"ከአምስት ጊዜ በላይ ምን እንዳጠፋ ሳይነገረው ማስጠንቀቂያ የተጻፈበት ሚዲያ የለም" አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት አምባሳደር ሬድዋን
የምስሉ መግለጫ, የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት አምባሳደር ሬድዋን
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከአምስት ጊዜ በላይ "ምን እንዳጠፋ እና የትኛውን ሕግ እንደጣሰ" ሳይነገረው ማስጠንቀቂያ የተጻፈበት መገናኛ ብዙኃን የለም አሉ።

አምባሳደሩ ይህንን ያሉት ጥቅምት 26/2019 ዓ.ም. የሚዲያ ልህቀት ማዕከል ምረቃ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን የቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት አምባሳደር ሬድዋን ማንም ሚዲያ ከአምስት ጊዜ በላይ በማስረጃ ምን እንዳጠፋ፣ ምን እንዳጎደለ፣ የትኛውን ሕግ እንደጣሰ ሳይነገረው ማስጠንቀቂያ የተጻፈበት የለም ሲሉ ተናግረዋል።

አምባሳደሩ ይህን የተናገሩት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ሰኞ ዕለት ለ30 ዓመታት በሕትመት ላይ የቆየውን ሪፖርተር እና እንግሊዘኛውን 'ዘ ሪፖርተር' ጋዜጦች የሚያሳትመውን 'የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ሴንተር' የምዝገባ ምስክር ወረቀት "ላልተወሰነ ጊዜ" መታገዱን ካሳወቀ በኋላ ነው።

ባለሥልጣኑ በተቋሙ ሥር የሚታተሙት ጋዜጦች "ከህትመት እና ከሥርጭት ሙሉ በሙሉ ታግዶ እንዲቆይ" መወሰኑን ገልጿል።

በሪፖርተር ይዘቶች ላይ ከአንድ ዓመት በላይ ክትትል ማድረጉን እና ተደጋጋሚ "የሕግና የሙያ ሥነ ምግባር" ጥሰቶች እንደተፈጸሙ ማረጋገጡን የገለጸው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን፣ ጋዜጣውን "ላልተወሰነ ጊዜ" ማገዱን አስታውቋል።

ባለሥልጣኑ በሪፖርተር ላይ ካቀረባቸው ክሶች መካከል፤ ከብሔራዊ ጥቅም ጋር የሚጻረሩ ይዘቶችን ማሠራጨት፣ ከፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አውድ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ ያላቸውን ርዕሰ ጉዳዮች ማጮህ፣ በቁንጽል ዘገባዎች በኅብረተሰቡ ዘንድ ጥርጣሬና ብዥታ መፍጠር እና የሕዝቦችን አብሮነትና እሴት የሚሸረሽሩ መረጃዎችን ማስተላለፍ የሚሉት ይገኙበታል።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ዳይሬክተር የሆኑት አምባሳደሩ "በኃላፊነት የሚሰራ ሚዲያን እናበረታታለን" ካሉ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ የመገናኛ ብዙኃን ቁጥር መጨመሩን ተናግረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የሕትመት ሚዲያ ግን እየቀነሰ ሄዷል ያሉት አምባሳደሩ፤ ይህ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የሚታይ መሆኑን ጠቅሰዋል።

" 'ስንት ኤምባሲ ያውቀኛል፤ ስንት ፈረንጅ ይናገርልኛል፤ ስንት ገንዘብ ይዣለሁ፤ ስንት ዓመት ኖሬያለሁ' ብሎ ሕጉን እስከ ጥግ ተጠቅሞ ከሕጉ በላይ ግን መኖር አይቻልም" ሲሉም አስጠንቅቀዋል።

"አንዳንዶቹ 15 ጊዜ ያህል ተመክረዋል" ያሉት አምባሳደር ሬድዋን፣ በእያንዳዱም ቃለ ጉባዔ መያዙን አንስተዋል። "እያንዳንዱም ምን ምን እንዳጠፉ አይተው ለማስተካከል ቃል ገብተዋል" ሲሉ የመገናኛ ብዙኃኑ ስህተታቸውን ለማረም መስማማታቸውን ተናግረዋል።

ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተቋም 'ሂውማን ራይትስ ዎች' ሪፖርተር ጋዜጣ መታገድ የኢትዮጵያ መንግሥት "በአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን እና ሲቪል ምኅዳር ላይ እያካሄደ ያለው ጥቃት አካል ነው" ሲል መተቸቱ ይታወሳል።

ሂውማን ራይትስ ዎች ጥቅምት 25/2019 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ "አገሪቱ ውስጥ ከቀሩት ጥቂት ገለልተኛ ተቋማት አንዱ" ሲል በገለጸው ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ የተወሰደውን እርምጃ ተቃውሟል።

