ተመድ የግብፅን የፕሬስ አፈና ሲያወግዝ፤ ካይሮ የታዋቂዋን ጋዜጠኛ የፍርድ ሂደት አራዘመች

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የግብፅ ፍርድ ቤት ዓለም አቀፍ ውግዘትን ያስተናገደው የታዋቂዋን ጋዜጠኛ ሊና አትላህን የክስ ሂደት አራዘመ።

ረቡዕ ዕለት 'ማዳ ማሰር' የተባለው መገናኛ ብዙኃን ዋና አርታኢ የሆነችው ሊና ጠበቆች አዲስ ዳኛ እንዲመደብላቸው መጠየቃቸውን ተከትሎ ቅድመ ችሎቱ ለሚቀጥለው ሳምንት ተዘዋውሯል።

የመንግሥታቱ ድርጅት "የግብፅ ባለሥልጣናት ነፃ ጋዜጠኞችን ዒላማ ማድረግን፣ መወንጀል እና መከታተልን ጨምሮ በፕሬስ ነፃነት ላይ ሰፊ ጥቃት እየፈፀሙ ነው" ሲል አስጠንቅቋል።

ሊና አትላህ ለቢቢሲ በቅርቡ ጋዜጠኞች ላይ እየተወሰደ ያለውን እርምጃ በቀሩ ጥቂት ነፃ የዜና ክፍሎች ላይ "አስደንጋጭ መልዕክት ለመላክ" ነው ብላለች።

"ሁሉም ሰው መጠንቀቅ አለበት፣ ሁሉም መፍራት አለበት፣ ቀጥሎ ምን ሊመጣ እንደሆነ ሁሉም ሰው ማሰላሰል አለበት" ብላለች።

'ማዳ ማሰር' የተባለው መገናኛ ብዙኃን ከ13 ዓመት በፊት የተቋቋመ፣ በሊና አትላህ የጋራ መስራችነት እና ዋና አርታኢ የሚመራ የግብፅ ዋነኛ ነፃ የዜና ድረ ገፅ ነው።

ባለፈው ወር የግብፅ ፍርድ ቤት ጋዜጠኛዋን ፈቃድ በሌለው ድረ ገፅ ሥራ በመስራት ጥፋተኛ ብሏታል። ጋዜጠኛዋ ፈቃድ ለማግኘት ለዓመታት መታገሏን ተናግራለች።

ፍርድ ቤቱ 56 ሺህ ዶላር (ሦስት ሚሊዮን የግብፅ ፓውንድ) እንድትከፍል እና ማዳ ማሰር እንዲዘጋ የሚል ከባድ ቅጣት ጥሎባታል።

ከብይኑ በኋላ ፍርድ ቤቱ ያለ እውቅናዋ ጋዜጠኞችን ለማሳደድ እንደ መሣሪያ በአብዛኛው በሚቀርበው "ሐሰተኛ መረጃ ማሰራጨት" ክስ እና ያለ ፈቃድ ድረ ገፅ ላይ በመስራት የአንድ ዓመት እስራት እንደፈረደባት አውቃለች።

ጋዜጠኛዋ ምንም እንኳ አገር ውስጥ የነበረች ቢሆንም እ.አ.አ በ2024 በሌለችበት ተፈርዶባታል።

የሊና አትላህ ክስ በተመሳሳይ ዳኛ እንደገና እየታየ ነው።

በቅደመ ችሎቱ የጋዜጠኛዋ ጠበቆች ዳኛው "ተከሳሿን ጥፋተኛ ናት የሚል ድምዳሜ ላይ አስቀድመው ደርሰዋል" በሚል አዲስ ዳኛ እንዲመደብ ጠይቀዋል።

ማዳ ማሰር ጠበቃ ሀሰን አል-አዛህን ጠቅሶ ባወጣው መረጃ ዳኛው የተከሳሿን አቤቱታ ለማጤን ችሎቱን በሚቀጥለው ሳምንት ቀጥረዋል።

በግብፅ የፕሬስ ነፃነት የታፈነ ሲሆን፤ በድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን ትንተና ካይሮ በፕሬስ ነፃነት ደረጃ ከ180 አገራት 169ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

ቡድኑ ባለፉት ዓመታት በግብፅ የታሰሩ 26 ጋዜጠኞች አሁን እስር ላይ እንደሚገኙ ተናግሯል።

አብዛኞቹ ጋዜጦች እና የቴሌቭዥን ጣቢያዎች መንግሥት በሚሰጣቸው ፈቃድ የሚሰሩ ቢሆንም፤ ማዳ ማደር በግብፅ ልዩ፣ ነፃ እና የምርመራ ዜና ምንጭ ሆኖ ቀጥሏል።

ይሁን እንጂ እ.አ.አ ከ2017 ጀምሮ ድረ ገፁ ከአገር ውጭ ብቻ የሚታይ ሆኗል።