ጆሴፍ ካቢላ እንዴት በማዕድን ከበለጸገችው አገር ፕሬዝዳንትነት ወደ አማፂ መሪነት ደረሱ?

ጆሴፍ ካቢላ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ጆሴፍ ካቢላ በአውሮፓውኑ 1997 አባታቸውን የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መሪ ያደረገው የአማፂ ኃይሎች ጥምረት አዛዥ ነበሩ። በኋላም አባታቸውን ተክተው ፕሬዝደንት ሆኑ። አሁን ደግሞ በ55 ዓመታቸው ዳግም የአማፂ ቡድን መሪ ሆነዋል።

ይበልጥ የሚያስገርመው ደግሞ ከሥልጣን ሊያስወግዷቸው የሚታገሏቸው ሰው፣ ከ18 ዓመታት የፕሬዝዳንትነት ዘመናቸው በኋላ ሥልጣናቸውን በእጃቸው ያስረከቧቸው እና ከሥልጣን ከወረዱ በኋላ ደግሞ አብረዋቸው የጥምረት መንግሥት የመሠረቱት ፌሊክስ ቺሼኬዲ ናቸው።

የሚገርመው ይህ ብቻ አይደለም፤ ካቢላ በፕሬዝዳንትነታቸው ዘመን ይዋጉት ከነበረው አማፂ ቡድን አንዱ ዛሬ በአዲሱ ጥምረታቸው ውስጥ ተካትቷል።

የካቢላ ሕይወት፣ የዲሞክራቲክ ኮንጎን የፖለቲካ መለዋወጥ እንዲሁም ፈጣን የጥምረት እና የግንኙነት ለውጦች የሚያንጸባርቅ ነው። በአገሪቱ ጥምረቶች አጭር ዕድሜ ሲኖራቸው የትጥቅ እንቅስቃሴ ደግሞ ሁልጊዜ የሚታይ ስጋት ነው።

ካቢላ ከሳምንታት በፊት ኤፍአርኤን የተባለው የአማፂያን ኃይሎች መሪ ሆነው ሲሰየሙ፣ በብዙ የአገሪቱ ዜጎች ዘንድ ለረዥም ጊዜ የነበረውን እምነት አረጋግጧል። ይኸውም የቀድሞው ፕሬዝዳንት ባለፈው ዓመት ጎማ እና ቡካቩ ከተሞችን ጨምሮ የምሥራቅ ኮንጎን ሰፊ ክፍል ከተቆጣጠረው ኤም23 አማፂ ቡድን ጋር ይሠራሉ የሚለው ነው።

ይህ እውነታ በዲሞክራቲክ ኮንጎ ከፍተኛ መናወጥ ፈጥሯል።

የምዕራብ አውሮፓን ሁለት ሦስተኛ ያህል ስፋት ያላት ሰፊዋ አገር ዲሞክራቲክ ኮንጎ በወርቅ፣ በአልማዝ እንዲሁም ለሞባይል ስልኮች እና ለኤሌክትሪክ መኪና ባትሪዎች ሥራ በሚውሉ ማዕድናት የበለፀገች ናት።

ለካቢላ፣ ይህ ጥምረት ያጡትን ስልጣን መልሰው ለማግኘት መንገድ ሊፈጥርላቸው ይችላል።

እስካሁን ሰፊ አገራዊ ቅቡልነት ለሌላቸው ለኤም23 አማፂያን ደግሞ፣ የቀድሞ የአገር መሪ ቡድኑን መቀላቀሉ ለልምድ እና ከቀድሞ ግንኙነታቸው አንዳች ጥቅም እንዲያገኙ ይረዳቸዋል።

ነገር ግን ካቢላ እና ኤም23 ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ቺሼኬዲን ከሥልጣን የማስወገድ ዓላማቸውን ሊያሳኩ ይችላሉ ወይስ አይችሉም የሚለውን ለመተንበይ ጊዜው በጣም ገና ነው።

ጆሴፍ ካቢላ እና ፌሊክስ ቺሴኬዲ
Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የፖሊሲ ተንታኝ የሆኑት ሄንሪ-ፓሲፊክ ማያላ፣ ካቢላ የፖለቲካ ተፅዕኗቸውን መልሰው ለማግኘት የሚያስችላቸው ሌላ አማራጭ የተጣበበ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋለ። "በእውነቱ ሌላ ምርጫ አልነበረውም" ብለዋል።

ካቢላ በአገር ክህደት ወንጀል በሌሉበት ተከሰው ሞት የተፈረደባቸው ከመሆኑ በተጨማሪ፣ ኤም23ን ደግፈዋል በሚል ክስ በአሜሪካ ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል። በመሆኑም ከኤም23 ጋር ጥምረት የፈጠሩት ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ የሚያስችል ዋስትና ፈልገው ሊሆን እንደሚችል ማያላ ጠቁመዋል።

"ከፍተኛ ዋስትና ሳይሰጠው ይህን ወደሚያክል ትልቅ ተግባር ዘልሎ ይገባል ብዬ አላምንም" ሲሉ ማያላ ተናግረዋል።

የኤም23 ወታደራዊ ጥንካሬ ካቢላ ወደፊት ከኮንጎ መንግሥት ጋር በሚደረጉ ድርድሮች የበለጠ የመደራደሪያ አቅም እንዲኖራቸው ሊያደርግ እንደሚችልም ጨምረው ገልፀዋል።

የካቢላ ተሳትፎ ግጭቱ ከምሥራቅ ኮንጎ አልፎ ወደ ሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ሊስፋፋ ይችል እንደሆነም ጥያቄ አስነስቷል።

