ቀጥታ , በኬንያ ለ191 ሰዎች ሞት ተጠያቂ የሆነው የአምልኮ ቡድን መሪ 200 ዓመት ተፈረደበት

በኬንያ 190 ህጻናት እና አንድ አዋቂ ሰውን በመግደል የተወነጀለው የአምልኮ ቡድን መሪ ፖል ማኬንዚን የ200 ዓመት እስር ተፈረደበት። ማኬንዚ እና በመዝገቡ ውስጥ የተካተቱ ሌሎች 27 ተከሳሾች፣ የአምልኮ ቡድኑ አባላት ልጆቻቸው “ከኢየሱስ ጋር እንዲገናኙ” ለማድረግ በርሃብ እንዲገድሏቸው ትዕዛዝ በመስጠት ወንጀል ጥፋተኛ ተብለዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. በጋምቤላ ወረዳ ከምሽት አንድ ሰዓት በኋላ ነዋሪዎች እንዳይንቀሳቀሱ ተከለከለ

    ከጋምቤላ ክልል ዋና ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኘው ጋምቤላ ወረዳ ከምሽት አንድ ሰዓት በኋላ ነዋሪዎች ከቤት ውጪ እንዳይንቀሳቀሱ ገደብ ተጣለ።

    ከዛሬ አርብ ጥቅምት27/2019 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረገው ሰዓት እላፊ የተጣለው፣ ክልሉ ውስጥ እና ከውጭ የሚመጡ የጸጥታ ስጋቶችን አስቀድሞ ለመከላከል እንደሆነ የወረዳው ሰላም እና ፀጥታ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኡጁሉ አኳይ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    ይህ ገደብ እንዲጣል የወሰነው፣ የአኙዋ ብሔረሰብ ዞን መስከረም ላይ ያቋቋመው የወረዳው ጊዜያዊ አስተዳደር ነው።

    የወረዳው አስተዳደር በፌስቡክ ገጹ ባወጣው መረጃ፣ “ከማታ 1፡00 ሰዓት አንስቶ እስከ ንጋት 12፡00 ሰዓት ድረስ ሕብረተሰቡ ከቤት ውጭ መንቀሳቀስ እንደማይችል” አስታውቋል።

    “ሕጋዊ ፈቃድ ካላቸው የጸጥታ አካላት ውጭ” ማንኛውም ግለሰብ የጦር መሣሪያ ይዞ የሚያደርገው እንቅስቃሴ “በጥብቅ የተከለከለ” እንዲሁም “ጥብቅ ክትትል” የሚደረግበት መሆኑን ገልጿል።

    እንደ ወረዳው ገለጻ፣ እነዚህ እገዳዎች የተጣሉት “የጸጥታ ማስከበር ሥራውን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ እና ቀጠናውን በፍጥነት ወደ መደበኛ ሰላም ለመመለስ” በማሰብ ነው።

    ለቢቢሲ ማብራሪያ የሰጡት የወረዳው ሰላም እና ፀጥታ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኡጁሉ፤ በክልሉ ውስጥ የሚታየው የጸጥታ መደፍረስ ገደቡ እንዲጣል ምክንያት የሆነ አንድ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰዋል።

    ከደቡብ ሱዳን ይነሳሉ ያሏቸውን ታጣቂዎች የሚያደርሱት ጉዳትም ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል። “እንደሚታወቀው በጋምቤላ የእርስ በእርስ ግጭት አለ። በዚያ መሠረት ድምበሩም ክፍት ስለሆነ ሾልከው የሚገቡ ታጣቂዎች አሉ።

    ወጣ ያሉ ቀበሌዎቻችን ላይ ጥቃት ያደርሳሉ” ብለዋል። በጥቅምት መጀመሪያ በአንድ ቀበሌ ላይ በደረሰ ጥቃት የአንድ ሰው ሕይወት አልፎ አራት ሰዎች መጎዳታቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

    ከትናንት ሐሙስ ዕለት አንስቶም ሌላ ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል የሚያመለክት እንቅስቃሴ መታየቱን ተናግረዋል።

    “ተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት የመፍጠር አዝማመሪያዎች አሉ እርሱን ለመከላከል ነው” ሲሉ የተጣለው ሰዓት እላፊ ከዚህ ጋር የተያያዘ መሆኑን አብራርተዋል።

    ከወረዳው በ18 ኪሎ ሜትር ላይ በሚገኘው የክልሉ መዲና ጋምቤላ ከተማም በጥቅምት መጀመሪያ ላይ በተመሳሳይ ከ12 ሰዓት ጀምሮ እስከ ንጋት ድረስ የሰዎችና የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ እንዳይደረግ ክልከላ ጥሎ ነበር።

