የፓራጓይ ፕሬዚደንት ሳንቲያጎ ፔኛ ከሥልጣን ተወግደው ታሰሩ

ሳንቲያጎ ፔኛ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የፓራጓይ ፕሬዚደንት ሳንቲያጎ ፔኛ ከግል የንግድ ጥቅማቸው ጋር ግንኙነት ያለው የዲጂታል ባንክ ለውድቀት መዳረጉን ተከትሎ ከሥልጣን ተወግደው የቁም እስረኛ ተደረጉ።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ዩኤኖ ባንክ ለውድቀት ከተዳረገ በኋላ የተከሰተው ቀውስ እየተባባሰ በመሄዱ ምክንያት የራሳቸውን ፓርቲ አባላት ጨምሮ የሕግ አውጪዎች በሙሉ ድምፅ ከሥልጣን እንዲነሱ ከወሰኑ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ዓርብ ዕለት ነው ፔኛ ለእስር የተዳረጉት።

ፔኛ ሐሙስ ዕለት ከሥልጣን ለመልቀቅ ጥያቄ አቅርበው ነበር። ሆኖም ሴናተሮች የሥልጣን መልቀቂያቸውን ከመቀበል ይልቅ ፔኛን በብልሹ አስተዳደር ክስ ከሥልጣን አስወግደዋቸዋል። በመሆኑም በተለምዶ ለቀድሞ ፕሬዚደንቶች የሚሰጠውን ልዩ ያለመከሰስ መብት አጥተዋል።

እስካለፈው ዓመት ድረስ በባንኩ የባለቤትነት ድርሻ የነበራቸው ፔኛ፣ ምንም ሕገወጥ ድርጊት አልፈፀምኩም ብለዋል።

ይህ ዲጂታል ባንክ ህልውናው ማክተሙን ተከትሎ በፓራጓይ ማዕከላዊ ባንክ ቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ ከፓራጓይ ሕዝብ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የቆጠቡትን ገንዘብ ማግኘት አልቻሉም።

በግምት ሦስት ሚሊዮን ሰዎች ቁጠባቸውንና የጡረታ ገንዘባቸውን እስካሁን ማግኘት አልቻሉም። ይህም በአገሪቱ በተለይም በዋና ከተማዋ አሱንሲዮን ሰፊ ተቃውሞዎችን አስከትሏል።

ፔኛ ከሥልጣን እንዲወርዱ ድምፅ በተሰጠበት ወቅት ከቀረቡባቸው የክስ ነጥቦች ውስጥ፣ የጥቅም ግጭት ውስጥ እንደሆኑ፣ የቁጥጥር ተቋማትን ክትትል እንዳዛቡ፣ የጡረታ ገንዘቦችን እንዳዘዋወሩ እና ማዕከላዊ ባንኩን ያካተተ በተቋም የመደበቅ ሂደት ውስጥ እንደተሳተፉ የሚገልፁ ይገኙበታል።

አቃቤ ሕግ ሲልቪያ ማርጋሪታ ጎንዛሌዝ ቬስተር እንዳሉት፣ ፔኛ ቅዳሜ ዕለት እምነትን ማጉደል፣ በንግድ ስርዓት ላይ ተፅዕኖ መፍጠር እና ገንዘብን አላግባብ መጠቀም በሚሉ ክሶች ለምርመራ ይቀርባሉ።

ከ45 የአገሪቱ ከፍተኛ ምክር ቤት (ሴኔት) አባላት 44ቱ ፔኛን ከሥልጣን እንዲወገዱ ድምፅ ሰጥተዋል። የተቀሩት አንድ ሕግ አውጪ በስብሰባው ላይ አልተገኙም።

ከውሳኔው በኋላ የሴኔቱ ፕሬዚዳንት ባሲሊዮ ኑኔዝ፣ ፔኛ "ኃላፊነቱን በአግባቡ ባለመወጣት" ጥፋተኛ ሆኖ መገኘቱን ገልፀዋል።

ውሳኔውን ተከትሎ የፓራጓይ ምክትል ፕሬዚደንት ፔድሮ አሊያና ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት ሆነው ቃለ መሃላ ፈፅመዋል።

እአአ እስከ 2028 ድረስ የፕሬዚዳንትነት ሥልጣኑን ይዘው የሚቆዩት አሊያና "በገንዘብ ተቋሙ ውድቀት ምክንያት በአሁኑ ጊዜ ከባድ ችግር ውስጥ የሚገኙ ወገኖቻችን ሙሉ በሙሉ ካሳ ያገኛሉ" ሲሉ ተናግረዋል።

ፔድሮ አሊያና ከሳንቲያጎ ፔኛ መወገድ በኋላ ጊዜያዊ የፓራጓይ ፕሬዚዳንት ሆነው ቃለ መሃላ ሲፈፅሙ
የምስሉ መግለጫ, ፔድሮ አሊያና ከሳንቲያጎ ፔኛ መወገድ በኋላ ጊዜያዊ የፓራጓይ ፕሬዚዳንት ሆነው ቃለ መሃላ ፈፅመዋል

ራፋኤል ፊሊዞላ የተባሉ የአገሪቱ ምክር ቤት ሴናተር "በዴሞክራሲያዊ ታሪካችን ትልቁን የሙስና ቅሌት እየተጋፈጥን ነው። ይህ በመንግሥት፣ በግለሰቦች እንዲሁም በአገሪቱ ተዓማኒነትና ገጽታ ላይ የደረሰ እጅግ ከባድ ጉዳት ነው" በማለት ድርጊቱን ኮንነዋል።

ፔኛ ከባንኩ ውድቀት ጋር በተያያዘ ጉዳይ በቅርቡ በይፋ ክስ ሊመሰረትባቸው እንደሚችል ተንታኞች እየገለፁ ነው።

የፔኛ ጠበቃ ሪካርዶ ፕሬዳ በበኩላቸው፣ በደንበኛቸው ላይ የቀረቡትን ክሶች "በግድየለሽነት የቀረቡ" እንዲሁም "ኃላፊነት የጎደላቸውና ለፖለቲካዊ ጥቅም ተብለው የቀረቡ" ናቸው በማለት አጣጥለዋል።

ፔኛ ሐሙስ ዕለት ለአገሪቱ ሕዝብ ባስተላለፉት መልዕክት ስለተፈጠረው ነገር ይቅርታ ጠይቀው፣ "በእኔ ላይ የጣላችሁትን እምነት መክዳት ፈጽሞ ዓላማዬ አልነበረም" ሲሉ ተናግረዋል።