ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከአምስት ሺህ በላይ ሰዎች በኢቦላ ቫይረስ ሕይወታቸው አለፈ
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ ከ5,000 በላይ ሰዎች መሞታቸውን የመንግሥት መረጃ አሳየ።
ከ26ቱ የአገሪቱ ግዛቶች ውስጥ ስምንቱ በበሽታው የተጎዱ ሲሆን፣ ከ10,300 በላይ የሚሆኑት ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።
ባለፈው ዓመት በግንቦት ወር የተቀሰቀሰው ይህ ወረርሽኝ ከሁለት ወራት በኋላ በአገሪቱ ታሪክ ውስጥ እጅግ ገዳዩ መሆኑን የኅብረተሰብ ጤና ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
አሁን የተቀሰቀሰው ቫይረስ የሞት ምጣኔ 48.6 በመቶ ነው።
የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር ባወጣው የቅርብ ጊዜ መረጃ፤ በአገሪቱ ሰሜን ምስራቅ የምትገኘው ኢቱሪ ግዛት የወረርሽኙ ማዕከል ሆና እንደቀጠለች ነው። ይህ አካባቢ የግጭት ቀጣና በመሆኑ ቫይረሱን ለመቆጣጠር አስቸጋሪ አድርጎታል።
በኬንያ፣ ናይጄሪያ እና ኡጋንዳም በበሽታው የተያዙ ሰዎች መገኘታቸው ተረጋግጧል።
እንደ መንግሥታቱ ድርጅት መረጃ የአሁኑ የኢቦላ ወረርሽኝ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ታሪክ ውስጥ 17ተኛው ወረርሽኝ እና በታሪክ ሁለተኛው ትልቁ በሽታ ነው።
የዓለም የጤና ድርጅት የአፍሪካ ቢሮ ወረርሽኙን ለማስቆም "ዋና ዋና የቁጥጥር እርምጃዎችን ማሳደግ፣ የተጎዱ አካባቢዎችን የበለጠ ተደራሽ ማድረግ እና የማኅበረሰብ አገልግሎት መስጠትን መቀጠል" እንደሚያስፈልግ አስታውቋል።
ምርመራ እና ሕክምና እንዲሁም የክትባት ሙከራዎች እየተካሄዱ መሆናቸውንም ቢሮው አክሏል።
የ'ቡንዲቡጋዮ' ዝርያ በአሁኑ ወቅት ከተቀሰቀሰው ወረርሽኝ ጀርባ የሚገኝ ሲሆን፤ ይሁን እንጂ ለዚህ ዝርያ እስካሁን ምንም ዓይነት ሕክምና ወይም ክትባት አልተገኘም።
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከዚህ ቀደም የተከሰተው እጅግ ገዳይ የሆነው ወረርሽኝ እ.አ.አ ከ2018 እስከ 2020 ባሉት ዓመታት ሲሆን፤ በበሽታው 2,299 ሰዎች መሞታቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።
በታሪክ እጅግ ገዳይ የሆነው ወረርሽኝ በምዕራብ አፍሪካ ከ2014 እስከ 2016 ባለው ጊዜ ውስጥ የተከሰተ ሲሆን፤ ከ11,325 በላይ ሰዎችን ገድሏል። በሽታው በጣሊያን፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና አሜሪካን ጨምሮ በተለያዩ አገራት መሰራጨቱን የዓለም ጤና ድርጅት ገልጿል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአሁኑ ወረርሽኝ "በፍጥነት ሕይወትን እየቀጠፈ ነው" ሲልም አስጠንቅቋል።
ኢቦላ ልዩ እና በቫይረስ የሚከሰት ገዳይ በሽታ ሲሆን፤ ምልክቶቹም በድንገት የሚታዩ ናቸው።
በሽታው እየገፋ ሲሄድ ማስታወክ እና ተቅማጥ ይፈጠራሉ፤ የሰውነት ክፍሎችን ሊያዳክም ይችላል። ሁሉም ሳይሆኑ አንዳንድ ታካሚዎች የውስጥ እና የውጭ ደም መፍሰስ ያጋጥማቸዋል።
ቫይረሱ ከአንድ ሰው ወደ ሌላ ሰው የሚተላለፈው እንደ ደም ወይም ትውከት ካሉ ከተበከሉ እና ከሰውነት ከሚወጡ ፈሳሾች ጋር በሚፈጠር ንክኪ ነው።
በአሁኑ ወቅት በሽታውን ለማከም የሚደረገውን ጥረት፤ ወረርሽኙን ለመከላከል በሚሰሩ የጤና ባለሙያዎች እና ፖለቲከኞች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ፈታኝ አድርጎታል።