    በዋና ከተማው እግዳ የተጣለው ሰዎች የተገደሉበት ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ ነው። ቀጥሎ በከተማው በተፈጠረ ግጭት ምክንያት የክልሉ መንግሥት መስሪያ ቤቶች ተዘግተው ነበር።

  2. በዩናይትድ ኪንግደም የሥራ ማስታወቂያ የሚያወጡ ኩባንያዎች ደመወዙንም የመግለጽ ግዴታ ሊጣልባቸው ነው

    የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር አንዲ በርንሀም የንግድ ድርጅቶች የሥራ ማስታወቂያ ሲያወጡ ደወወዙንም አያይዘው እንዲገልጹ አሳሰቡ።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከሥራ ማስታወቂያ ጋር ደመወዝ አብሮ እንዲገለጽ የሚያስገድድ አዲስ ሕግ ከመውጣቱ በፊት ኩባንያዎች ይህንኑ ማድረግ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

    የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ከሥራ ማስታወቂያ ጋር የደመወዝ ዝርዝር በአስገዳጅነት አብሮ እንዲወጣ የማድረግ ውጥን ይዟል።

    ይህን ገቢራዊ የሚያደርግ ሕግ “በተቻለ ፍጥነት” ይቀርባል ተብሏል።

    ለውጡ ሥራ ፈላጊዎች በዋናነት ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ የሥራ ማመልከቻ የሚያስገቡ ሠራተኞች የክፍያ አድልኦን ይከላከላል ተብሏል።

    ይሁን እንጂ የሰው ኃይል ማኅበር ደመወዝን ከሥራ ማስታወቂያ ጋር አብሮ ማውጣት ውስብስብ ሂደት እንደሆነ እና ደመወዝን ሁሌም መቆጣጠር የሚመች አይደለም ብሏል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት የዩኬ የእኩልነት ተከታታይ ተቋም ሠራተኞች ባልደረቦቻቸው ምን ያህል እንደሚከበፈላቸው የማወቅ ሕጋዊ መብት ሊኖራቸው ይገባል ካለ በኋላ ነው።

    ጠቅላይ ሚኒስትር በርንሀም ደመወዝን ከሥራ ማስታወቂያዎች ጋር አብሮ ማውጣት የፆታ መካከል ያለውን የክፍያ ልዩነትም ያጠባል ሲሉ አክለዋል።

    ተመሳሳይ እርምጃ በአውሮፓ ሕብረትም እየቀረበ ነው።

  3. በኬንያ ለ191 ሰዎች ሞት ተጠያቂ የሆነው የአምልኮ ቡድን መሪ 200 ዓመት ተፈረደበት

    በኬንያ 190 ህጻናት እና አንድ አዋቂ ሰውን በመግደል የተወነጀለው የአምልኮ ቡድን መሪ ፖል ማኬንዚን የ200 ዓመት እስር ተፈረደበት።

    ማኬንዚ እና በመዝገቡ ውስጥ የተካተቱ ሌሎች 27 ተከሳሾች፣ የአምልኮ ቡድኑ አባላት ልጆቻቸው “ከኢየሱስ ጋር እንዲገናኙ” ለማድረግ በርሃብ እንዲገድሏቸው ትዕዛዝ በመስጠት ወንጀል ጥፋተኛ ተብለዋል።

    የ190 ህጻናትን የቀጠፈው ይህ ክስተት በኬንያ ከታዩ አሰቃቂ የሃይማኖታዊ ፅንፈኝነት ድርጊቶች አንዱ ሆኖ ተቆጥሯል።

    መዝገቡብ የተመለከቱት ዳኛ ዲያና ሞቻቼ፣ ተከታዮቹ እስኪሞቱ ድረስ እንዲጾሙ በማዘዝ “ዋነኛውን የወንጀል ተጠያቂነት” የሚሸከመው ማኬንዚ ላይ እንደሆነ ገልጸዋል።

    ዳኛዋ “እንዲህ አይነቶቹ ጭካኔዎች በሕግ የተደነገገውን ከፍተኛ ቅጣት እንደሚያስከትሉ ግልጽ መልዕክት ለማስተላለፍ ስለሚያስችል ቅጣቱ ትክክለኛ እና ፍትሐዊ ነው” ብለዋል።

