ዩኬ ሳዑዲ አረቢያን ከሁቲ ጥቃቶች ለመከላከል የጦር አውሮፕላን ልታሰማራ ነው

የፎቶው ባለመብት, UK MOD
የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ሳዑዲ አረቢያን እየተባባሰ ከመጣው የሁቲ የሚሳዔል እና የድሮን ጥቃቶች ለመካከል ‘ራፍ ታይፉን’ የተባሉትን የጦር አውሮፕላኖችን እንደሚያሰማራ አስታወቀ።
ጠቅላይ ሚኒስትር አንዲ በርናም እርምጃው እንዲወሰድ ፈቅደዋል። የመከላከል ተልዕኮው የሳዑዲ ከተሞችን እና መሠረተ ልማቶችን በኢራን ከሚደገፈው ቡድን ጥቃቶች ለመከላከል እንደሚያግዝ ተነግሯል።
የዩኬ እርምጃ በሳዑዲ ዋና ከተማ ሪያድ እንዲሁም በኃይል ጣቢያዎች ላይ ሁቲዎች ጥቃቶችን መፈፀማቸውን ተከትሎ የመጣ ነው።
የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ዌስ ስተርሊንግ “አውሮፕላኖቹ የመከላከል ሚና የሚወጡ፣ በሁቲዎች ላይ የጥቃት እርምጃ የማይወስዱ ናቸው” ብለዋል።
የሁቲ ታጣቂዎች በሳዑዲ አረቢያ በሚደግፈው እና ዓለም አቀፍ እውቅና ካለው የየመን መንግሥት ጋር ጦርነት ውስጥ ናቸው። ታጣቂዎቹ እ.አ.አ በ2014 መንግሥትን ከዋና ከተማው ሰንዓ ማስወጣት ችለዋል።
ከመስከረም ጀምሮ ሳዑዲ አረቢያ የአየር ክልሏን ከሁቲ ጥቃቶች መከላከል አልቻለችም። ሁቲዎች እውቅና ባለው የየመን መንግሥት ላይ አዲስ ጥቃት የከፈቱ ሲሆን፤ ወሳኙን የባብ አል መንደብን ወሽመጥ ተቆጣጥረዋል።
በሳዑዲ ድጋፍ የመንግሥት ኃይሎች የመልሶ ማጥቃት ዘመቻቸውን ሲያጠናክሩ፤ በምላሹ ሁቲዎች ሳዑዲ ግዛት ውስጥ ዘልቀው በመግባት ዒላማዎችን መትተዋል።
ታጣቂዎቹ የንጉስ ኻሊድ አየር ማረፊያ፣ የኃይል ጣቢያዎች እና ቁልፍ ወደቦችን ጨምሮ የሳዑዲ መሠረተ ልማቶችን ደብድበዋል።
የሳዑዲ ባለሥልጣናት ሁቲዎች አየር ማረፊያዎች ላይ በፈፀሟቸው ጥቃቶች 19 ሰዎች መገደላቸውን ባለፈው ሳምንት ተናግረዋል።
ሳዑዲ አረቢያ የሚሳኤል እና ድሮን ጥቃቶችን ማክሸፍ ያልቻለችው የመከላከል አቅሟን ባለፈው ዓመት ለኢራን ጥቃቶች በመጠቀሟ እንደሆነ ተነግሯል።
የዩኬ የጦር አውሮፕላኖች ሳዑዲ የአየር ክልሏን መከላከል ብቻ ሳይሆን አገሪቱ የራሷ የጦር አውሮፕላኖች በሁቲዎች ላይ ጥቃት እንዲፈፅሙ ነፃ ያደርጋሉ ተብሏል።


















