የሳዑዲ ነዳጅ ኩባንያ አራምኮ ሕንፃ በሚሳኤል ጥቃት ጉዳት እንደደረሰበት እማኞች ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በሳዑዲ አረቢያ ሪያድ የሚገኘው የአገሪቱ ብሔራዊ የነዳጅ ኩባንያ (አራምኮ) ሕንፃ አካበቢ እሑድ ጠዋት ከፍተኛ ፍንዳታ መስማታቸውን ለፈረንሳይ የዜና ወኪል ኤኤፍፒ የዓይን እማኞች ተናገሩ።
በሪያድ ንጉስ አብደላ ፋይናንስ ዲስትሪክት የሚገኘው የአራምኮ ሕንፃ በበርካታ ወለሎች ላይ ጉዳት መድረሱን እማኞች ጨምረው ገልጸዋል።
በጥቃቱ አንዳንድ ወለሎች ክፉኛ የተጎዱ ሲሆኑ፣ ሌሎች ወለሎች ላይ ደግሞ በውጫዊ ክፍሎቻቸው (መስኮቶች) ላይ ጉዳት ታይቷል።
የዓይን እማኞች በደኅንነት ስጋት ምክንያት ስማቸው እንዳይገለጽ ጠይቀዋል።
በሳዑዲ አረቢያ የሚመራው ጥምር ጦር እሁድ ማለዳ ወደ ሪያድ እና ሌሎች ክልሎች ያነጣጠሩ ያላቸው ሁለት ባለስቲክ ሚሳኤሎችን እና ሁለት ክሩዝ ሚሳኤሎችን ማክሸፉን አስታውቋል።
ጦሩ ሚሳኤሎቹን የተኮሱት ሁቲዎች ናቸው ሲል ከስሷል።
የሳዑዲ የኢነርጂ ሚኒስቴር በበኩሉ የተሞከረው ጥቃት “የወዳደቁ ቅሪቶች በሕንፃው ላይ ቀላል ጉዳት አስከትለዋል” ብሏል።
በአደጋው የተጎዳ ወይም የሞተ ሰው እንደሌለም ጨምሮ ገልጿል።
አሶሼትድ ፕሬስ የሳዑዲን ዓለም አቀፍ ግንኙነት ማዕከል እና አራምኮ አስተያየት እንዲሰጡ ቢጠይቅም ወዲያውኑ ምላሽ አላገኘም።
በሳዑዲ አረቢያ የሚመራው ጥምር ጦር አክሎም ከየመን ጋር በድንበር የሚዋሰነውን ደቡባዊ ክልል ዒላማ ያደረገ አንድ ባለስቲክ ሚሳኤል ማክሸፉን አስታውቋል።
ይህ አካባቢ በተደጋጋሚ በሁቲ ታጣቂዎች ጥቃቶች ይደበደባል።
የሁቲ ጥቃት የተሰማው ቅዳሜ እለት በአማፂዎች ቁጥጥር ስር ባለችው የየመን ዋና ከተማ ሰንዓ አቅራቢያ በሳዑዲ የአየር ጥቃቶች ከተፈፀሙ በኋላ ነው።
የሁቲ ባለሥልጣናት እንዳሉት በእነዚህ ጥቃቶች ቢያንስ 27 ሰዎች ተገድለዋል።

















