ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
"ወላጆቼ አብረው ለመሞት ስለወሰኑ ብቻዬን ሐዘን ተቀመጥኩ"
ማሳሰቢያ፡ ይህ ጽሑፍ አንዳንድ አንባቢዎችን ሊረብሽ ይችላል
በሰሜን ኔዘርላንድስ በአውሮፓውያኑ ሰኔ 2024 ባስ በወላጆቹ መኖሪያ ጋር መኪናውን አቆመ።
አባቱ ጃን እና እናቱ ኤልስ አብዛኛውን ዘመናቸውን ያሳለፉት በውሃ ላይ በሚንሳፈፍ ጀልባ ውስጥ እየኖሩ ነው። በ70ዎቹ ዕድሜ ክልል ሲደርሱ ለመኖሪያነት የተዘጋጀ ተሽከርካሪ ገዙ።
ባስ ወላጆቹ የሚኖሩበት ተሽከርካሪ አጠገብ መኪናውን አቆመ። ወላጆቹም መኪናው ውስጥ ገቡ። ይህ ለመጨረሻ ጊዜ ቤተሰቡን በመኪናው ያጓጓዘበት ዕለት ነው።
ወላጆቹ በሕክምና በታገዘ መንገድ አብረው ለመሞት ወስነዋል። በኔዘርላንድስ በሕክምና ታግዞ መሞት (euthanasia) በሕግ የተፈቀደ ነው።
ጥንዶቹ ለመሞት ቀጠሮ ከያዙበት ዕለት ሦስት ቀናት አስቀድመው ለቢቢሲ ቃላቸውን ሰጥተዋል።
ጃን ለዓመታት በካርጎ ሥራ ላይ ስላሳለፉ ሰውነታቸው በማያቋርጥ ሕመም ውስጥ ነው።
ኤልስ ዳይሜንሽያ (የመዘንጋት ሕመም) አለባቸው።
ጥንዶቹ አብረው ከሞቱ ሁለት ዓመት አልፏቸዋል። ብቸኛ ልጃቸው ባስ ወላጆቹ ለመሞት ያሰቡበትን ቀን እንዲያዘገዩ ሲጠይቃቸው ነበር። ሆኖም ግን ውሳኔያቸውን እንደሚያከብር ይናገራል።
ወላጆቹ ከሞቱ በኋላ በብቸኝነት ስሜት እንደተጎዳ ይገልጻል።
ከወላጆቹ ጋር ያሳለፈውን የመጨረሻ ቀን አይረሳውም።
"ሙሉ ጉዞውን አስታውሰዋለሁ። መኪና ውስጥ እናቴ ከኋላ፣ አባቴ ከጎኔ ተቀምጠው ነበር። እናቴ ለመሞት በመወሰኗ እርግጠኛ ነበረች። አባቴ ግን ስሜታዊ ሆኖ ነበር።"
ጃን ትክክለኛውን ነገር እያደረግን ነው? ሲሉ ልጃቸውን ጠይቀዋል።
ባስ እንደሚለው እናቱ ለውሳኔ እንደሚያመነቱ ጠብቆ ነበር።
"እናቴ ሕይወትን ታጣጥም ነበር። 80 ወይም 90 ዓመት ብኖር ደስ ይለኛል ትል እንደነበር አስታውሳለሁ።"
አባቱ ከፍተኛ አካላዊ ስቃይ ውስጥ ስለነበሩ ለረዥም ጊዜ በሕክምና ስለታገዘ ሞት ያወሩ ነበር።
እናቱን እና አባቱን ወደ ሆስፒታል እየወሰዳቸው ሳለ አባቱን ለማረጋጋት ይሞክር ነበር።
ከዚያም አብረው ሙዚቃ እየሰሙ፣ የሚያልፉበትን መንገድ እያዩ ጉዞ ቀጠሉ።
እናት እና አባቱ ለመሞት ከመወሰናቸው ከወራት በፊት ሐሳባቸውን ለማስቀየር ሞክሯል።
"የሚሞቱበትን ቀን ትንሽ እንዲገፉት ለማድረግ ሞከርሙ። ምናልባት በቀጣይ ዓመት ቢሆንስ? አልኳቸው።"
ወላጆቹ በሕክምና በታገዘ ሁኔታ ለመሞት መወሰናቸውን አልተቃወመም። ግን ቀኑ እንዲራዘም መፈለጉ አልቀረም።
"አባቴ ለ10 እና 15 ዓመታት ሲሰቃይ ነበር። ለተጨማሪ ዓመታት መሰቃየት አይችልም። ተጨማሪ ዓመት ከቆየን እናቴም ችግር ውስጥ ትገባለች" ይላል።
