ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢትዮጵያ ከሩሲያ የተረከበቻቸው የጦር ጄቶች ወታደራዊ አቅሟን ምን ያህል ይለውጡታል?
ለሩሲያ-አፍሪካ ጉባዔ ሞስኮ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እጅግ ዘመናዊ የጦር ጄቶች እንደተረከቡ እና በቀጣይም የአየር መከላከያ ሥርዓቶችን እንደሚረከቡ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ 12፣ ሱ-35 የጦር ጄቶችን የተረከበች ሲሆን፤ በቀጣይም አራት ኤስ-400 የአየር መከላከያ ሥርዓት ባትሪዎችን እንደምትረከብ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
እነዚህን የጦር ጄቶች በመታጠቅ ኢትዮጵያ "ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት ቀዳሚ" እንደምትሆንም ገልጸዋል።
የጦር ጄቶቹ ምን ያህል ዘመናዊ ናቸው? እነዚህ ጄቶች ለኢትዮጵያ አየር ኃይል ምን ማለት ናቸው? የሚለውን እንደሚከተለው ቃኝተናል።
ሱ-35 ተዋጊ ጄት
የጦር መሣሪያዎችን በተመለከተ ትንታኔ የሚሰጡ ድረ ገጾች እንደሚጠቁሙት (ሱክሆይ) ሱ-35 (Su-35) የሩሲያ ዘመናዊ ተዋጊ ጄት ነው።
ሱ-27 የተባለው ተዋጊ ጄት ተሻሽሎ ወደ ሱ-35 ተዋጊ ጄት ማደጉን መረጃዎች ያሳያሉ።
አውሮፕላኖቹ አንድ መቀመጫ እና ሁለት ሞተር ያላቸው የጦር ጄቶች ሲሆኑ፤ በአየር ላይ ለሚደረግ ውጊያ እንዲሁም በየብስ ላይ ጥቃት ለማድረስም ይውላሉ።
ሱ-35 ተዋጊ ጄት '4++ generation' በሚል ስያሜ የሚጠራ ሲሆን፤ ይህም በአራተኛ ትውልድ የተዋጊ ጄቶች እና በአምስተኛ ትውልድ ተዋጊ ጄቶች መካከል ያስቀምጠዋል።
ሱ-35 የተባሉት የጦር ጄቶች አራተኛው ትውልድ የሚባሉ ዘመናዊ የጦር መሣሪያ መሆናቸውን ያመለከቱት ዐቢይ፤ አሁን የኢትዮጵያ መንግሥት የተቀበላቸው 12 የጦር ጄቶች የመጀመሪያው ዙር አቅርቦት መሆናቸውን ገልጸዋል።
ሱ-35 የተገጠሙለት ሞተሮች በከፍተኛ ፍጥነት እንዲጓዝ እንዲሁም ከሚቃጡበት ጥቃቶች አቅጣጫ በመለወጥ እንዲያመልጥ እንደሚረዱ ወታደራዊ መረጃ የሚሰጡ ድረ ገጾች ያትታሉ።
እነዚህ "የላቁ የሩሲያ የጦር ጄቶች" በአውሮፓውያኑ 2016 በሶሪያ እና ከ2022 አንስቶ በዩክሬን ጥቅም ላይ ውለዋል።
ሩሲያ አሉኝ ከምትላቸው የጦር ጄቶች መካከል በዋናነት የሚጠቀሱ ሲሆኑ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ በሙከራ ደረጃ የተሠራው ሱ-35 የጦር ጄት የበረረው በአውሮፓውያኑ 2008 መሆኑን ይነገራል።
በ2014 እነዚህ የጦር ጄቶች አግልግሎት መስጠት የሚችሉበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን የወታደራዊ መረጃ ምንጮች ይጠቁማሉ።
ኢትዮጵያ በአውሮፓውያኑ 1990ዎቹ አካባቢ የዚህ ጄት ቀዳሚ ዝርያ የሆኑ ሱ-27 የጦር ጄቶች ታጥቃ እንደነበር ይነገራል።
ጀቲፋይ እና ሚግፍላግ የተባሉ ጦር መሣሪያ መረጃ የሚያቀርቡ ድረ ገጾች እንደሚጠቁሙት፤ ዘመናዊው ሱ-35 የጦር ጄት በሰዓት እስከ 2,400 ኪሎሜትር የመጓዝ ፍጥነት አለው።
የሩሲያው የጦር መሣሪያ አምራች በሆነው 'ሱኮሆይ' የሚመረተው ሱ-35 የጦር ጄትን ከዚህ በፊት ቻይና እና ኢራን ገዝተው ታጥቀውታል።
እስካሁን ባለው መረጃ በአፍሪካ ደግሞ የጦር ጄቶቹ ያሏት አገር አልጄሪያ ናት።
በአየር ላይ በከፍተኛ ፍጥነት በመተጣጠፍ (Supermaneuverability) ታዋቂ የሆነው የጦር ጄት፤ እስከ 8,000 ኪሎግራም የሚመዝኑ 12 መሣሪያዎችን (አር-37ኤም የረዥም ርቀት ሚሳዔል፣ አር-77 ቢቪአር ሚሳዔል፣ ፀረ መርከብ ሚሳዔል እና ዒላማ ተኮር ቦምብን ጨምሮ) መሸከም ይችላል።
