ተጠባቂ የሆነው የአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ምንድን ነው?

አሜሪካ ዐይን የተጣለበትን የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ማክሰኞ ጥቅምት 24/2019 ዓ.ም. ታካሂዳለች። መራጮች ድምፅ ሲሰጡ በቀሪው ሁለት ዓመት የዶናልድ ትራምፕ የፕሬዝዳንትነት ዘመን ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ይኖረዋል።
የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ምንድን ነው?
ጥቅምት 24/2019 ዓ.ም. አሜሪካዊያን የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት (ኮንግረስ) አባላትን ይመርጣሉ።
የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (የታችኛው ምክር ቤት) እና የላይኛው ምክር ቤት (ሴኔት) አንድ ላይ የያዘ ነው።
ምርጫው በየሁለት ዓመቱ እና በፕሬዝዳንት የአራት ዓመት የሥልጣን ዘመን አጋማሽ ላይ ስለሚደረግ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ የሚል ስያሜ አለው።
የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ቁልፍ ሥራው ሕጎችን በማውጣት በመላው አገሪቱ እንዲተገበሩ የፌደራል ሕግ ማፅደቅ ነው።
የዘንድሮው የአጋማሽ ዘመን ምርጫ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱን የፕሬዝዳንት ትራምፕ ሪፐብሊካን ፓርቲ ወይም የዲሞክራቶች ፓርቲ እንደሚቆጣጠረው እና ፕሬዝዳንቱ ውጥናቸውን ለመተግበር ምን ያህል እንደሚቀላቸው የሚወስን ነው።
ውጤቱ እስካሁን ባለው የፕሬዝዳንቱ አፈፃፀም ዙሪያ ሰዎች ምን ያህል ደስተኛ እንደሆኑ መለኪያ ተደርጎ ይታያል።
ዕጩዎች እነማን ናቸው?
የታችኛው የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት (የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት) ሁሉም 435 አባላት ይመረጣሉ። ሁለት ዓመት ቋሚ የሥልጣን ዘመን አላቸው። ምክር ቤቱ ረቂቅ ሕጎች የሚቀርቡበት እና ሙግት የሚደረግበት ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከ100 መቀመጫዎች 35ቱ የላይኛው ምክር ቤት (ሴኔት) አሸናፊዎቻቸውን እየተጠባበቁ ነው።
ሴናተር የሚባሉት የዚህ ምክር ቤት አባላት ስድስት ዓመት የሥልጣን ዘመን አላቸው። ከሌሎች ተግባራት በተጨማሪ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚቀርቡ ሕጎችን ያፀድቃሉ ወይም ውድቅ ያደርጋሉ።
ጥቅምት 24 በመላው አሜሪካ የሚገኙ አብዛኞቹ መራጮች በተጨማሪም ሌሎች ፖለቲከኞችን ይመርጣሉ።
በካሊፎርኒያ፣ ፍሎሪዳ፣ ጆርጂያ እና ሚሽጋን የግዛት ገዢዎች ምርጫ ዐይን ከተጣለባቸው የምርጫው ሂደቶች መካከል ናቸው።
ቁልፍ ጉዳዮቹ የትኞቹ ናቸው?
በነዳጅ፣ በሸቀጦች፣ በመኖሪያ ቤት እና በጤና አገልግሎት ዋጋ እየተቸገሩ ላሉ መራጮች የአሜሪካ ምጣኔ ሃብት ሐሳባቸው ውስጥ ነው።
ባለፈው ዓመት የካቲት ወር አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ በከፈቱት ጦርነት ምክንያት ግማሹ የዋጋ ግሽበት የአገሪቱ ግምጃ ቤት ካስቀመጠው አሐዝ በላይ እንደሆነ ቀጥሏል።
ዲሞክራቶች የፕሬዝዳንት ትራምፕ የንግድ ታሪፎች ለአሜሪካዊያን ዋጋ እንዲያሻቅብ አድርጓል ብለው ይሞግታሉ።
የስደተኞች ጉዳይ ሌላኛው ቁልፍ ነገር ነው። ሪፐብሊካኖች ትራምፕ በ2024ቱ የምርጫ ዘመቻቸው ወቅት ቃል የገቧቸውን ጥብቅ የድንበር ቁጥጥር እና ሕገ ወጥ ስደተኞችን በቁጥጥር ሥር ማዋል አሳክተናል ይላሉ።
በቅርብ ሳምንታት ደግሞ በሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ቁጥጥር ላይ ስጋቶች ብቅ ብለዋል።
ከሁለቱም ፓርቲዎች ከፍተኛ ፖለቲከኞች ቁጥጥር እንደሚያስፈልግ ተስማምተዋል። ይህም የቴክኖሎጂውን እድገት በሕግ ማሰር ነው ብለው ውድቅ ካደረጉት ዶናልድ ትራምፕ በተቃራኒ አድርጓቸዋል።
ምርጫው ምን ይለውጣል?
የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት (ኮንግረስ) ከአሜሪካ ሦስት የመንግሥት ቅርንጫፎች አንዱ ነው። ምክር ቤቱን መቆጣጠር የሕግ ቅርፆችን ለመለወጥ ወሳኝ ነው።
በአሁኑ ወቅት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የላይኛው ምክር ቤት (ሴኔት) ሁለቱም በሪፐብሊካን ፓርቲ ቁጥጥር ሥር ይገኛሉ።
ብልጫው ግን በቀጭን መስመር የተሰመረ ነው። ሪፐብሊካኖች የተወካዮች ምክር ቤትን ለመቆጣጠር የሚያስፈልገው ዝቅተኛው 218 ወንበሮች አሏቸው። በተጨማሪም አንድ የግል ተመራጭ ደግሞ የድምፅ ድጋፍ ይሰጣቸዋል።
በላይኛው ምክር ቤት (ሴኔት) ደግሞ 53 መቀመጫዎች አሏቸው። ይህ ምክር ቤት የሚለወጠው ዲሞክራቶች 51 መቀመጫዎችን ካሸነፉ ነው። ይህም ማለት 50/50 መቀመጫዎች ካሏቸው ምክትል ፕሬዝዳንቱ የመጨረሻውን ድምፅ መስጠቱን መቀልበስ አለባቸው።
ዲሞክራቶች ቢያንስ አንደኛውን ምክር ቤት ከተቆጣጠሩ የራሳቸውን ሕጎች ለማቅረብ ሥልጣኑን ያገኛሉ።
ማን ሊያሸንፍ ይችላል?
