ኢትዮጵያ ዘመናዊ ጄቶችን መታጠቋ በቀጣናው ኃይል አሰላለፍ ላይ ምን ተጽእኖ ይኖረዋል?

ሁለት ሱ-35 የጦር ጄቶች በአየር ላይ ሚሳይል እያስወነጨፉ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

ኢትዮጵያ 12፣ ሱ-35 የጦር ጄቶችን የተረከበች ሲሆን፤ በቀጣይም አራት ኤስ-400 የአየር መከላከያ ሥርዓት ባትሪዎችን እንደምትረከብ ተገልጿል።

እነዚህን በአራተኛ እና በአምስተኛ ትውልድ ተዋጊ ጄቶች መካከል የሚገኙ ዘመናዊ የጦር ጄቶች በመታጠቅ ኢትዮጵያ "ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት ቀዳሚ" እንደምትሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናግረዋል።

እስከአሁን ከኢትዮጵያ ውጭ ይህን የጦር ጄት የታጠቀች አፍሪካዊት አገር አልጄሪያ ብቻ ናት።

ብዙ የተባለለትን ይህን የጦር ጄት በተመለከተ ከቢቢሲ አማርኛ ጋር ቆይታ ያደረጉት አንጋፋው የጦር አውሮፕላን አብራሪ እና አሠልጣኝ ካፒቴን ተሾመ ተንኮሉ፣ ኢትዮጵያ እነዚህን ዘመናዊ ጄቶች መታጠቋ እንዳስደነቃቸው ይገልፃሉ።

ካፒቴን ተሾመ ተንኮሉ ከ1973 ዓ.ም ጀምሮ ለ22 ዓመታት በኢትዮጵያ አየር ኃይል ውስጥ በአብራሪነት፣ በአሠልጣኝነት እና በተዋጊ ጄት ማሠልጠኛ 'ስኳድሮን' ኃላፊነት ያገለገሉ እንዲሁም በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ጭምር ሚግ 23 ሲያበሩ የነበሩ አንጋፋ የአየር ኃይል ባለሙያ ናቸው።

"በዚህ ሙያ ውስጥ እንዳለ ሰው እንዲህ አይነት ዘመናዊ ቴክኖሎጂ አገር ስትታጠቅ የሚያመጣው ጥቅም በቀላሉ ይገባኛል" ይላሉ ካፒቴን ተሾመ።

እነዚህ የሱ-35 አውሮፕላኖች፣ ከፊታቸው አምስተኛው ትውልድ የጦር አውሮፕላን በመኖሩ የአቪዬሽን ቴክኖሎጂ የመጨረሻው ውጤቶች ባይሆኑም፣ አሁን ያለውን በጣም ፈጣን እና ውድድር ያለበት የአቪዬሽን ቴክኖሎጂ ዘመን ተከትለው የመጡ "የ4 እና 5 ትውልድ" አውሮፕላኖች መሆናቸውን በመጥቀስ ከፍተኛ አገልግሎት እንደሚሰጡ አብራርተዋል።

የሱ-35ን ባህሪያት ሲያስረዱ "በመተጣጠፍ አቅማቸው፣ መሳሪያ በመሸከም፣ ከፍታ በመውጣት እና ከሩቅ ዒላማ በመለየት አቅማቸው እንዲሁም በፍጥነታቸው የሚታወቁ በጣም ዘመናዊ አውሮፕላኖች ናቸው" ይላሉ።

በተጨማሪም "አብራሪው ዒላማውን በዐይኑ ማየት ሳይጠበቅበት ራዳሩ ካየው ሎክ አድርጎ [ቆልፎ] ሚሳዔሉን ቢያስወነጭፍ ዒላማውን ፈልጎ የሚመታ ቴክኖሎጂ ያለው" እንደሆነ የአየር ኃይል ቴክኖሎጂዎችን በቅርበት የሚከታተሉት ካፒቴኑ ገልፀዋል።

