ትራምፕ ቀጣይ ፕሬዚዳንቶች በኦቫል ኦፊስ ላይ ለውጥ እንዳያደርጉ የሚከለክል ትእዛዝ ፈረሙ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የአሜሪካ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ወደፊት የሚመጡ ፕሬዚዳንቶች በዋይት ሐውስ ኦቫል ኦፊስ ላይ የተወሰኑ ለውጦችን እንዳያደርጉ የሚያግድ ነው ያሉትን የአስፈጻሚ ትእዛዝ ፈረሙ።
ከዚህ ቀደም በሪል እስቴት [በመኖሪያ ቤቶች ግንባታ] ዘርፍ የሚታወቁት ትራምፕ፣ በሁለተኛ የሥልጣን ዘመናቸው በተለይም በርካታ ወርቃማ ጌጣጌጦችን በመጨመር የፕሬዚዳንቱን ይፋዊ ቢሮ ገጽታ በእጅጉ ቀይረዋል።
ትራምፕ ሐሙስ ዕለት ለጋዜጠኞች ሲናገሩ፣ "ብሔራዊ መታሰቢያ ሐውልት እያደረግነው ነው፤ ማንም ሰው እንዲነካው፣ እንዲያፈርሰው ወይም በሞኝ ሰዎች በትንሹም ቢሆን የተለየ ቅርጽ ያለው ነገር እንዲገነባ አይፈቀድም" ብለዋል።
ይህ ትእዛዝ፣ ትራምፕ የዋይት ሐውስን ምሥራቃዊ ክንፍ ሙሉ በሙሉ በማፍረስ የጀመሩት እና የሕግ ተግዳሮቶች ያጋጠሙት ፕሮጄክት ከተጀመረ ከወራት በኋላ የተፈረመ ነው።
ፕሮጄክቱ በአሜሪካ ኮንግረስም ጸድቋል። የግንባታ ሥራውም በመቀጠል ላይ ሲሆን፣ ቦታውን አዲስ የዝግጅት ክብ አዳራሽ ለማድረግ ታቅዷል።
በአሁኑ ጊዜ የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች በዋይት ሐውስ ውስጥ የተወሰኑ ለውጦችን የማድረግ ሥልጣን ቢኖራቸውም፣ ትላልቅ የግንባታ ወይም የማሻሻያ ፕሮጀክቶች ግን የኮንግረሱን ፈቃድ ይፈልጋሉ።
ትራምፕ ሐሙስ የፈረሙት ትሬዚዳንታዊ የአስፈጻሚ ትእዛዝ፣ ኦቫል ኦፊስ እና በዙሪያው ያሉ አንዳንድ ክፍሎች ብሔራዊ የመታሰቢያ ሀውልት እንደሆኑ ይገልጻል።
ሆኖም ሰነዱ፣ "ፕሬዚዳንቱ መታሰቢያውን እንደገና የማስዋብ፣ የቤት እቃዎችን የመምረጥ ወይም የሐውልቱን ታሪካዊ መዋቅር ወይም ሥነ ሕንፃዊ ባህሪ በከፍተኛ ደረጃ የማይጎዱ መደበኛ የአሠራርና የደህንነት ለውጦችን የማድረግ ሥልጣኑን አይገድብም" ሲል ይጠቅሳል።
"ኦቫል ኦፊስን እንወደዋለን፤ ልክ እንደ ዋይት ሐውስ ራሱን የቻለ ምልክት ነው። የአገራችን እና የአገራችንን ታላቅነት የሚወክል ምልክት ነው" ሲሉ ትራምፕ ተናግረዋል። በተጨማሪም ባለፉት ወራት ኦቫል ኦፊስን የጎበኙ የዓለም መሪዎች ክፍሉን ለማስዋብ ያደረጓቸውን ለውጦች እንዳደነቁ ተናግረዋል።
ትራምፕ እንዳሉት፣ ለውጦቹን ከማድረጋቸው በፊት ዋይት ሀውስና ኦቫል ኦፊስ ጥገና ያስፈልጋቸው ነበር፤ የነበረውን ሁኔታም "በጣም የተጎዳ" ሲሉ ገልጸዋል። የተሰበሩ መስኮቶች፣ የተሰነጠቁ ግድግዳዎች እና የተበላሹ የድንጋይ ክፍሎች እንደነበሩም አስረድተዋል።
