አሜሪካ በአርሲ የተፈጸሙ ግድያዎች በጽኑ እንዳሳሰቧት ገልጻ በአግባቡ እንዲመረመሩ ጠየቀች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካ በኦሮሚያ ክልል አርሲ ውስጥ በንፁሃን ዜጎች ላይ የተፈጸሙ ግድያዎች በአግባቡ ተመርምረው የወንጀሉ ፈጻሚዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ የኢትዮጵያ መንግሥትን ጠየቀች።
በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ ቅዳሜ ዕለት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ ባወጣው ጽሁፍ አርሲ ውስጥ ዒላማ በለየ ሁኔታ የሚፈጸመውን ግድያ በተመለከተ በቅርብ ጊዜ እየወጡ ያሉ ሪፖርቶች የአሜሪካ መንግሥትን በጽኑ እንዳሳሰቡት ገልጿል።
ከአንድ ሳምንት በፊት በቀድሞው የኦሮሚያ ክልል አወቃቀር አርሲ ዞን በአዲሱ አደረጃጀት በደቡብ ምሥራቅ ዞን ሥር በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች በነዋሪዎች ላይ በተፈጸሙ ጥቃቶች ከ60 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አስታውቃለች።
ቤተ ክርስቲያኗ ጥቃቱ ለዓመታት የቀጠለ እና በዋናነት ዒላማ የሆኑት ምእመኖቿ መሆናቸውን በማመልከት መንግሥት የንጹኃንን ግድያ እንዲያስቆም እና የዜጎችን በሕይወት የመኖር እና በነጻነት የማምለክ መብት እንዲያስከብር ጠይቃለች።
በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ በወጣው መግለጫ "ዩናይትድ ስቴትስ በሃይማኖት፣ በብሔር ወይም በፖለቲካ ተነሳስተው የሚፈጸሙ ጥቃቶችን አጥብቃ ታወግዛለች" በማለት አርሲ ውስጥ የተፈጸሙ ዓይነት "አሰቃቂ ጥቃቶች በማንኛውም ቡድን ላይ መፈጸማቸው መቆም አለበት" ሲል አሳስቧል።
ጨምሮም አሜሪካ የኢትዮጵያ መንግሥት ይህን አሳዛኝ ክስተት በአግባቡ እንዲያጣራ እና ወንጀሉን የፈጸሙትን ለፍትሕ እንዲያቀርብ ጥሪ ታቀርባለች ብሏል።
ባለፉት ሳምንታት አርሲ ውስጥ በሚገኙ አካባቢዎች በተከታታይ በተፈጸሙ ጥቃቶች ሕጻናት እና ሴቶችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ይህንን በስፋት አነጋጋሪ የሆነውን ግድያ በተመለከተ የፌደራል መንግሥቱ እስካሁን በይፋ ምንም ያለው ነገር ባይኖርም የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ ባለፈው ሳምንት በሰጡት መግለጫ ለተፈጸመው ጥቃት የአማጽያን በትብብር የሆነው ስብስብ ተጠያቂ አድርገዋል።
ባለሥልጣኑ ይህ ቡድን "በሰሜን ኢትዮጵያ የደረሰበትን ከባድ ኪሳራ አቅጣጫ ለማስቀየር የብሔር እና የሃይማኖት ግጭት ለመፍጠር ያደረገው እንቅስቃሴ ከሽፏል" በማለት ክልሉ ጥቃቱን በፈጸሙ አካላት ላይ "መውሰድ የጀመረውን እርምጃ" ይቀጥላል ብለዋል።
በኦሮሚያ ክልል በቀድመው አርሲ ዞን በአሁኑ በደቡብ ምሥራቅ ዞን ውስጥ እስካሁን ማንነታቸው እና ዓላማቸው በይፋ ያልታወቁ ኃይሎች ነዋሪዎችን በተለይም የኦርቶዶክስ ክርስትና ሃይማኖት ተከታዮችን ዒላማ ሲያደርጉ ዓመታት ተቆጥረዋል።
በተለያዩ ጊዜያት በተፈጸሙ ጥቃቶች በርካታ ነዋሪዎች ሲገደሉ፣ ቤቶች እና አብያተ ክርስቲያናት ላይም ጉዳት መድረሱ መዘገቡ ይታወሳል።
































