ስደተኛ እንክብካቤ ሰጪዎች በዩኬ ቋሚ መኖሪያ ለማግኘት 15 ዓመት እንዲጠብቁ የሚያደርገው ዕቅድ ተሰረዘ

የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሯ ሻባና መሐሙድ
የምስሉ መግለጫ, የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሯ ሻባና መሐሙድ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ የሚሠሩ እንክብካቤ ሰጪ ባለሙያዎች በአገሪቱ ቋሚ መኖሪያ ለማግኘት እስከ 15 ዓመት እንዲጠብቁ ለማድረግ ተይዞ የነበረው ዕቅድ ተሰረዘ።

ለሕጻናት፣ አዛውንቶች እና አካል ጉዳተኞች የሕክምና ወይም ሥነ ልቦና ድጋፍ የሚሰጡ የውጭ አገራት ዜጋ የሆኑ እንክብካቤ ሰጪዎች (care workers) ቋሚ መኖሪያ ለማግኘት 15 ዓመት እንዲጠብቁ ሐሳብ አቅርበው የነበሩት የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሯ ሻባና መሐሙድ ነበሩ።

ቋሚ መኖሪያ ለማግኘት አምስት ዓመት ይጠብቁ የነበሩ ስደተኛ እንክብካቤ ሰጪዎች 10 ዓመት እንዲጠብቁ ለማድረግ ሚኒስትሯ ሐሳብ አቅርበው ነበር። በዚህ አሠራር አንዳንድ ስደተኞች እስከ 15 ዓመት ድረስ መጠበቅ ይኖርባቸዋል።

ሆኖም ግን የሌበር ፓርቲ አባል የሆኑ የሕዝብ እንደራሴዎች ባሰሙት ተቃውሞ ሚኒስትሯ ዕቅዳቸውን ሰርዘዋል።

ከአውሮፓውያኑ ግንቦት 2025 በፊት ዩናይትድ ኪንግደም የገቡ እና ቢያንስ 25,000 ፓውንድ የሚከፈላቸው ስደተኛ እንክብካቤ ሰጪዎች ከአምስት ዓመት በኋላ ቋሚ መኖሪያ ለማግኘት ብቁ እንደሚሆኑም ተገልጿል።

ሚኒስትሯ ሐሳባቸውን መለወጣቸው ዜጎችን "በቢሊዮን ፓውንድ እንደሚያስወጣቸው" ወግ አጥባቂ የሕዝብ እንደራሴዎች ተናግረዋል።

ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ፣ ስደተኞች በዩኬ ላልተገደበ ጊዜ እንዲሠሩ እና እንዲማሩ ያስችላል። የአገሪቱ ዜጋ ለመሆን ማመልከትም ይችላሉ።

የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሯ ሻባና፤ ቋሚ መኖሪያ ለማግኘት የሚወስደውን ጊዜ ከፍ እንደሚያደርጉ የገለጹት ጥያቄውን የሚያቀርቡ ስደተኞች ቁጥር ከመጨመሩ ጋር በተያያዘ ነበር።

ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱም "ዩኬ የሚኖሩ 500,000 ሰዎች በአምስት ዓመት ውስጥ ቋሚ መኖሪያ አያገኙም" ብለዋል።

ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ እስከሚያገኙ መጠበቅ እንዳለባቸውም ገልጸዋል። ለእንክብካቤ ሰጪዎች ግን በተለየ ሁኔታ "ፍትሐዊ መፍትሔ" መስጠታቸውን ተናግረዋል።

ዩኬ ገብተው በሚወጡ እና እዚያው በሚቀሩ ሰዎች መካከል ያለው ልዩነት እንደሰፋ የአገር ውስጥ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ገልጿል። መሥሪያ ቤቱ ባወጣው አሐዝ መሠረትም ከአውሮፓውያኑ 2021 እስከ 2024 ባሉት ዓመታት የአገሪቱ ዜጎች ቁጥር በ2.6 ሚሊዮን አድጓል።

ከ2026 እስከ 2030 ባሉት ዓመታት ተጨማሪ ከ1.3 እስከ 2.2 ሚሊዮን ሰዎች በዩኬ እንደሚኖሩም ግምቱን አስቀምጧል።

በዩኬ እየኖሩ ያሉ ስደተኞችን የመኖሪያ ሁኔታ ለመለወጥ መሞከር ከሕዝብ እንደራሴዎች ጥያቄ አስነስቷል።

የሌበር ፓርቲ አባላት "እንግሊዛዊ ያልሆነ አካሄድ" ብለውታል።

በእንክብካቤ መስጠት ዘርፍ የባለሙያ እጥረት እንደሚያስከትል አስጠንቅቀዋል።

ሻባና መሐሙድ በበኩላቸው በዩኬ መኖር "በዘፈቀደ የሚገኝ ሳይሆን የልፋት ውጤት ነው" ሲሉ ተከራክረዋል።

ከ50,000 ፓውንድ በታች የሚከፈላቸው ስደተኞች በ10 ዓመት ውስጥ ቋሚ መኖሪያ የሚያገኙበት አሠራር ይዘረጋል።

"የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ ስንጠራቸው የመጡ" ያሏቸው እንክብካቤ ሰጪ ባለሙያዎች በአምስት ዓመት ውስጥ ቋሚ መኖሪያ የማግኘት ዕድል እንደሚኖራቸው ሚኒስትሯ ተናግረዋል።