ቀጥታ , የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ከኢራን ከፍተኛ የደኅንነት ባለሥልጣን ጋር ተገናኝተው ሊወያዩ እንደሚችሉ ተዘገበ

የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ከኢራን ብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ከፍተኛ የደኅንነት ባለሥልጣን ሞሄሲን ራይዚ ጋር በአካል ተገናኝተው መወያየት የሚችሉበትን ዕድል እየተመለከቱ መሆኑን ዎል ስትሪት ጆርናል ዘገበ።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ስፔን በኮከናት ውስጥ ተደብቆ ሊገባ የነበረ 2600 ኪሎ ግራም ኮኬይን መያዟን አስታወቀች

    የስፔን ባለሥልጣናት ከጋና በተላከ የኮኮናት ጭነት ውስጥ ተደብቆ የነበረ 2600 ኪሎ ግራም ኮኬይን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን አስታወቁ። ይህ በቁጥጥር ስር የዋለው አደንዛዥ ዕፅ ረቡዕ ዕለት በስፔን የግብር ኤጀንሲ እና በሲቪል ጥበቃ ይፋ ተደርጓል።

    እንደ ሁለቱ ተቋማት ገለጻ፣ አደንዛዥ ዕፁ እንደ አውሮጳውያኑ አቆጣጠር ነሐሴ 2 /2016 በቴማ ወደብ ተጭኖ ነሐሴ 22 ቫሌንሲያ ወደብ በደረሱ ሁለት ኮንቴይነሮች ውስጥ ተደብቆ ነበር።

    ኮንቴይነሮቹ ከፍተኛ ስጋት ያለባቸው ተብለው በመለየታቸው ለፍተሻ መመረጣቸውን ኤጀንሲዎቹ ገልጸዋል።

    ባለሥልጣናት፣ ኮኮናቶቹንለመያዝ በተዘጋጁት የእንጨት ሳጥኖች ውስጥ በተገጠሙ ሐሰተኛ መደቦች ስር ኮኬይኑ ተጠቅጥቆ እንደተገኘ ተናግረዋል።

    ተቋማቱ እንዳሉት ግለሰቦቹ የታሰሩት ዕቃዎቹን ወደ አገር ውስጥከማስገባትና ከማራገፍ ጋር በተያያዘ ነው። የግለሰቦቹ ማንነት ግን አልተገለጸም።

    የስፔን ባለሥልጣናት ኮኬይኑበሳጥኖቹ ውስጥ የት ቦታ ላይ እንደተቀመጠም ሆነ ከጭነቱ ጋር በተያያዘ በጋና ውስጥ የተያዘ ሰው ስለመኖሩ የገለጹት ነገር የለም።

    በቫሌንሲያ የተያዘው ይህ ዕፅ፣ ከጋና ጋር ግንኙነት ባላቸው ጭነቶች ላይ በአውሮፓ እና በመካከለኛው ምሥራቅ በተከታታይከተያዙት ከፍተኛ መጠን ያላቸው አደንዛዥ ዕፆች መካከል ነው።

    ባለፈው መስከረም ወር የፈረንሳይ ጉምሩክ በደንከርክ ወደብ ወደ 3.9 ቶን የሚጠጋ ኮኬይን በቁጥጥር ስር አውሏል። በገበያ ላይ 225 ሚሊዮን ዩሮ ይገመታል የተባለው ይህ አደንዛዥ ዕፅ፣ ከጋና የመጣ የፕላስቲክ ቆሻሻ ተብሎ በተመዘገበ ኮንቴይነር ውስጥ ተደብቆ የተገኘ ነበር።

    በቀጣናው አንዳንድ አካባቢዎች ያለውን የላላ የድንበር ቁጥጥር እና ደካማ የሕግ ማስከበር ስርዓት በመጠቀም የወንጀል ቡድኖች ወደ አውሮፓ ለሚላክ ኮኬይን ምዕራብ አፍሪካን እንደ መሸጋገሪያ መስመር እየተጠቀሙባት ይገኛሉ።

  2. ማንችስተር ዩናይትድ ማይክል ካሪክን አሰናበተ

    የእንግሊዙ ክለብ ማንችስተር ዩናይትድ ዋና አሰልጣኝ ማይክል ካሪክን ማሰናበቱን አስታውቋል።

    ማይክል ካሪክ ባለፈው ዓመት የሩበን አሞሪምን መሰናበት ተከትሎ ክለቡን በጊዜያዊነት ተረክበው ውጤታማ የውድድር ዓመት አሳልፈዋል።

    ክለቡን የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ እንዲሆንም አስችለዋል። ይህንን ተከትሎ የዘንድሮው የውድድር ዓመት ከመጀመሩ በፊት ካሪክን በዋና አሰልጣኝነት አስፈርሟቸው ነበር።

    ነገር ግን ባለፈው ዓመት ያስመዘገቡት ውጤት ዘንድሮ ሊመጣ አልቻለም። እስካሁን 10 ጨዋታዎችን አድርገው ማሸነፍ የቻሉት አንድ ብቻ ነው።

    አምስቱን አቻ በመለያየት በአራቱ ተሸንፈዋል። ይህም ክለቡን ወራጅ ቀጠና ውስጥ 18ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጦታል። በውጤቱ ደስተኛ ያልሆኑት የክለቡ አመራሮች ካሪክን ከዋና አሰልጣኝነት ማንሳታቸውን አስታውቀዋል።

    ካሪክን በመተካት የቀድሞው የቶትንሃም እና ቼልሲ አሰልጣኝ ማውሪሲዮ ፖቺቲኖ እንደሚሾሙ እየተነገረ ነው። ፖቺቲኖ በአሁኑ ወቅት የአሜሪካ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ናቸው።

  3. በኡጋንዳ የሞቱ አራት ተማሪዎች ተመርዘው ሊሆን ይችላል በሚል ፖሊስ ምርመራ ጀመረ

    በኡጋንዳ መዲና ካምፓላ አራት ተማሪዎች መሞታቸውን ተከትሎ ፖሊስ ምርመራ መክፈቱን አስታወቀ።

    ተማሪዎቹ ተመርዘው ሊሆን ይችላል በሚል ምርመራው እየተካሄደ መሆኑ ተገልጿል።

    አራቱ ሴት ተማሪዎች ዕድሜያቸው ከዘጠኝ እስከ 11 ዓመት ይሆናል። ከተማሪዎቹ መካከል ሦስቱ የሞቱት ቤት ከገቡ በኋላ ሲሆን አራተኛዋ ተማሪ ሆስፒታል ሕክምና እየተደረገላት ሳለ ሕይወቷ አልፏል።

    የታሊም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እና የቁርዓን ማስተማሪያ ማዕከል በምርመራው ድጋፍ እንደሚሰጥ አስታውቋል።

    ስምንት ተማሪዎች ሌላ ተማሪ የሰጠቻቸውን ብርቱካን መመገባቸው ተገልጿል።

    የሞቱትን አራት ተማሪዎች ጨምሮ በአጠቃላይ አምስት ተማሪዎች እንዳስመለሳቸው የተገለጸ ሲሆን፤ አምስተኛዋ ተማሪ ሆስፒታል ገብታለች።

