ሩሲያ ኢትዮጵያ እና ኤርትራን ለማሸማገል ፈቃደኛ መሆኗን አስታወቀች

በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ ሩሲያ የአሸማጋይነት ሚና ለመጫወት ፈቃደኛ መሆኗን የአገሪቱ ባለሥልጣን ተናገሩ። የሩሲያ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሌክሳንደር አሊሞቭ፤ ሁለቱ አገራት ፈቃደኞች ከሆኑ ከአንድ ሳምንት በኋላ በሚካሄደው የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ ወቅት ንግግር እንዲያካሂዱ መድረክ ለማመቻቸት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ሁቲዎች፤ አሜሪካ በየመን ጦርነት ውስጥ ከገባች “የሚያሳምም ምላሽ” እንደሚሰጡ ዛቱ

    አሜሪካ በየመን ጦርነት ውስጥ እጇን የምታስገባ ከሆነ “የሚያሳምም ምላሽ” እንደሚሰጡ ሁቲዎች ዝተዋል።

    ኤኤፍፒ እንደዘገበው ከሆነ ሳዑዲ አረቢያ የሁቲ አማጺያንን ለመዋጋት ከአሜሪካ ድጋፍ ጠይቃለች።

    የሁቲ የፖለቲካ ቢሮ አባል መሐመድ አል-ባክሀቲ ለኤኤፍፒ “የመን ላይ በሚፈጸመው ጥቃት አሜሪካ ጣልቃ የምትገባ ከሆነ ምላሽ ለመስጠት አናቅማማም። አሜሪካ እና በቀጣናው ያሉ ይዞታዎቿ ላይ በማነጣጠር ፈጣን እና የሚያም ምላሽ እንሰጣለን” ብለዋል።

    የሳዑዲ አረቢያ ኢነርጂ ሚኒስትር ልዑል አብዱል አዚዝ ቢን ሳልማን ሁቲዎች ላይ “ከባድ” እርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል።

    በሳዑዲ አውሮፕላን ማረፊያዎች እንዲሁም የነዳጅ እና ጋዝ ፋብሪካዎች ላይ ሁቲዎች ላደረሱት ጥቃት “ከባድ” የአጸፋ ምላሽ እንደሚሰጣቸው ገልጸዋል።

    የሁቲዎች የፖለቲካ ቢሮ አባል በበኩላቸው “የሳዑዲ አረቢያ አውሮፕላን ማረፊያዎች እና የነዳጅ ፋብሪካዎች ሠራተኞች ባጠቃላይ ከአካባቢው መራቅ አለባቸው፤ እነዚህን ተቋማት ዒላማ አድርገናል” ብለዋል።

    ቅዳሜ ሁቲዎች በንጉሥ ኻሊድ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ባስወነጨፉት ሚሳዔል 13 ሰዎች በመገደላቸው አውሮፕላን ማረፊያው ተዘግቷል።

    እሑድ ደግሞ በአውሮፕላን ማረፊያው ላይ በደረሰ ጥቃት አንድ ፓኪስታናዊ መሞቱ ተገልጿል።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሳዑዲ አረቢያ ሁቲዎች ላይ የምታደርውን ጥቃት ለመደገፍ እያሰቡ እንደሆነ አስታውቀዋል።

    ከዚህ ቀደም ግን የሳዑዲ አረቢያው ልዑል አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሳልማን ድጋፍ እንዲደረግ ሲጠይቋቸው ትራምፕ ፈቃደኛ አልሆኑም ነበር።

  2. የሳዑዲ ሚኒስትር ሁቲዎች ላይ “ከባድ” እርምጃ እንደሚወሰድ አስታወቁ

    የሳዑዲ አረቢያ ኢነርጂ ሚኒስትር ሁቲዎች ላይ “ከባድ” እርምጃ እንደሚወሰድ አስታወቁ።

    በሳዑዲ አውሮፕላን ማረፊያዎች እንዲሁም የነዳጅ እና ጋዝ ፋብሪካዎች ላይ ሁቲዎች ላደረሱት ጥቃት “ከባድ” የአጸፋ ምላሽ እንደሚሰጣቸው ልዑል አብዱል አዚዝ ቢን ሳልማን ተናግረዋል።

