ቀጥታ, የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር በእስራኤል ባደረጉት ይፋዊ ያልሆነ ጉብኝት ከኔታንያሁ ጋር መገናኘታቸው ተዘገበ

የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግዜት ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር መገናኘታቸውን አክሲዮስ ዘገበ። የአሜሪካው የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን አክሲዮስ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሁለት ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው ሄግዜት ወደ እስራኤል ይፋ ያልተደረገ ጉብኝት አድርገዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ዩኬ ሳዑዲ አረቢያን ከሁቲ ጥቃቶች ለመከላከል የጦር አውሮፕላን ልታሰማራ ነው

    የጦር ጄት

    የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ሳዑዲ አረቢያን እየተባባሰ ከመጣው የሁቲ የሚሳዔል እና የድሮን ጥቃቶች ለመካከል ‘ራፍ ታይፉን’ የተባሉትን የጦር አውሮፕላኖችን እንደሚያሰማራ አስታወቀ።

    ጠቅላይ ሚኒስትር አንዲ በርናም እርምጃው እንዲወሰድ ፈቅደዋል። የመከላከል ተልዕኮው የሳዑዲ ከተሞችን እና መሠረተ ልማቶችን በኢራን ከሚደገፈው ቡድን ጥቃቶች ለመከላከል እንደሚያግዝ ተነግሯል።

    የዩኬ እርምጃ በሳዑዲ ዋና ከተማ ሪያድ እንዲሁም በኃይል ጣቢያዎች ላይ ሁቲዎች ጥቃቶችን መፈፀማቸውን ተከትሎ የመጣ ነው።

    የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ዌስ ስተርሊንግ “አውሮፕላኖቹ የመከላከል ሚና የሚወጡ፣ በሁቲዎች ላይ የጥቃት እርምጃ የማይወስዱ ናቸው” ብለዋል።

    የሁቲ ታጣቂዎች በሳዑዲ አረቢያ በሚደግፈው እና ዓለም አቀፍ እውቅና ካለው የየመን መንግሥት ጋር ጦርነት ውስጥ ናቸው። ታጣቂዎቹ እ.አ.አ በ2014 መንግሥትን ከዋና ከተማው ሰንዓ ማስወጣት ችለዋል።

    ከመስከረም ጀምሮ ሳዑዲ አረቢያ የአየር ክልሏን ከሁቲ ጥቃቶች መከላከል አልቻለችም። ሁቲዎች እውቅና ባለው የየመን መንግሥት ላይ አዲስ ጥቃት የከፈቱ ሲሆን፤ ወሳኙን የባብ አል መንደብን ወሽመጥ ተቆጣጥረዋል።

    በሳዑዲ ድጋፍ የመንግሥት ኃይሎች የመልሶ ማጥቃት ዘመቻቸውን ሲያጠናክሩ፤ በምላሹ ሁቲዎች ሳዑዲ ግዛት ውስጥ ዘልቀው በመግባት ዒላማዎችን መትተዋል።

    ታጣቂዎቹ የንጉስ ኻሊድ አየር ማረፊያ፣ የኃይል ጣቢያዎች እና ቁልፍ ወደቦችን ጨምሮ የሳዑዲ መሠረተ ልማቶችን ደብድበዋል።

    የሳዑዲ ባለሥልጣናት ሁቲዎች አየር ማረፊያዎች ላይ በፈፀሟቸው ጥቃቶች 19 ሰዎች መገደላቸውን ባለፈው ሳምንት ተናግረዋል።

    ሳዑዲ አረቢያ የሚሳኤል እና ድሮን ጥቃቶችን ማክሸፍ ያልቻለችው የመከላከል አቅሟን ባለፈው ዓመት ለኢራን ጥቃቶች በመጠቀሟ እንደሆነ ተነግሯል።

    የዩኬ የጦር አውሮፕላኖች ሳዑዲ የአየር ክልሏን መከላከል ብቻ ሳይሆን አገሪቱ የራሷ የጦር አውሮፕላኖች በሁቲዎች ላይ ጥቃት እንዲፈፅሙ ነፃ ያደርጋሉ ተብሏል።

  2. የትግራይ ባለአደራ አስተዳደር የመንግሥት ሠራተኞች በሦስት ቀናት ውስጥ ወደ ሥራ እንዲመለሱ አሳሰበ

    መሣሪይ ይዞ አስፓልት ላይ የቆመ ታጣቂ

    ባለፈው ሳምንት በፌደራል መንግሥት የተመሠረተው የትግራይ ባለአደራ አስተዳደር የክልሉ መንግሥት ሠራተኞች ከዛሬ ማክሰኞ ጀምሮ ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ ጥሪ አቀረበ።

    አራት የተለያዩ ዘርፎችን የሚመሩ ዋና አስፈፃሚዎች እና የመቀለ ከተማ ከንቲባ የተመደበለት የባለአደራ አስተዳደር ይህንን ጥሪ ያቀረበው ዛሬ ማክሰኞ ጥቅምት 10/2019 ዓ.ም. ነው።

    ባለአደራ አስተዳደሩ ክልሉን የመምራት ኃላፊነትን የተረከበው፣ በመስከረም አጋማሽ የተነሳውን ውጊያ ተከትሎ የፌደራል መንግሥት እና አጋሮቹ በክልሉ ሥልጣኑን ተቆጣጥሮ በነበረው ህወሓት ሥር የነበሩትን ዋና ዋና ከተሞች በእጃቸው ካስገቡ በኋላ ነው።

    በመንግሥት ቁጥጥር ሥር በገባው የትግራይ ቴሌቪዥን ፌስቡክ ገጽ ላይ የተላለፈው መልዕክት፣ የክልሉ የመንግሥት ሠራተኞች ከዛሬ አንስቶ “በሶስት ተከታታይ የሥራ ቀናት ውስጥ ወደሚሠሩበት ተቋም በአካል በመገኘት ሪፖርት እንዲያደርጉ” ይጠይቃል።

    “በተገለጹት ሦስት ቀናት ውስጥ ሪፖርት ያላደረገ [ሠራተኛ] ራሱ ኃላፊነቱን ይወስዳል” ሲል አዲሱ አስተዳደር አሳስቧል።

    በየመስሪያ ቤቱ የሚገኙት የሰው ኃይል አስተዳደር አስተባባሪዎችም ወደ ተቋሞቻቸው ተመልሰው ሪፖርት ለሚያደርጉ ሠራተኞች ምዝገባ እንዲያደርጉ ትዕዛዝ ተላልፎላቸዋል።

    ባለፈው ሳምንት አርብ ዕለት ይፋ የተደረገው ባለአደራ አስተደዳር ትግራይ ክልልን የሚያስተዳድረው ምርጫ እስከሚደረግ ድረስ ስድስት ወራት እንደሆነ ተገልጿል።

    አስተዳደሩ ከተጣሉበት ኃላፊነቶች አንዱ የፈረሱ የመንግሥት መዋቅሮችን መልሶ መዘርጋት የሚለው ይገኝበታል። ይህንን በማድረግ “ሕዝቡ የመደበኛ አገልግሎት ተጠቃሚ የሚሆንበትን ሁኔታ መፍጠር” እንደሚኖርበትም ፌደራል መንግሥት አስታውቋል።