    የሞቱት ተማሪዎች ላይ የአስከሬን ምርመራ እየተካሄደ ይገኛል።

    የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን የፖሊስ ቃል አቀባይን ጠቅሰው እንደዘገቡት፤ መርማሪዎች ብርቱካኑ ወደተለቀመበት መንደር ሄደዋል።

  4. የኢራንን ዛቻ ተከትሎ የአሜሪካ ግምጃ ቤት ኃላፊ ወደ ወታደራዊ ሰፈር መዘዋወራቸው ተገለጸ

    የአሜሪካ ግምጃ ቤት ኃላፊ ስኮት ባሴት፤ ከኢራን የተቃጣ ነው በተባለ ዛቻ ምክንያት ዋሽንግተን ዲሲ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ወደ ወታደራዊ ሰፈር መዘዋወራቸው ተገለጸ።

    የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት የግምጃ ቤት ኃላፊው ሕይወት ላይ የተቃጣ ዛቻ ተሰንዝሯል።

    የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ እንደዘገበው፤ ኃላፊው ከቤታቸው ወጥተው ወደ ወታደራዊ ሰፈሩ እንዲዘዋወሩ የተደረገው በዎል ስትሪት ጆርናል ላይ ምሥላቸው መውጣቱን ተከትሎ ነው።

    ሲቢኤስ በዘገባው የጠቀሳቸው ምንጭ “የግምጃ ቤት ኃላፊው ምሥል በዎል ስትሪት ጆርናል ላይ መውጣቱን ተከትሎ በጆርጅታውን የሚገኘው ቤታቸውን ትክክለኛ ሥፍራ ለማወቅ ስለሚቻል የደኅንነት ስጋቱ ተባብሷል” ብለዋል።

    ኢራን ላይ የምጣኔ ሃብት ጫና ለማሳደር ማዕቀቦች እንዲጣሉ በዋናነት ንቅናቄ ከሚያደርጉ ባለሥልጣናት ዋነኛው ናቸው።

    በግምጃ ቤት ኃላፊው ላይ የተሰነዘረው ዛቻ ምን ዓይነት እንደሆነ በዝርዝር ባይታወቅም፤ ኢራን አሜሪካውያን ባለሥልጣናትን ዒላማ የማድረግ እንቅስቃሴዋ “በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን” የዋሽንግተን የደኅንነት ክፍል አስታውቋል።

  5. በስፔን በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በተሳተፉበት የሥራ ማቆም አድማ ላይ ግጭት ተነሳ

    በስፔን፣ ባርሴሎና በተካሄደው አጠቃላይ የሥራ ማቆም አድማ ላይ ጭምብል ባጠለቁ ቡድኖች እና በፖሊስ መካከል ግጭት ተነሳ።

    በስፔን ከ14 ዓመታት በኋላ በተካሄደው አጠቃላይ የሥራ ማቆም አድማ ላይ በአሥር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተሳትፈዋል።

    የአገሪቱ ዋነኛ የሠራተኛ ማኅበራት የኑሮ ውድነት እና የቤት አቅርቦት ውስንነትን በመቃወም የሥራ ማቆም አድማ ጠርተዋል።

    በሥራ ማቆም አድማው በማድሪድ 120,000 የሚጠጉ ሰዎች በባርሴሎና ደግሞ ከ50,000 በላይ ሰዎች ተሳትፈዋል።

    በማድሪድ እና ባርሴሎና ነዋሪዎች ተቃውሟቸውን ለመግለጽ አደባባይ ወጥተዋል።

    በባርሴሎና ጭምብል ያጠለቁ ቡድኖች ቆሻሻ መጣያ ሲያቃጥሉ እና የመደብሮችን መስኮት ሲሰብሩ ታይቷል። ፖሊስ ተቃዋሚዎቹን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ ተኩሷል።

    በተቃውሞው ምክንያት የስፔን የትራንስፖርት እና ሕዝብ አገልግሎት ተስጓጉሏል።

    የሠራተኛ ማኅበሩ ዩጂቲ መሪ ፔፔ አልቫሬዝ የሥራ ማቆም አድማው በርካቶችን በማሳተፍ ስኬታማ መሆኑን ገልጸዋል።

    ሲሲ ኦኦ የተባለው ማኅበር ኃላፊ ኡናይ ሶሮዶ በሥራ ማቆም አድማው “በርካቶች” መገኘታቸውን ተናግረዋል።

    በማዕከላዊ ባርሴሎና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ፖሊሶች ተሠማርተዋል።

  6. እስራኤል በጋዛ ሆስፒታል ባደረሰችው ጥቃት ቢያንስ ስድስት ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ

    እስራኤል በደቡብ ጋዛ በሚገኘው ናስር ሆስፒታል ባለ ሕንጻ ላይ ባደረሰቸው የአየር ጥቃት ቢያንስ ስድስት ሰዎች እንደተገደሉ ተገለጸ።

    በሐማስ የሚመራው ሲቪል መከላከያ ተቋም እንደገለጸው፤ የአየር ጥቃቱ በሆስፒታሉ የቀዶ ሕክምና ክፍል ላይ ነው የደረሰው።

    ቃል አቀባዩ ማሕሙድ ባስል ለኤኤፍፒ እንደተናገሩት፤ በካሀን ዩኑስ በሚገኘው ሆስፒታል ላይ በደረሰው ጥቃት ቢያንስ 20 ሰዎች ቆስለዋል፤ ሆስፒታሉ ላይም ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል።

    በጥቃቱ ከተገደሉት መካከል የቀዶ ሕክምና ባለሙያ ይገኙበታል።

    የእስራኤል ጦር እስካሁን በይፋ ያለው ነገር የለም። ቢቢሲ ከእስራኤል መከላከያ ኃይል ምላሽ ጠይቋል።

    ቢቢሲ ከጋዛ ሰርጥ ዘገባ እንዳይሠራ በእስራኤል ታግዷል። ስለደረሰው ጥቃትም ከገለልተኛ ወገን ማጣራት አልቻለም።

    የጋዛ ሲቪል መከላከያ ተቋም በዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር ድጋፍ መልሶ የማገገም አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

    ናስር ሆስፒታል በደቡብ ጋዛ የሚገኘው ትልቁ ሆስፒታል ነው። በአውሮፓውያኑ ነሐሴ 2025 ላይ በደረሰበት ተከታታይ ጥቃት ጋዜጠኞች እና የሕክምና ባለሙያዎችን ጨምሮ ቢያንስ 20 ሰዎች ተገድለዋል።

    ያለፈው ዓመት ጥቅምት ላይ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ቢደረስም እስራኤል የምትፈጽመው የአየር ጥቃት ቀጥሏል።

