ሪፐብሊካኖች ክፉኛ እንዲሸነፉ ያደረጉ አምስት ምክንያቶች

የትራምፕ ደጋፊ በቴክሳስ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

በአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ዴሞክራቶች ሁለቱንም ምክር ቤቶች በበላይነት የሚቆጣጠሩበትን ድል ተጎናጽፈዋል።

የፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ፓርቲ በዚህ ምርጫ ከመሸነፉም በላይ፣ የሪፐብሊካኖች የሽንፈት መጠን ፕሬዚደንቱ በዋይት ሀውስ ላሳለፉት ሁለት ዓመት በግልጽ የተሰጠ የተቃውሞ ውሳኔ እንደሆነ ተቆጥሯል።

ሪፐብሊካኖች ብዙ መቀመጫዎችን ያጡባቸው አምስት ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

1. የኑሮ ውድነት መባባስ

ከጫፍ እስከ ጫፍ ያሉ አሜሪካውያን መራጮች፣ በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረውን የመሠረታዊ አቅርቦቶች ዋጋ ለመቋቋም በትግል ላይ ያሉ ናቸው። ይህ ቁጣ ምርጫውን በሚወስኑ የአሜሪካ ግዛቶች ጭምር በተሰጠው ድምፅ በግልጽ ታይቷል።

"የነዳጅ ቢሆን የሸቀጣ ሸቀጦች ዋጋ፣ ሁሉም ነገር እየጨመረ ነው።" አንዲት የሰሜን ካሮላይና መራጭ ከምርጫው በፊት ለቢቢሲ የሰጠችው አስተያየት ነው።

በመሆኑም ወትሮውን የሪፐብሊካኖች ደጋፊ የሆነችው ይህች አስተያየት ሰጭ አሁን ግን ዴሞክራቶችን ለመምረጥ ወስናለች።

እስከ መስከረም ወር ድረስ ባለው አንድ ዓመት ውስጥ የመሠረታዊ አቅርቦቶች የዋጋ ግሽበት በ3.7 በመቶ ጨምሯል። ለዚህም ዋነኛው ምክንያት የነዳጅ እና የኃይል ዋጋ መጨመር ነው።

በመራጮች ላይ የተደረገ የዳሰሳ መረጃ እንደሚያሳየው፣ ከ10 መራጮች ውስጥ 8ቱ (79%) የሚሆኑት ባለፈው ዓመት የቀጠለው የዋጋ ንረት በእነርሱ እና በቤተሰቦቻቸው ላይ ከመካከለኛ እስከ ከባድ ደረጃ የሚደርስ ችግር እንዳስከተለ ተናግረዋል።

60 በመቶ የሚሆኑት መላሾች፣ ከተለመደው በጣም ከፍ ያለ የዋጋ ጭማሪ የተከሰተው በፕሬዚደንት ትራምፕ ፖሊሲዎች ምክንያት ነው በማለት ዶናልድ ትራምፕ ላይ ጣታቸውን ቀስረዋል።

2. ድጋፍ ያጣው የኢራን ጦርነት

የዋጋ ንረት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር ካደረጉት ዋና ምክንያቶች አንዱ፣ አሜሪካ እና እስራኤል በየካቲት ወር በኢራን ላይ የከፈቱት ጦርነት ነው።

ሁለቱ አገራት የከፈቱባትን ጦርነት ተከትሎ፣ ቴህራን በአጸፋው የሆርሙዝ ወሽመጥን መዝጋቷ የነዳጅ ዋጋዎች በፍጥነት ከፍ እንዲሉ አድርጓል። ይህ ቀጭን የባሕር መተላለፊያ ለዓለም የነዳጅ ዘይት እና ለፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ጉልህ ሚና ያለው ትልቅ የመጓጓዣ መስመር ነው።

ጦርነቱ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ ጀምሮ የአሜሪካ መራጮች የሆርሙዝ መዘጋት ባሳደረው ጫና በነዳጅ ማደያዎች ከፍተኛ ገንዘብ እየከፈሉ ቀጥለዋል።

በመሆኑም ይህ ጦርነት በአብዛኞቹ አሜሪካውያን ዘንድ ድጋፍ አላገኘም። በተጨማሪም ለሪፐብሊካን ደጋፊዎች፣ የጦርነቱ መጀመር "አሜሪካ ትቅደም" በሚል መፈክር ሥር "ተጨማሪ ጦርነቶች አይኖሩም" የሚለውን የትራምፕ የምርጫ ዘመቻ ቃል የጣሰ እንደሆነ ተሰምቷቸዋል።

