በአሜሪካ የዴሞክራቶች ድል መቀዳጀት ለኢትዮጵያውያን ስደተኞች ምን ዕድል ይዞ ይመጣል?

ጥቁር አሜሪካውያን ድምጽ ሲሰጡ
የምስሉ መግለጫ, ምስል ከክምችት
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

በአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ዴሞክራቶች አብላጫ ድምጽ በማግኘት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ማሸነፍ ችለዋል።

በዚህ ምርጫ ዴሞክራቶች 228 መቀመጫ ሲያገኙ ሪፐብሊካኖች ደግሞ 139 መቀመጫ አግኝተዋል። በሴኔቱ (በላይኛው ምክር ቤትም) ዴሞክራቶች እየመሩ ነው።

ለትራምፕ አስተዳደር እንደ "ሕዝበ ውሳኔ" ተደርጎ በታየው የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ዴሞክራቶች ማሸነፋቸው ለስደተኞች ትልቅ ተስፋ የሰጠ ይመስላል። የትራምፕ አስተዳደር በስደተኞች ላይ ጥብቅ ፖሊሲ እያራመደ ሲሆን በሚወስዳቸው እርምጃዎች ሲተችም ቆይቷል።

ባለፈው ዓመት፣ ከሦስት ዓመት በፊት ኢትዮጵያውያን በጊዜያዊ የሕግ ጥበቃ በአገሪቱ ውስጥ እንዲኖሩ የተፈቀደበትን አሠራር እንዲያበቃ ያደረገ ሲሆን ሰኔ ወር ላይም የአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይህንኑ የሚደግፍ ውሳኔ አስተላልፏል።

ጊዜያዊ የሕግ ጥበቃ መብት የሚሰጠው በአገራቸው ግጭት፣ የተፈጥሮ አደጋ ወይም ሌላ ለደኅንነታቸው አስጊ የሆነ የተለየ ክስተት ካለባቸው አገራት ለመጡ ስደተኞች ነው።

ከዚህም ባሻገር የትራምፕ አስተዳደር ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ የአፍሪካ አገራት ላይ የቪዛ ገደቦችን ጥሏል። በአሜሪካ የሚገኙ ሕገ ወጥ ስደተኞችን ለመቆጣጠር በሚወስደው ያልተመጣጠነ እርምጃም ሲወቀስ እና ሲከሰስ ቆይቷል።

አሁን ላይ ዴሞክራቶች በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አብላጫ መቀመጫ ማግኘታቸው ይህን ሊለውጥ ይችላል በሚል በርካቶች ተስፋ አድርገዋል። በእርግጥ የዴሞክራቶች ድል ይህን ማድረግ ይችላል? ምክር ቤቶቹን በአብላጫ መያዛቸውስ ለኢትዮጵያውያን እና ሌሎች ስደተኞች ምን አንደምታ ይኖረዋል?

በአሜሪካ ሜኔሶታ ግዛት የኢሚሬሽን ጠበቃ አቶ ሙሉአለም ጌታቸው፣ ዴሞክራቶች በምክር ቤት በጀትን ጨምሮ ሌሎች ጉዳዮች ላይ ውሳኔ የማሳለፍ ሥልጣን ቢኖራቸውም፣ ጥብቅ የሆነ ስደተኞችን የሚደግፍ ፖሊሲ ላያራምዱ እንደሚችሉ ይናገራሉ።

Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ለዚህ ምክንያታቸውን ሲያስቀምጡ የትራምፕ አስተዳደር ሕገ ወጥ ስደተኞችን ለማስቆም የሚከተለውን ሒደት ዴሞክራቶች "ሙሉ በሙሉ የሚቃወሙ አይደሉም" ይላሉ።

ዴሞክራቶች በተለይ በቀድሞው ፕሬዚደንት ጆ ባይደን አስተዳደር ወቅት ድንበሮችን በመክፈት ሕገ ወጥ ስደተኞች ወደ አገሪቱ እንዲገቡ አድርገዋል በሚል በሪፐብሊካኖች ይከሰሳሉ።

