"ይህን የሰውነት ቅርጽ ለማምጣት ከወንዶች በላይ መጣር ይጠይቃል" - በጡንቻ የፈረጠሙት ኢትዮጵያውያን ሴት ቦዲ ቢልደሮች

ኤዶም
የምስሉ መግለጫ, ኤዶም
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

የ21 ዓመቷ ቦዲ ቢዩልደር ኤዶም ፍሬዘውድ በቲክቶክ ቪዲዮዎቿ ሥር ከሚደርሷት አስተያየቶች መካከል ስለ ሰውነቷ፣ ሴትነቷ እና ወደፊት ልጅ መውለዷን የሚመለከቱ ይገኙበታል።

ኤዶም የሰውነት ግንባታ (ቦዲ ቢዩልዲግ) ስፖርትን መሥራት ከጀመረች አንድ ዓመት ገደማ ሆኗታል።

ወደ ስፖርቱ ስትገባ ስለ ቦዲ ቢዩልዲንግ ብዙ ዕውቀት እንዳልነበራት ትናገራለች። በሶሻል ሚዲያ ላይ ስፖርቱን መከታተል ጀምራ፣ ከሁለት ዓመት በፊት በተካሄደ ውድድር ላይ መታደሟ ያላትን ፍላጎት ይበልጥ አሳደገው።

ሆኖም ስፖርቱን መጀመር እና መቀጠል ቀላል አልነበረም። ከቤተሰቧ የምትፈልገውን ድጋፍ እንዳላገኘች የምትናገረው ኤዶም፣ በራሷ ውሳኔ ስፖርቱን ጀምራ መቀጠሏን ታስረዳለች።

ኤዶም በማኅበራዊ ሚዲያዎች (ቲክቶክ) ላይ በምትለቃቸው ቪድዮዎች አስተያየት መስጫ ስር የሚጻፉ አስተያየቶች አንዳንዶቹ ሴትነቷን ከሰውነቷ ጋር በማያያዝ የሚሰጡ ሲሆኑ፣ ሌሎች ደግሞ ወደፊት ትዳር ከመመሥረት ወይም ልጅ ከመውለድ ጋር የተያያዘ እንደሆኑ ትገልጻለች።

"ልጅሽ ሲያድግ ምንድን ነው የሚጠባው?" የሚል አስተያየት እንደሚደርሳት የምትገልጸው ኤዶም "ወደፊት አገባለሁ፣ እወልዳለሁ፣ አጠባለሁ" ስትል ጉዳዩ ከዚህ ጋር እንዳማይያያዝ እና አስተያየቶቹንም ስቃ ታልፋቸዋለች።

ኤዶም ስፖርቱ ከማኅበረሰቡ ባህል እና አለባበስ ጋር በተያያዘ የሚያጋጥመው የተቀባይነት ችግር አንዳንዶችን ወደ ኋላ እንደሚያስቀር ታምናለች።

በተለይም ሴቶች ቅርጻቸውን በሚያሳዩበት የውድድር መድረክ ላይ የሚለብሱት ልብስ (ቢኪኒ) የብዙዎች ትችት ምንጭ ነው።

በመጀመሪያ ይህን አለባበስ ለመልመድ እንደከበዳት የምትናገረው ኤዶም ከተለያዩ ሰዎች እና ከቤተሰብ የሚመጡ አስተያየቶችን መቋቋምም ፈታኝ ሆኖባት ነበር።

"አሁን ቢኪኒ ለብሰን ስንወጣ ልብሱን አይደለም የምናሳየው፤ ምን ያህል ለፍተን ያመጣነውን ነገር ለማሳየት ነው እዚያ መድረክ ላይ የምንወጣው" ስትል ዓላማው የልፋት ውጤት ማሳያ ብቻ መሆኑን ታስረዳለች።

ኢትዮጵያ ውስጥ ጥቂት የማይባሉ ሴቶች ስፖርት ቤት (ጂም) ሲሄዱ መመልከት የተለመደ ነው። ለአንዳንዶቹ የአካል ብቃትን ለማሻሻል፣ ለሌሎች ደግሞ የሰውነት ቅርጻቸውን ለመቀየር የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ነው።

ሆኖም የሰውነት ግንባታ (ቦዲ ቢልዲንግ) ስፖርትን በውድድር ለመሳተፍ መሥራት ከዚህ የበለጠ ጥረት፣ የተለየ አመጋገብ እና ከማኅበረሰቡ የሚመጡ የተለያዩ አስተያየቶችን መጋፈጥ ይጠይቃል።

ኢትዮጵያ ውስጥ በዘርፉ ተሰማርተው ያሉ ሴቶችም በጣት የሚቀጠሩ ናቸው። ውድድሮችም ቢሆኑ ጥቂት ቁጥር ያላቸውን ሴቶች ብቻ በማሳተፍ የሚካሄዱ ናቸው።

በ16 ዓመቷ ስፖርቱን እንደጀመረች የምትናገረው የ20 ዓመቷ ሜሮን ሂርጶ በውድድር ደረጃ የሚሳተፉ ሴቶች ቁጥር አነስተኛ መሆኑን ታስረዳለች።

