ቀጥታ, ለምርጫ አንድ ቀን የቀራቸው የእስራኤሉ መሪ ኔታንያሁ 90 በመቶ የሚሆነውን የኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም አውድመናል አሉ

ነገ ማክሰኞ ፓርላሜንታዊ ምርጫ የሚጠብቃቸው የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ፣ የኢራንን የኒውክሌር መርሃ ግብር የማውደሙ ሥራ 90 በመቶው መጠናቀቁን እና የቀረው 10 በመቶ ያህሉ ብቻ እንደሆነ ተናገሩ። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው “አብረን የጀመርነውን ሥራ እንድናጠናቅቅ ኔታንያሁን ምረጡ” ሲሉ ለእስራኤላውያን መልዕክት አስተላልፈዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. የሰርቢያው አንጋፋ መሪ ቩቺች በተማሪዎች የአመጽ እንቅስቃሴ በመሸነፋቸው የአገሪቱ ዜጎች ደስታቸውን እየገለፁ ነው

    ሰርቢያን ለረጅም ጊዜ የመሩት አሌክሳንደር ቩቺች የተማሪዎችን የተቃውሞ ንቅናቄ ተከትሎ በድንገተኛ የፓርላማ ምርጫ መሸነፋቸውን አምነው ተቀበሉ።

    “የመጨረሻውን ውጤት እስካሁን ባይደርሰንም በምርጫው መሸነፋችን ግን ግልጽ ነው” ሲሉ የቀኝ ዘመሙ ሕዝበኛ መሪ እሁድ ምሽት ሽንፈታቸውን ተቀብለዋል።

    የሰርቢያ የምርጫ ኮሚሽን ይፋ ያደረጋቸው የመጀመሪያ ደረጃ ውጤቶች፣ በአገሪቱ ታሪክ ከፍተኛ የሆነ የመራጮች ተሳትፎ እንደነበረ አመልክተዋል።

    ቩቺች ሽንፈታቸውን ከተቀበሉ በኋላ በሰርቢያ በርካታ አካባቢዎች ሰዎች አደባባይ በመውጣት ደስታቸውን ገልፀዋል።

    ቩቺች ድንገተኛ ምርጫ እንዲደረግ ጥሪ ያቀረቡት በኖቪ ሳድ ከተማ የባቡር ጣቢያ ጣሪያ ወድቆ 16 ሰዎች መሞታቸውን ተከትሎ በአገሪቱ ለሁለት ዓመታት የቀጠሉ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ከተካሄዱ በኋላ ነው።

    የባቡር ጣቢያው አደጋ በሰርቢያ ውስጥ የተንሰራፋው ሙስና እና የቸልተኝነት ምልክት ተደርጎ በመታየቱ ነው ተቃውሞ የተቀሰቀሰው።

    የሰርቢያ ፕሮግሬሲቭ ፓርቲ መሪው ቩቺች፣ ለሁለት የፕሬዚደንትነት ዘመናት ካገለገሉ በኋላ ለሦስተኛ ጊዜ መወዳደር የማይችሉ በመሆኑ፣ እአአ ከ2017 ጀምሮ ወደለቀቁት የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣን የመመለስ ዓላማ ነበራቸው።

    የተማሪዎችን የተቃውሞ እንቅስቃሴ ተከትሎ የተመሰረተው እና ምርጫውን ያሸነፈው የ’ስቱደንት ሊስት’ መሪ ኢሊያ ስርዳኖቪች “ነጻ መንግሥት ይመሰረታል” ሲሉ ለቢቢሲ ሰርቢያ ተናግረዋል።

    በመላው ሰርቢያ የሚገኙ የመንግሥት ተቃዋሚ መራጮችን ያሰባሰበው የፀረ ሙስና ንቅናቄ “አገሪቱን ከግፍና ከጭቆ እና አገዛዝ ነጻ ያወጣል” የሚል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።

