ቀጥታ , የሁቲ አማፂያን ሳዑዲ አረቢያ በፈጸመችው የአየር ጥቃት ቢያንስ 33 ሰዎች መገደላቸውን አስታወቁ

የመን ከሁቲ ጋር የቅርብ ግንኙነት ያላቸው መገናኛ ብዙኃን ሳዑዲ አረቢያ በፈጸመችው የአየር ጥቃት እናቶች እና ሕፃናትን ጨምሮ ቢያንስ 33 ሰዎች መገደላቸውን ዘገቡ። በየመን ዓለም አቀፍ ዕውቅና ላለው መንግሥት ድጋፍ የሚያደርገው በሳዑዲ አረቢያ የሚመራው ጥምር ኃይል እስካሁን ስለጥቃቱ አስተያየት አልሰጠም። በሁቲዎች የሚተዳደረው አል ማሲራ የቴሌቪዥን ጣቢያ በቀጥታ ባሰራጨው ምስል፣ ከዋና ከተማዋ ሰነዓ በስተምሥራቅ በምትገኘው አል-ሻሪያ ከተማ ውስጥ የሕይወት አድን ሠራተኞች ከፈራረሱ ሕንጻዎች ሥር አስከሬኖችን ሲያወጡ አሳይቷል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. አሜሪካ በአርሲ የተፈፀሙ ግድያዎች ላይ ኢሰመኮ ያወጣውን “ዝርዝር እና ግልጽ” ሪፖርት እንደምትደግፍ ገለጸች

    አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ

    በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የሆኑት ኧርቪን ማሲንጋ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በቅርቡ በአርሲ የተፈፀሙ ግድያዎችን በተመለከተ ያቀረበውን “ዝርዝር እና ግልጽ ሪፖርት” አሜሪካ እንደምትደግፍ ገለጹ።

    አምባሳደር ማሲንጋ በኤምባሲው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ላይ ባጋሩት ጽሑፍ፣ ኮሚሽኑ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በርካታ እስረኞች እንዲፈቱ በማመቻቸት ያደረገውን ጥረትም አገራቸው ትደግፋለች ብለዋል።

    ኮሚሽኑ በተለይ በግጭት በተጎዱ እንደ ትግራይ ባሉ አካባቢዎች ምጣኔ ሃብት እንዲያገግም ፣ ተቋማት እንዲገነቡ፣ የፍትሕ ሥርዓት፣ ዲሞክራሲ እና ማሕበራዊ ግንኙነቶች እንዲመለሱ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ያለውን ትብብር ያጠናክራል ብላ አሜሪካ ተስፋ እንደምታደርግም አክለዋል።

    ትናንት ሐሙስ፣ ጥቅምት 26/2019 ዓ.ም. ከኢሰመኮ ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ ጋር ውይይት ማድረጋቸውን የገለጹት አምባሳደር ማሲንጋ፣ ለኮሚሽኑ ሪፖርት ድጋፋቸውን የገለጹት፣ ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ ክልል አርሲ ውስጥ በንፁሃን ዜጎች ላይ የተፈጸሙ ግድያዎች በአግባቡ ተመርምረው የወንጀሉ ፈጻሚዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ የኢትዮጵያ መንግሥትን ከጠየቁ በኋላ ነው።

    ከሁለት ሳምንት በፊት በቀድሞው የኦሮሚያ ክልል አወቃቀር አርሲ ዞን በአዲሱ አደረጃጀት በደቡብ ምሥራቅ ዞን ሥር በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች በነዋሪዎች ላይ በተፈጸሙ ጥቃቶች ከ60 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አስታውቃለች።

    እስካሁን ለጥቃቱ ኃላፊነቱን የወሰደ አካል የለም። ሆኖም የክልሉ ኮሚዩኒኬሽን “ ጽምዶን” ተጠያቂ አድርጓል።

    ኢሰመኮ ጥቅምት 24 ፣ 2019 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት በኦሮሚያ ክልል ሽርካ ወረዳ በተፈጸሙ የተለያዩ ጥቃቶች 48 ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል።

    ጥቃቱም "በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት" እና "ኢመደበኛ ታጣቂዎች" መፈፀሙን ገልጿል። በአርሲ ዞን አሁንም ጥቃቶች መቀጠላቸውን እና ባለፉት ቀናትም በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    ተያያዥ ዜናዎች፡

  2. ኢራን በኒውክሌር ጉዳይ ላይ ለአሜሪካ ምክረ ሐሳብ መላኳን የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣን ተናገሩ

    በቴህራን አደባባይ ላይ የተሰቀለ ፖስተር

    የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በእስላማዊቷ ሪፐብሊክ ላይ የቀረውን ሁሉ “እናጠፋዋለን” በማለት ከዛቱ በኋላ ቴህራን ለዋሺንግተን ኒውክሌርን በሚመለከት የስምምነት ሀሳብ መላኳ ተገለጸ።