    ራሱን ፓስተር ብሎ የሚጠራው ግለሰብ በቁጥጥር ስር የዋለው በአውሮፓውያኑ 2023 በአንድ ጫካ በተቆፈረ ጥልቀት የሌላው ጉድጓድ ውስጥ ከ400 በላይ አስከሬኖች ከተገኙ በኋላ ነበር።

    በኬንያ የባህር ዳርቻ አቅራቢያ በሚገኘው የሻካሆላ ጫካ ውስጥ ይህንን ያህል ቁጥር ያላቸው አስከሬኖች መገኘታቸው ኬንያውያንን ያስደነገጠ ሲሆን ዓለም አቀፍ ትኩረትንም ስቦ ነበር።

    በሞምባሳ ፍርድ ቤት የቀረበውን ክስ የመሠረቱት አቃቢያነ ሕግ፣ የወንጀሉን ክብደት ከግምት ውስጥ በማስገባት ማኬንዚ ላይ የሞት ፍርድ እንዲሰጥ ተከራክረዋል።

    በተጨማሪም ማኬንዚ ለፈጸማቸው ወንጀሎች ምንም አይነት የጸጸት ስሜት አለማሳየቱንም ጠቅሰዋል። ከአውሮፓውያኑ 1987 ወዲህ ኬንያ ውስጥ የሞት ቅጣት ተፈጻሚ ሆኖ አያውቅም።

    ሌሎቹ ተከሳሾቹ ላይ ደግሞ የዕድሜ ልክ እስራት እንዲፈረድ ጠይቀው ነበር።

    ማኬንዚ እና አብረውት የቀረቡት ተከሳሾች ፍርድ ቤቱ ምህረት እና የቅጣት ማቅለያ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።

    ከሦስት ሳምንት ገደማ በፊት የጥፋተኝነት ውሳኔ ከተመተላለፉ አስቀድሞ፣ ሁሉም ተከሳሾቹ ጥፋተኛ እንዳልሆኑ በመግለጽ የተከራከሩ ሲሆን ማንም ሰው እንዲሞት አልተገደደም ብለዋል።

    ዳኛ ዲያና ሞቻቼ፣ የማኬንዚ ተከታዮች እርሱን “የኢየሱስ ልሳን” እንደሆነ ያምኑበት እንደነበር በወቅቱ ገልጸዋል። የማኬንዚን ትምህርት የተቃወሙ ሰዎች ተደብድበው እንዲሞቱ ይደረግ ነበር።

    የአምልኮ ቡድኑ ይንቀሳቀስበት በነበረው ጫካ ውስጥ የሚካሄዱ የቀብር ሥነ ሥርዓቶች “ሰርግ” ተብለው ይጠሩ የነበረ ሲሆን፣ የሞቱትም “ከኢየሱስ ጋር እንደተጋቡ ተደርገው” ይቆጠሩ እንደነበር ዳኛዋ አስረድተዋል።

    የድኅረ ሞት ምርመራ ውጤቶች እንደሚያሳዩት የአብዛኞቹ ተጎጂዎች ሞት ምክንኣት ርሃብ ነው። ሌሎች ደግሞ በአየር በመታፈን፣ በመታነቅ ወይም ጭንቅላት ላይ በደረሰ ከባድ ጉዳት የተነሳ ህይወታቸው አልፏል።

  4. የዴሞክራቶች ማሸነፍ በፈጠረው ድንጋጤ የተነሳ የኤአይ ኩባንያዎች ዋጋ በትሪሊዮኖች አሽቆለቆለ

    በአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ውጤትን ተከትሎ የሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ቴክኖሎጂ እድገትን ያቀዘቅዘዋል የሚል ስጋት በመፈጠሩ በዓለም አቀፍ የአክስዮን ገበያዎች ከፍተኛ የዋጋ ማሽቆልቆል ተመዘገበ።

    በአጋማሽ ዘመን ምርጫው፣ ዴሞክራቶች ኮንግረስን መቆጣጠራቸው ያሰጋቸው ባለሀብቶች በቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ውስጥ የነበሯቸውን አክስዮኖችን ሸጠዋል።

    በአሜሪካ የተጀመረው አክስዮኖችን በከፍተኛ መጠን የመሸጥ እንቅስቃሴ ወደ እስያ እና አውሮፓም ተስፋፍቷል። በዚህም የዋና ዋና የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የአክስዮን ዋጋ ላይ በትሪሊዮኖች ዶላር የሚቆጠር ማሽቆልቆል አጋጥሟል።