የኤም23 የመሬት ቁጥጥር ስኬቶች በአብዛኛው በአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል የተገደበ ሲሆን፣ እነዚህ አካባቢዎች ከዋና ከተማዋ ኪንሻሳ 1,500 ኪሎ ሜትር ያህል ይርቃሉ።

የካቢላ የፖለቲካ ትስስሮች የአማፂያኑ ተፅዕኖ እንዲጨምር ሊያደርጉ ቢችሉም፣ ይህ ግን ወታደራዊ ዘመቻቸውን በመላው አገሪቱ ለማስፋፋት ያስችላቸዋል ማለት አይደለም።

ካቢላ በመላው አገሪቱ ያላቸው ፖለቲካዊ ተፅዕኖ እስከ ምን ድረስ እንደሆነም ግልጽ አይደለም።

በአውሮፓውያኑ 2001 አባታቸው ሎረንት ካቢላ በምሥጢራዊ ሁኔታ ከተገደሉ በኋላ ወደ ሥልጣን የመጡት ጆሴፍ ካቢላ በኪንሻሳ በአብዛኛው እንደ ውጭ አገር ሰው ነው የሚታዩት።

በኪንሻሳ በስፋት ከሚነገረው ሊንጋላ ቋንቋ ይልቅ፣ በምሥራቃዊ ዲሞክራቲክ ኮንጎ እና በምሥራቅ አፍሪካ በሰፊው የሚነገረውን ስዋሂሊ ቋንቋ ይበልጥ ይናገራሉ።

የአባታቸው አማፂ ቡድንም ከምሥራቅ ኮንጎ ተነስቶ ከሰባት ወራት ያህል ጉዞ በኋላ ኪንሻሳ በመግባት አገሪቱን ከ30 ዓመታት በላይ እንደግል ንብረታቸው ሲያስተዳድሩ የቆዩትን ሞቡቱ ሴሴ ሴኮን ከሥልጣን አስወግዶ ግንቦት 1997 ላይ የአገሪቱን ሥልጣን መቆጣጠር ችሏል።

ነገር ግን የጆሴፍ ካቢላ ኤፍአርኤን ያንን ታሪካዊ ጉዞ መድገም እንደሚችል የሚያሳይ ብዙ ምልክት የለም። ሆኖም ካቢላ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ባደረጉት ንግግር ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ቲሼኬዲን ከሞቡቱ ጋር አመሳስለው ነበር።

ካቢላ በንግግራቸው ቲሼኬዲን ሲገልጿቸው "አምባገነን ነው፤ እሱ ትክክል ነው ብሎ የሚያስበውን ለመጫን እና ለመወሰን ይፈልጋል፤ የአገሪቱ ከፍተኛ ሕግ የሆነውን ሕገ መንግሥት ለመከተል ዝግጁ አይደለም" ብለዋል።

የካቢላ እና የቲሼኬዲ ፀብ የጀመረው የ2019 አወዛጋቢ ምርጫን ተከትሎ ሥልጣንን የሚጋሩበት ስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ ቲሼኬዲ የካቢላን የፓርላማ የበላይነት መያዝ የሚያስችላቸውን እርምጃ በመውሰዳቸው ምክንያት በታኅሣሥ 2020 ስምምነቱ ከፈረሰ ወዲህ ነው።

ይህም የቀድሞ አጋሮች ወደ ተቀናቃኝነት እንዲቀየሩ ሲያደርግ ካቢላም በስደት ወደ ደቡብ አፍሪካ እንዲሄዱ አድርጓል።

ካቢላ በስደት ላይ እያሉ በቲሼኬዲ ላይ የሚያቀርቡት ትችት እየበረታ መጥቶ በ2025 ወደ ኮንጎ ተመልሰው በአማፂያን ቁጥጥር ስር በነበረችው ጎማ ከተማ ታይተዋል።

በዚያው ዓመት መስከረም ወር፣ አንድ ወታደራዊ ፍርድ ቤት በአገር ክህደት እና በምሥራቅ ኮንጎ ዓመፅን በገንዘብ መደገፍን ጨምሮ በተለያዩ ክሶች በሌሉበት ሞት ፈርዶባቸዋል።

በወቅቱ ካቢላ ክሶቹን አጣጥለው ነበር።

ካቢላ፣ የዲሞክራቲክ ኮንጎ አማፂያንን ከሚደግፉት ከርዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ጋር የቆየ ግንኙነት እንዳላቸውም ይታመናል።

የዓለም አቀፍ ደኅንነት ተንታኝ ኦቪግዌ ኤጉዌጉ እንደሚሉት፣ ካቢላ የፖለቲካ ተፅዕኗቸውን መልሰው ለማግኘት ተስፋቸውን በወታደራዊ ኃይል ላይ ሲጥሉ፣ ቲሼኬዲ ደግሞ በሕገ መንግሥቱ ከተፈቀደው በላይ የሥልጣን ዘመናቸውን ለማራዘም እየሞከሩ ይመስላሉ።

"በዚህ ሁኔታ የኮንጎ ሕዝብ በሁለቱም አጋጣሚዎች ተሸናፊ የሚሆን ይመስላል፤ ምክንያቱም ከእነዚህ ሁለት ወገኖች አንዳቸውም ለምሥራቅ ኮንጎም ሆነ ለመላው አገሪቱ አሳማኝ የኢኮኖሚ ለውጥ ዕቅድ አያቀርቡም" ሲሉ ኤጉዌጉ ተናግረዋል።