    “በቅርብ ሳምንታት የተፈጠሩት ክስተቶች ከባድ ናቸው። እኛ የምንሰጠው ምላሽም በዚያው ልክ ከባድ ይሆናል” ሲሉ በሪያድ በተደረገው የኢነርጂ ጉባዔ ላይ ተናግረዋል።

    እሑድ በንጉሥ ኻሊድ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ በደረሰ ጥቃት አንድ ፓኪስታናዊ መሞቱ ተገልጿል።

    ቅዳሜ ሁቲዎች ባስወነጨፉት ሚሳዔል 13 ሰዎች በመገደላቸው አውሮፕላን ማረፊያው መዘጋቱ ይታወሳል።

    ሳዑዲ አረቢያ ሁቲዎች በሚቆጣጠሩት ምዕራብ የመን ላደረሰቸው “የጭካኔ ድርጊት” ምላሽ ለመስጠት ጥቃቱን ማድረሳቸውን አማጺያኑ ገልጸዋል።

    ሁቲዎች የሚያስተዳድሩት የጤና ሚኒስቴር እንዳለው ሳዑዲ እሑድ በሰንዓ በፈጸመችው የአየር ጥቃት አንድ ልጅ ሲገደል፣ ስድስት ሰዎች ቆስለዋል።

    በቀይ ባሕር እና አዋሳኝ አካባቢዎች በኢራን የሚደገፉትን ሁቲዎች በሳዑዲ የሚመራው ወታደራዊ ጥምረት እየተዋጋ ይገኛል።

    ትናንት ሰኞ ምሽት በሪያድ የፍንዳታ ድምጽ የተሰማ ሲሆን፤ በሳዑዲ የሚመራው ወታደራዊ ጥምረት ባለስቲክ ሚሳዔል ማክሸፉን ይፋ አድርጓል።

    የሁቲ ቃል አቀባይ እንደተናገረው ታጣቂ ቡድኑ በድጋሚ አውሮፕላን ማረፊያው ላይ ያነጣጠረ ጥቃት አድርሰዋል።

  3. ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከእስራኤሉ አቻቸው ቤንያሚን ኔታኒያሁ ጋር በስልክ ተወያዩ

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከእስራኤሉ አቻቸው ቤንያሚን ኔታኒያሁ ጋር የስልክ ውይይት ማድረጋቸውን አስታወቁ።

    ይህ የሁለቱ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ውይይት መደረጉ የተገለጸው የአገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ተመሳሳይ የስልክ ንግግር ማድረጋቸው ከተገለጸ ከሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ነው።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከኔታኒያሁ ጋር ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሳወቁበት ጽሁፍ ላይ እንዳሉት “በሁለቱ አገራት ግንኙነት እና በቀጣናዊ ጉዳዮች” ላይ ተነጋግረዋል።

    ሁለቱ ጠቅላይ ሚኒስትሮች “በጋራ ጉዳዮች ላይ” የሚያደርጉትን ትብብር የበለጠ ለማጠናከር በድጋሚ ማረጋገጣቸውን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዝርዝር ጉዳዮችን በተመለከተ ያሉት ነገር የለም።

    ውይይቱን በተመለከተ ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በኩል የተባለ ነገር የለም።

    ባለፈው ማክሰኞ መስከረም 26/2019 ዓ.ም. የእስራኤሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ሳዓር ከኢትዮጵያው አቻቸው ጌዲዮን ጤሞቲዮስ (ዶ/ር) ጋር በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ በስልክ መወያየታቸውን አሳውቀው ነበር።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወቅታዊ ያሏቸው ጉዳዮች የትኞቹ እንደሆኑ በዝርዝር ያሉት ነገር የለም።

    አክለውም በውይይታቸው ስለኢትዮጵያ አንድነት እና መረጋጋት አስፈላጊነት እንዲሁም የአፍሪካ ቀንድ ሰላም እና መረጋጋትን ለሁለቱ አገራት ስላለው የጋራ ጥቅም መነጋገራቸውን አመልክተዋል።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ እና የጠቅላይ ሚኒስትሮቹ የስልክ ውይይት የተካሄደው በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ዳግም ጦርነት ካገረሸ በኋላ ነው።