በመራጮች ዳሰሳ ውስጥ ከተጠየቁት ሰዎች 63 በመቶ ያህሉ፣ አሜሪካ በኢራን ላይ ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ የወሰነችው ውሳኔ የተሳሳተ ነበር ብለው ያምናሉ።

74 በመቶ የሚሆኑ መራጮች፣ የኢራኑ ጦርነት ለኮንግረስ የሚሰጡትን ድምፅ በከፍተኛ ደረጃ የሚወስን ምክንያት እንደሆነ ተናግረዋል።

ከምርጫው በኋላ ትራምፕ ለፎክስ ኒውስ በሰጠው ቃለ መጠይቅ፣ ጦርነቱ ለፓርቲያቸው ሽንፈት ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ቢያምኑም፣ ኢራን የኒውክሌር መሣሪያ እንዳትታጠቅ ለማድረግ ወደ ጦርነት ከመግባት በቀር ምርጫ አልነበረም ሲሉ በአጽንኦት ገልፀዋል።

3. የዴሞክራቶች የተቀናጀ መልዕክት እና ቅስቀሳ

ዴሞክራቶች ጠንካራ ዕጩዎችን በማቅረብ በተለምዶ የሪፐብሊካኖች የምርጫ ቀጣናዎች በሚባሉ ግዛቶች ጭምር በስፋት እና በጥልቀት ያደረጉት የቅስቀሳ ዘመቻ ማዕበል የምርጫውን ውጤት ከወሰኑ ዋነኛ ጉዳዮች አንዱ ነው።

እነዚህ እጩዎች በኑሮ ውድነት እና በጤና አገልግሎት ተደራሽነት ዙሪያ በተቀናጀ ሁኔታ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ይህ የተቀናጀ የቅስቀሳ ዘመቻቸው፣ የቀድሞው መምህር ጀምስ ታላሪኮ እና ፓስተር አዳም ሃሚልተን በቅደም ተከተል በቴክሳስ እና በካንሳስ ከመራጮች ጋር ጥሩ ግንኙነት ፈጥረው እንዲያሸንፉ አስችሏቸዋል። በሌላኛው የሪፐብሊካኖች ግዛት በደቡብ ካሮላይናም ዴሞክራቷ አኒ አንድሪውስ ያልተጠበቀ ድል አስመዝግባለች።

የቀድሞ የሕፃናት ሐኪም የነበረችው አንድሪውስ፣ ትኩረቷን በተመጣጣኝ ዋጋ በሚገኝ የጤና አገልግሎት ላይ በማድረግ ብዙዎች የጤና ሥርዓቱ ተበላሽቷል ብለው በሚያምኑባት አገር የመራጮችን ድጋፍ ማግኘት ችላለች።

በጆርጂያ ዳግም ምርጫ ያሸነፈው የዴሞክራቶች ሴናተር ጆን ኦሶፍ ደግሞ፣ የኑሮ ውድነትንና ሙስናን የዘመቻው ማዕከላዊ መልዕክት አድርጎ ተንቀሳቅሷል።

39 ዓመቱ ፖለቲከኛ፣ ትራምፕ ሁለት ጊዜ ባሸነፈባት ግዛት በቀላሉ ድል ማስመዝገብ መቻሉ፣ እንደ አውሮፓውያኑ በ2028 ለፕሬዚደንትነት ሊወዳደር ይችላል የሚሉ ግምቶችን ይበልጥ አጠናክሯል።

ፕሬዝደንት ትራምፕ ራሱ "ጥሩ ሥራ ሰርተዋል" ሲሉ ዴሞክራቶችን በማድነቅ ተናግረዋል።

4. የትራምፕ ተወዳጅነት መቀነስ

በመራጮች ላይ ከፍተኛ ቅሬታ ያሳደሩባቸው ሁለቱ ዋና ዋና ጉዳዮች ማለትም የዋጋ ንረት እና የኢራን ጦርነት በቀጥታ ከፕሬዚደንቱ ጋር የተያያዙ ናቸው።

ይህም የትራምፕ ተወዳጅነት እንዲቀንስ ማድረጉ በሪፐብሊካኖች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል።

