ለዓመታት በዘር ማጥፋት ወንጀል ውስጥ መሳተፉን የደበቀ ሩዋንዳዊ በአሜሪካ ፍርድ ቤት ጥፋተኛ ተባለ

በሩዋንዳ ዘር ማጥፋት የተገደሉ ሰዎች ስም ዝርዝር ግድግዳ ላይ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በቀድሞው የዩኒቨርሲቲ ጓደኛው የፍርድ ሂደት ወቅት ፍርድ ቤት ሲቀርብ በመሐላ ሥር ሆኖ ከ32 ዓመት በፊት በተካሄደው ዘር ማጥፋት ላይ ስለነበረው ተሳትፎ ዋሽቷል የተባለ አንድ ሩዋንዳዊ በአሜሪካ የጥፋተኝነት ውሳኔ ተላለፈበት።

በቦስተን የሚገኝ የፌዴራል ፍርድ ቤት፣ የ54 ዓመቱን ኤሪክ ንሺሚዬ ሐሰተኛ ምስክርነት በመስጠት ፍትሕን የማደናቀፍ ወንጀል ጥፋተኛ ብሎታል።

ሩዋንዳዊውን ጥፋተኛ ያስባለው ክስተት የተፈጠረው በአውሮፓውያኑ 2019 ነበር። በወቅቱ በሩዋንዳ ዘር ማጥፋት ላይ ተሳትፏል እና የስደተኝነት ማጭበርበር ፈጽሟል የሚል ክስ በቀረበበት ዣን ሌዮናርድ ቴጋንያ የፍርድ ሂደት ላይ የምስክርነት ቃል ሰጥቶ ነበር።

ንሺሚዬ በአውሮፓውያኑ 1994 ከሩዋንዳ ወደ ኬንያ የሸሸ ሲሆን ከአንድ ዓመት በኋላም ስደተኛ ሆኖ አሜሪካ ገብቷል።

ለ100 ቀናት በቆየው የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ ወቅት አክራሪ የሁቱ ብሔር አባላት፣ በብዛት አናሳ በሆኑ የቱትሲ ብሔር አባላትን ገድለዋል። በዚህ የዘር ማጥፋት ድርጊት 800,000 ገደማ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን አብዛኛዎቹ ቱትሲዎች ናቸው።

ዓቃቢያነ ሕግ እንደሚገልጹት፣ ንሺሚዬ ወደ አሜሪካ ለመግባት ሲል በዘር ማጥፋት ድርጊቱ ውስጥ ተሳትፎ እንደነበረው ደብቋል።

በፍርድ ሂደቱ ላይ የቀረበው ማስረጃ እንደሚያመለክተው፣ የሩዋንዳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበረበት ወቅት ቱትሲዎች ላይ በተፈጸሙ ጥቃቶች ላይ ተሳትፏል። ከፈጸማቸው ድርጊቶች አንዱ፣ የቱትሲዎችን ጭንቅላት በዱላ መደብደብ ይገኝበታል።

ሩዋንዳዊው አራት የሐሰት ምስክርነት ክሶች የቀረቡበት ሲሆን በእያንዳንዳቸው እስከ አምስት ዓመት ሊፈረድበት ይችላል። ፍትሕን በማደናቀፍ ወንጀል ደግሞ ከፍተኛው እስከ 10 ዓመት የሚደርስ እስራት ሊወሰንበት ይችላል።

የቅጣት ውሳኔው በመጪው ጥር ወር እንደሚሰጥ ይጠበቃል።

የአሜሪካ የፍትሕ መስሪያ ቤት አቃቤ ሕግ ታይሰን ዱቫ፣ "ተከሳሹ ሰዎችን በዱላ ደብድቦ እስከ መግደል ድረስ የፈጸማቸውን ዘግናኝ የጥቃት ድርጊቶች ጨምሮ በ1994ቱ የሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ወንጀል ውስጥ የነበረውን ተሳትፎ ለሦስት አስርት ዓመታት ለሚቆጠር ጊዜ ደብቆ ቆይቷል" ብለዋል።

"ቀጥሎም የአሜሪካ ዜግነት ለማግኘት ለስደተኞች ባለሥልጣናትን የሐሰት ቃል ሰጥቷል፤ ራሱንና ሌላኛውን የሩዋንዳ ዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጻሚ ለመከላከልም በፌዴራል ፍርድ ቤት በሐሰት መስክሯል" ሲሉም አክለዋል።

የንሺሚዬ ጠበቃ ኩርት ከርንስ በበኩላቸው "በውሳኔው እጅግ ማዘናቸውን" እና "ሁሉንም የይግባኝ መንገዶች" እንደሚከተሉ ባወጡት መግለጫ ተናግረዋል።

ጠበቃው ጥቅምት ላይ የፍርድ ሂደቱ ሲጀመር ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የቀረቡትን ክሶች "የተፈበረኩ ውንጀላዎች" ላይ የተመሰረቱ ሲሉ ጠርተዋቸው ነበር። ጥቃቱ ሲጀመር ንሺሚዬ በስፍራው ውስጥ እንዳልነበር ተከራክረዋል።

አክለውም፣ ንሺሚዬ የተከሰሰው የዩኒቨርሲቲ ጓደኛው ስለነበረው ቴጋንያ ጠባይ ምስክርነት ለመስጠት ፍርድ ቤት ከቀረበ በኋላ ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል።

ቴጋንያ በዘር ማጥፋቱ ውስጥ ስለነበረው ተሳትፎ በመዋሸቱ በአውሮፓውያኑ 2019 የስምንት ዓመት እስር ተፈርዶበታል። በወቅቱ አቃቢያነ ሕግ ቴጋንያ ላይ የቀረበውን ክስ የገለጹት "እጅግ የከፋ የስደተኞች ማጭበርበር ወንጀል" በሚል ነበር።

በተጨማሪም ቢያንስ በሰባት ግድያዎች እና በአምስት የመድፈር ወንጀሎች ተሳትፏል የሚል ክስ ቀርቦበት የነበረ ሲሆን የዘር ማጥፋቱ ድርጊቱ ውስጥም አለመሳተፉን ተናግሮ ነበር።