    “ተቋርጠው የነበሩ ማኅበራዊ አገልግሎቶች እንዲቀጥሉ ማድረግም” ሌላኛው የአስተዳደሩ ኃላፊነት ነው። በባለአደራ አስተዳደሩ ውስጥ የአስተዳደር እና የሕዝብ አገልግሎት ዘርፍን እንዲመሩ በዋና አስፈጻሚነት የተሾሙት አሰፋ አብርሃ ናቸው።

    ከመንግሥት ጋር ውጊያ ላይ ያለው ህወሓት ባወጣው መግለጫ፣ የባለአደራ አስተዳደር መቋቋሙን ተቃውሟል።

    በየትኛውም እርከን የሚገኙ የክልሉ መዋቅሮች በፌደራል መንግሥት ከተመሠረተው ባለአደራ አስተዳደር ጋር እንዳይተባበሩ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።

    "በየትኛውም እርከን 'በባለአደራ አስተዳደር' ስም የሚሰጥ ማንኛውም ውሳኔ ሕጋዊነትም ሆነ ተፈጻሚነት እንደሌለው መላው ሕዝባችን ሊያውቅ ይገባል" ብሏል።

  3. የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ከአሜሪካ ጋር በኦስሎ ሊነጋገሩ ነው

    የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘሌንስኪ ከፕሌን እየወረዱ

    የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘሌንስኪ እና የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግንኙነት በተቀዛቀዘበት በዚህ ጊዜ አገራቱ በኖሩዌይ ሊነጋገሩ ነው።

    የኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆናስ ሰቶር ዘሌንስኪ “ለዩክሬን ወሳኝ በሆነው ወቅት” ኦስሎን እና ጎረቤቷን ፊንላንድን ከአሜሪካ እና አውሮፓ አጋሮች ጋር ምክክር እንዲያዘጋጁ መጠየቃቸውን ተናግረዋል።

    ከንግግሩ አስቀድሞ ዋሽንግተን ለኪየቭ የደኅንነት መረጃዎችን ባለመስጠቷ ዩክሬናዊያን እየሞቱ ነው መባሉን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ አጣጥለዋል።

    በቅርብ ሣምንታት የኪየቭ እና የአሜሪካ ግንኙነት ሻክሯል። ትራምፕ ዩክሬን አዲስ ፕሬዝዳንት የምታገኝበት ጊዜ አሁን ከማለታቸው ባለፈ ዩክሬንን ወክሎ የሚደራደር ሌላ ሠው ያስፈልጋል ሲሉ መሪዎቹ መቃቃራቸውን አመልክተዋል።

    የኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትር የኦስሎ ንግግር የአጋራቱን ግንኙነት የበለጠ ገንቢ ወደ ሆነ መንገድ የመውሰድ ዓላማ ያለው እንደሆነ ተናግረዋል።

    የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ ከፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ጋር ለመነጋገር ቀደም ብለው ኦስሎ ደርሰዋል።

    ልዩ ልዑኩ ከኦስሎ ንግግራቸው በኋላ ወደ ሩሲያ እንደሚያቀኑ እስካሁን ግልፅ አይደለም። ሆኖም የክሬምሊን ቃል አቀባይ ከትራምፕ ልዩ ልዑክ ጋር በቅርቡ ንግግር ይደረጋል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

    በዚህ ወር መጀመሪያ ፕሬዝዳንት ፑቲን እና ትራምፕ ስለ ዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነት በስልክ ተነጋግረዋል። የአውሮፓ መሪዎች አሜሪካ በሩሲያን በተመለከተ በቅርብ ያወጣቻቸው መግለጫዎች ላይ ስጋታቸውን ገልፀዋል።

  4. አንጋፋዋ የሲኤንኤን ጋዜጠኛ ክርስቲያን አማንፑር ከ40 ዓመት በላይ የሠራችበትን ተቋም ልትለቅ ነው

    ክርስቲያን አማንፑር

    አንጋፋዋ የሲኤንኤን ጋዜጠኛ እና መሰናዶ አቅራቢ ክርስቲያን አማንፑር ከ40 ዓመት በላይ ያገለገለችበትን የቴሌቭዥን ጣቢያ በሚቀጥለው ዓመት ልትለቅ መሆኑን ገልፃለች።

    አማንፑር ከሥራ እንደምትለቅ ባሳወቀችበት መግለጫዋ “ከብዙ ወራቶች ሐሳብ በኋላ እና ከጥቂት እንቅልፍ አልባ ሌሊቶች በኋላ ለ43 አስደናቂ ዓመታት አጋሬ ከነበረው ከሲኤንኤን ለመለየት ወስኛለሁ” ብላለች።

    በዚሁ መግለጫዋ የጣቢያውን ሠራተኞች፣ የዝግጅት ክፍሏን ባልደረቦች እንዲሁም የመስክ ሥራ ባለሙያዎችን አመስግናለች።

    የ68 ዓመቷ ክርስቲያን አማንፑር ወደፊት በአዳዲስ ፕሮጀክቶች ላይ እንደምትሳተፍ ተናግራለች።

    የሲኤንኤን ኃላፊ ማርክ ቶምፕሰን፤ አማንፑር ከቴሌቭዥን ጣቢያው ከመልቀቋ በፊት የምስጋና ፕሮግራም እንደሚዘጋጅ ጠቁመው “በየትኛውም ቦታ ታማኝ እና ተወዳጅ ጋዜጠኛ ናት” ሲሉ አሞግሰዋታል።

    አማንፑር ሲኤንኤን የገባችው በአውሮፓውያኑ 1983 ሲሆን፤ በዓለም አቀፍ የዜና ክፍል ውስጥ ረዳት ሆና ነው የጀመረችው።

    አብዛኛውን ጊዜ በምትዘግባቸው የጦርነት እና የግጭት ዜናዎች በጣቢያው ጥሩ እውቅና ካላቸው ጋዜጠኛዎች ውስጥ ተጠቃሽ መሆን ችላለች።

  5. የሰዓት እላፊ ገደቦችን ተከትሎ የፈረንሳይ ከተሞች ሌሊቱን በሰላም ማደራቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለፁ

    ሰኞ ምሽት የሊዮን ከተማ ጎዳናዎች ጸጥ ብለው ነበር
    የምስሉ መግለጫ, ሰኞ ምሽት የሊዮን ከተማ ጎዳናዎች ጸጥ ብለው ነበር

    ቅዳሜ እና እሑድ በመላ አገሪቱ የተከሰተውን ሁከትና ዘረፋ ተከትሎ በበርካታ የፈረንሳይ ከተሞች ውስጥ የተጣሉ የሰዓት እላፊ ገደቦች፣ ሌሊቱ በአንጻራዊ ሰላም እንዲያልፍ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ሴባስቲያን ለኮርኑ ተናገሩ።

    ተቃዋሚዎች ቅዳሜ እና እሁድ ተሰባስበውበት የነበረውን ፕላስ ደ ላ ሬፑብሊክ እና የሌይ አል የገበያ አካባቢን ጨምሮ፣ በማዕከላዊ ፓሪስ በሚገኙ የተወሰኑ አካባቢዎች የሰዓት እላፊ ገደቦች ተጥለዋል።