የትራምፕ የተቀባይነት ደረጃ በሪፐብሊካን መራጮች መካከል ጭምር መቀነሱ፣ በ2024 የደገፏቸው አንዳንድ ግዛቶች ሳያመነቱ ፊታቸውን ወደ ዴሞክራቶች እንዲያዞሩ አድርጓል።

ትራምፕ ደጋፊዎቻቸውን ለማነቃቃት በማሰብ፣ እርሳቸው በምርጫው ላይ በቀጥታ ተወዳዳሪ እንደሆኑ አድርገው እንዲያስቡ ቢጠይቁም ውጤት አላስገኘላቸውም።

እንዲያውም የምርጫው ውጤት፣ ከ10 ዓመታት በላይ በአሜሪካ ፖለቲካ ተፅዕኖ ፈጣሪ የነበሩት የትራምፕ ፖለቲካዊ 'ብራንድነት' እየደበዘዘ መምጣቱን የሚያመለክት እንደሆነ አንዳንዶች ገልፀዋል።

እናም የሕዝብ ቁጣ እየጨመረ በመጣበት ሁኔታ፣ ራሳቸውን የሪፐብሊካኖች የምርጫ ዘመቻ ዋና ትኩረት ማድረጋቸው አደገኛ ውሳኔ ሲሆን በመጨረሻም እርሳቸው ካሰቡት በተቃራኒው መልስ አግኝቷል።

5. የስፓኒሽ ተናጋሪዎች እና የጥቁር መራጮች ዳግም መቀየር

ከሁለት ዓመታት በፊት በነበረው ምርጫ ላይ የአንዳንድ የስፓኒሽ ተናጋሪዎች እና ጥቁር መራጮች ወደ ሪፐብሊካኖች ማዘንበል ትራምፕ አሳማኝ ድል እንዲቀዳጁ ረድቷቸው ነበር። በአሁኑ የአማካይ ዘመን ምርጫ ላይ ግን ይህ አዝማሚያ የተቀየረ ይመስላል።

ዴሞክራቶች በቴክሳስና በሜክሲኮ ድንበር አካባቢ በሚገኙ እና አብዛኛው ሕዝባቸው ስፓኒሽ ተናጋሪ (ሂስፓኒክ) በሆነባቸው ሦስቱም የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልሎች ድል አድርገዋል።

በኒውዮርክ ታይምስ ትንታኔ መሠረት፣ አብዛኛው ነዋሪዎቻቸው ሂስፓኒክ በሆኑ አካባቢዎች ከ2024ቱ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ጋር ሲነጻጸር ለሪፐብሊካን የሴኔት እጩዎች የተሰጠው ድምፅ ከ22 በመቶ በላይ ቀንሷል።

ይህ ለውጥ የመጣው ስደተኞችን የሚመለከተውን ሕግ ከማስከበር ሂደቶች ጋር በተገናኘ የተነሱ ቁጣዎች በተስፋፉበት ሁኔታ ነው።

የፒው ምርምር ማዕከል ያደረገው ጥናት እንደሚያሳየው፣ 56 በመቶ የሚሆኑ አሜሪካውያን በኢሚግሬሽን እና የጉምሩክ ሕጎች አስፈጻሚ ተቋም (አይስ) ላይ አሉታዊ አመለካከት አላቸው።

አብዛኛው ሕዝባቸው ጥቁር የሆኑ አካባቢዎችም በሴኔት ምርጫዎች ላይ በግልፅ ለዴሞክራቶች እጩዎች ድጋፋቸውን ሰጥተዋል።

ለአብነትም ከሁሉም ግዛቶች በላቀ 37 በመቶ ገደማ ጥቁር መራጮች ባሏት ወትሮውን የሪፐብሊካኖች ግዛት ሚሲሲፒ ለሴኔቱ በሚደረገው ውድድር እስካሁን በተቆጠሩት ድምጾች እጅግ ተቀራራቢ ውጤት ተመዝግቧል።

ዴሞክራቶችን ወክሎ የሚወዳደረው ስኮት ኮሎም በጥቂት ድምጾች በመምራት ላይ ሲሆን፣ ማሸነፍ ከቻለ እአአ ከ1982 ወዲህ በሚሲሲፒ ግዛት ለአሜሪካ ሴኔት የሚመረጥ የመጀመሪያው ዴሞክራት ይሆናል።