በጋምቤላ ወረዳ ከምሽት አንድ ሰዓት በኋላ ነዋሪዎች እንዳይንቀሳቀሱ ተከለከለ

የፎቶው ባለመብት, Gambella Press Secretariat
ከጋምቤላ ክልል ዋና ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኘው ጋምቤላ ወረዳ ከምሽት አንድ ሰዓት በኋላ ነዋሪዎች ከቤት ውጪ እንዳይንቀሳቀሱ ገደብ ተጣለ።
ከዛሬ አርብ ጥቅምት27/2019 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረገው ሰዓት እላፊ የተጣለው፣ ክልሉ ውስጥ እና ከውጭ የሚመጡ የጸጥታ ስጋቶችን አስቀድሞ ለመከላከል እንደሆነ የወረዳው ሰላም እና ፀጥታ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኡጁሉ አኳይ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ይህ ገደብ እንዲጣል የወሰነው፣ የአኙዋ ብሔረሰብ ዞን መስከረም ላይ ያቋቋመው የወረዳው ጊዜያዊ አስተዳደር ነው።
የወረዳው አስተዳደር በፌስቡክ ገጹ ባወጣው መረጃ፣ “ከማታ 1፡00 ሰዓት አንስቶ እስከ ንጋት 12፡00 ሰዓት ድረስ ሕብረተሰቡ ከቤት ውጭ መንቀሳቀስ እንደማይችል” አስታውቋል።
“ሕጋዊ ፈቃድ ካላቸው የጸጥታ አካላት ውጭ” ማንኛውም ግለሰብ የጦር መሣሪያ ይዞ የሚያደርገው እንቅስቃሴ “በጥብቅ የተከለከለ” እንዲሁም “ጥብቅ ክትትል” የሚደረግበት መሆኑን ገልጿል።
እንደ ወረዳው ገለጻ፣ እነዚህ እገዳዎች የተጣሉት “የጸጥታ ማስከበር ሥራውን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ እና ቀጠናውን በፍጥነት ወደ መደበኛ ሰላም ለመመለስ” በማሰብ ነው።
ለቢቢሲ ማብራሪያ የሰጡት የወረዳው ሰላም እና ፀጥታ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኡጁሉ፤ በክልሉ ውስጥ የሚታየው የጸጥታ መደፍረስ ገደቡ እንዲጣል ምክንያት የሆነ አንድ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከደቡብ ሱዳን ይነሳሉ ያሏቸውን ታጣቂዎች የሚያደርሱት ጉዳትም ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል። “እንደሚታወቀው በጋምቤላ የእርስ በእርስ ግጭት አለ። በዚያ መሠረት ድምበሩም ክፍት ስለሆነ ሾልከው የሚገቡ ታጣቂዎች አሉ።
ወጣ ያሉ ቀበሌዎቻችን ላይ ጥቃት ያደርሳሉ” ብለዋል። በጥቅምት መጀመሪያ በአንድ ቀበሌ ላይ በደረሰ ጥቃት የአንድ ሰው ሕይወት አልፎ አራት ሰዎች መጎዳታቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
ከትናንት ሐሙስ ዕለት አንስቶም ሌላ ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል የሚያመለክት እንቅስቃሴ መታየቱን ተናግረዋል።
“ተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት የመፍጠር አዝማመሪያዎች አሉ እርሱን ለመከላከል ነው” ሲሉ የተጣለው ሰዓት እላፊ ከዚህ ጋር የተያያዘ መሆኑን አብራርተዋል።
ከወረዳው በ18 ኪሎ ሜትር ላይ በሚገኘው የክልሉ መዲና ጋምቤላ ከተማም በጥቅምት መጀመሪያ ላይ በተመሳሳይ ከ12 ሰዓት ጀምሮ እስከ ንጋት ድረስ የሰዎችና የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ እንዳይደረግ ክልከላ ጥሎ ነበር።
በዋና ከተማው እግዳ የተጣለው ሰዎች የተገደሉበት ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ ነው። ቀጥሎ በከተማው በተፈጠረ ግጭት ምክንያት የክልሉ መንግሥት መስሪያ ቤቶች ተዘግተው ነበር።