ሆኖም ብዙዎቹ በቀላሉ የሚታዩ ለውጦች የውበት ማሻሻያዎች ናቸው። ከእነዚህም መካከል ከቢሮው ውጭ "Oval Office (ኦቫል ኦፊስ)" የሚል ትልቅ ወርቃማ ሰሌዳ መትከል፣ የሮዝ አትክልት ስፍራን በመንገድ ንጣፍ መቀየር እና አዲስ ሄሊኮፕተር ማረፊያ መገንባት ይገኙበታል።
ትራምፕ እንዳሉት፣ ይህ ትእዛዝ "ይህን አስደናቂ ቦታ ማንም ሰው ወደፊት ማውደም እንዳይችል ያደርገዋል።"

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአጠቃላይ የዋይት ሐውስ ሕንፃ ከዚህ ቀደምም ቢሆን ብሔራዊ ታሪካዊ ምልክት ተብሎ የተመዘገበ ሲሆን ይህም በሕንፃው ላይ በድንገት ሊደረጉ የሚችሉ ትላልቅ ለውጦችን ለመከላከል ያለመ ነው።
እንደ ፕሬዚደንት፣ ትራምፕ ብሔራዊ የመታሰቢያ ሐውልቶችን የመፍጠር ሥልጣን አላቸው። ይህም ከብሔራዊ ፓርኮች ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነው።
ትራምፕ የፈረሙት ትእዛዝ፣ ኦቫል ኦፊስ "ታሪካዊ ባህሪውን፣ ሥነ ሕንፃዊ ቅርጹን እና ከፕሬዚዳንታዊ ተቋም ጋር ያለውን ትስስር በጠበቀ መልኩ" በብሔራዊ ፓርክ አገልግሎት እንዲጠበቅ ይጠይቃል።
ሰነዱ ከዚህ ቀደም ለዋይት ሀውስ የተደረጉ የጥበቃ እርምጃዎች መኖራቸውን ቢገልጽም፣ "ሆኖም ኦቫል ኦፊስ በብሔራዊ ደረጃ ጠቀሜታ ያለው የተለየ ታሪካዊ መዋቅር በመሆኑ ልዩ እውቅናና የጥበቃ አስተዳደር ይገባዋል" ይላል።
የአሜሪካ ኮንግረስ ፕሬዚዳንቶች አስፈላጊ ለውጦችን እንዲያደርጉ ለማስቻል ከብሔራዊ ታሪካዊ ጥበቃ የተለየ መብት ሰጥቷቸዋል። አሁን ያለው ኦቫል ኦፊስ ደግሞ በፕሬዚደንት ፍራንክሊን ዲ. ሩዝቬልት ሐሳብ መሠረት እአአ ከ1930ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ጀምሮ ባለበት ቆይቷል።
በታሪካዊ ቅርስ ጥበቃ ላይ የተካነ ልምድ ያለው የሕግ ተቋም "ካልቸራል ሄሪቴጅ ፓርትነርስ" አባል የሆኑት ግሬግ ወርክሃይዘር እንደሚሉት፣ እንደ የቤት እቃዎችና ማስዋቢያዎች ያሉ ጊዜያዊ ለውጦችን ማድረግ "ሙሉ በሙሉ በፕሬዚዳንቱ ውሳኔ ላይ የተመሰረቱ ናቸው"።
"ቋሚ የሆኑትን የሥነ ጥበብ ሥራዎችና የሕንፃውን መዋቅር እስካልጎዱ ድረስ፣ በአጠቃላይ የፈለጉትን ማድረግ ይችላሉ" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
