  2. ሁቲዎች በሳዑዲ አየር ማረፊያ እና ነዳጅ ማውጫዎች ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ገለጹ

    የየመን ሁቲዎች ዛሬ ሰኞ የሪያድ አየር ማረፊያ እና በሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ የሚገኙ የድፍድፍ ነዳጅ ጣቢያዎች ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን አስታወቁ።

    በየመን የሚገኘው እና በሳዑዲ የሚመራው ጥምረት በበኩሉ ሁቲዎች ዛሬ ጠዋት ወደ ሪያድ የተተኮሰን ሚሳዔል ማክሸፉን እና በየመን ሰንዓ ውስጥ ሁለት የባለስቲክ ሚሳኤል ማስወንጨፊያዎችን ማውደሙን አስታውቋል።

    ሁቲዎች በሳዑዲ መዲና የሚገኘውን የኪንግ ካሊድ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ላይ ባሊስቲክ ሚሳዔል ማስወንጨፋቸውን እና ጥቃቱ “ዒላማውንም በትክክል መምታቱን” የቡድኑ ቃል አቀባይ ከሁቲ ጋር ግንኙነት ላለው አል ማሲራህ የቴሌቪዥን ጣቢያ ተናግረዋል።

    ሁቲዎች አየር ማረፊያው ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ገለጹት በጥቅምት መጀመሪያ በተፈጸመበት እና 13 ሰዎች በተገደሉበት ጥቃት ምክንያት ያቆመውን አገልግሎት ትናንት እሁድ በከፊል መጀመሩን ባስታወቀ ማግሥት ነው።

    ታጣቂ ቡድኑ ከአየር መንገዱ በተጨማሪ በአገሪቱ የሚገኙ የድፍድፍ ነዳጅ ማውጫ ጣቢያዎችን በድሮን መምታቱን ገልጿል። ሳዑዲ በአየር ማረፊያው ላይም ሆነ በነዳጅ ማውጫዎች ላይ ተፈጽመዋል ስለተባሉን ጥቃቶች እስካሁን አስተያየት አልሰጠችም።

    የሳዑዲ ሲቪል መከላከያ በዋና ከተማው ሪያድ ውስጥ አደጋ ሊኖር እንደሚችል የሚገልጽ ማስታወቂያ አውጥቶ የነበረ ሲሆን፣ ኋላ ላይም ስጋቱ ማለፉን አስታውቋል።

    ሁቲዎች ጥቃት ማድረሳቸውን ያስታወቁት በሳዑዲ የሚመራው ጥምር ጦር በየመን መዲና ሰንዓ የሚገኙ ሁለት የሚሳዔል ማስወንጨፊያዎችን ማውደሙን ካስታወቀ በኋላ ነው። ከእነዚህ ማስወንጨፊያዎች አንዱ ጥምር ጦር እንዳከሸፈው የገለጸውን እና ወደ ሪያድ የተተኮሰውን ባለስቲክ ሚሳዔል ለማስወንጨፍ ጥቅም ላይ የዋለ እንደነበር ተገልጿል።

    በኢራን የሚደገፉት ሁቲዎች ሳዑዲ ላይ የሚፈጽመውን ጥቃት ማጠናከራቸውን ተከትሎ አሜሪካ በአገሪቱ የሚገኙ የአስቸኳይ ጊዜ ሠራተኞች ያልሆኑ ባልደረቦች እና ቤተሰቦቻቸው ከሳዑዲ እንዲወጡ ማዘዟ ይታወሳል።

  3. ጋቦን ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ጥላ የነበረውን እገዳ ከስምንት ወራት በኋላ አነሳች

    በማዕከላዊ አፍሪካ የምትገኘው ጋቦን ሰፊ ተቃውሞ እና ትችት አስከትሎባት የነበረውን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የጣለችውን እገዳ ከስምንት ወራት በኋላ ማንሳቷን አስታወቀች።