ተጨማሪ ነዳጅ ሳይሞላ እስከ 3,600 ኪሎ ሜትር መጓዝ ይችላል። በርቀት ላይ (እስከ 200 ኪሎ ሜትር ድረስ) ያሉ የአየር መሣሪያዎችን ለይቶ ዒላማ ማድረግ የሚችል የጦር ጄት ነው።
በአየር ላይ ውጊያ ወቅት በፍጥነት አቅጣጫውን መቀየር የሚችል የጦር ጄት እንደሆነም ይነገርለታል። ይህም በሚተኮሱበትን የአየር መሣሪያዎች በቀላሉ ዒላማ እንዳይደረግ ያግዘዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎቹን የተረከቡት ሁለቱ አገራት ከተስማሙበት ጊዜ ከአንድ ዓመት አስቀድሞ መሆኑን ተናግረዋል።
አክለውም "ፕሬዝዳንት ፑቲን አውሮፕላኖቹን እንድንረከብ ስላሳዩት ትጋት" አመስግነዋል። "ፑቲን ኢትዮጵያን ይወዳሉ፣ ኢትዮጵያን ማገዝ ይፈልጋሉ" ሲሉም ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እንደገለጹት ኢትዮጵያ በቀጣይ አራት ኤስ-400 (S-400) የአየር መከላከያ ሥርዓት ባትሪዎችን ትረከባለች።
እነዚህ ጄቶች ለኢትዮጵያ አየር ኃይል ምን ማለት ናቸው?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሞስኮ ባደረጉት ንግግር፤ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የብሪክስ ጉባዔ በሕንድ ሲካሄድ መሣሪያዎቹ ከተያዘላቸው ጊዜ ቀድመው ለኢትዮጵያ እንዲደርሱ አዝዘዋል።
የጦር መሣሪያዎቹ "ለኢትዮጵያ በጣም ትርጉም ያላቸው ናቸው" ሲሉም ገልጸዋል።
"በብዙ አገራት ለምናየው ምስቅልቅል፣ በሰላሙ ጊዜ መደረግ የሚገባውን ዝግጅት ካለማድረግ ችግር ሲፈጠር አገራት ተጋላጭ ይሆናሉ ብለዋል።
የወታደራዊ ኢንተለጀንስ ባለሙያ የሆኑት ቃለአብ ስጋቱ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ተጨማሪ የጦር አውሮፕላኖች ማግኘቷ የአየር ኃይሏን አቅም በማጎልበት ራሷን ለመከላከል ቁልፍ መሳሪያዎች ናቸው ይላሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሩሲያ እንደተረከቡ የጠቀሷቸው እነዚህ ሱ-35 እና ለወደፊት የሚረከቧቸው ኤስ-400 የተባሉት ተዋጊ ጄቶች እና የአየር መከላከያ ሥርዓቶች "ኢትዮጵያ ከአገር ውስጥ ግጭቶች ባለፈ ከሌሎች አገራት ጋር ሊደረጉ ለሚችሉ ጦርነቶች ጭምር እየተዘጋጀት መሆኑን" አመላካች መሆናቸውን ዶ/ር ቃለአብ ይናገራሉ።
አክለውም እነዚህ ጄቶች እና መከላከያዎች የአየር የበላይነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም ረዥም ርቀት መቃኘት የሚችሉ ራዳር ያላቸው በመሆኑ፣ ሰፊ ቦታዎችን የሚመለከቱ፣ ከፍተኛ የመንቀሳቀስ ብቃት ያላቸው መሣሪያዎች መሆናቸውን አመለክተዋል።
ተዋጊ ጄቶቹ እና የአየር መከላከያ ሥርዓቶቹ በአንድ ላይ ሲቀናጁ "ቁልፍ የሆነ ስትራቴጂክ የአየር የበላይነትን በማስገኘት ታላላቅ ከተሞችን፣ የሕዳሴ ግድብን የመሳሰሉ ወሳኝ መሠረተ ልማቶችን ለመጠበቅ እና ለመከላከል ትልቅ አቅም ይፈጥራሉ" በማለት ዶ/ር ቃለአብ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የጦር መሣሪያዎቹን የተረከበችው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ካገረሸ ከሳምንታት በኋላ ነው።
ከጎረቤት አገር ኤርትራ ጋር ጦርነት ሊነሳ እንደሚችል ስጋትም ያለ ሲሆን፤ ሩሲያ ሁለቱን አገራት ለማሸማገል ጥያቄ አቅርባለች።
