ትራምፕ ሩዋንዳ እና ደቡብ አፍሪካን ከአጎዋ የንግድ ስምምነት ሊያስወጡ ነው

ሲሪል ራማፎሳ እና ዶናልድ ትራምፕ በዋይት ሀውስ ሲነጋገሩ
የምስሉ መግለጫ, ባለፈው ዓመት ትራምፕ በዋይት ሀውስ ከሲሪል ራማፎሳ ጋር በነበራቸው ውይይት ላይ ደቡብ አፍሪካን "በነጮች ላይ የዘር ማጥፋት" በመፈፀም ከሰዋል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደቡብ አፍሪካን እና ሩዋንዳን ከአውሮፓውያኑ አዲስ ዓመት ጥር 1/2027 ጀምሮ ከሰሐራ በታች ላሉ የአፍሪካ አገራት ልዩ ዕድል ከሚሰጠው የንግድ ፕሮግራም ለማስወገድ ማቀዳቸውን ለኮንግረሱ አሳወቁ።

አጎዋ በሚል ምኅፃር የሚጠራው የአፍሪካ የዕድገትና የተጠቃሚነት ዕድል ሕግ፣ ብቁ ለሆኑ የአፍሪካ አገራት በሺህዎች የሚቆጠሩ ምርቶችን ወደ አሜሪካ ከቀረጥ ነፃ እንዲልኩ የሚያስችል ነው።

የአሜሪካ የንግድ ተወካይ ጄሚሰን ግሪር በሰጡት መግለጫ፣ በዓመታዊ ግምገማ ውጤት መሠረት ሁለቱ አገራት ከፕሮግራሙ የብቃት መስፈርቶች ጋር የማይስማሙ ተግባራት ላይ መሰማራታቸውን አመልክተዋል።

የትራምፕ አስተዳደር ይህን ውሳኔ ለሁለቱም አገራት እንዳሳወቀም አክለው ገልፀዋል።

የትራምፕ አስተዳደር ከውሳኔው ጋር በተያያዘ ለአሜሪካ ንግድና ኢንቨስትመንት መሰናክል የሆኑ ጉዳዮችን እንዲሁም በአካባቢው ካሉ የብሔራዊ ደህንነትና የውጭ ፖሊሲ ጥቅሞች ጋር የተያያዙ ስጋቶችን ጠቅሷል።

በተለይ ሩዋንዳን በተመለከተ ዋሽንግተን የሰብዓዊ መብቶች፣ የፖለቲካ ብዝኃነት፣ የሕግ የበላይነት እና የሠራተኞች መብቶች እንደሚያሳስቧት አስታውቃለች።

ይህ እርምጃ ይፋ የሆነው፣ የሩዋንዳ መከላከያ ሚኒስቴር በምስራቃዊ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በሚካሄደው የትጥቅ አመፅ ውስጥ ተሳትፎ አለው በሚል በአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስቴር ማዕቀብ ከተጣለበት ከአንድ ሳምንት ገደማ በኋላ ነው።

የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የሩዋንዳ መከላከያ ሚኒስቴር በምስራቃዊ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከኤም23 አማፂያን ጎን የሚዋጉ በሺህዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን እንዳሰማራ እና ለአማፂያኑ መሣሪያ፣ ቁሳቁስ፣ የሎጂስቲክስ ድጋፍ እና ስልጠና እንደሚሰጥ ገልጿል።

Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ደቡብ አፍሪካን በተመለከተ ደግሞ አሜሪካ የሙስና ችግርን በተጨማሪነት ጠቅሳለች።

"የትራምፕ አስተዳደር የአፍሪካ አጋሮቻችን የፕሮግራሙን የብቃት መስፈርቶች ለማሟላት የሚያስፈልጉ እርምጃዎችን እንዲወስዱ እየሠራ ነው" ሲሉ ግሪር ተናግረዋል።

የደቡብ አፍሪካ የንግድ ሚኒስትር ፓርክስ ታው የትራምፕን ውሳኔ "አሳዛኝ" ሲሉ ገልፀው፣ ዋሽንግተን በሁለቱ አገራት መካከል በ2025 በተጀመሩት የንግድ ድርድሮች ውስጥ ያልተነሱ አዳዲስ ጉዳዮችን እያነሳች መሆኑን ተናግረዋል።

"የዜጎችን ሥራ ለመጠበቅ የደቡብ አፍሪካን የወጪ ገበያዎች የማስፋትና የማብዛት ተግባራትን እናፋጥናለን" ሲሉ ታው አክለው ገልፀዋል።

በደቡብ አፍሪካ የአሜሪካ አምባሳደር ሊዮ ብሬንት ቦዜል ሦስተኛ በበኩላቸው፣ የደቡብ አፍሪካ ፖሊሲዎች አገሪቱ ከአጎዋ እንድትሰረዝ ማድረጋቸው አሳዛኝ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

"ይህ ውጤት የሚጠበቅ እና አስቀድሞ መከላከል የሚቻል ነበር፤ ሆኖም የደቡብ አፍሪካ መንግሥት አሜሪካ ያነሳቻቸውን ተጨባጭ ስጋቶች ባለመቀበሉ የተከሰተ ነው" ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

የትራምፕ አስተዳደር እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው፣ ዋሽንግተን ከሁለቱም አገራት ጋር ያላት ግንኙነት በሻከረበት ወቅት ነው። ሁለቱን አገራት ከአጎአ ፕሮግራሙ የማስወገዱ ዕቅድ፣ አገራቱ ከአሜሪካ ጋር በሚኖራቸው የተመረጡ የንግድ ሥርዓቶች ተጠቃሚነት ላይ ስጋት ፈጥሯል።

ባለፈው ዓመት ትራምፕ በዋይት ሀውስ ከደቡብ አፍሪካው ፕሬዚደንት ሲሪል ራማፎሳ ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ደቡብ አፍሪካን "በነጮች ላይ በሚደረግ የዘር ማጥፋት" ወንጀል የከሰሱ ሲሆን፣ በዚህም ሳቢያ 'አፍሪካነርስ' በመባል የሚታወቁ የአገሬው ነጮች ወደ አሜሪካ መሰደድ የሚያስችላቸውን መርሃ ግብር አስጀምረው ነበር።