ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ለመገንባት ከ30 በላይ ቦታዎች
ሲጠኑ መቆየታቸውን ገልጸው ሦስት ቦታዎች መለየታቸውን አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት ዛሬ ጥቅምት 11/2019 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ኒውክሌር ኃይል ኮሚሽንን በጎበኙበት ወቅት በሰጡት ማብራሪያ ላይ ነው።
ጠቅላይ
ሚኒስትሩ የኒውክሌር ቴክኖሎጂ አሁን ላይ የጥናት ቡድን ተዋቅሮ፣ ተቋሙ በሕግ ተመሥርቶ፣ መሪዎች
እና ባለሙያዎች ተመድበውለት፣ እንዲሁም የቢሮ እና የሰው ሀብት ዝግጅቱ ተጠናቅቆ ሙሉ ተቋማዊ ቁመና መያዙን ተናግረዋል።
አክለውም የኒውክሌር ፕሮጀክቱ የሚገነባበትን ቦታ ለማመቻቸት በሙያተኞች ከ30 በላይ ቦታዎች ሲጠኑ መቆየታቸውን ገልጸው፤ የጥናቱ ሂደት ደረጃ በደረጃ ወደ ሦስት ቦታዎች መለየታቸውን ይፋ አድርገዋል።
“ከ30 ወደ 13 ገደማ፣ ከዛ አምስት ከዚያ ሦስት እያሉ ቦታ ለይተዋል፤ እነዚህን
ቦታዎች እኛ ‘አፕሩቭ’ ማድረግ [ማጽደቅ] አንችልም” በማለት የውጭ ተቋማት የቦታውን አዋጭነት እና ለግንባታው ምቹነት ማረጋገጥ
እንደሚኖርባቸው ተናግረዋል።
የቦታው ምቹነት ከተረጋገጠ በኋላ ቦታውን የማዘጋጀት፣ ቴክኖሎጂውን ከሚሰጥ ተቋም
ጋር ስምምነት መፈራረም እንደሚኖር ተናግረዋል።
ሥራው እንደ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ አንዴ ኮንትራት ተሰጥቶ በአጭር ጊዜ የሚጠናቀቅ አለመሆኑን ያብራሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በርካታ ተቋማትን እና ዲፓርትመንቶችን የሚነካ፣ ሰፊ የሰው ሀብት እና ዝግጅት የሚጠይቅ የረጅም ጊዜ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ
ኒውክሌር ኃይል ኮሚሽንን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከሕዝብ ተወካዮች
ምክር ቤት አፈ ጉባዔ እና ሌሎች ኃላፊዎች ጋር በመሆን የጎበኙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ የትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት
ተቋሙ ለኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ የልማት ርዕይ ከፍተኛ
ስልታዊ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።
ኢትዮጵያ
እጅግ ከፍተኛ በሆነ እምቅ አቅሟ እና በተትረፈረፈ ተፈጥሯዊ ሀብቷ ለረጅም ጊዜ እንደምትታወቅ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲሱ ምዕራፍ
ደግሞ እነዚህን ሀብቶች ወደ ተጨባጭ ልማት፣ የቴክኖሎጂ እድገት እና ወደ ጋራ ብልጽግና መለወጥ ላይ ያተኮረ መሆኑን ጠቁመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ግንባታ እንደሚጀመር ይፋ ያደረጉት ጳጉሜ 4/2017 ዓ.ም. ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኢትዮጵያ ኒውክሌር ኃይል ኮሚሽን ለአገሪቱ የረዥም ጊዜ የልማት ርዕይ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት ለአጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ሽግግር ማዕከላዊ በመሆኑ፣ የኒውክሌር ቴክኖሎጂ እየጨመረ የመጣውን የኃይል ፍላጎት ለማሟላት ትልቅ ዕድል ይፈጥራል ሲሉም ተናግረዋል።
ቴክኖሎጂው ከኃይል ምርት ባለፈ በጤና፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በአካባቢ ጥበቃ ዘርፎች ለአገራዊ ልማት መሠረታዊ አስተዋጽኦ እንዳለውም በማብራሪያቸው ላይ ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ ዐሥር ዓመታት ውስጥ እያንዳንዳቸው 1 ሺህ 200 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያላቸው ሁለት የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ዩኒቶችን ለመገንባት ዕቅድ እንዳላት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተናግረዋል።
ይህ በድምሩ 2 ሺህ 400 ሜጋ ዋት ያመነጫል ተብሎ የታቀደው ፕሮጀክት፣ እንደ ውኃ፣ ፀሐይ እና ነፋስ ኃይል በወቅቶች መፈራረቅ አቅሙ የማይዋዥቅ በመሆኑ፣ ዓመቱን ሙሉ ወጥ በሆነ አቅም በሚያመርተው የኃይል መጠን ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እንደሚበልጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
"በእኛ ሁኔታ የምንፈልገው ሁለት ዩኒት እያንዳንዱ 1200 ሜጋ ዋት የሚያመነጭ ነው። ይህንን ለመስራት በጣም ከፈጠንን አስር ዓመት ይፈጃል"።
የኒውክሌር ኢንቨስትመንት የመጀመሪያ ወጪው ከፍተኛ ቢሆንም፣ አንዴ ከተገነባ ከ60 እስከ 100 ዓመታት የሚዘልቅ እና ለትውልድ የሚተርፍ ፕሮጀክት ነው ሲሉም አክለው ተናግረዋል።