    በደቡባዊ ፈረንሳይ በሚገኙት ማርሴይ፣ ቦርዶ፣ ኒስ እና ሊዮንን ጨምሮ በሰሜኖቹ ሊልና ሌሎች ከተሞች፣ የወጣቶችን እንቅስቃሴና መሰባሰብ የሚገድቡ ሌሎች እርምጃዎችም ተግባራዊ ሆነዋል።

    የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ለኮርኑ እርምጃዎቹን ላስፈፀሙ የፖሊስ አባላት ምስጋና አቅርበው፣ ማክሰኞ ምሽት ተጨማሪ የሰዓት እላፊ ገደብ የሚጣሉባቸው ቦታዎች ጉዳይ እንደ አስፈላጊነቱ እንደሚወሰን ገልፀዋል።

    ለኮርኑ በኤክስ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ፣ ውሳኔዎቹ በየአካባቢው ባለው ሁኔታ መሠረት በፈረንሳይ የክልል ባለሥልጣናትና በአካባቢ ከንቲባዎች እንደሚወሰኑ አስገንዝበዋል።

    ቅዳሜ እና እሁድ በነበረው ሁከት በርካታ ንብረት የተዘረፈ እና የወደመ ሲሆን ከ2,500 በላይ ሰዎች ታስረዋል። ወደ 1,000 የሚጠጉ የፖሊስ አባላትም ቆስለዋል።

  6. የዩክሬንን ጦርነት ዕጣ ፈንታ ይወስናል የተባለ የአሜሪካ፣ የሩሲያ እና የቻይና መሪዎች ስብሰባ ሊካሄድ ነው

    ትራምፕ

    የዩክሬንን ጦርነት ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ሊወስን ይችላል የተባለ ስብሰባ ከሩሲያ እና ከቻይና ፕሬዝዳንቶች ጋር ለማድረግ መስማማታቸውን ዶናልድ ትራምፕ ተናገሩ።

    ስብሰባው አምስት ዓመት ሊሆነው በተቃረበው የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ላይ ዋና ትኩረት እንደሚያደርግ የተገመተ ሲሆን፣ ትራምፕ በበኩላቸው የስብሰባው ዋነኛ ትኩረት የኒውክሌር መሣሪያ ትጥቅ ቅነሳ እንደሚሆን ገልፀዋል።

    የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ይህ ስብሰባ እንዲካሄድ ቭላድሚር ፑቲን ሐሳብ ማቅረባቸውን ከዘገቡ በኋላ፣ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ሩሲያ በዩክሬን ጉዳይ ላይ ያላት አቋም “ተቀባይነት ያለው” መሆኑን ተናግረዋል።

    ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል ፑቲን ስላቀረቡት ሐሳብ ያወጣው ዘገባ አውሮፓን ያሳሰበ ሲሆን፣ ከኪየቭም ውግዘት አስከትሏል።

    ትራምፕ፣ ኪየቭን ወክሎ ድርድር የሚያደርግ ሌላ መሪ መምጣት ያለበት ጊዜ ሳይደርስ አልቀረም በማለት በቅርቡ የዩክሬኑን ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪን መተቸታቸው ይታወሳል።

  7. ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኬንያ ገቡ

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአየር መንገድ ወታደራዊ አቀባበል እየተደረገላቸው

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ማክሰኞ ጥር 10/2019 ዓ. ም. ወደ ኬንያ ኤልዶሬት ከተማ ማቅናታቸውን ጽሕፈት ቤታቸው አስታወቀ።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ኬንያ የሄዱት፣ በአገሪቱ የማሹጃ ቀን (የጀግኖች ቀን) ብሔራዊ በዓል አከባበር ላይ በክብር እንግድነት ለመታደም መሆኑንም ጽሕፈት ቤቱ ገልጿል።

    ኬንያ ከቅኝ ግዛት ነጻ ከወጣችበት ጊዜ አንስቶ በየዓመቱ ጥቅምት 10 የሚከበረው የማሹጃ ቀን፣ ለአገሪቱ ነፃነት፣ ሉዓላዊነት እና ልማት የላቀ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ጀግኖች የሚከበሩበት ነው።

    63ኛው የዘንድሮው የማሹጃ ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ በኤልዶሬት ከተማ በሚገኘው ኪፕቾጌ ኬይኖ ስታዲየም እየተከበረ ይገኛል።

    በበዓሉ ላይ የሚታደሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ወደ ኬንያ ሲያቀኑ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የዛሬው ሁለተኛቸው ነው።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኬንያ ላሙ በሚገነባው የዳንጎቴ የምሥራቅ አፍሪካ የነዳጅ ማጣሪያ እና ፔትሮኬሚካል ፕሮጀክት መሠረተ ድንጋይ የማስቀመጥ ሥነ ሥርዓት ላይ ለመሳተፍ ባለፈው ወር መስከረም 20 ኬንያ ገብተው ነበር።

  8. የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር በእስራኤል ባደረጉት ይፋዊ ያልሆነ ጉብኝት ከኔታንያሁ ጋር መገናኘታቸው ተዘገበ

    ፒት ሄግዜት

    የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግዜት ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር መገናኘታቸውን አክሲዮስ ዘገበ።

    የአሜሪካው የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን አክሲዮስ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሁለት ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው ሄግዜት ወደ እስራኤል ይፋ ያልተደረገ ጉብኝት አድርገዋል።

    ሄግዜት ወደ እስራኤል መጓዛቸውን በገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ እንዳልቻለ ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

    ፔንታጎን ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም። በዋሽንግተን የሚገኘው የእስራኤል ኤምባሲም ለሮይተርስ ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም።

    ዘገባው መውጣቱን ተከትሎ ግን ሄግዜት ወደ መካከለኛው ምሥራቅ መሄዳቸውን ይፋ አድርገዋል። በትክክል የትኛው አገር እንደሄዱ ግን አልገለጹም።

    በኤክስ ገጻቸው ከአሜሪካውያን ወታደሮች ጋር የተነሱትን ፎቶ “እንደ ሁልጊዜው የማዕከላዊ ዕዝ ተዋጊዎቻችንን ማግኘት ክብር ይሰጠኛል” ከሚል ጽሑፍ ጋር አጋርተዋል።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ እዝ ወታደሮች በመካከለኛው ምሥራቅ የተለያዩ አካባቢዎች ተሰማርተዋል።

    የእስራኤሉ ቫላ ሚዲያም ሄግዜት ከጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ጋር “ምሥጢራዊ ውይይት” ማድረጋቸውን ዘግቧል።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቀጣይ ሳምንት በሚካሄደው የእስራኤል ምርጫ ኔታንያሁን እንደሚደግፉ ተናግረዋል።