ለአብራሪው "ሁሉን ነገር በጣም ቀላል" የሚያደርግ ከመሆኑም ባለፈ የኃይል ምቱም "ከፍተኛ" የሆነ ዘመናዊ አውሮፕላን መሆኑን ቀደም ሲል እርሳቸው ሲያበሯቸው ከነበሩ የሚግ ዘመን እና ቀጥለው ከመጡ የተለያየ ትውልድ ተዋጊ አውሮፕላኖች ጋር በማነፃፀር ያስረዳሉ።

አየር ኃይሉ በቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ከተቋቋመ በኋላ፣ በፍጥነት እያደገ ሄዶ በደርግ ዘመን "በጣም ግዙፍ" የሚባል ደረጃ ላይ ደርሶ እንደነበር ካፒቴን ተሾመ ይገልፃሉ።

"በጃነሆይ ጊዜ ጥቂት ግን አየር በአየር ውጊያ ላይ ጠላታቸውን በመጣል የታወቁ ውጤታማ አብራሪዎች ነበሩ። በደርግ ዘመን ደግሞ በጣም ግዙፍ፣ ብዙ ኤርቤዞች ያሉት፣ አውሮፕላንን በራሱ የመገጣጠም ሥራዎችን ይሠራ የነበረ ለኢትዮጵያ አይደለም ለአፍሪካ የሚበቃ ግዙፍ ኃይል የተፈጠረበት ነው" ሲሉ ለእነዚያ ዘመናት አድናቆታቸውን ገልፀዋል።

ከዚያ ኋላ አየር ኃይሉ "ስብራት ደርሶበታል" የሚሉት ካፕቴን ተሾመ፣ "ያንን ስብራት አልፎ ዛሬ በዚህ አጭር ጊዜ እዚህ ደረጃ ላይ መድረሱ እንደባለሙያ በጣም ነው ያስደነቀኝ" ሲሉ አክለዋል።

"በአካባቢው ላይ ከፍተኛ የበላይነትን ይፈጥራል"

Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ኢትዮጵያ ካለችበት ውስብስብ እና ብዙ ፉክክር ያለበት መልክዓ-ምድራዊ አቀማመጥ አንጻር አየር ኃይልን ማዘመን "አስገዳጅ" እንደሆነ ነው የሚያምኑት።

"በጃነሆይ ጊዜ ንጉሡ ቀድመው ነው ይሔንን የተረዱት፤ አየር ኃይሉን ሲመሠርቱ ዝምብለው አይደለም፤ በሚገርም መሠረት ላይ ጥለው በጣም ከአፍሪካ ውጤታማ አየር ኃይል ፈጥረው ነው ያለፉት"።

አሁን አየር ኃይሉ ዳግም በማንሰራራት ዘመናዊውን ሱ-35 እስከመታጠቅ መድረሱ "በአካባቢው ላይ ከፍተኛ የበላይነትን ይፈጥራል" ይላሉ።

ይህ ከአካባቢው አገራት አልፎ "ማንንም ሊያስደነግጥ ይችላል፤ አገራት ስጋት ሊገባቸው ይችላል" ሲሉም ገልፀዋል።

በተለይም፣ ከዓባይ ወንዝ ውሃ ጋር በተገናኘ ከኢትዮጵያ ጋር ለዘመናት አለመግባባት ውስጥ ያለችውን ግብፅን በመጥቀስ "እነሱም ይዘጋጃሉ ኢትዮጵያም ትዘጋጃለች" ካሉ በኋላ፣ ነገር ግን ኢትዮጵያ "ለአግሬሽን [ሌሎችን ለማጥቃት] ሳይሆን ራሷን ለመከላከል" በቂ ዝግጅት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የተረከበቻቸው 12 ሱ-35 ጄቶች ለአየር ኃይሉ ትልቅ ግብዓት ቢሆኑም፣ ነገር ግን አገሪቱ ያለችበት ቀጣና "የተወሳሰበ ጂኦ ፖለቲካዊ ቀውስ ያለበት" እንደመሆኑ ተጨማሪ የውጊያ አውሮፕላኖች እንደሚያስፈልጓት ያምናሉ።