    ኢትዮጵያ እና እስራኤል ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የአገራቱ ባለሥልጣናት በአገራቱ ውስጥ ጉብኝት አድርገዋል።

  4. የአሜሪካ ኢሚግሬሽን ተቆጣጣሪዎች በኢልሃን ኦማር ቤት ውስጥ ፍተሻ አደረጉ

    የአሜሪካ የኢሚግሬሽን ተቆጣጣሪዎች ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በተደጋጋሚ ሲከስሷት የነበረችው ትውልደ ሶማሊያዊቷ የምክር ቤት አባል ኢልሃን ኦማር ቤት ላይ ፍተሻ ማካሄዳቸውን አስታወቁ።

    በአሜሪካ ሰዓት ዛሬ ሰኞ ጠዋት በአገሪቱ ምክር ቤት የሚኒሶታ ተወካይ የሆነችውን ኢልሃን ኦማር ዋሽንግተን አካባቢ ባላት ቤቷ ላይ የተካሄደው ፍተሻ “የወንጀል ምርመራ” አካል መሆኑን ገልጿል።

    የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደኅንነት ምርመራ መኮንኖች “በፍርድ ቤት ፈቃድ የተሰጠ የፍተሻ ትዕዛዝ” ተግባራዊ ማድረጋቸውን የአሜሪካ ፍትህ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ ኒውስ ተናግረዋል።

    ቃል አቀባዩ እንዳሉት፣ በኢልሃን ቤት ውስጥ የተካሄደው ፍተሻ “በሂደት ላይ ያለ የፌዴራል ወንጀል ምርመራ” አካል ነው፣ ከማለት ውጪ ምንም ተጨማሪ ዝርዝሮች አልተሰጡም።

    ኢልሃን ኦማር ሶማሊያ ውስጥ ተወልዳ በስምንት ዓመቷ ነበር ከጦርነት ሸሽታ ወደ አሜሪካ የገባችው። በአውሮፓውያኑ 2018 ለመጀመሪያ ጊዜ የኮንግረስ አባል ሆና ተመርጣለች፤ ኢልሃን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን በይፋ በመተቸት ትታወቃለች።

    ፕሬዝዳንቱ እና ደጋፊዎቻቸው ኢልሃንን በተለያዩ ሕገወጥ ድርጊቶች በተደጋጋሚ ሲከስሱ የነበሩ ከመሆናቸው በተጨማሪ የአሜሪካ ዜግነቷ እንዲገፈፍም ሲጠይቁ ነበር።

    በአሁኑ ጊዜ የአሜሪካ ኮንግረስ በእረፍት ላይ ሲሆን ኢልሃን በፍተሻው ወቅት ቤቷ ውስጥ መኖር አለመኖሯ አልታወቀም።

    ቢቢሲ ከኢልሃን ኦማር በጉዳዩ ላይ አስተያየት ለማግኘት ጥያቄ አቅርቧል።

  5. የሽብር ተከሳሹ ካናዳዊው እሱባለው በለጠ ከአንድ ዓመት እስር በኋላ በነጻ ተሰናበተ

    ትውልደ ኢትዮጵያዊው የካናዳ ዜግነት ያለው እሱባለው በለጠ በነጻ ተሰናብቶ ከእስር መፈታቱን ለቢቢሲ ተናገረ።

    ከመስከረም 24/2018 ዓ.ም ጀምሮ ከአንድ ዓመት በላይ በእስር ላይ የቆየው እሱባለው፣ መስከረም 28/2019 ዓ.ም መለቀቁን ገልጿል።

    የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የጸረ ሽብር እና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በነጻ እንዲለቀቅ ውሳኔ በሰጠበት እለት ነው ከእስር የተለቀቀው።