  7. ለስድስት ቀናት በአውስትራሊያ ጥቅጥቅ ጫካ ውስጥ ጠፍቶ የነበረው ወጣት በሕይወት ተገኘ

    ዊልያም የተባለው የ17 ዓመት ታዳጊ በጥቅጥቅ የአውስትራሊያ ጫካ ውስጥ ለስድስት ቀናት ጠፍቶ ከቆየ በኋላ በሕይወት ተገኝቷል።

    ከጓደኛው ጋር በደን ውስጥ ሽርሽር ለማድረግ ከወጣ በኋላ መጥፋቱ የታወቀው ከቀናት በፊት ነበር።

    ዊልያም ጠፍቶ የነበረው ከምሥራቅ ሜልበርን፣ ቪክቶሪያ 180 ኪሎሜትር በሚርቅ ደን ውስጥ መሆኑ ተገልጿል።

    ሌሊት ላይ ባለው ከፍተኛ ቅዝቃዜ ምክንያት የ17 ዓመቱ ወጣት ደኅንነት አስጊ ሁኔታ ውስጥ ገብቶ ነበር።

    የፖሊስ ውሾች፣ ባሕር ጠላቂዎች እና ሔሊኮፕተሮች በመጠቀም ፍለጋ ሲካሄድ ነበር።

    ያለፈው አርብ ከተገኘ በኋላ ወደ ቤተሰቡ ተወስዷል። ጉዳት እንዳልደረሰበት እና ሕይወቱም “የተረጋጋ ሁኔታ ላይ” እንደሚገኝ ተገልጿል።

    ዊልያም ከተገኘ በኋላ ዶናት እና ውሃ ተሰጥቶት ለሕክምና ወደ ሆስፒታል ተወስዷል።

    እናቱ ኤልዛቤት ቤክሊ “የተወሰነ ጭረት ሰውነቱ ላይ ነበር” ያለች ሲሆን ከዚያ ውጭ ግን ጤናማ መሆኑን ገልጻለች።

    “ደኅና ነው። ሁሉም ነገር ሰላም ይመስላል። ጥሩ ጤና ላይ ነው የሚገኘው” ብላለች።

    “ከዚህ በኋላ ግን ከቤት የሚወጣ አይመስለኝም” ስትል እናቱ በስላቅ ተናግራለች።

    ዊልያም በሕይወት ሲገኝ ስሜታዊ ሆኖ እንደነበር ፖሊሶች ገልጸዋል።

    የቪክቶሪያ ፖሊስ “ይሄ ሁሌ የሚገጥመን ነገር አይደለም። ብዙ የሚነግረን ታሪክ እንደሚኖር አምናለሁ” ብለዋል።

  8. የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ከኢራን ከፍተኛ የደኅንነት ባለሥልጣን ጋር ተገናኝተው ሊወያዩ እንደሚችሉ ተዘገበ

    የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ከኢራን ብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ከፍተኛ የደኅንነት ባለሥልጣን ሞሄሲን ራይዚ ጋር በአካል ተገናኝተው መወያየት የሚችሉበትን ዕድል እየተመለከቱ መሆኑን ዎል ስትሪት ጆርናል ዘገበ።

    ጄዲ ቫንስ ከኢራኑ ከፍተኛ የደኅንነት ባለሥልጣን ጋር የሚገናኙ ከሆነ ጦርነቱን ለማስቆም በከፍተኛ አመራሮች ደረጃ የተደረገ ዋነኛ ውይይት ይሆናል።

    ዎል ስትሪት ጆርናል ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የአሜሪካ እና መካከለኛው ምሥራቅ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ ትናንት ረቡዕ ባወጣው ዘገባ ሁለቱ አመራሮች ሊገናኙ እንደሚችሉ ጠቁሟል።

    ዘገባው እንዳተተው ከኢራን ጋር የሚደረገው ውይይት በምክትል ፕሬዝዳንቱ መሪነት እንዲቀጥል ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ መስማማታቸውን ለከፍተኛ አማካሪዎቻቸው እና ለውጭ አገራት ተወካዮች ተናግረዋል።

    የዲፕሎማሲ ጥረቱን ለመቀጠል ትራምፕ ለምክትላቸው አስፈላጊውን ሥልጣን መስጠታቸው ተገልጿል።

    የአሜሪካ ባለሥልጣናት እንዳሉት ጄዲ ቫንስ ከኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣን ጋር በአካል የመገናኘታቸው ጉዳይ ገና በጅምር ያለ ሲሆን የሚገናኙበት ቀንም አልተወሰነም።

    የኢራን ብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ጸሐፊ የሆኑት ሞሄሲን ራይዚ ከዚህ ቀደም የአገሪቱ እስላማዊ አብዮታዊ ዘብን መርተዋል።

    ያለፈው ጥቅምት ላይ በተላከ ደብዳቤ ቫንስ ከራይዚ ጋር ለመወያየት ጥያቄ ማቅረባቸውን የዎል ስትሪት ጆርናል ዘገባ ይጠቁማል።

    ሁለቱ ወገኖች በአሸማጋዮች እና ቀጣናዊ አጋሮች በኩል ንግግር መቀጠላቸውም ተዘግቧል።

    ቀጣዩ ዙር ውይይት በኳታር ሊከናወን ይችላል። የቀጣናው አገራት መተማመኛ ለመስጠት ምክረ ሐሳቦች ማቅረባቸውን የዎል ስትሪት ጆርናል ዘገባ ይጠቁማል።

    ከቀረቡት ሐሳቦች መካከል የአሜሪካ የጦር መርከቦችን ማስወጣት እና ኢራን ላይ የተጣሉ ማዕቀቦችን ማላላት ይጠቀሳሉ።

    ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ከፈቀደች በምላሹ ማዕቀቦች እንዲላሉላት ሐሳብ ቀርቧል።

    በእነዚህ ምክረ ሐሳቦች ላይ እስካሁን ከስምምነት አልተደረሰም።

  9. የኅዳር 3 ቀን 2019 ዓ. ም. የቀጥታ ስርጭት ተጀምሯል

    የቢቢሲ አማርኛ ወዳጆች እንደምን አደራችሁ፤ የኅዳር 3 ቀን 2019 ዓ. ም. የቀጥታ ስርጭታችን ተጀምሯል።

    የአገር ውስጥ እና የውጭ ዜናዎችን በአጭሩ እናቀርብላችኋለን። አብራችሁን እንድትቆዩ በአክብሮት እንጋብዛለን።

  10. በኬንያ ከኢቦላ ቫይረስ ያገገመው የመጨረሻው ታካሚ ከሆስፒታል ወጣ

    በኬንያ በኢቦላ ቡንዲቡግዮ ቫይረስ ያገገመው የመጨረሻ ታካሚ ከሆስፒታል ወጣ።

    ይህም በምሥራቅ አፍሪካዊቷ አገር በሽታውን ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት ወሳኝ እርምጃ ተደርጎ ተወስዷል።