ለረዥም ዘመናት ቀጣናው "ከፍተኛና ውስብስብ ጂኦ ፖለቲካዊ ችግር ያለበት ነው" የሚሉት ካፒቴን ተሾመ፣ ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ "ራሷን ተከላክላ፣ ግዛታዊ አንድነቷን እና ብሔራዊ ጥቅሟን አስጠብቃ ለመቀጠል ከፍተኛ ፍጥጫ ውስጥ ነች" ሲሉ ሁኔታውን ይገልፃሉ።

ስለሆነም ወታደራዊ ቴክኖሎጂው በፍጥነት እያደገ ባለበት በዚህ ወቅት፣ ዘመኑን የተከተለ ዝግጅት ማድረግ "የግድ" እንደሆነ ተናግረዋል።

በተጨማሪም፣ ኢትዮጵያ "ስሱ የሆኑ" ሲሉ የገለጿቸው የልማት ተቋማት ያሏት እንዲሁም ከብዙ ጎረቤቶቿ አንጻር ትልቅ አገር እንደመሆኗ የአየር ኃይል አቅሟም በዚያው መጠን ማደግ እና መዘመን እንዳለበት ይመክራሉ።

ሱ 35

"አየር ኃይል በጣም ውድ መሥሪያ ቤት ነው"

በሌላ በኩል የአየር ኃይል እጅግ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ተቋም መሆኑን ገልፀዋል። ምንም እንኳን 12ቱ የሱ-35 አውሮፕላኖች የተገዙበት ዋጋ በመንግሥት ይፋ ባይደረግም፣ የአንድ ሱ-35 አውሮፕላን ዋጋ ቢያንስ ከ80 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደሆነ የዘርፉ መረጃዎች ያመለክታሉ።

የአውሮፕላኖቹ ወጪ፣ ለሚጠቀሙት የጦር መሳሪያ፣ አብራሪ ለማሠልጠን እና ለመለዋወጫ ከሚወጣው ጋር ተዳምሮ ዘርፉን እጅግ ውድ እንደሚያደርገው ካፒቴን ተሾመ ገልፀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢትዮጵያ የሱ-35 አውሮፕላኖችን መረከቧን በተመለከተ ከዚያው ከሩሲያ ባደረጉት ንግግር ላይ፣ ላለፉት ጥቂት ዓመታት የበረራ እና ሌሎች የአየር ኃይል ባለሙያዎችን የማሠልጠን ሥራ ሲከናወን መቆየቱን ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ አሁን ላይ የሱ-35 የጦር ጄትን ማብረር የሚችሉ ባለሙያዎችን አገሪቱ ያፈራች እንደሆነ በይፋ አልገለፁም።

እንደዚህ አይነት ዘመናዊ አውሮፕላኖችን ለማብረር ከፍተኛ ሥልጠና እንደሚያስፈልግ የሚያነሱት ካፒቴን ተሾመ፣ ይህን አውሮፕላን ማብረር የሚችሉት ከስር ጀምሮ በቅደም ተከተል በሥልጠና በማለፍ "ከፍተኛው የተዋጊ ስኳድሮን" ውስጥ መካተት የቻሉ እንደሆኑ ያብራራሉ።

"አንድን በራሪ አሠልጥኖ ለግዳጅ ብቁ ለማድረግ በውጭ ምንዛሪ በሚሊዮኖች ነው የሚፈጀው። 10 ወጣቶችን ለሥልጠና አስገብተህ እንዲህ ያሉትን የማብረር ደረጃ ላይ ለማድረስ ምናልባት አንድ ሁለት ካገኘህ በጣም ዕድለኛ ነህ። እነዚህን ተዋጊ አውሮፕላኖች ማብረር ላይ የሚደርሱ አብራሪዎችን ማግኘት በጣም ውድ ነው። አስተማማኝ ባለሞያ ድርጎ ለማውጣት እስከ 7 ዓመት የሚፈጅ ሥልጠና ያስፈልጋል" ብለዋል።