    ሦስቱም የችሎቱ ዳኞች በነጻ እንዲሰናበት በሙሉ ድምፅ ውሳኔ መስጠታቸውን እሱባለው ለቢቢሲ አስረድቷል።

    ካናዳዊው እሱባለው በለጠ ብርሃኔ፣ በአማራ ክልል ካለው ቀውስ ጋር በተያያዘ በሽብር ለተከሰሱ እስረኞች የቀረበውን በቅድመ ሁኔታ ላይ የተመሰረተ "ይቅርታ መጠየቂያ ሰነድ" ለመፈረም ፈቃደኛ ካልሆኑ 30 ተጠርጣሪዎች አንዱ ነው።

    እሱባለው፣ የወላጅ እናቱን ህልፈተ-ሕይወት ተከትሎ ለለቅሶ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ በኋላ፣ መስከረም 24/2018 ዓ.ም ወደ ካናዳ ለመመለስ አውሮፕላን ሊሳፈር ሲል ከቦሌ አየር ማረፊያ ነበር በፀጥታ ኃይሎች የተያዘው።

    ተጠርጥሮ የተከሰሰበት የሽብር ወንጀል፣ በውጭ ካሉ የፋኖ ደጋፊዎች ጋር በመተባበር፣ በአማራ ክልል ለሚንቀሳቀሰው “ታጣቂ ኃይል የሎጂስቲክስ ድጋፍ በማድረግ" እንደነበር ጠበቃው እና ተከሳሹ ተናግረዋል።

    ከዚህ ጋር የተያያዙ አራት ክሶች ቀርበውበት እንደነበር የገለፀው እሱባለው፣ መከላከያ ካቀረበ በኋላ በነበሩ አምስት ቀጠሮዎች ዐቃቤ ሕግ በቂ ማስረጃ ማቅረብ እንዳልቻለ በፍርድ ቤቱ መገለፁን አስረድቷል።

    “ዐቃቤ ሕግ በተደጋጋሚ በተሰጠው ዕድል ያለውን ማስረጃ ማቅረብ እንዳልቻለ ገልጾ ነው ፍርድ ቤቱ በነጻ እንድሰናበት ውሳኔ የሰጠው” ሲል ተናግሯል።

    “በቁጥጥር ስር የዋልኩት በሀሰተኛ ጥቆማ ነበር” የሚለው እሱባለው፣ ጉዳዩ እልባት ማግኘቱ ቢያስደስተውም “መጓተቱ” ግን “ሕይወቴን አመሰቃቅሎታል” ይላል።

    በካናዳ የቶሮንቶ ፒርሰን አየር ማረፊያ "ከፍተኛ የአውሮፕላን ጥገና ባለሞያ (ግራውንድ ቴክኒሺያን)" ሆኖ ሲሠራ የነበረው እሱባለው በለጠ፣ በእስር ላይ በነበረበት ጊዜ ሥራውን ማጣቱን ተናግሯል። "አየር መንገዱ በእስር ላይ መሆኔን ተረድቶ ከ10 ወራት በላይ ከጠበቀኝ በኋላ፣ አሰናብቶኝ በቦታው ሌላ ሰራተኛ ቀጥሯል” ብሏል።

    በተጨማሪም “ክሬዲት ካርዴ ሙሉ በሙሉ ተበላሽቷል። የመኪና ኢንሹራንስ መክፈል ስላልቻልኩ ተዘግቷል፤ አንዴ ክሬዲት ካርድ ከተበላሸ እንደ ቤት ያሉ ከፍ ያሉ ነገሮችን ለመግዛት 7 ዓመት መጠበቅ አለብኝ። ተከራይቼ የምኖርበት ቤት ማስታወቂያ አውጥቶ መልስ የሚሰጠው ስላጣ እቃዬን በሙሉ አውጥቶ ለሌላ አከራይቷል” ሲልም የገጠመውን ሁኔታ አብራርቷል።

    እናም ወደ ካናዳ በሚመለስበት ወቅት ህይወትን "ከዜሮ ለመጀመር" እንደሚገደድ በመጥቀስ፣ “የፍትህ ስርዓቱ መጓተቱ ቅሬታ አሳድሮብኛል” ሲል ገልጿል።

    እሱባለው ከእስር ከተፈታ በኋላ ወደ ካናዳ ለመመለስ የሚያስፈልጉትን ቅድመ ሁኔታዎች እያጠናቀቀ መሆኑን ዛሬ ሰኞ ጥቅምት 2/2019 ዓ.ም ለቢቢሲ አስረድቷል። የቀረበበትን ክስ በሚከታተልበት ወቅት የካናዳ ኤምባሲ ባለሞያዎችን በመመደብ የማማከር አገልግሎት ሲሰጠው እንደነበረም ገልጿል።

