ስፔን በኮከናት ውስጥ ተደብቆ ሊገባ የነበረ 2600 ኪሎ ግራም ኮኬይን መያዟን አስታወቀች

የፎቶው ባለመብት, gbc
የስፔን ባለሥልጣናት ከጋና በተላከ የኮኮናት ጭነት ውስጥ ተደብቆ የነበረ 2600 ኪሎ ግራም ኮኬይን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን አስታወቁ። ይህ በቁጥጥር ስር የዋለው አደንዛዥ ዕፅ ረቡዕ ዕለት በስፔን የግብር ኤጀንሲ እና በሲቪል ጥበቃ ይፋ ተደርጓል።
እንደ ሁለቱ ተቋማት ገለጻ፣ አደንዛዥ ዕፁ እንደ አውሮጳውያኑ አቆጣጠር ነሐሴ 2 /2016 በቴማ ወደብ ተጭኖ ነሐሴ 22 ቫሌንሲያ ወደብ በደረሱ ሁለት ኮንቴይነሮች ውስጥ ተደብቆ ነበር።
ኮንቴይነሮቹ ከፍተኛ ስጋት ያለባቸው ተብለው በመለየታቸው ለፍተሻ መመረጣቸውን ኤጀንሲዎቹ ገልጸዋል።
ባለሥልጣናት፣ ኮኮናቶቹንለመያዝ በተዘጋጁት የእንጨት ሳጥኖች ውስጥ በተገጠሙ ሐሰተኛ መደቦች ስር ኮኬይኑ ተጠቅጥቆ እንደተገኘ ተናግረዋል።
ተቋማቱ እንዳሉት ግለሰቦቹ የታሰሩት ዕቃዎቹን ወደ አገር ውስጥከማስገባትና ከማራገፍ ጋር በተያያዘ ነው። የግለሰቦቹ ማንነት ግን አልተገለጸም።
የስፔን ባለሥልጣናት ኮኬይኑበሳጥኖቹ ውስጥ የት ቦታ ላይ እንደተቀመጠም ሆነ ከጭነቱ ጋር በተያያዘ በጋና ውስጥ የተያዘ ሰው ስለመኖሩ የገለጹት ነገር የለም።
በቫሌንሲያ የተያዘው ይህ ዕፅ፣ ከጋና ጋር ግንኙነት ባላቸው ጭነቶች ላይ በአውሮፓ እና በመካከለኛው ምሥራቅ በተከታታይከተያዙት ከፍተኛ መጠን ያላቸው አደንዛዥ ዕፆች መካከል ነው።
ባለፈው መስከረም ወር የፈረንሳይ ጉምሩክ በደንከርክ ወደብ ወደ 3.9 ቶን የሚጠጋ ኮኬይን በቁጥጥር ስር አውሏል። በገበያ ላይ 225 ሚሊዮን ዩሮ ይገመታል የተባለው ይህ አደንዛዥ ዕፅ፣ ከጋና የመጣ የፕላስቲክ ቆሻሻ ተብሎ በተመዘገበ ኮንቴይነር ውስጥ ተደብቆ የተገኘ ነበር።
በቀጣናው አንዳንድ አካባቢዎች ያለውን የላላ የድንበር ቁጥጥር እና ደካማ የሕግ ማስከበር ስርዓት በመጠቀም የወንጀል ቡድኖች ወደ አውሮፓ ለሚላክ ኮኬይን ምዕራብ አፍሪካን እንደ መሸጋገሪያ መስመር እየተጠቀሙባት ይገኛሉ።

