ለሠልጠና ከሚያስፈልገው ወጪ እና ጊዜ ባለፈ፣ ዘመናዊው የጦር ጄት የሚያስወነጭፋቸውን ሚሳዔሎች ማዘጋጀትን ጨምሮ አውሮፕላኑን ለማንቀሳቀስ እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቅ መሆኑን በማንሳት "አየር ኃይል በጣም ውድ መሥሪያ ቤት ነው" ሲሉ ይገልፃሉ።

"ውድ ነው ግን አገር መጠበቅ አለብህ። በማንኛውም መንገድ የአገር ኅልውና መጠበቅ አለበት" ሲሉም አክለዋል።

"ጦርነትን አየር ኃይል ይጀምራል፤ አየር ኃይል ያገባድዳል"

በአነስተኛ ወጪ የሚመረቱ የውጊያ ድሮኖች በአሁኑ ወቅት በጦርነቶች ላይ በከፍተኛ መጠን ጥቅም ላይ እየዋሉ፣ በውጊያዎች ላይ ከፍተኛ ለውጥም እየፈጠሩ ነው።

ይህን ዓይነት በቀላል ወጪ ከፍተኛ ውጤት ማስገኘት የሚችል የድሮን ቴክኖሎጂ እያለ ለዘመናዊ የጦር ጄቶች ከፍተኛ ዋጋ ማውጣት ምን ያህል አዋጭ እንደሆነ ለተነሳላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ ድሮኖች እንዳሉ ሆነው በዘመናዊ ጦርነት ላይ ዋነኛ ሚና ያለው አየር ኃይል እንደሆነ ካፒቴኑ አብራርተዋል።

"ዛሬ እንደድሮው ወታደሮችን አሰልፎ፣ ጠመንጃ አስታጥቆ የምንዋጋበት ዘመን ላይ አይደለም ያለነው። ጦርነትን አየር ኃይል ይጀምራል፤ አየር ኃይል ያገባድዳል" ይላሉ።

"የምድር ኃይል በስተመጨረሻ ሰላምና መረጋጋትን ለማስከበር ይገባል እንጂ አየር ኃይል ነው ጦርነትን እየመራም፣ እየተዋጋም፣ እያሸነፈም ያለው"።

በጣም በቀላል ወጪ ተዘጋጅተው ብዙ ውድመት የሚፈጥሩ የድሮን ቴክኖሎጂዎችንም ቢሆን ኢትዮጵያ "የምታመርትበት ደረጃ ላይ" መድረሷን ይጠቅሳሉ።

ሆኖም ግን በድሮኖች ብቻ ውጤታማ መሆን እንደማይቻል ተናግረዋል።

"አንድ አውሮፕላን በአንድ ሰው፣ በሰከንዶች ውስጥ ሊያደርስ የሚችለው ጠላትን የማጥፋት ኃይል፣ ምናልባት አንድ የምድር ኃይል በተለያየ ባታሊዮን [ሻለቃ] ከሚያጠፋው በላይ ነው" ሲሉ በጦርነት ውስጥ አየር ኃይል ስለሚኖረው ሚና አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ 12 ዘመናዊ ሱ-35 የጦር ጄቶችን ከሩሲያ የተረከበችው፣ ከጎረቤት አገር ኤርትራ ጋር ጦርነት ሊነሳ ይችላል የሚሉ ስጋቶች ባየሉበት ወቅት ነው። ሩሲያ ሁለቱን አገራት ለማሸማገል ጥያቄ አቅርባለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በበኩላቸው፣ የጄቶቹ ግዢ ኢትዮጵያ ራሷን ለመከላከል እና የአየር ክልሏ እንዳይደፈር የምታደርገው ቅድመ-ዝግጅት አካል እንደሆነ ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም "ይህን አቅም ካልገነባን በእኛ አካባቢ እንደ አገር ኅልውናን ማስጠበቅ አስቸጋሪ ነው" ብለዋል።