ኤልስ ሳይሞቱ አንድ ዓመት ከቆዩ አልዛይመርስ እየተባባሰባቸው ይሄዳል። በሕይወታቸው ላይ የመወሰን አቅም ያጣሉ ማለት ነው።
ባስ ወላጆቹን ይዞ ሆስፒታል ደረሰ። አባቱ መኪናውን ይወዱት ስለነበር እንደተሰናበቱት ያስታውሳል።
"መኪናዬን ተሰናበተው፤ 'ጥሩ ሠርተሀል እናመሰግናለን' አለው። ከዚያም ወደ ሆስፒታሉ ገባን" ይላል።
ወደ ሆስፒታሉ በገቡበት ቅጽበት ወላጆቹ ምን እያሰቡ እንደነበር ለመገመት ይሞክራል።
ለሁለት ሰዓታት ያህል ቤተሰብ እና ጓደኞቻቸው እየሄዱ ተሰናበቷቸው። ትዝታቸውን ሲያወሩ፣ ሙዚቃ ሲሰሙ ቆዩ።
"የሆነ ሰዓት ላይ ለምን ጥለው አንሄድም? ብዬ አሰብኩ። ግን ጥርጣሬ ውስጥ የሚከታቸው ነገር ማለት አልፈለግኩም።በሕክምና የታገዘ ሞትን እደግፋለሁ። ሁሉንም ሰው አረጋግቼ ወደ ስንብቱ ተመለስኩ።"
ጃን እና ኤልስ የሚገድላቸው መድኃኒት በሐኪሞች ተሰጣቸው።
ጥንዶቹ የሆስፒታሉ አልጋ ላይ ጎን ለጎን ተኝተው ነበር። ሕይወታቸው ከማለፉ ከቅጽበቶች በፊት ባስ ወላጆቹ ምን ያህል እንደሚቀራረቡ እያየ ነበር።
"በመላው ሕይወቴ እጅ ለእጅ ተያይዘው ሲሄዱ ያየሁት ሦስቴ ወይም አራቴ ቢሆን ነው። በዚያ ሰዓት ግን እጅ ለእጅ ተያይዘው ነበር። አብረው መወሰናቸውን ስመለከት ጥሩ ስሜት ተሰማኝ።"
በመጀመሪያዎቹ 30 ደቂቃዎች ውስጥ ወላጆቹ መተንፈስ አቆሙ። እውነታው ይሰማውም ጀመር። "ፈጽሞ መገመት የማይቻል ስሜት ነው" ሲል ይገልጸዋል።
ጃን የሆኪ ጨዋታ ያሠለጥኑ ነበር። ወደ ጨዋታዎች ልጃቸውን ይወስዱትም ነበር።
ጃን ቤተሰቦቹ እንደሞቱ ከፍተኛ የብቸኝነት ስሜት ወረረው።
"ሐዘን እጅግ፣ እጅግ ጥልቅ ስሜት ነው። እህቶችም ወንድሞችም የሉኝም። ብቻዬን ቀረሁ።"
አንድ ወላጅ በሞት ሲለይ በሕይወት ከቀረው ወላጅ ጋር አብሮ ማዘን ይቻላል። በትውስታ ወደኋላ አብሮ በመመለስ ሐዘኑን ለማቅለል ይሞከራል።
ባስ ግን እናቱንም አባቱንም በአንድ ቀን አጣቸው። "እግሮቼ የተቆረጡ ነው የመሰለኝ" ሲል ጥልቅ ሐዘኑን ይገልጻል።
በሐዘኑ ምክንያት እስከ አምስት ሳምንታት ሙሉ ሰውነቱ በሕመም ተይዞ ነበር።
"ውሳኔው ከባድ ስለሆነ ሌሎች ይሄንን እንዲያደርጉ አልመክርም። ምናልባት ለቤተሰቦቼ ትክክለኛው ውሳኔ ይሆናል። እነሱን ማጣት እጅግ፣ እጅግ ያሳምማል" ይላል።
ኤልስ እና ጃን ልጃቸውን ወደ ጀልባ መቅዘፍ ውድድር ይወስዱት ነበር።
በኔዘርላንድስ እንደ ኤልስ ዳይሜንሽያ ያለባቸው ሰዎች በሕክምና የታገዘ ሞትን ይመርጣሉ።
በየትኛው ቅጽበት ላይ ልሙት የሚለውን መወሰን ግን ቀላል አይደለም።
በአገሪቱ በሕክምና የታገዘ ሞትን የተመለከቱ መረጃዎችን እንመልከት፦
- በአውሮፓውያኑ 2024 ላይ 9,958 የሚደርሱ ሰዎች በሕክምና ታግዘው ለመሞት መርጠዋል።