    የአሜሪካ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች አክስዮኖችን አጠቃሎ የያዘው የናስዳክ ኢንዴክስ ሐሙስ ዕለት ዋጋው በ5.5 በመቶ ወድቋል።

    ይህ የዋጋ ማሽቆልቆል የተከሰተው፣ በዚህ ሳምንቱ የአሜሪካ አጋማሽ ዘመን ምርጫ ኮንግረስን የተቆጣጠሩት ዴሞክራቶች ኤአይን በተመለከተ ጠንካራ የቁጥጥር ሕጎችን ሊያወጡ ይችላሉ የሚል ስጋት በመፈጠሩ ነው። ዴሞክራቶቹ እጩዎች ለቴክኖሎጂው የሚያስፈልጉ የዳታ ማዕከላትን መስፋፋታቸውን ሲቃወሙ ቆይተዋል።

    በተጨማሪም የአክስዮን ዋጋ ቅናሹ የተፈጠረው ግዙፍ ወጪዎች የሚደረግባቸው የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኩባንያዎች ትርፋማ የመሆናቸው ጉዳይ ላይም ስጋት በመቀስቀሱ ነው

    በአሜሪካ የተመዘገበው የአክስዮን ሽያጭ ማዕበል፣ አፕልን፣ ኤንቪዲያን እና ቴስላን ጨምሮ ‘ሰባቱ ድንቆች’ በሚል የሚጠሩት ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በአንድ ቀን ውስጥ ዋጋቸው በአንድ ትሪሊዮን ዶላር እንዲቀንስ አድርጓል። የኤንቪዲያ አክስዮን ብቻ ከዘጠኝ በመቶ በላይ አሽቆልቁሏል።

    የኤሎን መስክ ኩባንያዎች የሆኑት ስፔስ ኤክስ እና የኤሌክትሪክ መኪና አምራቹ ቴስላ አክስዮኖችም በስምንት በመቶ እና በ11 በመቶ ገደማ ዋጋቸው ቀንሷል። ይህ ቅናሽ ከኩባንያዎቹ የገበያ ዋጋ ላይ ከ300 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንዲቀነስ ምክንያት ሆኗል።

    መስክ በአጋማሽ ምርጫው በእጩነት የቀረቡት ሪፐብሊካኖች እንዲመረጡ 450 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ገንዘብ አውጥቷል። ለቴክሳስ የሴኔት አባልነት የቀረቡትን ሪፐብሊካኑ ኬን ፓክስተን የምርጫ ቅስቀሳ ለመደገፍ ብቻ ቢያንስ 45 ሚሊዮን ዶላር ሰጥቷል። ይሁን እንጂ ማክሰኞ ዕለት በተደረገው ምርጫ ከ38 ዓመት በኋላ ቴክሳስ ውስጥ ዲሞክራት የሴኔት ተወካይ ተመርጧል።

  5. ታንዛኒያዊው ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ግጭት በማነሳሳት ወንጀል ጥፋተኛ ተባሉ

    የታንዛኒያ ዋነኛ ተፎካካሪ ፖለቲከኛ ቱንዱ ሊሱ በምሥራቅ አፍሪካዊቷ አገር የፖለቲካ ነፃነት ላይ ስጋት በሳደረ ግጭት የማነሳሳት ወንጀል አራት ዓመት ተፈረደባቸው።

    የዳሬ ሰላም ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሦስት ዳኞች ችሎት ፖለቲከኛው የቀረበባቸውን ብርቱ የአገር ክህደት ክስ አቃቢ ሕግ በቂ ማስረጃ ባለማቅረቡ ነፃ ብሏቸዋል።

    ይሁን እንጂ ካለፈው ዓመት ሚያዚያ ጀምሮ በቁጥጥር ስር የሚገኙት የ58 ዓመቱ ፖለቲከኛ ደጋፊዎቻቸው የ2025ቱን ጠቅላላ ምርጫ እንዲረብሹ አበረታትተዋል ተብለዋል።

    ‘ቻደማ’ የተባለውን ተቀናቃኝ ፓርቲ የሚመሩት ሊሱ ክሱን ውድቅ አድርገው ውንጀላውን ፖለቲካዊ ግፊት ያለበት ነው ብለዋል።

    ፍርድ ቤቱ “ማሻሻያ ከሌለ፤ ምርጫ የለም” የሚለው የምርጫ ዘመቻቸው ግጭት በማነሳሳት ለቀረበባቸው ክስ በቂ ማስረጃ ነው ብሏል።

    ሊሱ በአገር ክህደት ወንጀል እንጂ ግጭት በማነሳሳት እንዳልተከሰሱ ተናግረዋል።

    “ግጭት የማነሳሳት ክስ እናንተ የተከበራችሁ ዳኞች የፈጠራችሁት ነው። ያልነበረ ክስ ፈጥራችኋል። እናም ይህንም በፖለቲካዊ ትዕዛዝ ነው ያደረጋችሁት” ብለዋል ሊሱ ለፍርድ ቤቱ።

