የኢራንን ጦርነት ለማስቆም የሚደረጉ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ከምን ደረሱ?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር ሼክ መሐመድ ቢን አብዱራህማን ቢን ጃሲም አል ታህኒ የአሜሪካ-ኢራን ግጭትን ለመፍታት የሽምግልና ጥረቶች እንደቀጠሉ ተናግረው፤ አሜሪካ “መፍትሄ ለማግኘት እርምጃዎችን ለመውሰድ” ፍላጎት እና ዝግጁነት አላት ብለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተያየት የተሰማው ዶናልድ ትራምፕ ዋይት ሐውስ ከኢራን ተወካዮች ጋር እየተነጋገረ መሆኑን እና “ከኢራን ጋር [በሚደረገው ድርድር] የተሻለ እመርታ አሳይተናል” ካሉ በኋላ ነው።
ይሁን እንጂ የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት፤ ትራምፕ በመከላከያ ሚኒስትሩ ፒት ሄግሴት እና በአሜሪካ ማዕከላዊ ጦር ኮማንድ (ሴንትኮም) አዛዥ ብራድ ኩፐር ዳግም ጥቃቶች እንዲጀምሩ ግፊት እየተደረገባቸው ነው።
የሴንትኮም አዛዥ የአሜሪካን የባሕር እገዳ በማስፋፋት፣ ከኢራን ወደቦች የሚነሱ የአቅርቦት መስመሮችን “ለማስተጓጎል” የተዘጋጀ አዲስ ዕቅድ አስተዋውቀዋል።
የኢራን የደኅንነት ጉዳዮች ኃላፊ ሞህሴን ሬዛኢ ደግሞ ትራምፕ ጥቃቶችን ዳግም እንዳይጀምሩ በማስጠንቀቅ፣ “ጦርነት ብትጀምሩ አውዳሚ ምላሽ ይገጥማችኋል” ብለዋል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ በ48 ሰዓታት ውስጥ ከ12 የቀጣናው አገራት አቻዎቻቸው ጋር ውይይት ማድረጋቸውን የእስላማዊ ሪፐብሊክ ዜና ወኪል ዘግቧል።
አራግቺ ከቀጣናው ውጭ ያሉ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት የሌለበት ክልላዊ የደኅንነት ሥርዓት እንዲፈጠር ጥሪ አቅርበዋል።

