    የሄግዜት የእስራኤል ጉብኝት ዜና የተሰማውም በትራምፕ ንግግር ማግሥት ነው።

    ሐማስ ከሦስት ዓመት በፊት በእስራኤል ላይ ጥቃት ካደረገ ወዲህ እስራኤል ለመጀመሪያ ጊዜ አገር አቀፍ ምርጫ ታካሂዳለች።

    እስራኤል ከሐማስ ጥቃት በኋላ በጋዛ፣ ሊባኖስ እና ኢራን ላይ ጥቃቶች አድርሳለች።

    የአሜሪካ አጋማሽ ምርጫ በመቃረቡ እና በእስራኤል ከሚካሄደው ምርጫ ጋር በተያያዘም ሁለቱ አገራት እንደ አዲስ ጥቃት መሰንዘር እንዳይጀምሩ ኢራን አስጠንቅቃለች።

    አሜሪካ እና እስራኤል ወደ አዲስ ዙር ጦርነት የሚገቡ ከሆነ ኢራንም ለውጊያ ዝግጁ መሆኗን የቴህራን ወታደራዊ ባለሥልጣናት ገልጸዋል።

    ኢራን “አዲስ ወታደራዊ ዒላማዎች እንደምትመታ እና የተለየ መሣሪያ እንደምትጠቀም” ባለሥልጣናቱ አስታውቀዋል።

    ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ቴህራን የተጓዙት የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ከኢራኑ አቻቸው ጋር ተወያይተዋል።

    የፓኪስታን ጦር ኮማንደር የሆኑት ፊልድ ማርሻል አሲም ሙኒር ከቴህራን ባለሥልጣናት ጋር መወያየታቸውም ተገልጿል።

  9. ህወሓት፤ ማርኮ ሩቢዮ በወታደራዊ ተቋማት ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶችን “በሽብርተኝነት” መፈረጃቸውን እንደማይቀበለው አስታወቀ

    ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል

    ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ወታደራዊ ተቋማት ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶችን በሽብርተኝነት መግለጻቸውን እንደማይቀበለው አስታወቀ።

    ህወሓት ዛሬ መስከረም 9/2019 ዓ. ም. ባወጣው መግለጫ፤ ማርኮ ሩቢዮ "የትግራይን እምቢተኝነት ተገንጣይ” ማለታቸውን እና “በወታደራዊ ተቋማት ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶችን የሽብርተኝነት ድርጊት አድርገው” የሰጡት መግለጫ እንዳሳዘነው ገልጿል።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቅዳሜ ጥቅምት 7/2019 ዓ. ም. ኢትዮጵያን በተመለከተ ለጋዜጠኞች በሰጡት አጭር ገለፃ በኢትዮጵያ ውስጥ ጥቃት የሚፈጽሙ "ተገንጣይ ቡድኖች" መኖራቸውን እና ለዚህም የኢትዮጵያ መንግሥት ምላሽ እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል። ሚኒስትሩ አክለውም በአዲስ አበባ ከተማ የድሮን ጥቃት መፈጸሙን በማመልከት ድርጊቱን ከሽብር ጋር አያይዘውታል።

    ህወሓት በዛሬው መግለጫ ሩቢዮ የተጠቀሙት ገለፃ “ዳግም ያገረሸውን ጦርነት ምክንያት፣ የፌደራል መንግሥቱ በፕሪቶሪያ የተፈረመውን የተኩስ አቁም ስምምነት እንዳይፈጸም ማድረጉን እና የትግራይ ሕዝብ ራሱን እንዲከላከል ያስገደዱትን ሁኔታዎች ችላ ያለ ነው” ብሎታል።

    በዚህ ምክንያት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን ንግግር “እንደማይቀበለው” አስታውቋል።

    ዳግም ያገረሸው ጦርነት ከመጀመሩ በፊት ለሰላማዊ ንግግር ተደጋጋሚ ጥሪ አድርጎ እንደነበር ያስታወሰው ህወሓት፣ አሜሪካም ሆነ ሌሎች ኃያላን ጦርነቱን ለማስቀረት “ውጤታማ እርምጃ አልወሰዱም” በማለት ወቅሷል።

    “የፌደራሉ መንግሥት ሙሉ ጦርነት ሲያውጅ ሕዝባችንን ከግድያ እና ውድመት ለመጠበቅ ተገድደናል” ያለው የዛሬው መግለጫ፣ አሜሪካ “ውጊያውን እንደምታስቆም እንዲሁም ገንቢ ውይይት እንደምታመቻች ጠብቀን ነበር” ብሏል።

    ህወሓት “ራስን መከላከል” ሲል የገለጸው እርምጃ እንደ “ተገንጣይ” ተደርጎ መገለጹ “እጅግ የሚያሳዝን ነው” በማለት ገልጾታል።

    እንዲህ ዓይነቱ ገለፃ “ለሰላም፣ ለእኩልነት እና ለኅልውና የሚደረገውን የሕዝብ ትግል ታሪክ እና ዓላማ የሚያዛባ ነው። በተጨማሪ ገዢው መንግሥት ሰላማዊ መፍትሔ እንዳይሰፍን ያለውን ሚና የሚጋርድ ነው” በማለት የማርኮ ሩቢዮን ንግግር ተችቷል።

    “የትግራይ ከተማዎች እና መንደሮች እየተደበደቡ ምንም ዓይነት ውግዘት ሳይሰጥ በወታደራዊ ተቋማት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት እንደ ሽብር መግለጽ” እንደማይቀበለውም አስታውቋል።

    አሜሪካ ይህን አካሄዷን “በድጋሚ እንድታጤን” እና በኢትዮጵያ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን “ወሳኝ ሚና እንድትጫወት” ህወሓት በመግለጫው ጠይቋል።

  10. ሩሲያ ከኢራን ጋር መተባበር እንደምትቀጥል አስታወቀች

    ሰርጌ ላቭሮቭ

    ሩሲያ ከኢራን ጋር ላላት የትብብር ማዕቀፍ ታማኝ እንደሆነች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ተናገሩ።

    የኢራን ጦርነት ከተነሳ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ቴህራን የተጓዙት ላቭሮቭ፤ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ስትራቴጂያዊ ግንኙነት መጠናከሩን ገልጸዋል።

    ለኢራን የምግብ እና የሕክምና ድጋፍ ለመስጠት ሐሳብ ማቅረባቸውን አክለዋል።

    ከኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ጋር ያደረጉት ውይይት “ፍሬያማ” መሆኑን ላቭሮቭ ጠቁመዋል።

    የኢራኑ ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዤሽኪያን በሞስኮ የነዳጅ ጉባዔ እንደሚታደሙ የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተናግረዋል።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንደተናገሩት፤ ለመካከለኛው ምሥራቅ ጉዳይ ወታደራዊ መፍትሔ እንደሌለው ከላቭሮቭ ጋር ተስማምተዋል።

    በቀጣናው አለመረጋጋት የተፈጠረው በአሜሪካ፣ በኢራን ጦርነት እና በባሕር እንቅስቃሴ ክልከላ ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል።

    በካስፒያን ባሕር እና በባሕር ዳርቻው በኢራን እና በሩሲያ መርከቦች ላይ የሚደርሰው ጥቃት እንደሚያሳስባቸው ለሩሲያው አቻቸው መግለጻቸውን አራግቺ ተናግረዋል።

  11. የእስራኤል ፖሊስ በዌስት ባንክ በዲፕሎማቶች እና ጋዜጠኞች ላይ ጥቃት አድርሰዋል ያላቸውን 10 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር አዋለ