    ይህንንም ተከትሎ ባለሥልጣናት አገሪቷ ከቫይረሱ ነጻ መሆኗን ለማወጅ የሚያስችላትን 42 ቀናት መቁጠር ጀምረዋል።

    በአገሪቷ በቫይረሱ የተያዘው የመጀመሪያው ግለሰብ የተገኘው ጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ ነበር። ኬንያዊው ነጋዴ በመዲናዋ ናይሮቢ በገባ በቀናት ውስጥ ነበር ሕይወቱ ያለፈው።

    ግለሰቡ በበሽታው የተያዘው ግንቦት ወር ላይ በሽታው ከተከሰተባት ወዲህ ከአምስት ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ በሞቱባት ዲሞክራቲ ክሪፐብሊ ኮንጎ ነው።

    ከግለሰቡ ጋር ንክኪ ያላቸው 135 ግለሰቦች መለየታቸውን እና እነዚህ ግለሰቦች ለ21 ቀናት ለይቶ ማቆያ ውስጥ መቆየታቸውን የኬንያ የጤና ሚኒስትር አደን ዱዋል ገልጸዋል።

    በኬንያ በአጠቃላይ ሰባት ሰዎች በበሽታው መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን ሦስቱ የመጀመሪያውን የኢቦላ ታማሚ ያከሙ የጤና ባለሙያዎች ነበሩ።

    የጤና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው አሁን ላይ ሁሉም ከበሽታው ያገገሙ ሲሆን ሌሎቹ የተጠረጠሩ ግለሰቦችም ክትትላቸውን አጠናቀዋል።

    የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (ሲዲሲ) ይህ ቀጣናው ለበሽታው እየሰጠ ላለው ምላሽ ትልቅ ስኬት ነው ብሎታል።

    ተያያዥ ዜና፡

  11. የቡድን 7 አገራት የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ውጥረት ወደ ቀጣናዊ ግጭት ሊያመራ እንደሚችል አስጠነቀቁ

    የቡድን 7 አገራት ባወጡት የጋራ መግለጫ፣ በአፍሪካ ቀንድ በተለይም በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል እየተባባሰ የመጣው የፀጥታ ሁኔታ በከፍተኛ መጠን እንዳሳሰባቸው ገለፁ።

    የቡድኑ አባል አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ላለፉት ሁለት ቀናት በፓሪስ ያካሔዱትን ስብሰባ ተከትሎ ዛሬ ህዳር 2/2019 ዓ.ም. ባወጡት የጋራ መግለጫቸው፣ “በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያለው ውጥረት ከድንበር ተሻጋሪ ግጭቶች መጨመር ጋር ተዳምሮ ወደ ሰፋ ቀጣናዊ ግጭት ሊያመራ የሚችል አደጋ አለው” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

    በቡድኑ ውስጥ ከተካተቱት የዓለማችን 7 የበለፀጉ አገራት፡ ካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ጃፓን፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በተጨማሪ የአውሮፓ ኅብረት ከፍተኛ ተወካይም ለሁለት ቀናት በተካሔደው ስብሰባ ላይ ተሳትፈዋል።

    የጋራ መግለጫው፣ አሁን ያለው የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ሁኔታ ይበልጥ ተባብሶ መቀጠሉ ወትሮውንም በቀውሶች በተሞላው የቀጣናው መረጋጋት ላይ ከባድ መዘዝ ሊያስከትል እንደሚችል አጽንኦት ሰጥቷል።

    ቀድሞውኑም አሳሳቢ በሆኑት የአፍሪካ ቀንድ የሰብአዊ ቀውሶች እና የፀጥታ ሁኔታ ላይ እንዲሁም በቀይ ባሕር ዓለም አቀፍ የንግድ መስመሮች ላይ ተፅዕኖው የከፋ እንደሚሆንም ስጋቱን ገልጿል።

    ሁሉም ወገኖች ከፍተኛ ትዕግሥት እንዲያሳዩ እና ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔዎችን እንዲከተሉ የጠየቁት የቡድን 7 አገራት፣ የሰብአዊ ዕርዳታ ደኅንነቱ ተጠብቆ ያለምንም እንቅፋት እንዲደርስ እና ሲቪሎች፣ በተለይም ሴቶችና ሕፃናት ጥበቃ እንዲደረግላቸውም ጥሪ አቅርበዋል።

    በተጨማሪም፣ በቀጣናው ያሉ ሁሉም አገራት “ሉዓላዊነታቸው፣ የፖለቲካ ነፃነታቸው እና የግዛት አንድነታቸው ሊከበር እንደሚገባ” ያላቸውን አቋም በድጋሚ ገልፀዋል።

    ውጥረቱን ለመቀነስ እና አገራቱ ወደ ውይይት እንዲመጡ ለማድረግ በተባበሩት መንግሥታት እና በአፍሪካ ኅብረት ለሚደረጉ ጥረቶች ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ በመግለጫቸው አመልክተዋል።

  12. አሜሪካ የሩሲያ እና የማዳጋስካር ወታደራዊ ግንኙነት እየተጠናከረ መምጣቱን በመቃወም አስጠነቀቀች

    አሜሪካ፣ ማዳጋስካር ከሩሲያ ጋር ያላት ግንኙነት እየተጠናከረ መምጣቱ አለመረጋጋት ሊያስከትል ይችላል ስትል አስጠነቀቀች።

    አገሪቷ ማስጠንቀቂያውን የሰጠችው በምዕራብ አፍሪካ በወታደራዊ ሥርዓት ከሚመራ መንግሥት ጋር የተደረጉ ተመሳሳይ ትብብሮች የጸጥታ ሁኔታን ማሻሻል አልቻሉም በማለት ነው።

    የአሜሪካ የአፍሪካ ዕዝ ምክትል ኃላፊ ሌተናንት ጀነራል ጆን ብሬናን እንደተናገሩት ማዳጋስካር በሕንድ ውቅያኖስ ያላት ስትራቴጂያዊ መገኛ ለዓለም ንግድ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው።

    በመሆኑም “'የሳህል ሞዴል' ያሉትን እና በአህጉሩ አለመረጋጋት ያስከተለውን ግንኙነት” በመቃወም አስጠንቅቀዋል።

    የሳህል አገራቱ ማሊ፣ ቡርኪና ፋሶ እና ኒጀር በወታደራዊ ሥርዓት የሚተዳደሩ ሲሆን ከምዕራባውያን ጋር ያላቸውን ግንኙነት ቀንሰዋል።

    አገራቱ ጂሃዳዊ ቡድኖችን ለመዋጋት የሚያስችላቸውን ድጋፍ ለማግኘት ፊታቸውን ወደ ሩሲያ አዙረዋል።

    ሩሲያም የማዳጋስካር ጦር እአአ በ2025 ሥልጣን ከተቆጣጠረ ጀምሮ ትብብሯን እያስፋፋች ሲሆን የጦር መሣሪያዎች እና ወታደራዊ አሰልጣኞችን እያቀረበች ነው።