በዚህም ምክንያት አሁን ላይ ዴሞክራቶች ቢያሸንፉም ስደተኞችን የሚደግፍ ሴኔት እና ምክር ቤት የመምጣቱ ዕድል በጣም አነስተኛ እንደሚሆን አቶ ሙሉዓለም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ሪፐብሊካኖች በዚህ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ በሰፊ ልዩነት መሸነፋቸው ፓርቲውን ያስደነገጠ ቢሆንም፣ ከሪፐብሊካኑ ትራምፕ አስተዳደር ጋር የሻከረ ግንኙነት ያላቸው አገራት መሪዎች ውጤቱን በተስፋ ተቀብለውታል። አንዳንድ መሪዎች እንደ አዲስ ምዕራፍ እየተመለከቱት ነው።

በኮሎራዶ የሪፐብሊካን ተወካይ እና የአውሮራ ከተማ የቀድሞ ምክር ቤት ተወካይ አምሳሉ ፀጋዬ ካሳው፣ "ውጤቱ ያልተጠበቀ እና የሚያስደነግጥ ነው" ብለዋል።

ብዙ ጊዜ በአጋማሽ ዘመን ምርጫ የአንዱን ምክር ቤት አብላጫ መቀመጫ ማጣት ሊኖር ይችላል የሚሉት የቀድሞ የምክር ቤት አባል፣ በዚህ ምርጫ የነበረው ግምት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አብላጫ መቀመጫ ይታጣል የሚል እንደነበር ይናገራሉ።

ሆኖም በሴኔቱም፣ በምክር ቤቱም አብላጫ ማጣቱ ለፓርቲው መደናገጥን የፈጠረ እንደሆነ አስረድተዋል።

በሁለቱም ምክር ቤቶች ዴሞክራቶች ማሸነፋቸው ግን በፖሊሲ ረገድ እምብዛም የሚለውጠው ነገር እንደሌለ ይናገራሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት በትራምፕ አስተዳደር የተጣሉ ጥብቅ የቪዛ ገደቦችን፣ የስደተኞች ጊዜያዊ ከለላ ፈቃድን፣ የስደተኞች ጉዳይ መጓተትን እና ዲቪን ጨምሮ ሌሎች የስደተኞች ጉዳዮችን በተመለከተ ለውጥ አይኖርም።

ይህንንም ሲያስረዱ "የተለወጠው ሕግ አውጭው እንጂ የሕግ አስፈፃሚው አካል መርሆዎች አይደሉም" ብለዋል።

ቀድሞውኑም በቪዛ እና በሌሎች የኢሚግሬሽን ጉዳዮች ላይ ምንም የተለወጠ ነገር አልነበረም፤ ጥብቅ የሆነ የማጣራት ሥራ ነው እየተከናወነ ያለው የሚሉት የቀድሞ የምክር ቤት አባሉ፣ ዴሞክራቶች በሁለቱም ምክር ቤት አብላጫ መያዛቸው ምንም የሚለውጠው ነገር እንደሌለ ገልጸዋል።

"ሕጎችን በማውጣት እና ውሳኔዎችን በማሳለፍ ጫና ለማሳደር ቢሞክሩም እንኳን ፕሬዚደንቱ የበላይ ውሳኔ ሰጪ ስለሆኑ የሚለወጥ ነገር አይኖርም" ብለዋል።

በመሆኑም እንደ የምክር ቤት አባሉ ገለጻ፣ ለቀጣዩ ሁለት ዓመታት ምክር ቤቶቹ በበጀት ጉዳይ፣ ፕሬዚደንቱን ከሥልጣን ስለማባረር ወይም የተለያዩ የካቢኔ አባላትን ወደ ምክር ቤት በማምጣት የመፋጠጫ ጊዜ ነው የሚሆነው።