ከዚህ ቀደም በተደረጉ የአጋማሽ ዘመን ምርጫዎች መራጮች በዚህ ሂደት የፕሬዝዳንቱን ፓርቲ "ሲቀጡ" ተስተውሏል።
በቅርብ የተሰበሰበ የሕዝብ አስተያየት የፕሬዝዳንት ትራምፕ የቅቡልነት አሐዝ መውረዱን ያሳያል።
'ሲልቨር ቡለቲን' የተባለው የአስተያየት መሰብሰቢያ ድረ ገፅ ሁለተኛ የሥልጣን ዘመናቸውን በ50 በመቶው ቅቡልነት የጀመሩት ትራምፕ፤ ድጋፋቸው በጥቅምት መጀመሪያ ወደ 37 በመቶ ማሽቆልቆሉን ያሳያል። ይህ በእንዲህ እንዳለ 61 በመቶዎቹ ደግሞ አይቀበሏቸውም።
ይሁን እንጂ በምክር ቤቶች የሚገኙ ሁሉም መቀመጫዎች ለፉክክር ክፍት አይደሉም። አንዳንዶች ለሪፐብሊካኖች ወይም ለዲሞክራቶች አስተማማኝ ናቸው።
በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ኒውስ ወሳኝ የሆኑ 10 የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ፉክክሮችን ለይቷል።
እንደ አይዋ እና ኒው ሀምፕሻየር ባሉ ግዛቶች እና አሪዞና እና ኦሃዮን በመሰሉ ግዛቶች የሚገኙ 42 የተወካዮች ምክር ቤት ፉክክሮች ቀልብ የሚስቡ ናቸው ብሏል።
በተወካዮች ምክር ቤት የምርጫ ወረዳዎች አከላለል ውዝግብ ምክንያት የዘንድሮው ምርጫ ሊገመት የሚችል አይደለም።
ሪፐብሊካኖች በተወሰኑ ግዛቶች ወደ እነርሱ ያጋደለ የምርጫ ካርታ ያዘጋጁ ሲሆን፤ ዲሞክራቶችም ይህኑ ፈለግ ተከትለዋል።
ይህ ምርጫ ለትራምፕ ምን ማለት ነው?
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትንም ሆነ ሴኔቱን ዲሞክራቶች ቢያሸንፉ ትራምፕ ወደ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱ የትኛውንም ሕግ ለመውሰድ ይቸገራሉ።
ስለዚህ በአገር ውስጥ ፖሊሲዎቻቸው ችግር ይገጥማቸዋል። ቢሆንም ግን ትራምፕ ሥልጣናቸውን ማስፈፀሚያ ሌሎች መንገዶችን አግኝተዋል።
ዲሞክራቶች አንዱንም ምክር ቤት ቢቆጣጠሩ የትራምፕን አስተዳደር የሚመረምሩ ኮሚቴዎችን ለማቋቋም ሊጠቀሙበት ይችላሉ። የሙስና ክሶች፣ የዋይት ሐውስ አዲስ አዳራሽ እና የድንበር እና የጉምሩክ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን (አይስ) አካሄዶች የምርመራ አጀንዳዎች ሊሆኑ ይችላሉ።
በዲሞክራቲክ ፓርቲ ውስጥ ትራምፕ ይከሰሱ ወይስ አይከሰሱ የሚል ክርክር አለ። ይህም በኮንግረሱ ውስጥ የወንጀል ክስ ሳይሆን ፖለቲካዊ ክስ መመሥረት ማለት ነው።
ምክር ቤቶቹ ሪፐብሊካን ፓርቲ በቁጥጥሩ የሚያቆያቸው ከሆነ ትራምፕ በሥልጣን ቆይታቸው የሚፈልጓቸውን ዕቅዶች ማስፈፀም ይችላሉ።
ለ2028ቱ ፐሬዝዳንታዊ ምርጫስ ምን ማለት ነው?
በዘንድሮው የአጋማሽ ዘመን ምርጫ የፕሬዝዳንቱ ስም በምርጫ ወረቀቱ ላይ ባይኖርም፤ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ደጋፊዎቻቸው እሳቸው እንዳሉ በማሰብ እንዲመርጡ አሳስበዋል።
በየትኛውም አቅጣጫ ከምርጫው የሚገኝ ውጤት መራጮች በዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር አገራቸው የተጓዘችበትን አቅጣጫ በሚመለከት ምን እንደሚሰማቸው ማሳያ ነው የሚሆነው።
ትራምፕ ለሦስተኛ ጊዜ ፕሬዝዳንት ሆነው መወዳደር ስለማይችሉ፤ ከአጋማሽ ዘመን ምርጫው በኋላ እሳቸውን በ2028ቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዕጩ በመሆን የሚተካው ማን እንደሆነ እና በዲሞክራቶች በኩል ይህን ሰው የሚፎካከረውን ዕጩ ለመተንበይ መንገዱ ክፍት ይሆናል።
