    ጄነራል ብሬናን ለጋዜጠኞች በተናገሩበት ወቅት “ሩሲያ 'የሳህል ሞዴል' በአህጉሩ የተለያዩ ቦታዎች ለማስፋፋት መሞከሯ አሳስቦናል” ሲሉ ይህን ሞዴል በማዳጋስካር እና በሞዛምቢክ ማየት እንደማይፈልጉ ተናግረዋል።

    ጄነራል ብሬናን ማዳጋስካርን እና ሞዛምቢክን ከተቀረው የአፍሪካ ክፍል የሚለየው እና ለዓለም የመርከቦች እንቅስቃሴ እና ለንግድ ወሳኝ የሆነው ሞዛምቢክ ቻነል ደኅንነት ላይ ያላቸውን ስጋትም አንስተዋል።

    “አገራቱ ከፈለጉት ጋር ግንኙነት መመስረት ቢችሉም፣ ሊኖረው የሚችለውን አደጋ መረዳት አለባቸው” ሲሉ አሳስበዋል።

    ማዳጋስካር ለጄነራሉ አስተያየት በይፋ የሰጠችው ምላሽ የለም።

    ሆኖም ፕሬዚደንት ሚካኤል ራንድሪያኒሪና በቅርቡ በሩሲያ እና በአፍሪካ አገራት መካከል የሚኖረውን ጠንካራ ግንኙነት እንደሚደግፉ ገልጸዋል።

    ባለፈው ወር በተካሄደው የሩሲያ አፍሪካ ጉባዔ ወቅትም ማዳጋስካር እና ሩሲያ መከላከያን፣ ቱሪዝምን እና ንግድን የሚያካትት በርካታ የትብብር ስምምነቶችን ተፈራርመዋል።

    የካቲት ወር ላይም ራንደሪያኒሪና ሥልጣን ከያዙ ከጥቂት ወራት በኋላ ሞስኮን ጎብኝተዋል። በ50 ዓመታት ውስጥ የማዳጋስካር መሪ በሩሲያ ይፋዊ ጉብኝት ሲያደርግም ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር።

    • ተያያዥ ዜና፡
  13. አቶ ጌታቸው ረዳ ኤርትራ እና ሱዳን በኢትዮጵያ በሚፈጸሙ “ተከታታይ የድሮን ጥቃቶች” እጃቸው አለበት በማለት ወነጀሉ

    አቶ ጌታቸው ረዳ ኤርትራ እና ሱዳን በኢትዮጵያ በሚፈጸሙ “ተከታታይ የድሮን ጥቃቶች” እጃቸው እንዳለበት በመግለጽ ወነጀሉ።

    አቶ ጌታቸው ከተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ አምባሳደር ጉዋንግ ኮንግ ጋር ባደረጉት ውይይት፤ የኤርትራ እና የሱዳን መሪዎች በኢትዮጵያ “አፍራሽ ኃይሎች” ያሏቸውን አማጺያን “መሣሪያ እየሰጡ፣ እያስታጠቁ እና እያስተባበሩ” መሆኑን ማንሳታቸውን ገልጸዋል።

    ፕሬዝዳንት ኢሳያስ እና ጄነራል ቡርሀን በኢትዮጵያ ያሉ አማጺያንን በመሣሪያ እንደሚደግፉ ጠቅሰው ይህም “በኢትዮጵያ ተከታታይ የድሮን ጥቃቶችን መፈጸምን ያካትታል” ብለዋል።

    የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ አቶ ጌታቸው በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ከተመድ ልዩ ልዑክ ጋር የተወያዩባቸውን ቀጣናዊ ጉዳዮች ዘርዝረዋል።

    ውይይታቸው በሱዳን ያለውን ግጭት እና ሶማሊያንም የተመለከተ መሆኑን ጠቅሰዋል።

    “በዋናነትም የአሥመራ መንግሥት በቀጣናው ስላለው አፍራሽ ሚና” በውይይታቸው ማንሳታቸውን አቶ ጌታቸው አመልክተዋል። በሱዳን ያለውን ውጥረት ለማርገብ “ምን አማራጮች እንዳሉ” በውይይቱ መነሳቱን አክለዋል።

    አቶ ጌታቸው እንደተናገሩት የኤርትራ መንግሥት ያለውን “አለመረጋጋት የመፍጠር ሚና በተመለከተ” የኢትዮጵያን አቋም ለልዩ ልዑኩ አስታውቀዋል።

    ኤርትራ እና ሱዳን አማጺያን ቡድኖችን “ከመደገፍ እና መሣሪያ ማስታጠቅ” እንዲቆጠቡ ኢትዮጵያ እንደምታሳስብ ለተመዱ ልዩ ልዑክ መግለጻቸውን ተናግረዋል።

    “መካረር እና ውጥረት እንዳይባባስ ለማድረግ” ትርጉም ያለው ውይይት የሚካሄድ ከሆነ አማጺያንን “መደገፍ ማቆም” እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

    አቶ ጌታቸው እና የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ አምባሳደር ጉዋንግ ኮንግ “ከመተኮስ ይልቅ መነጋገር መፍትሔ መሆኑን እንደተስማሙበት” በጽሑፋቸው አመልክተዋል።

    ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደምም ኤርትራ እና ሱዳንን በኢትዮጵያ አማጺያንን በመደገፍ ከስሳለች። ሁለቱም አገራት ይህንን ውንጀላ አስተባብለዋል።

    የኢትዮጵያ እና ኤርትራ የዲፕሎማሲ ግንኙነት የተቋረጠ ሲሆን፤ ሱዳን እና ኢትዮጵያ አንዳቸው የሌላቻውን አምባሳደሮች ማባረራቸውም ይታወሳል።

    • ተጨማሪ ዜናዎች
  14. በጉራጌ ዞን የሞተ ግለሰብን ለማውጣት ወደ ጉድጓድ የገባ ሰው ባልታወቀ ምክንያት ሕይወቱ አለፈ

    በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ ዞን የውሃ ጉድጓድ ለመቆፈር ከገባ በኋላ የሞተ ግለሰብን ለማውጣት ወደ ጉድጓዱ የገባ ሁለተኛ ሰው ሕይወቱ ማለፉን የአረቅጥ ከተማ ፖሊስ ፅህፈት ቤት ገለጸ።

    በተመሳሳይ ጉድጓድ ውስጥ ሕይወታቸው ያለፈው ሁለቱ ሰዎች ለሞት ያበቃቸው ምክንያት ምንነት መነጋገሪያ ሆኗል።

    የከተማዋ ፖሊስ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ዋና ሳጅን አክመል ሺፋ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ ጥቅምት 27/2019 ዓ.ም. እየቆፈረ የነበረው የመጀመሪያው ሰው ሕይወቱ ያለፈው ጉድጓዱ ውስጥ ቁጭ እንዳለ ነው።

