ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሱዳን እና ኢትዮጵያ ውጥረት የት ይደርሳል? የድንበር አካባቢውን የሚቆጣጠረውስ ማን ነው?
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) እና የሱዳን ጦር ውጊያ አገሪቱን ወደ እርስ በርስ ጦርነት የከተታት በአውሮፓውያኑ የካቲት 2023 ነበር።
በጦርነቱ ከ150,000 በላይ ሰዎች ሲሞቱ፤ ወደ 12 ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት ከዓለም የከፋው ሰብአዊ ቀውስ በሱዳን መከሰቱን አስታውቋል።
በአውሮፓውያኑ የካቲት 2025 የሱዳን ጦር ካርቱም፣ ኦምዱርማን እና ባህሪን መልሶ ተቆጣጥሯል። የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይልን ወደ ምዕራብ እና ደቡብ ምዕራብ ሱዳን መግፋትም ችሏል።
ኢትዮጵያ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን ትደግፋለች በሚል የምትከስሰው ሱዳን ቅሬታዋን ለአፍሪካ ኅብረት የሰላም እና ፀጥታ ምክር ቤት እንዲሁም ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት አስገብታለች።
ሁለቱ አገራት 750 ኪሎሜትር የሚሸፍን ድንበር ይጋራሉ። ድንበሩ በይፋ የተካለለ አይደለም።
ከዚህ ቀደም በሁለቱ አገራት መካከል የግዛት ይገባኛል ውዝግቦች ተነስተዋል።
አሁን ላይ ውጥረቱን ያባባሰው ግን የድንበር ይገባኛል ጉዳይ አይደለም።
ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ከኢትዮጵያ ግዛት ተነስቶ በፈጸማቸው የድሮን ጥቃቶች በሱዳን በንጹኃን ዜጎች መሠረተ ልማት ላይ ጉዳት መድረሱን፣ የኃይል አቅርቦት ተቋማት ዒላማ መደረጋቸውን እና የጤና ተቋማት መጎዳታቸውን በመግለጽ የሱዳን መንግሥት ከስሷል።
ሱዳን ለምታቀርባቸው ክሶች ማስረጃ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማቅረቧን ትገልጻለች።
ቢቢሲ የኢትዮጵያ መንግሥትን አስተያየት ቢጠይቅም ይህ ዘገባ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ ምላሽ አላገኘም። ከዚህ በፊት ግን ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ከሱዳን የሚቀርቡባትን ክሶች አስተባብላለች።
ኢትዮጵያ የሱዳን አዋሳኝ በሆነችው እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መቀመጫ በሆነችው አሶሳ የሚገኘው የሱዳን ቆንስላ ስድስት ዲፕሎማቶች በ48 ሰዓታት ውስጥ አገሪቷን ለቅቀው እንዲወጡ ማዘዟን ሮይተርስ ዘግቧል።
ሱዳን በጋዳሪፍ ግዛት የሚገኙ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ግዛቷን ለቅቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ሰጥታለች።
የሁለቱም አገራት የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቶች ስለ ጉዳዩ ይፋዊ ማብራሪያ አልሰጡም።
የተባባሰው የሁለቱ አገራት ውጥረት
በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 30/2026 ሱዳን ባስገባችው ቅሬታ ላይ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ ኃይል እና ኢነርጂ አቅርቦትን ዒላማ ባደረጉ የድሮን ጥቃቶች ኢትዮጵያ መሳተፏን በመግለጽ ወንጅላለች።
ኢትዮጵያ ለዚህ ክስ ይፋዊ ምላሽ ባትሰጥም ከዚህ ቀደም ለፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ድጋፍ እንደማትሰጥ በመግለጽ የሚቀርቡባትን ክሶች አስተባብላለች።
የኢትዮጵያ መንግሥት ፈጥኖ ፈራሽ ኃይሉ ከኢትዮጵያ ግዛት ወደ ሱዳን ጥቃት እንዲሰነዝር ፈቅዷል መባሉንም አስተባብሏል።