በአሜሪካ ሜኔሶታ ግዛት የኢሚሬሽን ጠበቃ አቶ ሙሉዓለም በበኩላቸው ዴሞክራቶች ማሸነፋቸው ፕሬዚደንቱ በሚፈፅሟቸው ፖሊሲዎች ላይ ድርድር ለማድረግ ዕድል ይሰጣቸዋል ብለዋል።

"ፕሬዚደንቱ የፈለገ ፖሊሲ ቢያራምዱ ምክር ቤቱ እና ሴኔቱ ይሁንታ ካልሰጠው ትርጉም አይኖረውም" ይላሉ።

ሆኖም የኢሚግሬሽን እና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ፕሬዚደንቱ ሥልጣን ላይ የሚወድቅ ስለሆነ የትራምፕ አስተዳደር ውሳኔ ያሳለፈባቸው የቪዛ ገደቦች፣ የስደተኞች ጊዜያዊ ከለላ፣ የስደተኞች የጥገኝነት ጥያቄ መጓተትን ያስወግዳል ማለት እንዳልሆነ ያስረዳሉ።

በሌላ በኩል ግን የዴሞክራቶች ማሸነፍ ሪፐብሊካኖች በአገር አቀፍ ደረጃ ድጋፍ እንደሌላቸው ሊያሳይ ይችላል የሚሉት ጠበቃ ሙሉዓለም፣ ሪፐብሊካኖች በቀጣይ ምርጫ በተለይ ነጭ ያልሆኑ ዜጎችን ድምጽ ለማግኘት የኢሚግሬሽን ፖሊሲያቸውን ለማላላት እንዲያጤኑ ሊያደርጋቸው ይችላል ብለዋል።

አቶ አምሳሉም ከዚህ የራቀ ሐሳብ የላቸውም።

ሪፐብሊካኖች ወትሮውንም "ስደተኞች ጠል አይደሉም" የሚሉት አቶ አምሳሉ፣ የኢሚግሬሽን ሕጎች መጥበቅ እና ቁጥጥር መደረጉ ስደተኞቹ ራሳቸው ለደኅንነታቸው ሲሉ እንደሚፈልጉት በመግለጽ፣ የምርጫው ውጤት ከኢሚግሬሽን ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የመጣ እንዳልሆነ ያስረዳሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት በዚህ ምርጫ ሪፐብሊካኖች የተሸነፉት ከኢራን ጦርነት እና ከኢኮኖሚ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ነው።

በመሆኑም የዴሞክራቶች ማሸነፍ በኢሚግሬሽን ፖሊሲ ላይ የሚያመጣው ለውጥ አይኖርም ብለዋል።

በጆ ባይደን አስተዳዳር ጊዜ የተጀመረው እና በጦርነት ውስጥ ላሉ ዜጎች የሚሰጠው ጊዜያዊ ከለላ ላይ የሪፐብሊካኖች አቋም መለወጥ አለበት ብለው የሚያምኑት አቶ አምሳሉ፣ በኢትዮጵያ እንዲሁም በሌሎች አገራት ያሉት የግጭት እና የጦርነት ሁኔታዎች ታይተው ውሳኔው እንደገና ሊጤን እንደሚችል ገምተዋል።

ከሁለት ዓመት በኋላ ምርጫ ስለሚመጣም ፕሬዚደንቱ ሴኔቱ ጫና ባያሳድርም ካቢኔያቸው የየአገራቱን ሁኔታ በመመልከት የጊዜያዊ ከለላ ዕድሎችን እንደሚከፍት ያምናሉ።

በአሜሪካ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (የታችኛው ምክር ቤት) እና የላይኛው ምክር ቤት (ሴኔት) አንድ ላይ የያዘ ነው።

የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱ ምርጫ በየሁለት ዓመቱ እና በፕሬዝዳንት የአራት ዓመት የሥልጣን ዘመን አጋማሽ ላይ የሚደረግ ነው።

የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት የፌደራል ሕጎችን የማውጣት፣ ጦርነት የማወጅ፣ የግብር አሰባሰብ እና ሌሎች ሕግ አስፈፃሚ አካላትን የመቆጣጠር እና የመጠየቅ ሥልጣን አለው።