    የ50 ዓመቱ መክብብ ገብሬ የአራት ልጆች አባት እንደነበረ ገልጸዋል። ፖሊስ አዛዡ እንደሚያስረዱት፣ ስድስት ሜትር ገደማ ጥልቀት ወዳለው ጉድጓድ በገመድ ተይዞ የገባው መክብብ፣ ውስጥ ከወረደ ከቆይታ በኋላ “ወደ ታች ተንሸራቶ ተቀምጦ” ቀርቷል።

    አብሮት በስራ ላይ የነበረ አጋዡ ሟቹን ሲጠራው ምላሽ ሳያገኝ በመቅረቱ ለአካባቢው ነዋሪዎች እና ለፖሊስ ጥቆማ ተሰጥቷል።

    ፖሊስ ከመጣ በኋላም የሟች ጓደኛ የሆነው የ35 ዓመቱ ታምሩ አርጋ ወደ ጉድጓዱ ገብቶ አስከሬኑን ለማውጣት ፈቃደኛ መሆኑን ዋና ሳጅን አክመል ተናግረዋል።

    ዋና አዛዡ የሁለተኛው ግለሰብ አሟሟት ሲያስረዱ፤ “ገባ አስክሬኑ ጋር ደረሰ፣ አስክሬኑ አሳዘነው እና አቅፎ ሳመው፣ አቅፎ እያለቀሰ እያለ እሱም ማንቀጥቀጥ ጀመረው። ትንሽ እንደቆየ ከግድግዳ ተደግፎ ሁለት ደቂቃ ሳይሞላው ሕይወቱ አለፈ” ብለዋል።

    ሁለተኛውም ሰው ሕይወቱ ካለፈ በኋላ፣ አስከሬኖቹን ለማውጣት ሌላ ሰው ወደ ጉድጓዱ እንዳይገባ ተደርጓል። በምትኩም እንዲሸመቀቅ ተደርጎ የተዘጋጀ ገመድ አስክሬኖች አንገት ላይ በማጥለቅ በሰዉ ኃይል እየተጎተተ እንዲወጣ መደረጉን ኃላፊው አስታውቀዋል።

    አስከሬኖቹም ለቤተሰቦቻቸው ተላልፈው የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው ተፈጽሟል። ሁለቱም ሕይወታቸው ያለፈበት ምክንያት እስካሁን በትክክል አልታወቀም።

    የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ፖሊስ ኮሚሽን ስለ ጉዳዩ ባወጣው መረጃ፣ ሁኔታውን “ለማመን የሚቸግር አይነት አሟሟት” ሲል ገልጾታል። የአረቅጥ ፖሊስም እስካሁን ሁለት ሰዎችን ለሞት ያበቃው ጉዳይ ምንነት እንዳልታወቀ እና አስከሬኖቹ ላይ የሕክምና ምርመራ እንዳልተደረገ ገልጿል።

    “ብዙ ጊዜ እኛ ምርመራ የምናደርገው 'ሰው ገፋው፣ ገደለው' የሚለው ላይ ነው፣ ተገድሏል የሚል ጥርጣሬ ካለ ነው ምርመራ የምናደርገው” ሲሉ የአስከሬን ምርመራ ያልተደረገበትን ምክንያት ገልጸዋል።

    የፖሊስ ኃላፊው እንደገለጹት፣ ሁለቱም በጉድጓድ ቁፋሮ ሥራ ልምድ ያላቸው ሲሆን፣ በአካባቢው እንዲህ ያለ አደጋ ሲያጋጥም የመጀመሪያው ነው።

    በክስተቱ ላይ የግድያ ጥርጣሬ እንደሌለ ገልጸው፣ ሁለተኛው ሰው በጉድጓዱ ውስጥ ሕይወቱን ማጣቱ የመጀመሪያው ሰው ተገድሎ እንደሞተ የሚያስነሳውን ጥርጣሬ እንዳስወገደ ተናግረዋል።

    የፖሊስ ኃላፊው በጉድጓድ ቁፋሮ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች የደህንነት ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

  15. ኢራን የአርጀንቲናን የባሕር እና የአየር ኃይል “አሸባሪ ድርጅቶች” በማለት ፈረጀች

    ኢራን ረቡዕ ዕለት የአርጀንቲናን የባሕር እና የአየር ኃይሎች “አሸባሪ ድርጅቶች” በማለት ፈረጀች።

    ቴህራን እርምጃውን የወሰደችው ቦነስአይረስ የኢራንን የአብዮታዊ ዘብ እንደ አሸባሪ ድርጅት ከፈረጀች በኋላ ነው።

    በመንግሥት የሚተዳደረው ኢርና እንደዘገበው፣ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውሳኔው “የተመጣጠነ ምላሽ” ለመስጠት ያለመ እና እአአ በ2019 በፀደቀ ሕግ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ገልጿል።

    ሚኒስቴሩ አርጀንቲና፣ የኢራን ጦር ኃይል አካል የሆነውን አብዮታዊ ዘብ እንደ አሸባሪ ድርጅት በመፈረጅ መሠረታዊ የዓለም አቀፍ ሕግ መርሆችን የሚጥስ “ጠላትነት የተሞላበት” እርምጃ ወስዳለች ሲል ከሷል።

    ኢራን እአአ በ2019 ያጸደቀችው ሕግ አሜሪካ የአብዮታዊ ዘብ አሸባሪ ብላ መፈረጇን ተከትሎ ያንን የሚደግፉ ወይም የሚከተሉ አገራትን በተመሳሳይ የአጸፋ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ነው።

    በዚህ መሠረት ቴህራን የአርጀንቲናን የባሕር ኃይልና የአየር ኃይል “አሸባሪ ድርጅቶች” ብላ መፈረጇን አስታውቃለች።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአርጀንቲና መንግሥት ከዚህ ውሳኔ ተከትሎ ለሚመጡ ማንኛውም ነገሮች ኃላፊነት እንደሚወስድ አስጠንቅቋል፤ ሆኖም ዝርዝር ማብራሪያ አልሰጠም።

    አርጀንቲና እአአ ባለፈው ዓመት መጋቢት 31 አብዮታዊ ዘብን እንደ አሸባሪ ድርጅት መፈረጇን ያስታወቀች ሲሆን፣ ቡድኑ በ1990ዎቹ በቦነስ አይረስ በተፈጸሙ ሁለት የቦምብ ጥቃቶች ውስጥ ተሳትፎ አለው በሚል ክስ ውሳኔውን አስተላልፋለች።

    ኢራን በእነዚያ ጥቃቶች ውስጥ ምንም ተሳትፎ እንዳልነበራት በመግለጽ በተደጋጋሚ አስተባብላለች።

    ኢራን ከሳምንት በፊት የብሪታንያን ባሕር ኃይል እና አየር ኃይል “አሸባሪ ድርጅቶች” ያለች ሲሆን የብሪታንያን የውጭ መረጃ ተቋም የሆነውን ኤም6 ደግሞ “ጠላት ቡድን” በማለት ፈርጃለች።

