በፖላንድ የአገሪቱን ዋና ፍርድ ቤት ለመቆጣጠር ፍጥጫ በመፈጠሩ ፕሬዝዳንቱ ጉዟቸውን አየር ላይ አቋርጠው ተመለሱ

ሰልፈኞች እና ፖሊሶች ተፋጥጠው
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በፖላንድ መንግሥት እና ዋና በሚባሉ ዳኞች መካከል የተፈጠረው ውዝግብ መባባሱን ተከትሎ በአገሪቱ ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ፖሊስ ተሰማራ። የአገሪቱ ፕሬዝዳንት በውዝግቡ ምክንያት ጉዟቸውን አየር ላይ ሰርዘው ወደ አገር ተመልሰዋል።

ውዝግቡ የተፈጠረው፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ቱስክ መንግሥት እና ከዚህ ቀደም ሥልጣን ላይ በነበሩ ቀኝ ዘመሙ የሕግ እና ፍትሕ ፓርቲ አመራሮች መካከል ነው።

የፍትሕ ሚኒስትሩ ዋልዴማር ዡሬክ በፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቦግዳን ሽቪየንችኮቭስኪ እና ምክትል ፕሬዚዳንቱ ባርትዎሚዬይ ሶሃይንስኪ ላይ የወንጀል ክስ ለመመስረት ፍላጎት አላቸው።

ይህንን ለማድረግም የፕሬዝዳንቱ እና ምክትላቸው ያለመከሰስ መብት እንዲነሳ ጥያቄ ማቅረባቸውን አስታውቀዋል።

ጥያቄው ውዝግቡን በማካረሩ፣ የሕግ እና ፍትሕ ፓርቲ ደጋፊዎች በዋርሳው ከተማ የሚገኘው ፍርድ ቤት ደጅ ላይ ለተቃውሞ ተሰብስበዋል። ፖሊስም ሁኔታውን ለመቆጣጠር ጣልቃ ገብቷል።

የፍትሕ ሥርዓቱን ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ እንደሚያደርጉ ቃል የገቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ቱስክ፣ የፍርድ ቤቱ አመራሮች ላይ እርምጃ የመውሰዱን ሃሳብ ደግፈዋል።

በተቃዋሚው ፓርቲ የሚደገፉት የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ካሮል ናውሮትስኪ ወደ ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤቱ መግባታቸውን የጽሕፈት ቤታቸው ኃላፊ አስታውቀዋል።

ፕሬዝዳንቱ በዋና ከተማዋ ዋርሶ የተፈጠረውን ውዝግብ ለመፍታት ሲሉ ወደ ሴኔጋል ያደርጉት የነበረውን ጉዞ አየር ላይ አቋርጠው ወደ አገር ተመልሰዋል። ወደ ሴኔጋል እየሄዱ የነበረው በዳካር በሚካሄደው የበጋ የወጣቶች ኦሊምፒክ ውድድር ላይ ለመገኘት ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሰልፈኞች ወደ ፍርድ ቤቱ ግቢ እንዳይገቡ ለመከላከል ሲባል አድማ በታኝ ፖሊሶች ተሰማርተዋል።

ሕገ መንግሥታዊው ፍርድ ቤት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ባሰፈረው መልዕክት፣ መንግሥት ክስ ሊመሠርትባቸው የሚፈልጋቸው ሁለቱ ዳኞች፣ አሁንም በሕጋዊ መንገድ የተሾሙ የፍርድ ቤቱ ከፍተኛ ዳኞች መሆናቸውን ገልጿል።

"በእነዚህ እርምጃዎች ውስጥ የሚሳተፉ ሰዎች በሙሉ የመፈንቅለ መንግሥት ወንጀል እየፈጸሙ ነው" ብሏል።

የአገሪቱን መንግሥት የሚመሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቱስክ በበኩላቸው፣ "የሕግ የበላይነትን ማስፈን ግዴታችን ነው። ለዓመታት ከቆየው የሕግ እና ፍትሕ ፓርቲ ሕገ-ወጥነት በኋላ፣ ይህ ቆራጥ እርምጃ የሚጠይቅ አስቸጋሪ እና አንዳንዴም ህመም የሚፈጥር ሂደት ነው። ከዚህ ውጭ ሌላ መንገድ የለም" ሲሉ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ጽፈዋል።

የሕግ እና ፍትሕ ፓርቲ በአውሮፓውያኑ 2015 የአገሪቱን ሥልጣን ከያዘ በኋላ፣ በፍርድ ቤቱ ውስጥ አብላጫ ድምፅ ለማግኘት ሲል በቶሎ ዳኞችን ሾሞ ነበር። ይህንን ያደረገው ፍርድ ቤቱ በአገሪቱ የሚወጡ አዋጆችን ሕጋዊነት የመወሰን ሥልጣን ስላለው ነው።

ሁለት የአውሮፓ ዋነኛ ፍርድ ቤቶች፣ ፓርቲው ሦስት ዳኞችን የሾመበት መንገድ ሕጋዊ አሰራርን ያልተከተለ ነው በሚል ተቃውመዋል። የፖላንድ ሕገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤት "ገለልተኛ እና አድልዎ የሌለበት ችሎት" እንዳልሆነ የሚገልጽ ውሳኔም አሳልፈዋል።

የቱስክ መንግሥት ደግሞ እነዚህን ውሳኔዎች እንደ መሰረት በመጠቀም የፍርድ ቤቱ ውሳኔዎች በይፋ እንዳይታተሙ አግዷል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በቀደመው መንግሥት የተላለፉ ውሳኔዎችን ለመቀልበስ ያደረጓቸው ሙከራዎች አልተሳኩም። የዚህ አንዱ ምክንያት በተቃዋሚው ፓርቲ የሚደገፉት የቀድሞ መሪ አንድሬይ ዱዳ ሙከራዎቹን በፕሬዝዳንታዊ ድምፅ ውድቅ የማድረግ ሥልጣናቸው በማገዳቸው ነው።

የአሁኑ ፕሬዝዳንት ናውሮትስኪም በተመሳሳይ ፓርላማው ከመጋቢት ወዲህ የመረጣቸው አምስት የሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ዳኞች ቃለ መሃላ እንዲፈጽሙ ፈቃደኛ አልሆኑም።