የሳዑዲ አረቢያ የኢነርጂ ሚኒስቴር በአገሪቱ ምሥራቃዊ ግዛት የሚገኘው ከዓለም ትላልቅ የነዳጅ ተቋማት አንዱ የሆነው የአራምኮ (Aramco) የአስተዳደር ሕንጻ ላይ ማክሰኞ ዕለት ጥቃት ተፈጽሞ መለስተኛ የእሳት አደጋ መከሰቱን አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ በሰው ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት አለመድረሱን ገልጿል።
ይህ ጥቃት የተፈጸመው፣ በኢራን የሚደገፉት የሁቲ ታጣቂዎች እና የሳዑዲ ጥምረት ማክሰኞ ምሽት የተኩስ ልውውጥ ባደረጉበት ወቅት ነው። ይህ ግጭት እየሰፋ የመጣውን የመካከለኛው ምሥራቅ ቀውስ ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገረ ነው።
ጥቃቱ ከመፈጸሙ በፊት የሳዑዲ ጦር ዋና የነዳጅ አምራች ወደሆነው የአገሪቱ ምሥራቃዊ ግዛት እና ወደ ዋና ከተማዋ ሪያድ ሚሳዔሎች መተኮሳቸውን የሚገልጹ ተከታታይ ማስጠንቀቂያዎችን ለነዋሪዎች ተልኳል።
የሳዑዲ አረቢያ ሲቪል መከላከያ እንዳስታወቀው በአየር ላይ ሳሉ እንዲከሽፉ የተደረጉ ሁለት የሁቲ ሚሳይሎች ስብርባሪዎች በሪያድ በሚገኙ የመኖሪያ አካባቢዎች ላይ ወድቀው አራት ሰዎች ሲቆስሉ 15 ቤቶች ጉዳት ደርሶባቸዋል።
በሳዑዲ አረቢያ የሚመራውና በየመን የሚንቀሳቀሰው ጥምር ኃይል፣ በሁቲ አማፅያን ቁጥጥር ስር በሚገኘው የየመን ዋና ከተማ ላይ ማክሰኞ ዕለት አዲስ የአየር ጥቃት መፈጸሙን፣ በሁቲ ቁጥጥር ስር የሚገኘው 'አል-ማሲራህ' የተሰኘው መገናኛ ብዙኃን እና የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ጥቃቱ የተፈጸመው የጥምር ጦሩ ቃል አቀባይ ነዋሪዎች ለደህንነታቸው ሲሉ አካባቢውን ለቅቀው እንዲወጡ ጥሪ ካቀረቡ በኋላ ነው።
ጥምረቱ በከተማዋ ምዕራባዊ ክፍል የሚገኘውን የሱባሃ የነዳጅ ማከማቻ ጣቢያ ካጠቃ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ በሰነዓ ውስጥ ከባድ ፍንዳታዎች እንደተሰሙ የዐይን እማኞች ገልጸዋል።
ባልተለመደ ሁኔታ ከዚህ ቀደም ባወጣው መግለጫ፣ ጥምረቱ በሁቲዎች ቁጥጥር ስር ባለችው ዋና ከተማ የሚኖሩ ሰላማዊ ዜጎች፣ ሊኖር ከሚችል ጥቃት አስቀድመው ዋና ከተማዋን፣ የየመን ነዳጅ ኩባንያ እና በአቅራቢያው የሚገኙ የማከማቻ ቦታዎችን ለቅቀው እንዲወጡ ጥሪ አቅርቦ ነበር።
የጥምረቱ ቃል አቀባይ ሜጀር ጄኔራል ቱርኪ አል-ማሊኪ፣ ሁቲዎች ተቋሙን እና በስሩ የሚገኙትን የነዳጅ ማከማቻዎች ለሚሳዔል እና ለድሮን ማከማቻ እየተጠቀሙበት ነው ሲሉ ከስሰዋል።
የሁቲ ባለሥልጣናት ጥቃቱ እንደሚፈጸም አስቀድመው የሚያውቁ ይመስላል።
የነዳጅ ኩባንያው፣ የማከማቻ ተቋማቱ ባዶ መሆናቸውን እና የሳዑዲ ጥቃት በነዳጅ ክምችቱ ወይም ለነዋሪዎች በሚደርሰው አቅርቦት ላይ ምንም ዓይነት ተጽዕኖ እንደማያሳድር ገልጿል።
ሆኖም፣ የዓይን ምስክሮች የነዳጅ እጥረት ይፈጠራል በሚል ስጋት በአንዳንድ የነዳጅ ማደያዎች ላይ ተሽከርካሪዎች ረዥም ሰልፍ ይዘው መታየታቸውን ተናግረዋል።
ማስጠንቀቂያው በተሰጠ በአጭር ሰዓት ውስጥ የሁቲ ጦር ቃል አቀባይ ብርጋዴር ጄነራል ያህያ ሳሬ በቴሌግራም ገጻቸው ላይ በሰነዓ ላይ የሚፈጸም ጥቃት በሳዑዲ ዋና መዲና ሪያድ ላይ “ከባድ እና ሕመም የሚያስከትል” ምላሽ ይሰጣል ብለዋል።