    የእስራኤል ሰፋሪዎች ሄይዲ ሌቪን የተባለች የዋሽንግተን ፖስት የፎቶ ጋዜጠኛ ደብደው ከባድ ጉዳት እንዳደረሱባት ተገልጿል
    የምስሉ መግለጫ, የእስራኤል ሰፋሪዎች ሄይዲ ሌቪን የተባለች የዋሽንግተን ፖስት የፎቶ ጋዜጠኛ ደብደው ከባድ ጉዳት እንዳደረሱባት ተገልጿል

    የእስራኤል ፖሊስ ባለፈው ሳምንት በአሜሪካ ጋዜጠኞች እና በአውሮፓ ዲፕሎማቶች ላይ ጥቃት አድርሰዋል ያላቸውን 10 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስታውቋል።

    ተጠርጣሪዎቹ በዌስት ባንክ ከሚኖሩ እስራኤላውያን ሰፋሪዎች መካከል ናቸው።

    ስማቸው ያልተገለጸው በተለያየ አካባቢ የተያዙት ግለሰቦች በአመጽ፣ የተከለከለ ወታደራዊ ቀጠናን በመጣስ እና በሕገ ወጥ ግንባታ ተጠርጥረዋል።

    አርብ ዕለት ጭምብል የለበሱ የእስራኤል ሰፋሪዎች ሄይዲ ሌቪን የተባለች የዋሽንግተን ፖስት የፎቶ ጋዜጠኛ ደብደው ከባድ ጉዳት እንዳደረሱባት ተገልጿል።

    በዕለቱ ጋዜጠኛዋ አቡ ፋላህ በተሰኘ የፍልስጤም መንደር ውስጥ የወይራ ምርት ሲሰበሰብ የሚያሳይ ዘገባ እየሠራች ነበር።

    በማግሥቱ ደግሞ ከቤልጂየም፣ ፈረንሳይ፣ ፖላንድ እና የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሄዱ ዲፕሎማቶች ጭምብል ባጠለቁ ሰፋሪዎች ተመሳሳይ ጥቃት እንደደረሰባቸው ተገልጿል።

    በእስራኤል የአሜሪካ አምባሳደር ማይክ ሃካቢ የተጠርጣሪዎቹን መታሰር አድንቀዋል።

    አምባሳደሩ በኤክስ ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት “[ጋዜጠኛ] ሄይዲ ሌቪን ላይ ከፍተኛ ጥቃት እና ድብደባ የፈጸሙትን ለማግኘት እንዲሁም ለመቅጣት አዎንታዊ እርምጃ ነው” ብለዋል።

    በዌስት ባንክ በሚገኙ የእስራኤል ሰፋሪዎች የሚፈጸሙ ጥቃቶች በዚህ ዓመት ከምንጊዜውም በላይ እንደጨመሩ የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ያሳያል።

    ለፍልስጤማውያን የዕለት ተዕለት ኑሮ ወሳኝ የሆነው የወይራ ምርት በሚሰበሰብበት ወቅት በተለይ በዚህ ዓመት ጥቃቱ ጨምሯል።

    የእስራኤል የሰብአዊ መብት ቡድን “የሽዲን” እሑድ እንዳስታወቀው፤ ባለፉት 20 ቀናት ብቻ በቀጥታ ከወይራ ምርት መሰብሰብ ጋር የተያያዙ 269 የአመጽ ድርጊቶችን መዝግቧል።

    ከእነዚህ ውስጥ 98ቱ የወይራ ምርት መሰብሰብ ሥራ ላይ የነበሩ ፍልስጤማውያን ላይ አካላዊ ጥቃት ማድረስ፣ ምርቶቻቸውን ማውደም እና መስረቅ እንደሚገኝበት ገልጿል።

  12. ወላጆች የልጆቻቸው ሕይወት እስከሚያልፍ ድረስ እንዲጾሙ አስገድደዋል የተባሉት ፓስተር ፍርድ ቤት ቀረቡ

    ፖል ማኬንዚ እና 29 የሚሆኑ ተከታዮቻቸው የ191 ሰዎችን ሕይወት በማጥፋት ክስ ቀርቦባቸዋል
    የምስሉ መግለጫ, ፖል ማኬንዚ እና 29 የሚሆኑ ተከታዮቻቸው የ191 ሰዎችን ሕይወት በማጥፋት ክስ ቀርቦባቸዋል

    ፖል ማኬንዚ የተባሉት የኬንያ ፓስተር የዓለም መጨረሻ ደርሷል በማለት የበርካታ ሰዎች ሕይወት እንዲያልፍ አድርገዋል በሚል ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

    ማኬንዚ እና 29 የሚሆኑ ተከታዮቻቸው የ191 ሰዎችን ሕይወት በማጥፋት ክስ ቀርቦባቸዋል። ከሟቾቹ ውስጥ ከአንዱ በስተቀር ሁሉም ሕፃናት ናቸው።

    ፓስተሩ ከፈጣሪ ጋር ለመገናኘት እንድትችሉ በሚል ሕፃናቱ ሕይወታቸው እስከሚያልፍ ድረስ እንዲጾሙ ማድረጋቸው ተገልጿል።

    የዓለም ፍጻሜን የተመለከተው የፓስተሩ አስተምህሮት ዘመናዊ መድኃኒቶችን እንደ “መጥፎ” የሚቆጥር እና ትምሕርትን የሚከለክል ነው።

    ማኬንዚ እና 29 ተከታዮቻቸው በቀረበባቸው የግድያ ክስ ጥፋተኛ አይደለንም ሲሉ ክሱን ውድቅ ያደረጉ ሲሆን ማንም እንዲሞት አልተገደደም በማለት ተናግረዋል።

    የአገሪቱ ባለሥልጣናት እንደተናገሩት፤ ማኬንዚ ከተለያየ አካባቢ የሚመጡ ተከታዮችን በሚመሩበት በኬንያ የባሕር ዳርቻ በሚገኝ ሻካሆላ ጫካ ውስጥ 400 አስክሬን ከመቃብር ውስጥ ተቆፍሮ ወጥቷል።

    ከመቃብር ቆፋሪዎቹ ውስጥ ጀምስ የተባለ እማኝ “እያንዳንዱ መቃብር ቢያንስ 3 አስክሬኖች ነበሩት። አንዳንዱ አስክሬን የጥቂት ሳምታት ዕድሜ ያላቸው ሕፃናት ናቸው” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

    “በመቃብሩ በአንድ ጊዜ 12 የሕፃናት አስክሬን ልክ እንደ ልብስ ተደርድሮ አግኝተናል” ሲልም የተመለከተውን ተናግሯል።

    አንዳንዶቹ አስክሬኖች “እጅ እና እግራቸው የታሰሩ እንዲሁም በአንሶላ የተጠቀለሉ” መሆናቸው ተገልጿል።

    ስቲፈን ማዊቲ የተባሉ የ 48 ዓመት እናት በማኬንዚ አስተምህሮ 6 ልጆጃቸው እንደሞቱባቸው ተናግረዋል።

    በኬንያ የባሕር ዳርቻ በሚገኝ ሻካሆላ ጫካ ውስጥ 400 አስክሬን ከመቃብር ውስጥ ተቆፍሮ ወጥቷል
    የምስሉ መግለጫ, በኬንያ የባሕር ዳርቻ በሚገኝ ሻካሆላ ጫካ ውስጥ 400 አስክሬን ከመቃብር ውስጥ ተቆፍሮ ወጥቷል
  13. ፕሬዝዳንት ፑቲን ዩክሬንን በተመለከተ ከትራምፕ እና ሺ ጂንፒንግ ጋር ስብሰባ ለማድረግ መጠየቃቸው ተዘገበ

    ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የዩክሬን ጦርነትን በተመለከተ በሚቀጥለው ወር ከአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ከቻይናው መሪ ሺ ጂንፒንግ ጋር የመሪዎች ስብሰባ ለማካሄድ ጥያቄ ማቅረባቸውን የአሜሪካው ዎል ስትሪት ጆርናል ጋዜጣ ዘገበ።

    ሮይተርስ የጠቀሰው የጋዜጣው ዘገባ እንደሚያመለክተው ፑቲን ይህንን ጥያቄ ያቀረቡት አራት ዓመት የሆነውን ጦርነት ለሩሲያ በሚያደላ መልኩ በድርድር ለማጠናቀቅ መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ተናግረዋል።

    ጥያቄው የቀረበው የትራምፕ እና የፑቲን ግንኙነት እየተሟሟቀ በመጣበት ወቅት ነው። አሜሪካው ፕሬዝዳንት ከሩሲያ ነዳጅ ለመግዛት ስምምነት መፈጸማቸውን ይፋ ያደረጉ ሲሆን አርብ ዕለትም ሞስኮ ላይ ተጥለው የነበሩ ማዕቀቦች እንዲታገዱ የሚያደርግ ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝም ፈርመዋል።

    ፑቲን የስብሰባ ጥያቄውን ያነሱት በመስከረም ወር መጀመረጫ ከትራምፕ ጋር ባደረጉት የስልክ ንግግር ወቅት መሆኑን ስለ ጉዳዩ ገለፃ የተደረገላቸውን የቀድሞ የሩሲያ የስለላ መኮንን መናገራቸውን ጋዜጣው ዘገቧል።

    እንደ ዎል ስትሪት ጆርናል ዘገባ፣ ስብሰባው ሊካሄድ የታቀደው በመጪው ህዳር በቻይና ሼንዘን ከተማ በሚካሄደው የእስያ-ፓሲፊክ የኢኮኖሚ ትብብር የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን ነው።

    የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔሽኮቭ ሊካሄድ ስለሚችለው ስብሰባ ውይይቶች እየተደረጉ መሆናቸውን ለጋዜጣው ማረጋገጣቸው በዘገባው ተካትቷል።

    “ሦስቱም ወገኖች እንዲህ አይነቱ ስብሰባ ሊካሄድ የሚችልበት ዕድን እንዳለ እውቅና ቢሰጡም፣ ስለ ስብሰባው ወይም ሊነሳ ስለሚችለው አጀንዳ እስካሁን ግልጽ የሆነ መግባባት የለም” ሲሉ ለዎል ስትሪት ጆርናል ተናግረዋል።

    አንድ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣን በበኩላቸው፣ ትራምፕ ይህ አይነቱ ስብሰባ እንዲካሄድ ባይስማሙም፣ ሃሳቡን ሊቀበሉ እንደሚችሉ መናገራቸውን ጋዜጣው ዘግቧል።

  14. የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የኢራን ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ቴህራንን ሊጎበኙ ነው

    የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ
    የምስሉ መግለጫ, የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ

    የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ የኢራን ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ዛሬ ሰኞ ወደ ቴህራን በመጓዝ ጉብኝት ሊያደርጉ ነው።

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጋይ እሁድ ዕለት ስለ ጉብኝቱ አረጋግጠው “በቀጣናዊ እና በዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች” ላይ ውይይቶች እንደሚካሄዱ ተናግረዋል።

    ከኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ጋር ለመገናኘት ቀጠሮ የያዙት ላቭሮቭ፣ በቴህራን እና በዋሽንግተን መካከል የሚደረጉ ንግግሮች በተቋረጡበት በአሁኑ ወቅት የሞስኮ ጥረት “መጠነ ሰፊ የሆነ ጦርነት እንዳይቀሰቀስ ለመከላከል ያለመ" መሆኑን ተናግረዋል።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጉብኝት የሚካሄደው የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በጥቅምት ወር መጀመርያ ላይ ለኢራኑ ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን፣ ሞስኮ በማደራደር ጥረቶች ውስጥ አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን ከገለጹ በኋላ ነው።

    በዓለም ላይ ከፍተኛ ማዕቀብ ከተጣለባቸው አገራት መካከል የሚገኙት ሩሲያ እና ኢራን የጠበቀ ወዳጅነት አላቸው።

    በአውሮፓውያኑ 2022 ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረችበት ጊዜ አንስቶ፣ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትብብር ይበልጥ እየተጠናከረ መጥቷል።

    እስራኤል እና አሜሪካ በኢራን ላይ ጦርነት የከፈቱት ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ላይ ነው።

    አሜሪካ እና ኢራን ባለፈው ዓመት ሰኔ የመግባቢያ ሰነድ ቢፈራረሙም በሆርሙዝ ወሽመጥ ዙሪያ መግባባት ባለመቻላቸው ዳግም ግጭቱ አገርሽቷል።

    ኢራን በሆርሙዝ ላይ ሙሉ ቁጥጥር እንዳላት በመግለጽ ለማለፍ የሚሞክሩ የጭነት እና የነዳጅ መርከቦች ላይ ጥቃት ትፈጽማለች።

    ዋሺንግተን በኢራን ወደቦች ላይ ገደብ ጣለች ሲሆን የዓለም አንድ አምስተኛ ነዳጅ የሚተላለፍበት የሆርሙዝ ወሽመጥ ክፍት መሆኑን በተደጋጋሚ ትናገራለች።

    የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በላቭሮቭ ጉብኝት ወቅት የሚደረጉ ውይይቶች "አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ በፈጸሙት ሕገ-ወጥ ጥቃት የተቀሰቀሰውን አጣዳፊ ዓለም አቀፍ ቀውስ ለመፍታት በሚያስችሉ መንገዶች" ላይ ያተኩራሉ ብሏል።

    ሚኒስቴሩ አክሎም፣ ይህ ጦርነት "በመካከለኛው ምሥራቅ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም" ለመረጋጋት እና ለደኅንነት ትልቅ እንቅፋት መሆኑን ገልጿል።

  15. “ትብብር ለኅልውና” የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮን "ተገንጣይ" እና "ሽብርተኝነት" የሚሉ አገላለጾች ተቃወመ

    የትግራይ ኃይሎች

    የሰባት አማፂ ኃይሎች ጥምረት የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ኃይሎች ትብብር ለኅልውና ለአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ንግግር ምላሽ ሰጠ።