"ኢትዮጵያ በጠላት የተከበበች አገር ናት" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተደምጠዋል።
"ልጆቻችን አገር እንዲኖራቸው፣ የአየር ክልላችን እንዳይደፈር በቂ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅብናል" ብለዋል።
ሱ-35 "በዓለም ምርጡ" የሚባለውን የዘመኑን ቴክኖሎጂ የታጠቀ የጦር አውሮፕላን መሆኑን ተናግረዋል።
ሱ-35 በአየር ላይ በሚደረጉ ውጊያዎች እና ከአየር ወደ የብስ በሚደረግ ውጊያም አገልግሎት ይሰጣል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ "በተለይ ክሩዝ ሚሳዔል ኢንተርሴፕት [የማምከን] አቅሙ የተረጋገጠ ነው" ብለዋል።
ክሩዝ ሚሳኤል ከየትኛውም አቅጣጫ ቢላክ እስከ 200 ኪሎሜትር አነፍንፎ የማምከን አቅም እንዳለው ተናገረዋል።
"ይህን አቅም ካልገነባን በእኛ አካባቢ እንደ አገር ኅልውናን ማስጠበቅ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው" ብለዋል።
እነዚህን ተዋጊ ጄቶችን ለመጠቀምም ኢትዮጵያ ባለሙያዎችን ስታሠለጥን እንደቆየች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ አሁን የታጠቀችው ሱ-30 እና ከሩሲያ የተረከበችው ሱ-35 "በበቂ ደረጃ የአየር ክልሏን ለመከላከል" እንደሚያግዙ በንግግራቸው ጠቅሰዋል።
"በቂ ዝግጅት ያላቸው አገራት በቀላሉ አይደፈሩም። መዘጋጀት ውጊያን ያስቀራል። ያልተዘጋጀ ሰው ውጊያ ይጋብዛል" ሲሉም ያለውን ወታደራዊ ዝግጅት ገልጸዋል።
"ራቅ ካለ አካባቢ የሚቃጣ ማንኛውም ሙከራዎች ካሉ ለመግታት" እንደሚያግዝ በንግግራቸው ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ኤርትራ፣ ግብፅ እና ሱዳንን ታጣቂ ኃይሎች በመደገፍ በተደጋጋሚ ከስሳለች። ሦስቱን አገራት ይህንን አስተባብለዋል።
በተለይም የኤርትራ ወታደሮች ወደ ኢትዮጵያ ግዛቶች መግባታቸውን ተከትሎ ሁለቱ አገራት ወደ ጦርነት ሊገቡ ይችላል የሚል ስጋት ተፈጥሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢትዮጵያ ከሩሲያ ስለተረከበቻቸው የጦር መሣሪያዎች ሲገልጹ "በዚህ ፊልድ [ዘርፍ] ላሉ ሰዎች ትልቅ ብስራት፣ ትልቅ ዜና ነው" በማለት ነው የገለጹት።
"የምንገነባው አቅም በዓመታት ውስጥ ተደምሮ ኢትዮጵያን ከጉድ ሲያወጣ፣ ኢትዮጵያን ከአጓጉል የውጊያ ፍላጎቶች ሲከላከል በተግባር እናያለን" ብለዋል።
በሚቀጥሉት ዓመታትም አገሪቱ በብዙ መልኩ "የመከላክለ አቅሟን" እንደምትገነባ ጠቅሰውም "እንደ ከዚህ ቀደሙ በልመና፣ በችሮታ የምንጎናጸፈው የሉዓላዊነት ጉዳይ አይኖርም" ሲሉ ተደምጠዋል።
ኢትዮጵያ ኤስ-400 ስትረከብ እና ሱ-35 ተዋጊ ጄቶች "በተሟላ አቅም" አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ ክሩዝ ሚሳዔል እና ባለስቲክ ሚሳዔል የማምከን አቅም "በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያድግ" ጠቅላይ ሚኒስሩ ጠቅሰዋል።
"ኢትዮጵያ የማጥቃት ብቻ ሳይሆን የመከላከል አቅም በጣም ማሳደግ ይኖርባታል" ያሉት ዐቢይ የኢትዮጵያ አየር ኃይልን "እንኳን ደስ አላችሁ" ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል አቅም ምን ይመስላል
የአገራትን ወታደራዊ አቅም የሚያወዳድረው ግሎባል ፋየርፓወር በአውሮፓውያኑ 2026 በወታደራዊ ኃይል ኢትዮጵያን ከ145 አገራት መካከል በ47ኛ ቦታ አስቀምጧታል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ካሉ ጠንካራ ወታደራዊ ኃይል ካላቸው አገራት መካከል እንደምትገኝ ተገልጿል።