    መንግሥት በበይነ መረብ የሚለቀቁ ይዘቶች ግጭትን እያባባሱ እና በአገሪቱ ውስጥ ክፍፍልን እያስፋፉ ነው በሚል ነበር ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ላይ እገዳውን የጣለው።

    ይህ እርምጃ ወደ 2.5 ሚሊዮን ሕዝብ ባላት ጋቦን ውስጥ መነጋገሪያ ሆኗ ቆይቷል። በአገሪቱ ፌስቡክ፣ ቲክቶክ፣ ዩቲዩብ እና ኢንስታግራም በተለይ በወጣቶች ዘንድ ለንግድም ሆነ ለመዝናኛ በስፋት ጥቅም ላይ የሚውሉ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ነበሩ።

    እገዳው ከተጣለ በኋላ በርካቶቹ የአገሪቱ ዜጎች ማኅበራዊ ሚዲያ ለመጠቀም ቪፒኤን የተባለውን በተዘዋዋሪ አገልግሎቱን የማግኛ መንገድን መጠቀም ጀምረው ነበር።

    እገዳው የተጣለው የጋቦን ፕሬዝዳንት ብሪስ ኦሊጊ ንጉኤማ ከተመረጡ አንድ ዓመት ሳይሞላቸው በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ ማኅበራዊ ተቃውሞ ካጋጠመ በኋላ ነበር።

    በወቅቱ መምህራን እና የመንግሥት ሠራተኞች ዝቅተኛ ደመወዝ እና አመቺ ያልሆነ የሥራ ሁኔታን እንደምክንያት በማቅረብ አድማ አድርገው ነበር።

    የአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ደግሞ በመንግሥት የተጣለው የማኅበራዊ ሚዲያው እገዳ ሥልጣንን አላግባብ መጠቀም ነው ሲሉ ወቅሰው ነበር።

    ፕሬዝዳንት ንጉዌማ ባለፈው ዓመት በተካሄደው ምርጫ ከ90 በመቶ በላይ ድምፅ በማግኘት ነበር ያሸነፉት። ምርጫው የተካሄደው ፕሬዝዳንቱ የመሩት መፈንቅለ መንግሥት ከሃምሳ ዓመታት በላይ የዘለቀውን የቦንጎ ቤተሰብ አገዛዝን ካበቃ ከሁለት ዓመታት በኋላ ነበር።

    በወቅቱ ንጉዌማ በነዳጅ እና በደን ሀብት የበለጸገችውን ትንሿ ጋቦንን ለማሻሻል ቃል ገብተው ነበር።

  4. ለምርጫ አንድ ቀን የቀራቸው የእስራኤሉ መሪ ኔታንያሁ 90 በመቶ የሚሆነውን የኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም አውድመናል አሉ

    ነገ ማክሰኞ ፓርላሜንታዊ ምርጫ የሚጠብቃቸው የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ፣ የኢራንን የኒውክሌር መርሃ ግብር የማውደሙ ሥራ 90 በመቶው መጠናቀቁን እና የቀረው 10 በመቶ ያህሉ ብቻ እንደሆነ ተናገሩ።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው “አብረን የጀመርነውን ሥራ እንድናጠናቅቅ ኔታንያሁን ምረጡ” ሲሉ ለእስራኤላውያን መልዕክት አስተላልፈዋል።

    ለሦስት ዓመት ከዘለቀው የቀጣናው ጦርነት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነገ ማክሰኞ የሚካሄደው የእስራኤል ምርጫ እጅግ ተጠባቂ ሆኗል። አርብ ዕለት የወጣ የሕዝብ አስተያየት ዳሰሳ እንዳመለከተው ከሆነ በአገሪቱ መንግሥት የመሠረተው ጥምረት እና ዋነኛ ተቃዋሚዎችን የያዘው ቡድን አንገት ለአንገት ተናንቀዋል።

    ከግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ እስራኤላውያን ለመጀመሪያ ጊዜ ድምፅ የሚሰጡ ሲሆን፤ በውጭ አገራት የነበሩ 70 ሺህ ገደማ የአገሪቱ ዜጎች ለዚሁ ምርጫ ሲሉ ወደ እስራኤል ገብተዋል።

    ምርጫ ሁለት ቀናት ሲቀሩት ትናንት እሁድ ለእስራኤሉ ቻናል 14 የቴሌቪዥን ጣቢያ ቃለ መጠይቅ የሰጡት ኔታንያሁ፣ የምርጫ ተቀናቃኞቻቸው የኢራንን ኒውክሌር የማውደምን ሥራ ለማጠናቀቅ የሚያስችል ብቃት እንደሌላቸው ሲናገሩ ተደምጠዋል።

    "እኛ የሥራውን 90 በመቶ አጠናቅቀናል፤ 10 በመቶ ብቻ ቀርቷል። ይህንን ማን ሊያደርገው ይችላል? አይዘንኮት እና የሙስሊም ወንድማማቾች? በፍጹም፣ ይህንን ማድረግ የምችለው እኔ ብቻ ነኝ” ብለዋል።

    ከቀድሞው የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጋዲ አይዘንኮት ጋር ከፍተኛ ፉክክር ውስጥ የሚገኙት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ በምርጫ ቅስቀሳቸው የመጨረሻ ቀናት የኢራንን የኒውክሌር መርሃ ግብርን ጉዳይ በድጋሚ የቅስቀሳቸው ዋነኛ አጀንዳ አድርገውታል።

    ኔታኒያሁ በትናንትናው ዕለትም በቴል አቪቭ ላይ የኒውክሌር ፍንዳታ ሲደርስ የሚያሳይ የሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ምሥል በኤክስ ገጻቸው ላይ አጋርተዋል። ከምሥሉ ጋርም ኢራን ለእስራኤል “የኅልውና ስጋት” መሆኗን የሚገልጽ የአንድ ቀኝ ዘመም እስራኤላዊ የፖለቲካ ተንታኝ ጽሑፍን አያይዘዋል።

    ተፎካካሪያቸው ጋዲ በበኩላቸው፣ ኔታንያሁ የመራጮችን ድጋፍ ለማግኘት ሲሉ ከኢራን የሚመነጭን ስጋት መጠቀሚያ እያደረጉ ነው ሲሉ ከስሰዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢራን ጋር ለተደረገው ጦርነት ራሳቸው ያስቀመጧቸውን ግቦች ማሳካል አለመቻላቸውንም ተናግረዋል።

    በዚህ ተጠባቂ ምርጫ ከኔታንያሁ ጎን የተሰለፉት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራም በበኩላቸው በድጋሚ ድጋፋቸውን ገልጸዋል። አሜሪካ እና እስራኤል ካለፈው ዓመት የካቲት አንስቶ ኢራን ላይ በጋራ ያካሄዷቸውን ወታደራዊ ዘመቻዎች ያስታወሱት ትራምፕ፣ “አብረን የጀመርነውን ሥራ እንድናጠናቅቅ” እስራኤላውያን መራጮች ለኔታንያሁ ድምፃቸውን ስጡ ሲሉ ጠይቀዋል።

    ፕሬዝዳንቱ ትሩዝ ሶሻል በተባለው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ፅሑፍ፣ እርሳቸው እና የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ጥሩ ግንኙነት እንዳላቸው እና በተለያዩ ወታደራዊ ዘመቻዎች የጋራ ድሎችን እንደተቀዳጁ ገልጸዋል።

    በ2017 ዓ.ም. አሜሪካ እና እስራኤል የኒውክሌር ተቋማት ላይ በፈጸሙት ድብደባ ቴህራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ባለቤት እንዳትሆን ማድረጋቸውን ተናግረዋል።