በተለይም የውድድር ደረጃ ላይ ለመድረስ የሚጠይቀው ጥረት፣ አመጋገብን መቆጣጠር፣ የኃይል ማነስ እና የሆርሞን ለውጦች ተጨማሪ ፈተናዎች ናቸው።

ከውጭ አገር መጥተው አገራቸውን በመወከል የሚወዳደሩ ሴቶች ካልሆኑ በስተቀር፣ ከኢትዮጵያ ተነስተው በውድድር ደረጃ የሚሳተፉ ሴቶች እንዳላጋጠማት ትናገራለች።

ሜሮን እና ኤዶም
የምስሉ መግለጫ, ሜሮን እና ኤዶም
Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሜሮን፣ ሴት ልጅ የጡንቻ ማጎልበት ስፖርት ስትሠራ ወንድ ልትሆን እንደሆነ፣ ማግባት እና መውለድ እንደማትችል የሚገልጹ አስተያየቶች ይሰጧታል።

ከቤተሰቦቿ ፈቃድ ሳታገኝ ቦዲ ቢልዲንግን እንደጀመረች የምትናገረው ሜሮን ስፖርቱን የቀጠለችው ከሌሎች አስተያየት ይልቅ ለስፖርቱ በነበራት ፍቅር ነው።

በስፖርቱ ውስጥ ያለው ፈተና ከማኅበረሰቡ አስተሳሰብ ጋር ብቻ የተያያዘ አለመሆኑን በማንሳት ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው የኢኮኖሚያዊ ሁኔታ በቦዲ ቢልዲንግ ላይ መሳተፍ እንቅፋት እንደሚሆንም ሜሮን ትናገራለች።

ሜሮን እንደምትለው፣ ስፖርቱ በተለይም ተገቢ አመጋገብን እና የሰውነት አልሚ ምግቦችን ስለሚፈልግ፣ ወጪውን መሸፈን ከባድ ነው።

ከስፖርቱ ጋር በተያያዘ ለ30 ዓመታት ልምድ ያለው የኢትዮጵያ የፊትነስ እና ቦዲ ቢልዲንግ ፌዴሬሽን ዳይሬክተር ዮናስ ግርማ ላለፉት ስድስት ዓመታት ሴቶችን ወደ ውድድር ለማምጣት እየሰሩ መሆናቸን ይናገራል።

በእነዚህ ዓመታት ታዲያ በአንድ ጊዜ ያወዳደሩት ከፍተኛ ቁጥር 5 ነው። አንድ ተወዳዳሪ ብቻ የተሳተፈበችበትም ወቅት አለ።

በባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ በተካሄደው ስድስተኛው ውድድር ሁለት የቢኪኒ እና ሁለት የቦዲ ቢልዲንግ ሴት ተወዳዳሪዎች ነበሩ።

በቢኪኒ ዘርፍ የተወዳደሩት ኤዶም ፍሬዘውድ እና ሜሮን ሂርጶ ናቸው፣ ውድድሩን ኤዶም አንደኛ በመሆን አሸንፋለች።

የሴቶች ቦዲ ቢልዲንግ ስፖርት አብዛኛውን ጊዜ ሰባት ዋና ዋና የውድድር ዓይነቶች ሲኖሩት ፊት ሞዴል፣ ቢኪኒ፣ ዌልነስ፣ ፊገር፣ ፊትነስ፣ ዊሜንስ ፊዚክ እና ዊሜንስ ቦዲ ቢልዲንግ የሚባሉት ናቸው።

የውድድር ክፍሎቹ በሚፈለገው የሰውነት ቅርጽ፣ በጡንቻ እድገት እና ተወዳዳሪዎች በመድረክ ላይ በሚያሳዩት ብቃት ይለያያሉ።

ከእነዚህ መካከል ቢኪኒ ከታዋቂ የውድድር ዓይነቶች አንዱ ነው። ተወዳዳሪዎች ከከፍተኛ የጡንቻ እድገት ይልቅ የተመጣጠነ፣ የዳበረ ስፖርታዊ የሰውነት ቅርጽ እንዲኖራቸው ይጠበቃል።

በተለይም የትከሻ፣ የወገብ፣ የዳሌ እና የእግር ቅርጽ እንዲመጣጠን ትኩረት ይሰጣል።

በቢኪኒ ውድድር የሚለበሰው አለባበስም የዚህ ክፍል አንዱ መለያ ነው። ተወዳዳሪዎች በተወሰነ የውድድር ልብስ እና ከፍ ያለ ተረከዝ ባለው ጫማ ወደ መድረክ ይወጣሉ። በዚያም የሰውነታቸውን ቅርጽ በማሳየት በራስ መተማመናቸውን፣ አቀራረባቸውን እና በመድረክ ላይ ያላቸውን ብቃት ያሳያሉ።

ውድድር

ከቢኪኒ በተጨማሪ ዌልነስ በዳሌ፣ በመቀመጫ እና በጭን የበለጠ የዳበረ ጡንቻ ላይ ያተኩራል። ፊገር ደግሞ ሰፊ ትከሻ እና ጠባብ ወገብ ያለው የተመጣጠነ ቅርጽ የሚያሳዩበት ነው።