    ሮይተርስ የዜና ወኪል አንድ ከፍተኛ የኢራን ባለሥልጣንን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ ምክረ ሃሳቡ በኳታር በኩል ለዋሽንግተን የተላለፈ ሲሆን፣ አሜሪካ የቴህራንን ሰባት ቅድመ ሁኔታዎች ካሟላች በኋላ ብቻ ለውይይት እንደሚቀርብ ተገልጿል።

    ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁት ከፍተኛ ባለሥልጣን፣ ዋሽንግተን ሀሳቡን እየገመገመች እንደሆነ ለሮይተርስ የተናገሩ ቢሆንም፣ ተጨማሪ መረጃ ለመስጠት ግን ፈቃደኛ አልሆኑም።

    የኢራን ከፍተኛ የደህንነት ኃላፊ ሞህሴን ሬዛኢ በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ “ዲፕሎማሲን በሚመለከት ለአሜሪካ ሰባት ቅድመ ሁኔታዎችን አሳውቀናል። እነዚህን ሰባቱን መስፈርቶች ተግባራዊ እስካላደረጉ ድረስ የሆርሙዝ ወሽመጥን አንከፍትም፣ እንዲሁም ወደ ድርድር አንገባም” ብለው ነበር።

    የኢራን ቅድመ ሁኔታዎች እስካሁን ድረስ በይፋ ባይገለጹም፣ በካህሌጅ ታይምስ በመባል የሚታወቀው መገናኛ ብዙኃን ባወጣው ዘገባ መሠረት ቴህራን ያቀረበቻቸው ጥያቄዎች ሊባኖስን ጨምሮ በክልሉ ያሉ ግጭቶች ሙሉ በሙሉ እንዲቆሙ፣ አሜሪካ በኢራን ወደቦች ላይ የጣለችውን የባሕር ኃይል እገዳ እንድታነሳ፤ በኢራን ላይ የተጣሉ የአሜሪካ ማዕቀቦች እንዲነሱ፤ የኢራን በውጭ የታገዱ ንብረቶችና ገንዘቦች እንዲለቀቁ፤ አሜሪካ በቀጣናው ያላትን ጦር እነድትቀንስ፤ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ለደረሱ ጉዳቶች ካሳ እንዲከፈል፣ በኢራን ግዛት ላይ የሚፈጸሙ የአሜሪካ ጥቃቶች እንዲቆሙ የሚሉ ናቸው።

    በሌላ በኩል፣ ዋሽንግተን ማንኛውም የመጀመሪያ ዙር ድርድር የኢራንን የኒውክሌር ፕሮግራም ጉዳይ ማካተት እንዳለበት ገልጻለች። ይህም በሁለቱ ወገኖች መካከል ማንኛውም ስምምነት ላይ ለመደረስ የኒውክሌር ጉዳይ አንዱ ዋና የውይይት አጀንዳ እንደሚሆን ያመለክታል።

    ይህ የኒውክሌር ስምምነት ሀሳብ የቀረበው፣ በአሜሪካና በኢራን መካከል ያለው ጦርነት ከአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫዎች በኋላ እንደገና ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት በተጠናከረበት እና አደራዳሪዎች ግጭቱን ለማስቆም ጥረታቸውን ባጠናከሩበት ወቅትነው።

    ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከምርጫው በኋላ ወታደራዊ ዘመቻዎች እንደገና ሊቀጥሉ እንደሚችሉ ያላስተባበሉ ሲሆን በሌላ በኩል ኢራንም ጦርነቱ እንደገና ከተቀሰቀሰ ጠንካራ ሰፊ ምላሽ ለመስጠት ማቀዷ ተነግሯል።

    አሜሪካና እስራኤል ባለፈው ዓመት የካቲት ወር መጨረሻ በኢራን ላይ ድብደባ ከፈጸሙ በኋላ፣ ኢራን በበኩሏ በእስራኤል እና የአሜሪካ ጦር ሰፈሮችን በሚያስተናግዱ የባህረ ሰላጤው አገራት ላይ ጥቃቶችን ፈጽማለች።

    ግጭቱ ወደ ሊባኖስ ተስፋፍቶ በኢራን በሚደገፈው ሄዝቦላህ እና በእስራኤል መካከል ውጊያዎች ተካሂደዋል። በቅርቡ ደግሞ ቀውሱ ወደ የመን ተሻግሮ ከኢራን ጋርየሚቀራረቡት የሁቲ ታጣቂዎች በሳዑዲ አረቢያ ውስጥ በሚገኙ የኃይል ማመንጫ ተቋማት፣ አውሮፕላን ማረፊያዎች እና ሌሎች ዒላማዎች ላይ ጥቃቶችን መፈጸማቸው ተዘግቧል።

    ተጨማሪ ዘገባ፡

  3. የጥቅምት 27/ 2019 ዓ. ም. የቀጥታ ስርጭት ተጀምሯል

    የቢቢሲ አማርኛ ወዳጆች እንደምን አደራችሁ፤ የጥቅምት 27/ 2019 ዓ. ም. የቀጥታ ስርጭታችን ተጀምሯል።

    የአገር ውስጥ እና የውጭ ዜናዎችን በአጭሩ እናቀርብላችኋለን። እንድትከታተሉን በአክብሮት እንጋብዛለን።