  6. የአሜሪካ አየር መንገድ በሳዑዲ አየር ላይ ሲበር ጥንቃቄ እንዲያደረግ ተነገረው

    የአሜሪካ አየር መንገድ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ወይም በአገሪቷ የአየር ክልል ሲበር ጥንቃቄ እንዲያደርግ የፌዴራል አቪየሽን አስተዳደር አሳሰበ።

    የአቪየሽን አስተዳደሩ ይህን ያለው እየተካሄደ ባለው ወታደራዊ እንቅስቃሴ እና ከክትትል ሥርዓቱ ላይ ጣልቃ ገብነት ጋር በተያየዘ ያለውን የደኅንነት ስጋት ጠቅሶ ነው።

    ተቋሙ እስከ አውሮፓውያኑ ታኅሳስ 10 ድረስ የሚዘልቀው እና ለአብራሪዎች ማስጠንቀቂያ የሰጠው ሁቲዎች ቅዳሜ እና እሁድ በሪያድ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ጥቃቶች ከተፈፀሙ በኋላ ነው።

    ቅዳሜ ዕለት በተፈፀመው ጥቃት 13 ሰዎች ሲገደሉ ከ300 በላይ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል። እሁድ ዕለት በተፈፀመ ሌላ ጥቃትም አንድ ሰው ሲገደል 11 ሰዎች ላይ ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገልጿል።

    ይህም “ የሚበሩ፣ የሚያርፉ እና የሚነሱትን ጨምሮ በየትኛውም ከፍታ ላይ በሚበሩ አውሮፕላኖች ላይ አደጋ ሊያስከትል ይችላል” ሲል የፌዴራል አቪየሽን ያለውን አደገኛ ሁኔታ በመግለጽ አስጠንቅቋል።

    ማስጠንቀቂያው በአሜሪካ የተመዘገቡ ሌሎች የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎችን የሚመለከት ነው ብሏል። የሁቲ ጥቃቶችን ተከትሎ የሪያድ አየር ማረፊያ እስከ ሌሊቱ 6፡00 ሰዓት ድረስ ተዘግተዋል።

    ሰኞ ዕለትም በሳዑዲ የሚገኘው የዩናይትድ ኪንግደም ኤምባሲ በማኅበራዊ ሚዲያው ላይ ባጋራው ጽሑፍ “ ከአስገዳጅ ጉዞዎች በስተቀር በጂዳህ እና ዳማን ከተሞች እንዲሁም ወደ ሁሉም የሳዑዲ አውሮፕላን ማረፊያዎች የሚደረግ ጉዞን” በተመለከተ አስጠንቅቋል።

  7. ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን ለመክፈት ላቀረበችው እቅድ አሜሪካ የሰጠችው ምላሽ “በቂ እንዳልነበር” ገለጸች

    ኢራን ወሳኝ የሆነውን የሆርሙዝ ወሽመጥ ለመክፈት ላቀረበችው ሰባት ቅድመ ሁኔታዎች አሜሪካ የሰጠችው ምላሽ "በቂ እንዳልነበር" የኢራን የደኅንነት ኃላፊ ሞህሰን ራዜ እሁድ ዕለት መናገራቸውን የአገሪቷ መገናኛ ብዙኃን ዘገበ።

    ኢራን በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ወቅት ወሽመጡ በሰባት ቀናት ውስጥ ሊከፈት የሚችልባቸውን እና የመርከቦች እንቅስቃሴን ወደ መደበኛ ሁኔታ ለመመለስ የሚያስችል እቅድ አቅርባ ነበር።

