ኤል ሳልቫዶር አራት የጠፉ ወታደሮችን ለመታደግ ከ2,000 በላይ ወታደሮችን ወደ ሄይቲ አሰማራች
ኤል ሳልቫዶር ከሁለት ሳምንታት ገደማ በፊት በሄይቲ የጠፉትን አራት ወታደሮቿን ሕይወት ለመታደግ ከ2,000 በላይ ወታደሮችን ወደ ሄይቲ መላኳን አስታወቀች።
የኤል ሳልቫዶር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፤ ወሳኝ የተባለው ይህን የወታደሮች ስምሪት በተመለከተ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ናይብ ቡኬሌ ለሄይቲው ጠቅላይ ሚኒስትር አሊክስ ዲዲዬር ፊልስ-አይሜ ገለፃ ማድረጋቸውን አስታውቋል።
ፕሬዝዳንት ቡኬሌ ስምሪት የተጣቸው ከ 2,000 በላይ የሚሆኑት ወታደሮች በሄይቲ የወንበዴ ቡድኖች ላይ የሚደረገውን የፀጥታ ማስከበር ጥረት እንደሚያግዙም መናገራቸውን በመግለጫው ተመላክቷል። ይህ ስምሪት በተለያዩ አገራት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የተደገፈ መሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጿል።
በሄይቲ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) በሚደግፈው ፀረ-ወንበዴ ተቋም ውስጥ ሲሰሩ የነበሩ አራት የአየር ኃይል ቴክኒሻኖች መጥፋትን ተከትሎ በሁለቱ የመካከለኛው አሜሪካ አገራት መካከል ያለው ውጥረት ተባብሷል።
በፀረ-ወንበዴ ኃይል ውስጥ አባል የሆኑት አራቱ ወታደሮች ጥይት በማይበሳው ተሽከርካሪ ወደ ጦር ሰፈራቸው እየተመለሱ ሳለ፣ በታጠቁ ቡድኖች ቁጥጥር ስር በሚገኝ አካባቢ ድንገተኛ ጥቃት ደርሶባቸዋል። ሆኖም እስካሁን ድረስ ኃላፊነቱን የወሰደ ቡድን የለም።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ፣ ሄይቲ የጠፉት ወታደሮች ናቸው በማለት አራት አስከሬን ለልዩ ኃይሎች ያስረከበች ቢሆንም፣ የኤል ሳልቫዶር ፕሬዝዳንት ቡኬሌ ግን አስከሬኖቹ ደብዛቸው ከጠፋ ወታደሮች ጋር እንደማይመሳሰል ገልጸዋል።