ዋይት ሐውስ ሪፐብሊካኖች በምርጫው ከተሸነፉ በኋላ የውጭ ጉዳይ እና የመከላከያ ሚኒስትሮቹ ከሥልጣን ይለቅቃሉ መባሉን አስተባበለ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
ዋይት ሐውስ ከምርጫው በኋላ በትራምፕ መንግሥት ውስጥ ሊካሄድ በሚችል ሹም ሽር የተነሳ የመከላከያ ሚኒስትሩ ፒት ሄግሴት እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርኮ ሩቢዮ ከኃላፊነታቸው ሊነሱ ይችላሉ የሚሉ አሉባልታዎችን አስተባበለ።
ለሪፐብሊካን መሸነፍ እንደምክንያት የቀረበውን የኢራን ጦርነት የመሩበት መንገድ ላይ ከፍተኛ ትችት የሚቀርብባቸው የመከላከያ ሚኒስትሩ ሄግሴት ከሥልጣን እንዲነሱ ግፊቶች መኖራቸውን የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
የሥልጣን ዘመናቸው የሚያበቃ አንድ የሪፐብሊካን የኮንግረስ አባል፣ መከላከያ ሚኒስትሩ ከሥልጣን አንዲነሱ ድምጽ እንዲሰጥ እስከ ሚቀጥለው ሳምንት ድረስ ለማቅረብ ዝተዋል።
በምላሹ ሄግሴት በቪዲዮ በሰጡት መግለጫ፣ አፈጻጸማቸውን በመከላከል በእሳቸው ላይ የሚካሄደውን ዘመቻ አውግዘዋል።
"እንደምታዩት እነሱ እኔን ያጠቃሉ፤ እኛን የሚያጠቁት ምክንያቱም ውጤታማ ሆነን እየሰራን ስለሆነ ነው። ይህ አይሳካም፤ ወደ ኋላ አንልም" ብለዋል።
በሌላ በኩል፣ ማርኮ ሩቢዮ እንደ አውሮፓውያኑ ከ2028 የፕሬዚዳንትነት ምርጫ በፊት ከኃላፊነታቸው ለመልቀቅ እያሰቡ ነው የሚሉ ሪፖርቶችን አስተባብለዋል።
ሩቢዮ ለኒው ዮርክ ታይምስ በሰጡት ቃለ መጠይቅ፣ "እስከ ትራምፕ የሥልጣን ዘመን መጨረሻ ድረስ መስራት የሁልጊዜ ዕቅዴ ነው" ብለዋል።
"እየሠራሁት ያለውን ሥራ በጣም እወደዋለሁ። በተጨማሪም 'ሥራውን ሊለቅ ነው' መባሉን ስሰማ ሁሌ እስቃለሁ። እኔም 'የትኛውን ሥራ?' እላለሁ" ሲሉ ተናግረዋል።
ዋይት ሐውስ እና የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ሩቢዮ ከዚህ ሳምንት የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ሽንፈት በኋላ ሊለቁ ይችላሉ የሚሉ ዘገባዎችን "ሐሰተኛ ዜና" በማለት አጣጥለዋል።
ሆኖም የመከላከያ ሚኒስትሩ ፒት ሄግሴት የወደፊት የፖለቲካ ሕይወት እርግጠኝነት የሚታይበት አይመስልም።
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ምክትል ፕሬዚዳንት ጄዲ ቫንስ፣ ሪፐብሊካኖች በሴኔቱና በተወካዮች ምክር ቤት አብላጫ መቀመጫ እንዲያጡ ያደረገው የኢራን ጦርነት መሆኑን ተናግረዋል።
ትራምፕ ለኤቢሲ ኒውስ በስልክ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ስለ ሄግሴት "ጥሪዎች እንደደረሷቸው" ቢገልጹም፣ እሳቸውን በኃላፊነታቸው ለማቆየት "ሙሉ ፍላጎት" እንዳላቸው አክለዋል።
በኋላም ሐሙስ ዕለት በዋይት ሐውስ ለጋዜጠኞች ሲናገሩ፣ "ፒት ሄግሴት ድንቅ ሥራ ሰርቷል" ብለዋል። ትራምፕ የመከላከያ ሚኒስትሩ ስኬቶች ብለው ከዘረዘሯቸው መካከል ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ የቬንዙዌላው መሪ ኒኮላስ ማዱሮን መያዛቸውን እና አሁን ወደ ዘጠነኛ ወሩ የገባውን የኢራን ጦርነት ነው።
ዋሽንግተን ፖስት ሐሙስ ዕለት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የጦር ኃይሎች አዛዦች ኮሚቴ ሊቀመንበር የሆኑትን ጄኔራል ዳን ኬን ወይም የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ አዛዥ አድሚራል ብራድ ኩፐርን ከኃላፊነታቸው ለማንሳት እያጤኑ ሊሆን ይችላል ሲል ዘግቧል።
ሁለቱም ወታደራዊ መሪዎች ከስምንት ወራት በፊት በተጀመረው ጦርነት ዙሪያ ለመንግሥቱ ወሳኝ የሆነ ወታደራዊ ምክርና መመሪያ በመስጠት ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።
በሌላ በኩል፣ በተደጋጋሚ የትራምፕ ተቺ የሆኑት ሪፐብሊካን የተወካዮች ምክር ቤት አባል ቶማስ ማሴ መከላከያ ሚኒስትሩ ፒት ሄግሴት ከሥልጣናቸው እንዲወርዱ ለማድረግ የጀመሩትን ሥራ እንደሚያስቀጥሉ ተናግረዋል።
ማሴ ለፖሊቲኮ እንደተናገሩት፣ የመከላከያ ሚኒስትሩን ከሥልጣን ለማስወገድ የሚጠይቀውን ውሳኔ መጪው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ያቀርባሉ።
እንዲሁም በኤክስ ገጻቸው ላይ፣ ፕሬዚዳንት ትራምፕ በጥር ወር አዲሱ በዴሞክራቶች የበላይነት የሚያዘው ኮንግረስ ሥራ ከመጀመሩ በፊት ሄግሴትን መተካት እንዳለባቸው ጽፈዋል።
"አዲስ ተሿሚዎችን በሴኔቱ ለማጽደቅ እድሉ እያለው ይህን ማድረግ አለበት" ሲሉ ማሴ በኤክስ ልጥፋቸው ላይ አስጠንቅቀዋል።

































