ኦፌኮ የሞያሌ ከተማ ግጭትን በተመለከተ የፌደራል መንግሥት "ዝምታ መምረጡን" ተቸ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ለቀናት የቀጠለ ግጭት ባስተናገደችው ሞያሌ ከተማ ጉዳይ የፌደራል መንግሥት "ዝምታ መምረጡን" ተቸ።

ተቃዋሚው የፖለቲካ ፓርቲ ትናንት ቅዳሜ ጥቅምት 14/2019 ዓ. ም. ባወጣው መግለጫ፤ በሞያሌ ከተማ እና ቦረና ዞን ውስጥ "እየተባባሰ የመጣውን ጥቃት፣ የታጠቁ ኃይሎችን ሰርጎ መግባት እና ኢ-ሕገመንግሥታዊ የአስተዳደር ለውጦችን" በጥብቅ አውግዟል።

ኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች በሚጋሯት የድንበር ከተማዋ ሞያሌ ባለፈው ሳምንት እሑድ ጥቅምት 8 የተጀመረው ግጭት የተቀሰቀሰው ከሶማሌ ክልል ባንዲራ መሰቀል በተያያዘ ነበር። በዚሁ ምክንያት አንዲት የ13 ዓመት ልጅ መገደሏ ግጭቱን አቀጣጥሎታል።

ከሐሙስ ዕለት ጀምሮ "በከባድ መሣሪያ የታገዘ" የተኩስ ልውውጥ እየተሰማ መቀጠሉን ባለፉት ቀናት ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል። መኖሪያ ቤቶች እና መደብሮችን ጨምሮ በርካታ ንብረቶች መቃጠላቸውንም ነዋሪዎቹ አስረድተዋል።

ቢቢሲ አርብ ዕለት ያነጋገራቸው አንድ ነዋሪ በዚያው ዕለት ብቻ ታጣቂዎች እና ንጹኃንን ጨምሮ ዘጠኝ ሰዎች መሞታቸውን ተናግረው ነበር። ቢቢሲ ይህንን ቁጥር ከሌሎች ምንጮች ማረጋገጥ አልቻለም።

የዜና ወኪሉ ሮይተርስ በተመመሳይ አርብ ዕለት ባወጣው ዘገባ፤ የተኩስ ልውውጥ በተደረገባቸው ቀናት "ቢያንስ ዘጠኝ ሰዎች" መገደላቸውን ጠቅሷል። አንድ የሞያሌ ሆስፒታል ምንጭን በመጥቀስም 30 ገደማ የተጎዱ ሰዎች ወደ ጤና ተቋሙ መምጣታቸውን ዘግቧል።

ይህንን ግጭት የሸሹ ቢያንስ 10 ሺህ ነዋሪዎች ወደ ኬንያ መሻገራቸውን የአገሪቱ የቀይ መስቀል ምንጭ እንደተናገሩ የፈረንሳዩ የዜና ወኪል ኤኤፍፒ ትናንት ባወጣው ዘገባ አመልክቷል።

ተቃዋሚው ፓርቲ ኦፌኮ ባወጣው መግለጫ፤ ባለፉት ሳምንታት "አሳሳቢ በሆነ ሁኔታ ጨምሯል" ላለው "የድንበር ጥሰት" ተጠያቂ ያደረገው "ከሶማሌ ክልል የመጡ" ሲል የገለጻቸውን ታጣቂ ቡድኖች ነው።

"ጉዳዩን ከሁሉ በላይ አሳሳቢ የሚያደርገው፣ በአንድ አገራዊ ገዢ ፓርቲ በሚመሩ ክልሎች መካከል የመንግሥት ታጣቂ ከቁጥጥር ዉጪ የወጣ በሚመስል መልኩ ወረራ መካሄዱ ነው" ሲል ተችቷል።

ለቀናት የዘለቀውን ግጭት በተመለከተ እስካሁን ድረስ በክልል ደረጃ ከኦሮሚያ እና ሶማሌ ባለሥልጣናት የተሰጠ አስተያየት የለም። ከፌደራል መንግሥት በኩልም አስተያየት አልተሰጠም።

ኦፌኮ በበኩሉ በአካባቢው ተፈጽመዋል ያላቸውን "መሬትን በኃይል የመያዝ፣ የቦረና ኦሮሞ አርብቶ አደሮችን የማፈናቀል እና የአስተዳደር ወሰኖችን በተናጠል የመቀየር ሙከራዎች" የገለጻቸው "ቀጥተኛ የሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ጥሰት" በማለት ነው።

"የኦሮሞ እና የሶማሌ ሕዝቦች ረዥም ጊዜ ያስቆጠረ ሰላማዊ አብሮ የመኖር፣ የንግድ እና የባህል ትስስር ታሪክ አላቸው" ያለው ኦፌኮ፤ የድንበር ውዝግቦች "በኃይል፣ በማስፈራራት ወይም በዘፈቀደ ባንዲራ በመስቀል ሊፈቱ አይችሉም" የሚል አቋም እንዳለው ገልጿል።

ፓርቲው አክሎም፣ "በቦረና ኦሮሞ ሕዝብ ላይ የሚሰነዘሩ በትጥቅ የታገዙ ጥቃቶች እና ወረራዎች በሙሉ በአስቸኳይ እንዲቆሙ" ጠይቋል።

ኦፌኮ በመግለጫው "ዝምታ" መርጧል ያለውን የፌደራል መንግሥትንም ተችቷል። "የፌደራል መንግሥት ከእንግዲህ ዝምታን መምረጥ ወይም ታሪካዊ ውስብስብ ጉዳዮችን እርምጃ ላለመውሰድ እንደ ምክንያት መጠቀም አይችልም" ብሏል።

"የንጹኃን ዜጎችን ደኅንነት የመጠበቅ" እንዲሁም "የአርብቶ አደሩን ማኅበረሰብ መፈናቀል የማስቆም ኃላፊነቱን መወጣት" እንዳለበትም አሳስቧል።

የኦሮሚያ ክልል ላይም ወቀሳ ያነሳው ኦፌኮ፣ የክልሉ መንግሥት "የነዋሪዎችን ደኅንነት መጠበቅ እና የኦሮሚያን ግዛት ማስከበር ባለመቻሉ ተጠያቂ ነው" ብሏል።

በ13 ዓመቷ ታዳጊ ሞት እና በሌሎችም ንጹኃን ዜጎች ላይ የደረሱት ጥቃቶችን በተመለከተ "ግልጽ፣ ገለልተኛ እና ፈጣን ምርመራ" እንዲካሄድ እንዲሁም "ትዕዛዝ የሰጡትን ጨምሮ በሁሉም እርከን የሚገኙ ፈጻሚዎች በሕግ እንዲጠየቁ" ጥሪ አቅርቧል።