    ፖለቲከኛው የአገር ክህደት ወንጀል ባለመከሰሳቸው እና ግጭት በማነሳሳት በመሆኑ የዋስትና መብታቸው እንዲከበር እንደሚጠይቁ ተናግረዋል።

    ፖለቲከኛው በቀጣይ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ፍርዱን ይግባኝ ማለት ይችላሉ።

    የአገር ክህደት ወንጀል በታንዛኒያ እጅግ ከባድ ከሚባሉ ወንጀሎች ውስጥ አንዱ ሲሆን እስከ ሞትም የሚያስቀጣ ነው።

    ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሉህ ሀሰን የ2025ቱን ምርጫ 98 በመቶ ድምፅ በማግኘት አሸንፈዋል።

    ይሁን እንጂ ሊሱን ጨምሮ ሁለት ዋነኛ ተቃናቃኞቻቸው ከምርጫው ውጭ ነበሩ።

  6. በኢራን የሚሳዔል ማዕከሎች አካባቢ አዳዲስ ግንባታዎች እየተካሄዱ መሆኑን የሳተላይት ምስሎች አሳዩ

    ኢራን ቢያንስ በሁለት ዋና ዋና የሚሳይል ማዕከሎቿ አካባቢ አዳዲስ ግንባታዎችን እያከናወነች እንደምትገኝ እንዲሁም ለወራት በአሜሪካና በእስራኤል የአየር ጥቃት የተጎዱ ወታደራዊ የጦር ሠፈሮቿን እየጠገነች መሆኑን የሳተላይት ምስሎች አሳዩ።

    የብሪታንያ የመረጃ ተንታኝ ኩባንያ ለቢቢሲ ቬሪፋይ እንደገለጸው፣ በኅዳር ወር የተነሱ የሳተላይት ምስሎች በቴህራን አቅራቢያ በካራጅ የሚገኘው የጋርምዳሬህ ወታደራዊ የጦር ሠፈር እና በሰሜን ኢራን የሚገኘው የሻህሩድ ጦር ሰፈር አካባቢ አዳዲስ ቁፋሮዎችና ሕንጻዎች እንደሚታዩ ያሳያሉ።

    ከእነዚህ በተጨማሪ የሚሳዔል ማዕከሎችንና የአየር ኃይል ጣቢያዎችን ጨምሮ ቢያንስ 12 ሌሎች ወታደራዊ ቦታዎች የጥገና ሥራዎች እየተካሄዱባቸው መሆናቸውን ምስሎቹ አሳይተዋል።

    በምዕራብ ኢራን ከኢራቅ ድንበር አቅራቢያ በሚገኘው የከርማንሻህ ሚሳዔል ጣቢያ በጥቃት የወደሙ ሕንጻዎች ላይ አዲስ ጣሪያዎች ሲሰሩ፣ ከዋና ከተማዋ በስተምሥራቅ በሚገኘው የፓርቺን ወታደራዊ ማዕከል ደግሞ የተጎዱ ሕንጻዎች እና ፍርስራሾች ተወግደዋል።

    በሻህሩድ አካባቢ የሚታዩት ቁፋሮዎች ከሚሳዔል ምርት ጋር የተያያዙ ሊሆኑ እንደሚችሉ በኢራን ጉዳዮች ላይ የሰሩት የቀድሞ የሲአይኤ ተንታኝ ጂም ላምሰን ተናግረዋል። በአካባቢው ያለው የአየር ኃይል ጣቢያ በተደጋጋሚ ዒላማ መደረጉን በመጥቀስ፣ የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የምርት ተቋማቱን ከመሬት በታች ለማዛወር መንገዶችን እየፈለገ መሆኑን ገልጸዋል።

    አንድ የብሪታኒያ የመረጃ ተንታኝ እንዳሉት ኢራን “መሠረተ ልማቶቿን ከተጨማሪ ጥቃቶች ለመጠበቅ ከመሬት በታች የማዛወር ልማድ አላት”። የመከላከያ ተንታኙና የአየርላንድ ጦር የቀድሞ ኃላፊ ማርክ ሜሌት ደግሞ ከመሬት በታች ተቋማትን መገንባት “ከውጭ ለሚመለከት የእነዚህን ተቋማት አቅምና የሥራ እንቅስቃሴ ደረጃ ለመገምገም የበለጠ አስቸጋሪ ያደርጋል” ብለዋል።

