እስራኤል በጋዛ በፈፀመችው ጥቃት ሕፃናትን ጨምሮ ስምንት ሰዎች ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
እስራኤል በጋዛ በፈፀመችው የአየር ጥቃት ሕፃናትን ጨምሮ ቢያንስ ስምንት ሰዎች መገደላቸውን ሆስፒታሎች አስታወቁ።
ጥቃቱ የተፈፀመው በእስራኤል እና ሐማስ መካከል አንድ ዓመት የሞላው የተኩስ አቁም ስምምነት እያለ ነው።
በሰሜናዊ ጋዛ ከተማ አል-ሪማል በተባለ የመኖሪያ መንደር በተሰባሰቡ ንፁኃን ሰዎች ላይ በተፈፀመ የሚሳኤል ጥቃት የአራት ዓመት ሕፃንን ጨምሮ ሦስት ሰዎች መገደላቸውን የሆስፒታል ኃላፊዎች ተናግረዋል።
በከተማዋ ደቡባዊ አካባቢ ኻን የኑስ ደግሞ የፖሊስ መኮንኖችን ዒላማ ባደረገ የድሮን ጥቃት የዕለት ተዕለት ኃላፊነታቸውን እየተወጡ የነበሩ አምስት ሰዎች መገደላቸውን ሐማስ መሩ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
የእስራኤል ጦር ወታደራዊ ተልዕኮዎች ብሎ በገለፀው እርምጃ ሁለት ጥቃቶችን መፈፀሙን ተናግሯል። ይሁን እንጂ ማስረጃም ሆነ ተጨማሪ መረጃ አልሰጠም።
ከጋዛ ከተማ ወጣ ብሎ የሚገኘው በሺፋ ሆስፒታል በነጭ ጨርቅ ከተሸፈኑ ሁለት ሰዎች እና አንድ የሕፃን ልጅ አስከሬን ጎን የተሰባሰቡ በርካታ ሰዎች የፀሎት ሥነ ስርዓት ሲያደርጉ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምሥል ተሰራጭቷል።
ቤተሰቦቻቸው የተገደሉባቸው አሊ ኦዊስ ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል ኤኤፍፒ "ልጄ እና የእርሱ ልጅ መስዋዕት ሆነዋል። ማንንም ሳያስቸግሩ ድንኳናቸው ውስጥ ተቀምጠው ነበር፤ እና በድንገት ሚሳኤል መጥቶ ሲመታቸው በአካባቢው ምንም የተፈጠረ ነገር አልነበረም። ሰማዕት ሆነዋል" ሲሉ ተናግረዋል።
"ምንም የተኩስ አቁም የለም። ጦርነቱ እንደቀጠለ ነው፤ እያያችሁ አይደል?"
ኻን ዩኑስ በሚገኘው ናሰር ሆስፒታል አስከሬኖች መሬት ላይ ሆነው የሚያለቅሱ ሴቶችን የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምሥል ተለቅቋል።
የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስቴር በጥቃቱ የተገደሉ የአምስቱንም የፖሊስ መኮንኖች ሥም ዝርዝር ይፋ ያደረገ ሲሆን፤ ሟቾቹ ከ23 እስከ 53 ዓመት እድሜ ያላቸው ናቸው።
ሚኒስቴሩ ጥቃቱን "ዘግናኝ ጭፍጨፋ" ብሎታል።
በጋዛ የተኩስ አቁም ባለፈው ዓመት ጥቅምት ላይ ስምምነት ቢደረስም የእስራኤል የአየር ጥቃቶች በየቀኑ እንደቀጠሉ ናቸው።
ከተኩስ አቁም ስምምነቱ በኋላ 1,580 ሰዎች መገደላቸውን በሐማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል። የሚኒስቴሩ አሃዛዊ መረጃዎች በመንግሥታቱ ድርጅት የሚታመኑ ናቸው።
እስራኤል ሐማስን ዒላማ እያደረገች እንደሆነ ትናገራለች። ይሁን እንጂ በአመዛኙ የሚገደሉት ንፁሃን ናቸው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሸማጋይነት ለጋዛ የተነደፈው የሰላም እቅድ ተጓትቷል።
የተኩስ አቁሙ በጋዛ ተይዘው በነበሩ 48 ታጋቾች ፋንታ በእስራኤል ታስረው የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማዊያን እንዲለቀቁ ያደረገ ነው።
ከዚህም ባሻገር ስምምነቱ ጦርነቱ እንዲያበቃ በይፋ ያወጀ ነበር።
ጦርነቱ የተቀሰቀሰው መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ሐማስ በእስራኤል ጥቃት ፈፅሞ 1,200 ሰዎችን ገድሎ፤ 251 ሰዎችን ካገተ በኋላ ነው።
ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ እንደ ጤና ሚኒስቴሩ መረጃ በጋዛ 74,594 ሰዎች ተገድለዋል።
