    ታጣቂ ኃይሎቹን “ተገንጣይ ቡድኖች” ሲሉ የጠሯቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ በአዲስ አበባ የድሮን ጥቃት መፈፀሙን ተናግረዋል።

    ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ስለ ጥቃቱ ምንም ባይባልም፤ ሩቢዮ ጥቃቱን እንደ ሽብርተኝነት አይተውታል።

    ጥምረቱ ጥቅምት 8/2019 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ እየወሰድኳቸው ያሉ “ራስን የመከላከል” ወታደራዊ እርምጃዎች “የተገንጣይነት ዒላማ” ያለው አይደለም ብሏል።

    ንቅናቄውን “ተገንጣይ” ብሎ መግለፅ ትክክል እና ተገቢ አይደለም በማለት መሠረታዊ ግቡ በአገሪቱ አንድነት፣ ሰላም እና መረጋጋት ማምጣት እንደሆነም በመግለጫው ጠቅሷል።

    “ትብብር ለኅልውና” ወታደራዊ እርምጃዎቹን የፕሪቶሪያ ስምምነትን ጨምሮ ለእርቅ ለማውረድ ሰላማዊ መንገዶች ውድቅ በመደረጋቸው “የመጨረሻ አማራጭ” ሲል ገልጿቸዋል።

    ወታደራዊ ተቋማት ላይ የሚፈፅማቸውን ተልዕኮዎች “ሽብር” ብሎ መጥራት "ለእውነታ የተንሸዋረረ መልክ" መስጠት ነው ሲልም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን ንግግር አጣጥሏል።

    “ትብብር ለሕልውና” ማርኮ ሩቢዮ ግጭቱን የገለፁበት መንገድ መንግሥት “የጦርነት አጀንዳውን ያለ ተጠያቂነት” እንዲቀጥል እና ለሁሉም የሰላም ጥረቶች በሩን የሚያዘጋ ነው ሲልም ነቅፏል።

    ጥምረቱ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት አሜሪካ በአጠቃላይ በግጭቱ ላይ “ሚዛናዊ እና ገንቢ” አቋም እንዲኖራት ጥሪ አቅርቧል።

    ሰባት ታጣቂ ቡድኖች "ትብብር ለኅልውና" የተሰኘ ጥምረት መመሥረታቸውን ያስታወቁት መስከረም 10/2019 ዓ.ም. ነው።

    ይህንን ጥምረታቸውን ይፋ ካደረጉ ከሦስት ቀናት በኋላ መስከረም 13/2019 ዓ.ም. ላይ በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግመኛ ግጭት ተቀስቅሷል።

  16. ከእስራኤል ወደ ኦስትሪያ እየበረረ የነበረ አውሮፕላን የቦምብ ጥቃት ሊኖር ይችላል በሚል በድንገት እንዲያርፍ ተደረገ

    ቡልጋሪያ እንዲያርፍ የተገደደው የኦስትሪያ አውሮፕላን ጋር የሚመሳሰል አውሮፕላን

    ከእስራኤል ወደ ኦስትሪያ እየበረረ የነበረ የኦስትሪያ አየር መንገድ አውሮፕላን የቦምብ ጥቃት ሊኖር እንደሚችል ማስጠንቀቂያ ከደረሰው በኋላ በድንገት ቡልጋሪያ ለማረፍ ተገደደ።

    የቡልጋሪያ የትራንስፖርት ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የኤርባስ ኤ320 አውሮፕላን እሁድ ምሽት ከቴል አቪቭ ወደ ቪየና እየተጓዘ ሳለ በዋና ከተማዋ ሶፊያ በድንገት እንዲያርፍ እና ተሳፋሪዎቹ ከአውሮፕላኑ እንዲወርዱ ተደርጓል ብሏል።

    የቡልጋሪያ አየር ኃይል አውሮፕላኑን ለማጀብ ሚግ-29 የተዋጊ አውሮፕላን ተጠቅሟል ሲል የትራንስፖርት ሚኒስትሩ ጨምሮ ገልጿል። በአውሮፕላኑም ሆነ በመንገደኞች ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት አለመድረሱን ጠቅሰው ምርመራም እንደተጀመረ አስታውቀዋል።

    ባለፈው ወር አንድ ረዳት አብራሪ ወደ ቴል አቪቭ ሲጓዝ የነበረውን የፍላይዱባይ አውሮፕላን ካፒቴን ላይ ጥቃት ፈጽሟል።

    የቡልጋሪያና የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን የቦምብ ማስፈራሪያ እንደተሰነዘረ ዘግበዋል። የኦስትሪያ አየር መንገድ ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ ሳይሰጥ ስጋት መፈጠሩን አረጋግጧል። አንድ ቃል አቀባይ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደተናገሩት በአውሮፕላኑ ውስጥ 51 ተሳፋሪዎች እና ስድስት የበረራ አባላት ነበሩ።

    ባለሥልጣናት አውሮፕላኑ ሶፊያ ውስጥ ካረፈ በኋላ የደኅንነት ፍተሻ አካሂደዋል።

    የበረራ ክትትል መረጃዎች እንደሚያሳዩት የኦስትሪያ አየር መንገድ አውሮፕላን እሁድ ምሽት ከቴል አቪቭ ቤን ጉሪዮን አውሮፕላን ማረፊያ ከወጣ ከሦስት ሰዓታት በኋላ ሶፊያ በሚገኘው ቫሲል ሌቭስኪ አውሮፕላን ማረፊያ አርፏል።

    ባለፈው ሳምንት ክሮሺያ እና ጀርመን ከግሪክ ደሴት ኮርፉ ወደ ጀርመን ኑረምበርግ ከተማ እየበረረ የነበረ አውሮፕላን ላይ በስህተት የጠለፋ ማስጠንቀቂያ ከተላከ በኋላ የጦር አውሮፕላኖቻቸውን አሰማርተው ነበር።

    ቢቢሲ የኦስትሪያ አየር መንገድ ባለቤት የሆነውን ሉፍታንዛን ተጨማሪ አስተያየት ጠይቋል።

  17. ኔታንያሁ አሜሪካን ወደ አዲስ ጦርነት እየገፉ ሲሉ የኢራኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሰሱ

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከእስር ለማምለጥ ሲሉ አሜሪካን ከኢራን ጋር ወደ ሌላ ጦርነት ለማስገባት እየሞከሩ ነው በማለት ወነጀሉ።

    ሚኒስትሩ ዋሽንግተን አዲስ ወታደራዊ እርምጃ እንዳትወስድ እሁድ ዕለት አስጠንቅቀዋል።

    አራግቺ “ኔታንያሁ ከእስር ለማምለጥ ሲሉ አሜሪካን ወደ ሌላ ጦርነት እየገፏት ነው” ሲል በኤክስ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

    ዳግም ጦርነት የሚቀሰቀስ ከሆነ በእስራኤል እና በአሜሪካ ላይ የሚኖረውን መዘዝ ችላ ብለዋል ሲሉም አክለዋል።

    “ባለፈው ጊዜ ማጠናቀቅ የሚፈልገው ስራ እንዳለ ተናግሮ፣ ኢራን የበለጠ ጠንካራ ሆና ብቅ አለች። ዕድልህን እንደገና መሞከር ትፈልጋለህ? እንግዲያው እንግዳችን እንድትሆን ተጋብዘሃል። ግን ተጠንቀቅ፤ እኛም ያልተጠናቀቁ ስራዎች አሉን” ሲሉ ዝተዋል።