ፊትነስ ከሰውነት ቅርጽ በተጨማሪ የጂምናስቲክ፣ የዳንስ፣ የጥንካሬ እና የመተጣጠፍ ችሎታ በትርኢት የሚቀርብበት ነው።

ዊሜንስ ፊዚክ ይበልጥ የዳበሩ እና ግልጽ የጡንቻ መስመሮች ያሏቸውን ሰውነቶች የሚፈልግ ሲሆን፣ ዊሜንስ ቦዲ ቢልዲንግ ደግሞ ከፍተኛ የጡንቻ መጠን እና ጥንካሬ ላይ ያተኩራል።

ፊት ሞዴል የሚባለው ክፍል በአንጻሩ በተፈጥሯዊ እና በተመጣጠነ የሰውነት ቅርጽ ላይ የበለጠ ትኩረት ያደርጋል።

ዮናስ እንደሚለው፣ በመድረክ ላይ ሲወዳደሩ የሚለብሱት ልብስ እና ሰውነታቸውን የሚያሳዩበት መንገድ አንዳንድ ሴቶች ምቾት እንዳይሰማቸው እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።

እነዮናስ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በሚለቁት ቪድዮዎች ላይ የሚሰጡት አስተያየቶች "አንዳንዴ ስድብ እና ንቀት የተሞሉ ናቸው" የሚለው ዮናስ በአንዳንድ ቪድዮዎች ላይ የአስተያየት መስጫውን ክፍል ለማጥፋት እንደሚገደዱ ይገልጻል።

በዚህ የስፖርት ዘርፍ ወደ ውድድር መድረክ ለመውጣት ተወዳዳሪዎች ቢያንስ ለሁለት ዓመታት በተከታታይ መሥራት ሊያስፈልጋቸው ይችላል።

የሴቶች እና የወንዶች የሥልጠና ዝግጅት በአንዳንድ ጉዳዮች እንደሚለያይም ዮናስ ይናገራል። ከወንዶች ጋር ሲነጻጸር ለሴቶች የጡንቻ እድገት እና የሰውነት ስብ ቅነሳ ረዘም ያለ ጊዜ ሊወስድ ይችላል ይላል።

ኤዶም በበኩሏ በተለይም ሌሎች ሰዎች ሊያሳኩት ያልቻሉትን ነገር እሷ ማሳካቷ አንዳንዶቹን እንደሚያስገርም ታስባለች።

ኤዶም የሴቶች እና የወንዶች የሆርሞን ልዩነት በሰውነት ግንባታ ላይ ተጽእኖ እንዳለው፣ በተለይም ወንዶች ከፍ ያለ የቴስቶስትሮን መጠን ስላላቸው ጡንቻ ለመገንባት የተለየ ጥቅም እንዳላቸው ታስረዳለች። ሴቶች ግን በተመሳሳይ ደረጃ የጡንቻ መዳበርን ለማምጣት የበለጠ ጥረት ሊያስፈልጋቸው እንደሚችል ታምናለች።

ከማኅበረሰቡ የሚመጡ ምላሾች ግን ሁልጊዜ አሉታዊ አይደሉም። ኤዶም በመንገድ ላይ ከሰዎች የምትሰማቸው አስተያየቶች አዎንታዊም እንደሆኑ ትናገራለች።

ወንዶችም ስለ ሰውነቷ የሚሰጧት ምላሽ እንደሚያበረታታት፣ ሴቶችም ከእሷ ልምድ ለመማር እና ስፖርቱን ለመጀመር አንዳንድ ጥያቄዎችን ያቀርቡላታል። ወንዶችም "እኔን ሲመለከቱ በስፖርቱ ላይ ፍላጎት ያሳድራሉ" ትላለች።

የሰውነት ግንባታ ስፖርት በጂም ውስጥ ረጅም ሰዓታትን ማሳለፍ ብቻ አይደለም። አመጋገብን ማስተካከል፣ የሥልጠና ፕሮግራምን መከተል፣ ምግብን አስቀድሞ ማዘጋጀት እና የዕለት ተዕለት ኑሮን ከስፖርቱ ጋር ማጣጣምንም ይጠይቃል።

ኤዶም አሁን ለሌሎች ሰዎች የግል አሠልጣኝ ሆና ትሠራለች። በኢንተርኔት አማካኝነት እና በጂም ውስጥ በቀጥታ የአንድ ለአንድ ሥልጠና ትሰጣለች።

በተጨማሪም ወደፊት በተሻለ ደረጃ ተዘጋጅታ ኢትዮጵያን ወክላ በውጭ አገር ውድድሮች ላይ ለመሳተፍ ከፍተኛ ፍላጎት አላት።

ሴቶች በራሳቸው እምነት እንዲኖራቸው እና ያመኑበትን ነገር እንዲከተሉ የምትመክረው ሜሮን ሰዎች ላይቀበሏቸው ወይም ላይደግፏቸው ቢችሉም፣ ያመኑበትን ነገር በተግባር በማሳየት ማኅበረሰቡን መቀየር እንደሚቻል ታምናለች።