    አሜሪካም በኋላ ላይ በኳታር አደራዳሪዎች በኩል ምላሽ ሰጥታለች።

    ሆኖም “በምላሻቸው የተወሰኑ ቅድመ ሁኔታዎችን የተቀበሉ ቢሆንም ሌሎቹ ግልጽ አይደሉም” ብለዋል የደኅንነት ኃላፊው።

    ዋሽንግተን ለቴህራን ግልጽ ያልሆነላትን ጉዳዮች ማብራራት አለባት ያሉት ራዜ፣ “ለአሜሪካውያን ሰባት ሁኔታዎችን አስቀምጠናል፤ እነዚህ ሁኔታዎች ካልተከበሩ የሆርሙዝ ወሽመጥ ለእነርሱ ክፍት እንደማይሆን እና ድርድሩም እንደማይቀጥል ገልፀንላቸዋል” ሲሉ ተናግረዋል።

    ሮይተርስ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ለማግኘት ዋይት ሐውስን ቢጠይቅም ወዲያውኑ ምላሽ አላገኘም።

    በኋላ ላይ ቴህራን በቅርብ ጊዜ የፈረሰውን በባሕረ ሰላጤው የተኩስ አቁም ስምምነት ለመጀመር ላቀረበችው እቅድ ከአሜሪካ ምላሽ እንዳገኘች ገልጻ ነበር።

    ከቀናት በኋላ ግን የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የቀረበውን እቅድ ውድቅ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።

    ኳታር እና ሌሎች አደራዳሪዎች ጦርነቱን ለማስቆም እና የሆርሙዝ ወሽመጥን ለማስከፈት በዋሽንግተን እና በቴህራን መካከል መልዕክቶችን ሲያለዋውጡ ቆይተዋል።

    አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጦርነት ከከፈቱ በኋላ አንድ አምስተኛው የዓለም ነዳጅ የሚተላለፍበት የሆርሙዝ ወሽመጥ በመዘጋቱ የዓለም የነዳጅ አቅርቦት የተስተጓጎለ ሲሆን የዋጋ ንረትም አስከትሏል።

  8. ሁቲዎች በሪያድ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ ጥቃት ፈጽመው አንድ ሰው ሲሞት 11 ሰዎች ቆሰሉ

    እሁድ ዕለት የሁቲ አማፂያን በሳዑዲ አረቢያ ዋና ከተማ ሪያድ በሚገኝ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ በፈጸሙት ሁለተኛ ጥቃት አንድ ሰው ሲገደል 11 መቁሰላቸውን የአገሪቱ ባለሥልጣናት ተናገሩ።

    የሳዑዲ ጦር ቃል አቀባይ፣ ምንነቱ ያልታወቀ ተተኳሽ ንጉሥ ኻሊድ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያን እሁድ ዕለት መመታቱን ገልጸው በመንገደኞች ማረፊያ ውስጥ እሳት መቀስቀሱን ተናግረዋል።

    የሳዑዱ አረቢያ ሲቪል አቪየሽን ባለሥልጣን በኤክስ ገጹ ላይ በጥቃቱ አንድ ፓኪስታናዊ መገደሉን አስታውቋል።

    በአውሮፕላን ማረፊያው ላይ ተወንጫፊ የተተኮሰው 13 ሰዎችን ገድሎ 308 ሰዎችን ያቆሰለው ጥቃት ከተፈጸመ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።

    በየመን የሚገኙት ሁቲዎች ጥቃቶቹ መፈጸማቸውን ገልጸው፣ አየር መንገዶች እና መንገደኞች የሳዑዲ አረቢያ አውሮፕላን ማረፊያዎችን እና የአየር ክልልን እንዳይጠቀሙ አስጠንቅቀዋል።

    ቡድኑ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ አውሮፕላን ማረፊያውን በባለስቲክ እና በክሩዝ ሚሳኤሎች እንዲሁም ድሮኖች ዒላማ እንዳደረገ ተናግሯል።

    በተጨማሪም በምሥራቅ ሳዑዲ አረቢያ የሚገኝን የነዳጅ ተቋማት እና የዳማም አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ጥቃት ፈጽመናል ሲሉ የጦር ኃይሉ ቃል አቀባይ ብርጋዴር ጄኔራል ያህያ ሳሪ ተናግረዋል።