ኢትዮጵያ ከግብፅ፣ ከአልጄሪያ፣ ከናይጄሪያ እና ከደቡብ አፍሪካ ቀጥላ አምስተኛ ጠንካራ ወታደራዊ ኃይል ያላት አገር ተብላለች።
ሪፖርቱ እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ ከ500 ሺህ በላይ ወታደሮች ያሏት ሲሆን፣ ብዙ ታንኮች፣ የመድፍ መሣሪያዎች እና የጦር አውሮፕላኖችም አሏት።
ግሎባል ፋየርፓወር ለአገራት በሚሰጠው የኃይል ምዘና ነጥብ ላይ ለኢትዮጵያ 0.8525 ተሰጥቷል።
እጅግ በጣም ጠንካራ ተደርጎ የሚወሰደው ነጥብ 0.0000 ሲሆን፤ በዝርዝሩ በአንደኛነት የተቀመጠችው አሜሪካን እንደ ማነጻጸሪያ ብንወስድ የተሰጣት ነጥብ 0.0741 ነው።
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በዝርዝሩ ከነበራት ሥፍራ ከፍ ያለች ሲሆን፤ ያለው አጠቃላይ የአየር ኃይል አውሮፕላኖች መጠን (Aircraft Total) 104 (ከ145 አገራት 66ኛ) መሆኑ ተመልክቷል።
አሁን ኢትዮጵያ ከሩሲያ እንደተረከበቻቸው የተነገረላቸው እጅግ ዘመናዊ የጦር ጄቶች በአየር ኃይሏ ውስጥ ሲካተቱ የወታደራዊ አቅሟን በከፍተኛ ሁኔታ ከፍ ስለሚያደርጉት በአፍሪካም ሆነ በዓለም የሚኖራት የግሎባል ፋየር ፓወር ደረጃን የሚለውጠው ይሆናል።
ግሎባል ፋየርፓወር ባስቀመጣቸው በእያንዳንዱ ዝርዝሮች ላይ ዝግጁነትን (Readiness) ይመዝናል።
ዝግጁነት የሚለካው ከአሜሪካ አየር ኃይል 75% አማካኝ ነጥብ አንጻር እንደሆነ ድረ ገጹ ይጠቁማል። ይህም አጠቃላይ የሠራዊት ዝግጁነት፣ የመሣሪያ ዘመናዊነት፣ የመሣሪያ እድሳት እና የመሳሰሉትን ያካትታል።
አገሪቱ ካላት አጠቃላይ የአየር መሣሪያ አንጻር እያንዳንዱ ዓይነት ምን ያህሉን ድርሻ እንደሚሸፍን ለመጠቆም በመቶኛ ተሰልቶ ተቀምጧል።
በእያንዳንዱ መስፈርት ኢትዮጵያ ከ145 አገራት ጋር ተወዳድራም ነጥብ ተሰጥቷታል።
- ተዋጊ አውሮፕላኖች (Fighters) - 25 (24.0%) ሲሆን፤ ዝግጁነት 15 ነው። በዚህም 46ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
- ጥቃት ፈጻሚ አውሮፕላኖች ዓይነት (Attack Types)- 0
- አውሮፕላኖች እና ሰው አልባ አውሮፕላኖችን (ድሮኖች) ጨምሮ ሌሎችም የአየር መሣሪያዎች (Transport/Fixed-wing)- 9 (8.7%) ሲሆን፤ ዝግጁነት 5 ነው። በዚህም 42ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
- የተዋጊዎች ማሠልጠኛ አውሮፕላኖች (Trainers)- 34 (32.7%) ሲሆን፤ ዝግጁነት 20 ነው። በዚህም 48ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
- ልዩ ተልዕኮ የሚፈጽሙ አውሮፕላኖች (Special Mission)- 0
- አውሮፕላኖች ነዳጅ ጫኝ/አመላላሽ (Tanker Fleet) - 0
- ሄሊኮፕተሮች (Helicopters) - 33 (31.7%) ሲሆን፤ ዝግጁነት 20 ነው። በዚህም 67ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
- ጥቃት የሚፈጽሙ ሄሊኮፕተሮች (Attack Helicopters) - 7 (6.7%) ሲሆን፤ ዝግጁነት 4 ነው። በዚህም 38ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
የግሎባል ፋየርፓወር መመዘኛ የወታደራዊ አቅምን ለመለካት የሰው ኃይል፣ መሣሪያ፣ የፋይናንስ አቅም፣ ሎጂስቲክስ እና የአገሮችን መልክዓ ምድራዊ ሁኔታ ጨምሮ ከ60 በላይ መለኪያዎችን ይጠቀማል።