  16. የአሜሪካ ገንዘብ ሚኒስትር ቤሰንት ኢራን ጥቃት ልትፈጽምባቸው ትችላለች በሚል ስጋት ወደ ወታደራዊ ጦር ሰፈር ተወሰዱ

    የአሜሪካ ገንዘብ ሚኒስትር ስኮት ቤሰንት በቅርቡ በዋሽንግተን ዲሲ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ወደ አንድ ወታደራዊ ማዘዣ መዛወራቸውን ሮይተርስ ምንጮቹን ጠቅሶ ዘገበ።

    ኃላፊው ወደ ወታደራዊ ማዘዣ የተዛወሩት ኢራን ጥቃት ልትፈጽምባቸው ትችላለች የሚለውን ስጋት ተከትሎ መሆኑን ጉዳዩን የሚያውቁ ሁለት ሰዎች ማክሰኞ ዕለት ለሮይተርስ ተናግረዋል።

    የቤሴንት ወደ ወታደራዊ ጦር ሠፈር መዛወር መጀመርያ የዘገበው ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ነው።

    ሮይተርስ ባለፈው ወር መጨረሻ የትራምፕ አስተዳደር ከፍተኛ የመረጃ ደኅንነት ባለሥልጣን ማስታወሻን ተመልክቶ እንደዘገበው ከሆነ ኢራን በአሜሪካ መንግሥት ኃላፊዎች እና በአሜሪካ ዜጎች ላይ የምታቅዳቸው ጥቃቶች ወደ ከፍተኛእና የተራቀቀ ደረጃ ደርሰዋል።

    ከነሐሴ ወር ጀምሮ የአሜሪካ ገንዘብ ሚኒስትር ስኮት ቤሰንት “ኦፕሬሽን ኢኮኖሚክ አውትካስት” በተሰኘው በኢራን ላይ የሚደረገውን የማዕቀብና የኢኮኖሚ ዘመቻ ሲመሩ ቆይተዋል።

    ዘመቻው የተጀመረው ቴህራን በመርከቦች ላይ የምትፈጽማቸውን ጥቃቶች እንድታቆም እና የሆርሙዝን ወሽመጥን ዳግም እንድትከፍት ለማስገደድ ነው። አሜሪካ እና እስራኤል ባለፈው ዓመት የካቲት 21 በኢራን ላይ ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ ይህ ወሳኝ የባሕር መተላለፊያ በአብዛኛው ዝግ ሆኖ ቆይቷል።

    ይህ የኢኮኖሚ ግፊት ዘመቻ ከአሜሪካ በኢራን ወደቦች ላይ ከምታደርገው የባሕር ከበባ ጋር ተያይዞ የሚካሄድ ሲሆን፣ ከኢራን ጋር ግብይቶችን የሚያስተባብሩ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ የባንክ ቅርንጫፎችና ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ላይም ማዕቀቦች ተጥለዋል።

    አንድ የአሜሪካ ገንዘብ መስሪያ ቤት ቃል አቀባይ በኢሜይል በላኩት መግለጫ “ሚኒስትሩ ኢራን በምትሰነዝራቸው ዛቻዎች አይሸበሩም፤ ኦፕሬሽን ኢኮኖሚክ አውትካስትን እና የባሕር ከበባውን ለማስቀጠል ቁርጠኛ ናቸው። እነዚህ እርምጃዎች በጋራ የኢራንን ኢኮኖሚ እያዳከሙ ነው” ብለዋል።

    ኒው ዮርክ ታይምስ እንደዘገበው፣ በቤሰንት ላይ የተሰነዘሩት ዛቻዎች ምን ያህል ከባድ እንደነበሩ ግልጽ አይደለም።

    ጉዳዩን የሚያውቅ ምንጭ ዎል ስትሪት ጆርናል ቤሰንት እንደ አውሮፓውያኑ በጥር 2025 የገንዘብ ሚኒስትር ሆነው ከተሾሙ በኋላ በ12.5 ሚሊዮን ዶላር የገዙትን በጆርጅታውን የሚገኘውን መኖሪያ ቤታቸውን የሚያሳይ ከአየር የተነሳ ፎቶ ካተመ በኋላ የደኅንነት ስጋታቸው ጨምሯል።

    ፎቶው የቤሰንትን መኖሪያ ሥፍራ በትክክል ለመለየት እንዳስቻለ ምንጩ ገልጿል። በዚህም ምክንያት ለደኅንነታቸው ሲባል ወደ ወታደራዊ ማዘዣ መዛወራቸውን አክሎ ጠቁሟል። “በሕዝብ ባለሥልጣናት ላይ የሚደርሱ ዛቻዎች እየጨመሩ ባሉበት ወቅት የዜና ተቋማት በኃላፊነት መንቀሳቀስ አለባቸው” ብሏል።

    ኢራን ቀደም ሲል በአሜሪካ ግዛት ውስጥ ባለሥልጣናትንም ሆነ ሌሎች ሰዎችን ለማጥቃት እያሴረች መሆኑን በመግለጽ የሚቀርቡ ውንጀላዎችን ታስተባብላለች።

    ኒው ዮርክ ታይምስ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ኢራን በአሜሪካና በሌሎች አገራት ውስጥ መጠነ ሰፊ ጥቃቶችን የመፈጸም አቅሟ ውስን መሆኑን ያምናሉ ብሏል።

  17. የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት አገራቸው ከሩሲያ ጋር እያደረገች ያለው የሰላም ውይይት ውጤታማ እንደሆነ ተናገሩ

    በዩክሬን እና በሩሲያ መካከል በአቡዳቢ እየተካሄደው ያለው የሦስትዮሽ ውይይት የመጀመርያ ቀን ውጤታማ እንደነበር ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ተናገሩ።

    ከኪየቭና ከሞስኮ የመጡ ከፍተኛ ባለሥልጣናት አራት ሰዓታት ከፈጀው ውይይት በኋላ ስለ ንግግሩ ዝምታን ቢመርጡም፣ በውይይቱ ያልተሳተፉት ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ግን ውይይቱ “ገንቢና በጣም ጥልቅ ይዘት ያለው” እንደነበር ተናግረዋል።

    ፓሪስ ያሉት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በበኩላቸው ስብሰባው “እጅግ ፍሬያማ” እንደነበረ ገልጸዋል።

    በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ለማስቆም የሚያበቃ ጉልህ ውጤት ከዚህ ውይይት ይገኛል የሚለው ተስፋ ዝቅተኛ ቢሆንም፣ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ከዚህ ቀደም ሞስኮና ኪየቭ ከጦርነቱ በኋላ የዩክሬንን ምሥራቃዊ ክልሎች ማን ይቆጣጠረው በሚለው ጉዳይ “አንዳንድ መለሳለሶች” እያሳዩ መሆኑን ገልጸው ነበር።

    ዜሌንስኪ የሰብዓዊ ጉዳዮች የጦር ምርኮኞችን እንደመለዋወጥ ያሉ ጉዳዮች ተነስተው መወያየታቸውን ተናግረዋል።

    ማክሰኞ ዕለት በሁለቱ አገራት መካከል ውይይቱ ሲጀመር የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የቤተሰብ አባል የሆኑት ጃሬድ ኩሽነር ለተሳታፊዎች ዝርዝር መረጃ ሳይሰጡ አሜሪካ በሁለቱ ወገኖች መካከል ያሉትን ልዩነቶች “ማጥበብ ችላለች” ብለዋል።