    "በሳዑዲ አረቢያ ውስጥ እየተባባሰ የመጣውን ዘመቻ ለመቀጠል” የዛቱት ቃል አቀባዩ፣ ሁሉም የሳዑዲ አውሮፕላን ማረፊያዎች በቅዱስ ከተሞች መካ እና መዲና ውስጥ ካሉት በስተቀር ዒላማ ሊሆኑ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።

    የሁቲ አማፂያን ሳዑዲ አረቢያ በየመን የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ለመንግሥት ኃይሎች ድጋፍ መስጠቷን እና በሰነዓ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ የአየር ጥቃት በመሰንዘሯ የተነሳ የአጸፋ እርምጃ እየወሰዱ መሆኑን ተናግረዋል።

    እሁድ ዕለት በሳዑዲ የሚመራው ወታደራዊ ጥምረት ቃል አቀባይ ሜጀር ጄኔራል ቱርኪ አል-ማሊኪ የእሳት አደጋ ሠራተኞች በመንገደኞች አዳራሽ ውስጥ "ምንነቱ ባልታወቀ ተወንጫፊ" ምክንያት የተከሰተውን እሳት ለመቆጣጠር ጥረት እያደረጉ ባለበት ወቅት የአየር መቃወሚያዎቹ በሪያድ አውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ አንድ ሚሳኤልን ማክሸፋቸውን ተናግረዋል።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሁቲ አማፂያን ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ወይም ላለመሰንዘር አሜሪካ "ውሳኔ ላይ እንደምትደርስ" እና "በፍጥነት እርምጃ እንደምትወስድ" ተናግረዋል።

    የዩናይትድ ኪንግደም የመከላከያ ሚኒስትር ዌስ ስትሪንግ ደግሞ ዩኬ ለሳውዲ አረቢያ የበለጠ ድጋፍ ልትሰጥ እንደምትችል ጠቁመዋል።

    ቅዳሜ የተፈፀመው ጥቃት ባለፈው ዓመት የካቲት ወር በእስራኤል፣ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ በአንድ የባሕረ ሰላጤ አረብ አገር ላይ የደረሰው እጅግ ከባድ ጥቃት ነው። በሳዑዲ የሚመራው ጥምረት ድርጊቱን "የጦር ወንጀል" በማለት ጠርቶታል።

    ከሟቾቹ መካከል አራት የሳዑዲ ዜጎች፣ ሁለት የባንግላዲሽ እና አንድ አንድ የአሜሪካ፣ የዮርዳኖስ፣ የፍልስጤም፣ የሶሪያ፣ የሱዳን እና የግብፅ ዜጎች እንደሚገኙበት የሳዑዲ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን አስታውቋል።

    በሳዑዲ አረቢያ የሚገኘው የሕንድ ኤምባሲ እሁድ ዕለት አንድ ሕንዳዊ በጥቃቱ በደረሰበት ጉዳት ምክንያት ሕይወቱ ማለፉን አስታውቋል።

    የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ጥቃቶቹን አውግዘው አንድ የአሜሪካ ዜጋ መገደሉን አረጋግጠዋል። የዩኬ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኤድ ሚሊባንድ "በጣም አስደንጋጭ" ብለውታል።

    የዩኬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከየመን ድንበር በ10 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ወደሚገኙ የሳዑዲ አረቢያ ክፍሎች ዜጎቹ እንዳይጓዙ ያስጠነቀቀ ሲሆን ሌሎች የምዕራባውያን ኤምባሲዎች ደግሞ ዜጎቻቸውን ወደ አገሪቱ ስለሚያደርጉት ጉዞ አስጠንቅቀዋል።

    በሁቲዎች ቁጥጥር ስር ያለው አል ማሲራህ ቲቪ "ጠላት የሆነችው ሳዑዲ" በየመን ዋና ከተማ ሰንዓ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ የአየር ጥቃት መፈጸሟን ዘግቧል። በከተማው ውስጥ ያለ መኖሪያ ቤትም ተመትቶ አንድ ሕፃን ሲገደል ስድስት ሰዎችን መቁሰላቸውን በዘገባው ላይ ጠቅሷል።

    ሳዑዲ አረቢያ ጥቃቶቹን ስለመፈጸሟ ምንም ያላለች ሲሆን ቢቢሲም ይህንን ዘገባ ማረጋገጥ አልቻለም።