    አሜሪካ ከአጋማሽ ዘመን ምርጫ መጠናቀቅ በኋላ በኢራን ላይ ዳግም ጥቃት ልትጀምር ትችላለች የሚል ስጋት ጨምሯል። ሆኖም ረቡዕ ዕለት ምክትል ፕሬዚዳንት ጄዲ ቫንስ ጦርነቱ በመራጮች ዘንድ ተወዳጅነት ስለሌለው ሪፐብሊካኖች በምርጫው ደካማ ውጤት እንዳስመዘገቡ ገልጸው፣ ይህም ፓርቲያቸው ለቀጣዮቹ ስድስት ዓመታት የሴኔቱን ቁጥጥር እንዲያጣ አድርጎት ሊሆን ይችላል ብለዋል።

    በመላ አገሪቱ ባሉ በርካታ ወታደራዊ ማዘዣዎች የኢራን ኃይሎች ከአሜሪካ-እስራኤል ጦርነት መጀመር አንስቶ በአየር ጥቃት በከፍተኛ ሁኔታ የተጎዱ ሕንጻዎችን በአነስተኛ ደረጃ የመጠገን ሥራ ላይ አተኩረዋል።

    ተንታኞች እንደሚሉት፣ በፓርቺን ወታደራዊ ማዕከል ውስጥ በሚገኘው ታሌጋን-2 ተቋም ከፍተኛ የግንባታ ሥራ ተጠናቋል። በጥቃት የተጎዱ ሕንጻዎች ፈርሰው አካባቢው ተስተካክሏል፣ በመሬት ውስጥ ባለ ምሽግ ላይ የደረሰው ጉዳትም በኮንክሪት ተጠግኖ ዳግም ተጠናክሯል።

    ተያያዥ ዜናዎች፡

  7. የሶማሊያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የፕሬዚደንቱ የሥልጣን ዘመን መራዘምን ውድቅ አደረገ

    የሶማሊያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ሃሰን ሸክ ሞሐሙድ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የሥልጣን ዘመናቸውን ለማራዘም ያደረጉትን የሕግ ማሻሻያ ውድቅ አደረገ።

    ፕሬዚደንቱ ሥልጣናቸውን ማራዘማቸው በአገሪቷ ውስጥ ያለውን ፖለቲካዊ ቀውስ እና በፕሬዚደንቱ እና በሕግ አካላት መካከል ያለውን ውዝግብ አባብሶታል።

    ፍርድ ቤቱ ሐሙስ ዕለት ውሳኔውን ያሳለፈው ፕሬዚደንቱ የፍርድ ቤቱ ፕሬዚደንት የሆኑትን ባሽ ዩሱፍ አሕመድን ከሥራ ካሰናበቱ ከአንድ ቀን በኋላ ነው። ፍርድ ቤቱ ፕሬዚደንቱ ይህን እርምጃ የመውሰድ ሕጋዊ ሥልጣን የላቸውም ብሏል።

    ከዚህም በተጨማሪ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የፖለቲካ መሪዎች በ30 ቀናት ውስጥ የምርጫ እቅዳቸው ላይ ከስምምነት እንዲደርሱ እና በ90 ቀናት ውስጥ ምርጫውን እንዲያካሂዱ ትዕዛዝ ሰጥቷል። ይህም ፕሬዚደንቱ ሚያዝያ ወር ላይ ለማካሄድ ካቀዱት ብሔራዊ ምርጫ ጋር የሚጋጭ ነው።

    የፕሬዚደንት ሞሐሙድ የአራት ዓመት የሥልጣን ዘመንም ግንቦት 7/2018 ዓ.ም. ላይ አብቅቷል።

    ሆኖም አስተዳደራቸው ባለፈው መጋቢት ወር ላይ ፓርላማው ባጸደቀው የሕግ ማሻሻያ የሥልጣን ዘመናቸውን በአንድ ዓመት አራዝሞታል።

    ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፕሬዚደንቱ ሥልጣናቸውን ለማራዘም የሕገ መንግሥት ማሻሻያ በማድረግ ከሰዋቸዋል።

    ፕሬዚደንቱ ግን የተደረገው የሕግ ማሻሻያ ሶማሊያን በጎሳ ላይ ከተመሰረተው እና የጎሳ መሪዎች ተወካዮቻቸውን ከሚመርጡበት ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ወደ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ለማሸጋገር አስፋላጊ ነው ሲሉ ይሞግታሉ።