መንግሥት በመገናኛ ብዙኃን ላይ እየተከተለ ያለውን አካሄድ "በአፋጣኝ እንዲቀለብስ" ጉዳዩ የሚመለከታቸው የአገሪቱ አጋራት መንግሥትን እንዲወተውቱም ጥሪ አቅርቧል።

አምባሳደር ሬድዋን በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ውስጥ ያለው ፈተና በማለትም፣ አንዳንዶች ገንዘብ ስላላቸው ሚዲያ ከፍተዋል ስለ መገናኛ ብዙኃን ግን አያውቁም፤ የቀጠሩትን ሰው እንኳን ማንነት አያውቁትም ሲሉ ከስሰዋል።

የተቀጠረው ግለሰብ ከመገናኛ ብዙኃኑ ባለቤት ባሻገር ሙያዊ ኃላፊነት እንዳለበት የተናገሩት አምባሳደሩ "ሆን ተብለው አገር የማመሳቀል ሥራ የሚሰሩ አሉ" ካሉ በኋላ እጅግ አብዛኛው ግን ባለማወቅ ስህተት የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

"የኢትዮጵያን ጉዳይ በሚዛን የሚሰሩ" የውጭ ሚዲያዎች "ከኢቢሲ እኩል የሚስተናገዱ አሉ" በማለት አልጀዚራን በምሳሌነት ጠቅሰዋል።

የሚዲያ ፈቃድ የወሰደ ከአገሪቱ ፓርላማም ከአገሪቱ መንግሥትም በላይ የሆነ እንዳይመስለው ሲሉም አስጠንቅቀዋል።

"ሚዲያም ይተቻል፤ ይጠየቃል" ያሉት አምባሳደሩ በዘመቻ የሚሆን ነገር የለም በሥነ ስርዓት የሚሆን አብሮ መስራት ይኖራል ሲሉ ተናግረዋል።

"አርባ ጊዜ ተመክረህ፤ አርባ ጊዜ አጥፍተህ አንድ ጊዜ ማስጠንቀቂያ ሲሰጥህ ዙሪያውን ዘመቻ የምታደርግ ከሆነ ከኢትዮጵያ በላይ አቅም አለኝ ብሎ ማሰብ ይሆናል።"

የኢትዮጵያ ሕግ፣ ፍላጎት ምን ድን ነው? የእኔ ድርሻ ምን ይሆናል የሚለውን ማወቅ አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረው ስናጠፋ ማረም ያስፈልጋል ብለዋል።

አጥፍተው የታረሙ መገናኛ ብዙኃኖች መኖራቸውን ያስታወሱት አምባሳደሩ፣ እነዚህ መገናኛ ብዙኃን "አምስቴም ቢያጠፉ አምስቴም ይታረማሉ" በማለት ዋናው የሚታየው ለመታረም ዝግጁ መሆናቸው፣ ሆን ብለው "እንደ ርዕሰ አንቀጽ አስቦት" ነወይ የሚለው ወይስ ጋዜጠኛ ነው ያበላሸበት የሚለው እንደሆነ ጠቅሰዋል።

ባለቤት ነው ወይስ ጋዜጠኛ ነው ያጠፋው ወይስ አመራሩ የሚለው ተቆጥሮ፣ ስንት ጊዜ ነው የሚለው ተሰልቶ፣ መነሻው ምንድን ነው የሚለው ታይቶ፣ እርግጠኛ ካልተሆነ በስተቀር" የሚሳቀል ጋዜጠኛ አይኖርም። የሚቀጭጭም ሚዲያ አይኖርም" ብለዋል።

"አሁን ሁለት ሦስት ጋዜጠኛ በማንገላታት፤ አንድ እና ሁለት ሚዲያ በማገድ የኢትዮጵያን ዲሞክራሲ ማስፋት አይደለም፤ ዓላማው መማሪያ ማድረግ ነው" ሲሉም መንግሥት የሚወስደውን እርምጃ ተከላክለዋል።

አንድ ሚዲያ "በመንቀል" ሃሳብ ማዳፈን አይቻልም ያሉት አምባሳደሩ "አንድም ሚዲያ ቢሆን ግን ስርዓት አልበኛ ሲሆን ፣ ከሕግ በላይ ሲሆን ስርዓት ማስያዝ ካልተቻለ አይነኬነት ባህሪው ይሆናል" ሲሉ አብራርተዋል።

ባለፈው ዓመት የአዲስ ስታንዳርድ እና ዋዜማ ፈቃዶች የተሰረዙ ሲሆን፣ የውጭ መገናኛ ብዙኃን የዘገባ ፈቃድ መሰረዙ ይታወሳል።