    ትራምፕ እሁድ ዕለት እስራኤል እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ጥቅምት 27 ከምታካሄደው ምርጫ በፊት ለኔታንያሁ ያላቸውን ድጋፍ ከገለጹ በኋላ፣ ከኢራን ጋር በነበራቸው ጦርነት ስላሳዩት አጋርነት አወድሰዋቸዋል።

    ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ “እስራኤል የተሳሳተ መሪ ከመረጠች፣ ይህም ከቢቢ ውጪ ሌላ ማንም ቢሆን፣ አሜሪካ ይህንን ሥራ ራሷ መሥራት አለባት፣ እኔ እንደዚያ እንዲሆን አልፈልግም” ሲሉ ጽፈዋል።

    ኔታንያሁ እአአ ከ2022 መጨረሻ ጀምሮ የአሁኑን መንግሥት ሲመሩ ቆይተዋል። የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በጉቦ፣ በማጭበርበር እና እምነትን በመጣስ ክስ ተመስርቶባቸዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን የቀረቡባቸውን ክሶች አስተባብለዋል።

    የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በበኩሉ በእርሳቸው እና በቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት ላይ በጦር ወንጀሎች ምክንያት የእስር ማዘዣ አውጥቷል።

    ኔታንያሁ ይህንን የፍርድ ቤቱን እርምጃ “ፀረ ሴማዊ” ሲሉ ማውገዛቸው ይታወሳል።

    ተቃዋሚ ፓርቲዎች የኔታንያሁን መንግሥት ከሥልጣን ለማውረድ ትብብራቸውን አጠናክረዋል።

    እስራኤል እና አሜሪካ ባለፈው ዓመት የካቲት 21/2018 ዓ.ም. ቴህራን ላይ በጋራ በመሆን ጦርነት ከፍተዋል። ይህም ቴህራን የአጸፋ እርምጃ እንድትወስድ እና በባሕረ ሰላጤው የሚገኙ የአሜሪካ አጋር አገራት ላይ በሚሳኤል እና በድሮን የታገዘ ጥቃት እንድትፈጽም አድርጓታል።

  18. ግብፅ የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ከሁቲ ታጣቂዎች ጋር የሚያደርገውን ውጊያ ለማገዝ ተስማማች

    የሁቲ አማጺያን

    የግብፅ ከፍተኛ የደኅንነት አካል ሳዑዲ አረቢያ በየመን ከሁቲ አማጺያን ጋር የምታደርገውን ጦርነት ለመደገፍ መስማማቱን እሁድ ዕለት አስታወቀ።

    ሳዑዲ አረቢያ አጋሮቿ ድጋፍ አንዲያደርጉላት ስትጠይቅ ቆይታለች። የሁቲ አማፂያን በተደጋጋሚ የሳዑዲ አረቢያ የነዳጅ መሠረተ ልማቶች እንዲሁም አውሮፕላን ማረፊያዎች በሚሳዔሎች እና ድሮኖች እያጠቁ ነው።

    ሁቲዎች ጥቃት የሚፈጽሙባቸው ሚሳዔሎች እየተምዘገዘጉ ሳለ አቅጣጫ መቀየር የሚችሉ በመሆናቸው ለማክሸፍ መቸገሯን ሳዑዲ አስታውቃለች።

    እስካሁን ድረስ በሳዑዲ አረቢያ ውስጥ ብቻ 19 ሰዎች ሲገደሉ በሺህዎች የሚቆጠሩ በረራዎች ደግሞ ተሰርዘዋል።

    እሁድ ዕለት የሳዑዲ መከላከያ ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ፕሬዝዳንት ጋር ተገናኝተው ሁለቱ አገራት ያላቸውን ትብብር ማጠናከር ስለሚችሉበት ሁኔታ ተነጋግረዋል።

    ሁለቱ አገራት በየመን ውስጥ የተለያዩ ቡድኖችን ስለሚደግፉ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመካከላቸው ውጥረት ሰፍኖ ነበር።

    ግብፅ ወታደራዊ ድጋፍ ለማድረግ የተስማማችው የሳዑዲው ልዑል አገሪቱን ከጎበኙ ከአንድ ወር በኋላ ነው።

    በፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ የሚመራው የብሔራዊ መከላከያ ምክር ቤት፣ ሳዑዲ አረቢያ ደህንነቷን እንድታስጠብቅ “የሚቻለውን ሁሉ ድጋፍ” ለማድረግ መስማማቱን በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።

    መግለጫው ዝርዝር ባይሰጥም አል ሲሲ እሁድ ዕለት ፓርላማው ጦሩን እና ጦር መሣሪያ ማሰማራት እንዲችሉ ፈቃድ እንዲሰጣቸው ጥሪ አቅርበዋል።

    እሁድ ከሰዓት በኋላ የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራጋቺ እና የግብፁ አቻቸው ባድር አብደላቲ “በቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ” በስልክ መወያየታቸው ተዘግቧል።

    በሳዑዲ እና ሁቲዎች መካከል እየተካሄደ ያለው ውጊያ በሁለቱም ወገን ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት አድርሷል።

    ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው የየመን መንግሥት የሚጠቀምበት አውሮፕላን ማረፊያ እንዲሁም ቤተ መንግሥት ባለፈው ሳምንት ጥቃት ደርሶበታል።

    እሁድ ዕለት በአማፂያኑ ቁጥጥር ስር በምትገኘው ሳዳ በተፈጸመ የአየር ድብደባ ሕጻናት እና ሴቶችን ጨምሮ ዘጠኝ ሰዎችን መግደሉን የሁቲ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

    ቃል አቀባዩ አኒስ አል-አስባሂ ጥቃቱ በሳሃር ወረዳ የሚገኝ አንድ መኖሪያ ቤት ላይ ያነጣጠረ ነው በማለት 11 ሕጻናትን ጨምሮ 19 ሰዎች ቆስለዋል ብለዋል።

    አንዳንዶቹ በከባድ የጤና ሁኔታ ላይ እንደሚገኙም ገልጸዋል። አል አስባሂ ለጥቃቱ ሳዑዲ አረቢያን ተጠያቂ ቢያደርጉም ከሳዑዲ አረቢያ በኩል ግን እስካሁን የተሰጠ አስተያየት የለም።

    ሁቲዎች በበኩላቸው ባለፉት 24 ሰዓታት በሳዑዲ በሚደገፉት ወታደሮች ላይ በፈጸሙት ጥቃት ከ30 በላይ መግደላቸውን አስታውቀዋል።

    የሁቲዎች ወታደራዊ ቃል አቀባይ ብርጋዴር ጄኔራል ያህያ ሳሪ፣ በሰነዓ እና በሌሎች ከተሞች በሚገኙ የሰላማዊ ሰዎች መኖሪያ ላይ 110 ሚሳኤሎች መተኮሳቸውን ወይም የአየር ጥቃቶች መፈጸማቸውን ተናግረዋል።