    ተያያዥ ዜና፡

  8. አሜሪካ በአርሲ የተፈፀሙ ግድያዎች ላይ ኢሰመኮ ያወጣውን “ዝርዝር እና ግልጽ” ሪፖርት እንደምትደግፍ ገለጸች

    በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የሆኑት ኧርቪን ማሲንጋ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በቅርቡ በአርሲ የተፈፀሙ ግድያዎችን በተመለከተ ያቀረበውን “ዝርዝር እና ግልጽ ሪፖርት” አሜሪካ እንደምትደግፍ ገለጹ።

    አምባሳደር ማሲንጋ በኤምባሲው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ላይ ባጋሩት ጽሑፍ፣ ኮሚሽኑ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በርካታ እስረኞች እንዲፈቱ በማመቻቸት ያደረገውን ጥረትም አገራቸው ትደግፋለች ብለዋል።

    ኮሚሽኑ በተለይ በግጭት በተጎዱ እንደ ትግራይ ባሉ አካባቢዎች ምጣኔ ሃብት እንዲያገግም ፣ ተቋማት እንዲገነቡ፣ የፍትሕ ሥርዓት፣ ዲሞክራሲ እና ማሕበራዊ ግንኙነቶች እንዲመለሱ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ያለውን ትብብር ያጠናክራል ብላ አሜሪካ ተስፋ እንደምታደርግም አክለዋል።

    ትናንት ሐሙስ፣ ጥቅምት 26/2019 ዓ.ም. ከኢሰመኮ ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ ጋር ውይይት ማድረጋቸውን የገለጹት አምባሳደር ማሲንጋ፣ ለኮሚሽኑ ሪፖርት ድጋፋቸውን የገለጹት፣ ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ ክልል አርሲ ውስጥ በንፁሃን ዜጎች ላይ የተፈጸሙ ግድያዎች በአግባቡ ተመርምረው የወንጀሉ ፈጻሚዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ የኢትዮጵያ መንግሥትን ከጠየቁ በኋላ ነው።

    ከሁለት ሳምንት በፊት በቀድሞው የኦሮሚያ ክልል አወቃቀር አርሲ ዞን በአዲሱ አደረጃጀት በደቡብ ምሥራቅ ዞን ሥር በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች በነዋሪዎች ላይ በተፈጸሙ ጥቃቶች ከ60 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አስታውቃለች።

    እስካሁን ለጥቃቱ ኃላፊነቱን የወሰደ አካል የለም። ሆኖም የክልሉ ኮሚዩኒኬሽን “ ጽምዶን” ተጠያቂ አድርጓል።

    ኢሰመኮ ጥቅምት 24 ፣ 2019 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት በኦሮሚያ ክልል ሽርካ ወረዳ በተፈጸሙ የተለያዩ ጥቃቶች 48 ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል።

    ጥቃቱም "በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት" እና "ኢመደበኛ ታጣቂዎች" መፈፀሙን ገልጿል። በአርሲ ዞን አሁንም ጥቃቶች መቀጠላቸውን እና ባለፉት ቀናትም በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    ተያያዥ ዜናዎች፡

  9. ኢራን በኒውክሌር ጉዳይ ላይ ለአሜሪካ ምክረ ሐሳብ መላኳን የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣን ተናገሩ

    የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በእስላማዊቷ ሪፐብሊክ ላይ የቀረውን ሁሉ “እናጠፋዋለን” በማለት ከዛቱ በኋላ ቴህራን ለዋሺንግተን ኒውክሌርን በሚመለከት የስምምነት ሀሳብ መላኳ ተገለጸ።

    ሮይተርስ የዜና ወኪል አንድ ከፍተኛ የኢራን ባለሥልጣንን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ ምክረ ሃሳቡ በኳታር በኩል ለዋሽንግተን የተላለፈ ሲሆን፣ አሜሪካ የቴህራንን ሰባት ቅድመ ሁኔታዎች ካሟላች በኋላ ብቻ ለውይይት እንደሚቀርብ ተገልጿል።

    ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁት ከፍተኛ ባለሥልጣን፣ ዋሽንግተን ሀሳቡን እየገመገመች እንደሆነ ለሮይተርስ የተናገሩ ቢሆንም፣ ተጨማሪ መረጃ ለመስጠት ግን ፈቃደኛ አልሆኑም።