- እዚህ ውሳኔ ላይ ከደረሱት ሰዎች መካከል 427 የሚሆኑት ዳይሜንሽያ አለባቸው። ስድስት የሚደርሱት ደግሞ በሕመሙ የተባባሰ ደረጃ ላይ ይገኙ ነበር።
- በአውሮፓውያኑ 2024 ላይ 108 ሰዎች (54 ጥንዶች) አብረው ለመሞት ወስነዋል።
በሕክምና ታግዘው ለመሞት የሚመርጡ ሰዎች ከአቅማቸው በላይ የሆነ ስቃይ ውስጥ መሆናቸውን ማረጋገጥ አለባቸው።
በራሳቸው ውሳኔ ላይ መድረስ ይችሉ እንደሆነም ሐኪሞች ምርመራ ያደርጋሉ።
በኤራስሙስ ሜዲካል ሴንተር የሚሠሩት ዶ/ር ሮዛማርጂን ቫን ቡርቹም እንደሚሉት፤ ዳይሜንሽያ ያለባቸው ሰዎች እዚህ ውሳኔ ላይ መድረስ ከባድ ጭንቀት ውስጥ ይከትታቸዋል።
"አሁን ላይ የመወን አቅሙ አለኝ ብለው ቢያስቡም ጊዜው የፈጠነ ይመስላቸዋል። ምናልባት በቀጣይ ወር ባደርገው ይዘገይ ይሆናል? ብለው ያስባሉ። ታዲያ በየትኛው ወቅት ነው መወሰን ያለብኝ? በሕክምና ታግዞ ለመሞት መስፈርቱን አሟላለሁ? ብዘገይ ዕድሉ ያመልጠኝ ይሆን? ብለውም ያሰላስላሉ።"
በሕክምና የታገዘ ሞት ሕጋዊ ቢሆንም ታካሚዎች ጭንቀት ውስጥ እንደሚገቡ ባለሙያው ያስረዳሉ።
ኤልስ ከመሞታቸው በፊት በአውሮፓውያኑ 2024 ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ከባለቤታቸው ጋር አብረው ለመሞት መወሰናቸውን ተናግረዋል።
አልዛይመርስ እየተባባሰባቸው በመሆኑ ውሳኔው ላይ መድረሳቸውን ገልጸውም ነበር።
ባለቤታቸው ጃን በበኩላቸው ከኤልስ ጋር አብረው ለመሞት መወሰናቸውን ተናግረዋል።
ሞታቸው ቅርብ መሆኑን ቢያውቁም፤ ሕይወትን ኖረው መጨረሳቸውን ያምናሉ።
ጥንዶቹ በአንድ ቀን መሞታቸው ልጃቸው ላይ ጫና እንደሚኖረው ያውቃሉ።
ከሐኪሞች ጋር ውይይት ሲያደርጉ ልጃቸውም አብሯቸው ይገኝ ነበር።
ለሚወዱትን ሰው መናገር የሚፈልጉትን ሳይገልጹ በሞት መነጠቅ ከባድ ሐዘን ውስጥ ይከትታል።
ባስ ወላጆቹ ከመሞታቸው ከሁለት ቀናት በፊት ደብዳቤ ጽፎላቸዋል።
"ስምንት ገጽ ይጠጋል። ከመሞታቸው ከሁለት ቀን በፊት ይኖሩበት ወደነበረው ተሽከርካሪ ሄጄ አነበብኩላቸው። ደብዳቤው ስለ ሕይወታችን ነበር። ስላደረጉልኝ ነገሮችም አመሰገንኳቸው።"
ጃን እና ኤልስ ፍቅራቸውን በአደባባይ የሚገልጹ ዓይነት ሰዎች ባይሆኑም፤ ልጃቸው የጻፈላቸውን ሲያነብላቸው ስሜታዊ ሆነዋል።
"እንደሚወዱኝ የሚሰማኝ በሚያደርጉልኝ ነገር ነው፤ ለምሳሌ ሲያቅፉኝ። እናቴ ዳይሜንሽያ ሳይዛት በፊት ታቅፈኝ ነበር። አባቴ ብዙም ሰዎችን አያቅፍም፤ እኔንም አቅፎኝ አያውቅም" ይላል ባስ።
ደብዳቤውን ያነበበላቸው ቀን ግን ሁሉም ነገር ተለወጠ። አባቱ እንዳቀፉት ያስታውሳል።
"ደብዳቤውን ካነበብኩ በኋላ አቀፈኝ። በሕይወቴ ደስተኛ የሆንኩበት ቅጽበት ነው።"