    በተጨማሪም “ጦርነቱን ያስቆማል ተብሎ የሚታሰብ መፍትሔ” ላይ ይደረሳል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።

    ኩሽነር ከዚህ ቀደም ውይይቶቹ “ከጦርነት በኋላ የደኅንነት ስጋቶችን” በመፍታት ላይ እንደሚያተኩሩ ገልጸው ነበር።

    በኋላ ላይም በኮፐንሃገን ስለ አሜሪካ ባለሥልጣናት የድርድር አቀራረብ የተጠየቁት ዜሌንስኪ “ለውጦችን እያየሁ ነው። የምሰማው ነገር በጣም አስደስቶኛል” ብለዋል።

    ጃሬድ ኩሽነር እና የትራምፕ የሰላም ልዑክ ስቲቭ ዊትኮፍ ከዋናው ስብሰባ ጎን ለጎን ከዩክሬን፣ ከአውሮፓ እና ከኔቶ ባለሥልጣናት ጋርም ተገናኝተው ተወያይተዋል።

    እስካሁን ድረስ የአውሮፓ መሪዎች ከሰላም ድርድሮቹ ውጭ ተደርገው ቆይተዋል። ሆኖም ስለ አህጉራቸው ደኅንነት የሚወሰኑ ውሳኔዎች ያለ እነርሱ ተሳትፎ እንዳይወሰኑ በመስጋታቸው በውይይቱ ውስጥ እንዲካተቱ ግፊት ሲያደርጉ ቆይተዋል።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በፓሪስ በነበራቸው ጉብኝት ወቅት አውሮፓውያን “ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የመፍትሔው አካል ናቸው” በማለት ተናግረዋል።

    ሆኖም አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን “ሩሲያውያን ከአውሮፓውያን ጋር በተያያዘ ጥሩ ልምድ የላቸውም” ብለዋል።

    የአውሮፓ ኅብረት ባለሥልጣናት የሚደግፏቸው አንዳንድ ሐሳቦች፣ ያለ ቅድመ ሁኔታ የተኩስ አቁም እንዲደረግ የሚጠይቁ ሐሳቦችን ጨምሮ በሞስኮ በተደጋጋሚ ውድቅ ይደረጋሉ።

    የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ማክሰኞ ዕለት የተኩስ አቁም ስምምነት ዩክሬን እንደገና ራሷን እንድታደራጅ ዐዕድል ይሰጣታል በማለት “ይህንን አንቀበለውም” ሲሉ ተናግረዋል።

    በአጠቃላይ ሞስኮና ኪየቭ ግጭቱን ለማቆም በሚያስችሉ ዋና ጉዳዮች ላይ አሁንም ከፍተኛ የአቋም ልዩነት አላቸው።

    ተያየዓዝ ዘገባዎች፡

  18. ጣሊያን የአውሮፓ አገራት የቀይ ባሕርን ደህንነት ለማረጋገጥ ቁርጠኛ አይደሉም ስትል ወቀሰች

    የጣሊያን መከላከያ ሚኒስትር ጉኢዶ ክሮሴቶ የአውሮፓ አገራት በቀይ ባሕር ላይ የሚቀዝፉ መርከቦች ደኅንነትን ለማጠናከር እስካሁን ተጨባጭ እርምጃ አልወሰዱም በማለት ተቹ።

    ክሮሴቶ በመስከረም ወር አውሮፓ ኅብረት እአአ በ2024 ያቋቋመውን የባሕር ጥበቃ ተልዕኮ እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበው ነበር። ተልዕኮው የተጀመረው በየመን የሚንቀሳቀሱት እና በኢራን የሚደገፉት ሁቲዎች በንግድ መርከቦች ላይ ከሚፈጽሙት ጥቃት ለመከላከል ነበር።

    ሚኒስትሩ ለሮይተርስ እንደተናገሩት “እስካሁን ተጨባጭ የሆነ ለውጥ አላየሁም” ብለዋል። ሆኖም የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ካጃ ካላስ የጣሊያንን ጥያቄ ተገቢነት ሙሉ በሙሉ እንደሚረዱ ተናግረዋል።

    ካላስ የጣሊያን መከላከያ ሚኒስትር ትችትን ተከትሎ ለ27ቱ የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት በጻፉት ደብዳቤ፣ ተልዕኮው በትክክል ውጤታማ ለመሆን ከ10 በላይ የጦር መርከቦች እንደሚያስፈልጉ ገልጸው አገራቱ አስተዋጿቸውን እንዲያሳድጉ ጠይቀዋል።

    የጣሊያን ኤል ሶሌ 24 ኦር ጋዜጣ እንደዘገበው፣ በአባል አገራቱ መካከል የሚደረገው ውይይት እስካሁን ውጤት አላመጣም። ከምክንያቶቹም አንዱ ውስን ወታደራዊ አቅም ያላቸው አንዳንድ አገራት መርከቦቻቸውን ለማሰማራት ፈቃደኛ አለመሆናቸው ነው ተብሏል።

    “የአውሮፓ ዘመቻዎች አንድ ሦስተኛ ያህሉ በጣሊያን አስተዋጾ ላይ የተመሰረቱ ናቸው። ከእኛ በጣም ትልልቅ የሆኑ አገራት ግን ከዚያ በጣም ያነሰ አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው” ሲሉ ክሮሴቶ ተናግረዋል።

    “በእነዚህ ተልዕኮዎች ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ ትክክል ከሆነ፣ ሁሉም አገራት በተመጣጣኝ ሁኔታ ማበርከት ይኖርባቸዋል” ሲሉም አሳስበዋል።

    በአሜሪካ፣ እስራኤል እና ኢራን መካከል ያለው ግጭት የዓለም ንግድና የኃይል አቅርቦት ወሳኝ መስመሮች የሆኑትን የባብ አል-መንዴብ እና የሆርሙዝ ወሽመጥን በማወክ የመርከብ ወጪን ከፍ እንዲል እና የዋጋ ንረት ጫናን እንዲጨምር አድርጓል።

    አሳርማቶሪ የተባለው የመርከብ ባለቤቶች ማኅበር 40 በመቶ ያህሉ ጣሊያን ከውጭ ዓለም ጋር ያላት ንግድ በቀይ ባሕር ሰሜናዊ ጫፍ በሚገኘው የሱዊዝ ካናልበኩል የሚያልፍ ነው።

    በቅርብ ጊዜ ሁቲዎች በንግድ መርከቦችና በስትራቴጂካዊ ተቋማት ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃት ሲያጠናክሩ፣ ሳዑዲ አረቢያም በየመን ውስጥ በሁቲዎች ዒላማዎች ላይ የአየር ድብደባዎችን ማካሄዷን ቀጥላለች።