊ አማካሪዎች አስቀድመው ወደ ሳዑዲ አረቢያ አቅንተዋል።

    በጉዳዩ ላይ ለመናገር ፍቃድ እንዳልተሰጣቸው የተናገሩት እነዚህ ባለሥልጣናት ሥማቸው እንዳይገለጽ ጠይቀው እስካሁን ምንም ተዋጊ ኃይል ወደ የመን አልተላከም ብለዋል።

    የሳዑዲ አረቢያ ባለሥልጣናት በጉዳዩ ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።

    በየመን ውስጥ በሁቲ አማፅያንና በሳዑዲ በሚደገፉት የመንግሥት ኃይሎች መካከል እየተደረገ ያለው ውጊያ ተባብሶ ቀጥሏል።

    ሁቲዎች በሳዑዲ አረቢያ ውስጥ በቀጥታ ጥቃቶችን መፈጸማቸውም ተዘግቧል።

    በሳዑዲ እና በሁቲ አማፂያን መካከል ያለው ግጭት የተስፋፋው አሜሪካና እስራኤል ባለፈው ዓመት የካቲት ወር በኢራን ላይ ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ ነው።

    ሶሪያ በረዥም የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የተፈተኑ ተዋጊዎች ቢኖሯትም፣ እስካሁን በቀጣናው የተስፋፋውን ግጭት ከሩቅ ስትከታተል ቆይታለች።

    ሳዑዲ አረቢያ በአሜሪካ የተሰጧት ዘመናዊ የውጊያ አውሮፕላኖች እና የሚሳዔል መከላከያ ሥርዓቶች ቢኖሯትም ሁቲዎችን ማሸነፍ ግን አልቻለችም።

    ከሳዑዲ አረቢያ አጋሮች ብዙዎቹ በሁቲዎች ላይ በምታደርገው ጦርነት የእግረኛ ጦር ለማሰማራት ፈቃደኛ ባይሆኑም፣ የሶሪያ መንግሥት ከአገሪቱ ጋር ያለው ግንኙነት የተለየ መሆኑ ይጠቀሳል።

    ሳዑዲ አረቢያ በሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት ለተለያዩ የተቃዋሚ ኃይሎች የገንዘብ ድጋፍ ታደርግ የነበረ ሲሆን፣ ከጦርነቱ በኋላ ለሚደረገው የሶሪያ መልሶ ግንባታም አገሪቱ በእጅጉ የምትፈልገውን የገንዘብ ድጋፍ እንደምትሰጥ ቃል መግባቷ ተነግሯል።

    አንድ የሶሪያ ባለሥልጣን እንደገለጹት፣ በመጀመሪያ ዙር 600 የሚጠጉ የሶሪያ ልዩ ኃይል ተዋጊዎች በመጪው ሳምንት ወደ ሳዑዲ አረቢያ እንደሚንቀሳቀሱ ይጠበቃል።

    ባለሥልጣኑ አክለውም ወደ ሳዑዲ አረቢያ የሚላኩት ተዋጊዎች የሶሪያ ዜጎች ብቻ እንዲሆኑ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።

    በሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት ወደ አገሪቱ በመምጣት የተለያዩ አማፂ ቡድኖችን የተቀላቀሉ የውጭ ተዋጊዎች እንዳይካተቱም አጽንዖት ተሰጥቷል።

    በተጨማሪም፣ በ82ኛው ክፍለ ጦር አዛዥ ካሊድ ኻጣብ የተመራ የሶሪያ ልዑክ በቅርቡ ለሁለት ሳምንታት ወደ ሳዑዲ አረቢያ ጉብኝት ማድረጉን ገልጸዋል።

    ሁለተኛ የሶሪያ ባለሥልጣን በበኩላቸው፣ 36 የሶሪያ ወታደራዊ ኃላፊዎች በጂዳ የሚገኝን በሳዑዲና በየመን ባለሥልጣናት የሚተዳደር የጦር ዕዝና የኦፕሬሽን ማዕከል መጎብኘታቸውን ተናግረዋል። በዚያም ስለ ተለያዩ የውጊያ ግንባሮችና የኦፕሬሽን ቦታዎች ማብራሪያ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል።

    በውይይቶቹ ላይ እውቀት ያለው አንድ የክልሉ ባለሥልጣን ደግሞ፣ ሶሪያ አስቀድማ “አነስተኛ ቁጥር” ያላቸው ወታደራዊ አማካሪዎችን ወደ ሳዑዲ አረቢያ ማሰማራቷን ገልጸዋል። እነዚህ አማካሪዎች በሳዑዲ ውስጥ የሚገኙ የየመን ኃይሎችን በማሰልጠን ላይ እንደሚሳተፉም ተነግሯል።

    ተጨማሪ ዘገባዎች፡

  15. የሰኞ የጥቅምት 30/ 2019 ዓ. ም. የቀጥታ ስርጭት ተጀምሯል

    የቢቢሲ አማርኛ ወዳጆች እንደምን አደራችሁ፤ የጥቅምት 30/ 2019 ዓ. ም. የቀጥታ ስርጭታችን ተጀምሯል።

    የአገር ውስጥ እና የውጭ ዜናዎችን በአጭሩ እናቀርብላችኋለን። እንድትከታተሉን በአክብሮት እንጋብዛለን።