በኒውዮርክ ሕንጻ ተደርምሶ ቢያንስ አራት ሰዎች ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በኒውዮርክ ከተማ ውስጥ ያለ አንድ ሕንጻ ረቡዕከሰዓት በኋላ ተደርምሶ ቢያንስ አራት ሰዎች ሞቱ።
የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ኒውስ የአካባቢ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ እንደዘገበው በአደጋው 19 ሰዎች የቆሰሉ ሲሆን ከእነዚህም መካከል አራቱ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ባለ ሦስት ፎቅ ሕንጻው ከተደረመሰ በኋላ ከ250 በላይ የድንገተኛ አደጋ ሠራተኞች ወደ ሥፍራው በማምራት ሰፊ የፍለጋና የማዳን ስራ ጀምረዋል።
የእሳት አደጋ ሠራተኞች በአቧራ የተሸፈነች እና ከአደጋው የተረፈች ሴት በቃሬዛ ከፍርስራሹ ሲያወጡ ታይተዋል። በኋላም ግለሰቧ ነፍሰ ጡርመሆኗ ተገልጿል።
ቢቢሲም ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የኒውዮርክ የእሳት አደጋ መምሪያን አነጋግሯል።
ሕንጻው በድንገት ለምን እንደተደረመሰ ለማወቅ ምርመራ ተጀምሯል።
በቦታው የነበሩ የዐይን እማኞች ሕንጻው ማለዳ 4:00 አካባቢ በወደቀበት ወቅት አስፈሪ የፍንዳታ ድምጽ መሰማቱን ተናግረዋል።
ኒውዮርክ ታይምስ ያነጋገራት ኢማኑዌላ ካርሊስ “በእርግጥ ከሕንጻው ጀርባ ነው የምኖረው” ካለች በኋላ “ትልቅ ፍንዳታየመሰለ ድምጽ ተሰማ፣ ከዚያም የሰዎች ጩኸት ብቻ ነበር የሚሰማው” ስትል የነበረውን ሁኔታ አስረድታለች።
ጋዜጣው በስፍራው በርካታ የእሳት አደጋ መኪኖችና የፖሊስተሽከርካሪዎች መሰባሰባቸውን የሚያሳዩ ምስሎችን አጋርቷል።
በአካባቢውም የሳይረን ድምጽ ሳይቋረጥ ሲሰማ እንደነበር ጽፏል።
ዳሺክ በመባል የተጠቀሰ ሌላ የዐይን እማኝ ለአካባቢው የቴሌቪዥን ጣቢያ ፒክስ 11 “እንደዚህያለ ነገር ተመልክቼ አላውቅም” ብሏል።
ባለሥልጣናት እስካሁን ድረስ የሟቾቹንም ሆነ የተጎዱትን ሰዎች ማንነት አላሳወቁም።


