    የኢራን ከፍተኛ የደህንነት ኃላፊ ሞህሴን ሬዛኢ በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ “ዲፕሎማሲን በሚመለከት ለአሜሪካ ሰባት ቅድመ ሁኔታዎችን አሳውቀናል። እነዚህን ሰባቱን መስፈርቶች ተግባራዊ እስካላደረጉ ድረስ የሆርሙዝ ወሽመጥን አንከፍትም፣ እንዲሁም ወደ ድርድር አንገባም” ብለው ነበር።

    የኢራን ቅድመ ሁኔታዎች እስካሁን ድረስ በይፋ ባይገለጹም፣ በካህሌጅ ታይምስ በመባል የሚታወቀው መገናኛ ብዙኃን ባወጣው ዘገባ መሠረት ቴህራን ያቀረበቻቸው ጥያቄዎች ሊባኖስን ጨምሮ በክልሉ ያሉ ግጭቶች ሙሉ በሙሉ እንዲቆሙ፣ አሜሪካ በኢራን ወደቦች ላይ የጣለችውን የባሕር ኃይል እገዳ እንድታነሳ፤ በኢራን ላይ የተጣሉ የአሜሪካ ማዕቀቦች እንዲነሱ፤ የኢራን በውጭ የታገዱ ንብረቶችና ገንዘቦች እንዲለቀቁ፤ አሜሪካ በቀጣናው ያላትን ጦር እነድትቀንስ፤ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ለደረሱ ጉዳቶች ካሳ እንዲከፈል፣ በኢራን ግዛት ላይ የሚፈጸሙ የአሜሪካ ጥቃቶች እንዲቆሙ የሚሉ ናቸው።

    በሌላ በኩል፣ ዋሽንግተን ማንኛውም የመጀመሪያ ዙር ድርድር የኢራንን የኒውክሌር ፕሮግራም ጉዳይ ማካተት እንዳለበት ገልጻለች። ይህም በሁለቱ ወገኖች መካከል ማንኛውም ስምምነት ላይ ለመደረስ የኒውክሌር ጉዳይ አንዱ ዋና የውይይት አጀንዳ እንደሚሆን ያመለክታል።

    ይህ የኒውክሌር ስምምነት ሀሳብ የቀረበው፣ በአሜሪካና በኢራን መካከል ያለው ጦርነት ከአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫዎች በኋላ እንደገና ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት በተጠናከረበት እና አደራዳሪዎች ግጭቱን ለማስቆም ጥረታቸውን ባጠናከሩበት ወቅትነው።

    ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከምርጫው በኋላ ወታደራዊ ዘመቻዎች እንደገና ሊቀጥሉ እንደሚችሉ ያላስተባበሉ ሲሆን በሌላ በኩል ኢራንም ጦርነቱ እንደገና ከተቀሰቀሰ ጠንካራ ሰፊ ምላሽ ለመስጠት ማቀዷ ተነግሯል።

    አሜሪካና እስራኤል ባለፈው ዓመት የካቲት ወር መጨረሻ በኢራን ላይ ድብደባ ከፈጸሙ በኋላ፣ ኢራን በበኩሏ በእስራኤል እና የአሜሪካ ጦር ሰፈሮችን በሚያስተናግዱ የባህረ ሰላጤው አገራት ላይ ጥቃቶችን ፈጽማለች።

    ግጭቱ ወደ ሊባኖስ ተስፋፍቶ በኢራን በሚደገፈው ሄዝቦላህ እና በእስራኤል መካከል ውጊያዎች ተካሂደዋል። በቅርቡ ደግሞ ቀውሱ ወደ የመን ተሻግሮ ከኢራን ጋርየሚቀራረቡት የሁቲ ታጣቂዎች በሳዑዲ አረቢያ ውስጥ በሚገኙ የኃይል ማመንጫ ተቋማት፣ አውሮፕላን ማረፊያዎች እና ሌሎች ዒላማዎች ላይ ጥቃቶችን መፈጸማቸው ተዘግቧል።

    ተጨማሪ ዘገባ፡

  10. የጥቅምት 27/ 2019 ዓ. ም. የቀጥታ ስርጭት ተጀምሯል

    የቢቢሲ አማርኛ ወዳጆች እንደምን አደራችሁ፤ የጥቅምት 27/ 2019 ዓ. ም. የቀጥታ ስርጭታችን ተጀምሯል።

    የአገር ውስጥ እና የውጭ ዜናዎችን በአጭሩ እናቀርብላችኋለን። እንድትከታተሉን በአክብሮት እንጋብዛለን።