ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በጀርመን የኑሮ ውድነትን ለመቃወም በተደረገ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ መደብሮች ተዘረፉ
በጀርመን የኑሮ ውድነትን በመቃወም የተጀመሩ ሰላማዊ ሰልፎች ወደ ነውጥ አምርተው መደብሮች ተዘረፉ።
መጀመሪያ ላይ ሰላማዊ የነበሩት የተቃውሞ ሰልፎች ወደ መደብር ዝርፊያ የተለወጡት በማዕከላዊ ፍራንክፈርት ነው። በሌሎች የጀርመን ከተሞች ደግሞ ተቃዋሚዎች ከፖሊስ ጋር ተጋጭተዋል።
የጀርመን የፋይናንስ ማዕከል ከሆነችው ፍራንክፈርት በተጨማሪ በበርሊን፣ ኮሎኝ እና ሀምቡርግ ነውጥ ተነስቷል።
ፖሊስ ሰልፈኞችን ለመበተን ውሃ መጠቀሙን አስታውቋል። ሰልፈኞቹ የድንገተኛ ጊዜ ሠራተኞችን በርችት፣ ድንጋይ እና ጠርሙስ ጥቃት መፈጸማቸውም ተገልጿል።
በአውሮፓውያኑ ከ1997 ወዲህ የተወለዱ ልጆች (ጄን ዚ) በዋናነት የሚመሩት ተቃውሞ በተለያዩ ከተሞች እየተስፋፋ ነው።
'ጄን ዚ ኃላፊነቱን ወስዷል' በሚል ስያሜ የተጀመረው ንቅናቄ የኑሮ ውድነትን፣ ለትምህትር ቤቶች የሚመደበው በጀት ማነስን፣ ወታደራዊ አገልግሎትን እና ለሕዝብ አገልግሎት የሚመደብ ገንዘብ መቀነስን ይነቅፋል።
ባለፉት ሳምንታት በፈንሳይ ወጣቶች በጀመሩት ተቃውሞ ወደ 320,000 ሰዎች አደባባይ ወጥተው ድምጻቸውን አሰምተዋል።
ኤኤፍፒ እንደዘገበው፤ በፍራንክፈርት የሚገኘው የንግድ ጎዳና በአብዛኛው በፖሊስ ተዘግቷል። በርካታ ሰዎች መታሰራቸውንም የፖሊስ ቃል አቀባይ ተናግረዋል።
በፍራንክፈርት፣ ሙኒክ እና በርሊን ወደ 18,000 ተቃዋሚዎች እንደነበሩ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል። የሰላማዊ ሰልፉ አስተባባሪዎች ከገመቱት ቁጥር ግማሹ መሆኑም ተገልጿል።
የጀርመን መገናኛ ብዙኃን በአሥር ሺህዎችን የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች መገኘታቸውን ዘግበዋል።
የጄን ዚ ተቃውሞ ቃል አቀባይ ሊና ፍሬድኒክ ሰላማዊ ሰልፉ የተካሄደው "ወደ ጦርነት እና ጫና ማሳደር ከመግባት ይልቅ ለሰላም እና ነጻነት ለመታገል ነው" ብላለች።
"ለኛ ትልቅ ዋጋ ያለው የጤና እና የትምህርት ሥርዓቱ የተሻለ ድጋፍ ቢሰጠው ነው። አስገዳጅ ወታደራዊ አገልግሎትን እንቃወማለን። ጫናው በፍትሐዊ መንገድ መከፋፈል አለበት" ስትልም ዓላማቸውን ገልጻለች።
ትናንት ቅዳሜ ቀን ላይ የነበረው ተቃውሞ በአብዛኛው ሰላማዊ ነበር። ምሽት ላይ ግን ወደ ነውጥ ተሻግሯል።
የፍራንክፈርት ፖሊስ በኤክስ ገጹ እንዳለው፤ በከተማው ማዕከል "ነውጠኛ ተቃውሞ" ተከስቷል።
የበርካታ መደብሮች መስኮት ተሰባብሯል። ቤት ውስጥ የሚሠሩ ተቀጣጣዮች በድንገተኛ ጊዜ ሠራተኞች ላይ ተወርውረዋልም ሲል ፖሊስ አስታውቋል።
የሽጉጥ መሸጫ ሱቅ መስኮት እንደተሰበረ እና ኋላ ላይ አንድ ተጠርጣሪ ሁለት መሣሪያ ይዞ እንደተገኘ ተገልጿል።
የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሮማን ፖሴክ "100 የሚደርሱ ግራ ዘመም አክራሪዎች" ተቃውሞውን እንደጠለፉት ጠቅሰው፤ ተቃውሞው ያለቀበትን ሁኔታ "አሳፋሪ" ብለውታል።
"ሁላችንም ከፈረንሳይ ያየናቸውን ምሥሎች እናስታውሳለን። ዝርፊያ፣ ቤት ማቃጠል፣ የፖሊስ መኪና ማጋየት፣ ፖሊሶች ላይ ጥቃት ማድረስ. . . ፈረንሳይ አርአያ ተደርጋ መወሰድ የለባትም" ሲሉም ተናግረዋል።