ኢትዮጵያ የሱዳንን ሉዓላዊት እና የግዛት አንድነት እንደምታከብር ገልጻለች።
የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደሚለው የፈጥኖ ፈራሽ ኃይሉ ከኢትዮጵያ ግዛት የድሮን ጥቃቶች ፈጽሟል። ጥቃቶቹ ቁልፍ በሆኑ የሕዝብ መሠረተ ልማቶች ላይ ያነጣጠሩ ናቸው ብሏል።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ክሱን ለዓለም አቀፍ ተቋማት ያቀረበው የሳተላይት ምሥሎችን በማስረጃነት በማቅረብ መሆኑን አስታውቋል።
የሱዳን ጦር ኅዳር 3 ከኢትዮጵያ ተነስቶ የአገሪቱን ክልል ጥሶ የገባ ድሮን መትቶ መጣሉን አስታውቋል። የሱዳን ጦር ባወጣው መግለጫ ድሮኑ የተያዘው በሱዳን ብሉ ናይል አካባቢ ነው።
ኢትዮጵያ በበኩሏ ሱዳን ህወሓትን እንደምትደግፍ በመግለጽ ወንጅላለች።
በኢትዮጵያ የአማጺያን ጥምረት ከፌደራል መንግሥቱ ኃይሎች ጋር ውጊያ ውስጥ ከመግባታቸው ጋር በተያያዘ ሱዳን እና ኤርትራ አማጺያኑን ይደግፋሉ ስትል ኢትዮጵያ ከስሳለች።
ሱዳን እና ኤርትራ ክሱን መሠረት አልባ ሲሉ አጣጥለዋል።
የመካከለኛው ምሥራቅ እና የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ ተንታኝ አብዱራሕማን ሰይድ አቡሐሺም "በኤርትራ እና ኢትዮጵያ መካከል ያለው ግጭት ወይም ህወሓትን ያካተተው ጦርነት ቢስፋፋ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት በሱዳን በኩል እነዚህ ኃይሎች ሊጋርጡ የሚችሉትን አደጋ ለማስወገድ ሊሞክር ይችላል" ይላሉ።
"ይሄንን ሊያደርግ የሚችለው በቀጥታ ወይም በአርኤስኤፍ በኩል ሊሆን ይችላል። ዒላማው እስከ ገዳሪፍ እና ካሳላ አካባቢውን መቆጣጠር ይሆናል" ሲሉም ያክላሉ።
ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የንጹኃን መሠረተ ልማትን ዒላማ ማድረጉን በተደጋጋሚ አስተባብሏል። ኦፕሬሽኖቹ የሱዳን ጦር ወታደራዊ ይዞታዎች ላይ ያነጣጠሩ መሆናቸውን ገልጿል።
በጥር 2026 ሮይተርስ እንደዘገበው ከሆነ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በሱዳን ድንበር አቅራቢያ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ወታደራዊ ማሠልጠኛ ማዕከል አቋቁሟል።
የሥልጠና ማዕከሉ በሺህዎች የሚቆጠሩ ተዋጊዎች ልምምድ እንደሚያደርጉበት እና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እንደሚደገፍ ዘገባው ያትታል። ኢትዮጵያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ክሱን አስተባብለዋል።
የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከጥር 15 እስከ መስከረም 27/ 2026 ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ በ70 ክስተቶች ከኢትዮጵያ የተነሱ ከ187 በላይ ድሮኖች የሱዳንን ድንበር አልፈው መግባታቸውን መግለጹን ኤኤፍፒ ዘግቧል።
ከኢትዮጵያ ግዛት የተነሱት ድሮኖች ከጥር አንስቶ ቢያንስ 484 ንጹኃንን እንደገደሉ መሥሪያ ቤቱ ገልጿል።
ቢቢሲ ይሄንን ቁጥር በገለልተኛ ወገን አላጣራም።
ከታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ የሱዳን እና ኢትዮጵያ ግንኙነት ውጥረት ውስጥ ገብቷል።
ግድቡ በኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን መካከል የረዥም ጊዜ አለመግባባት ምክንያት ሆኖ ቀጥሏል።
ሱዳን እና ግብፅ ግድቡ የውሃ ደኅንነታቸውን አደጋ ውስጥ እንደሚያስገባው ይገልጻሉ። በሦስቱ አገራት መካከል ያለው አሳሪ ስምምነትን የተመለከተ ውዝግብ መፍትሔ አላገኝም።
ኢትዮጵያ ግድቡ ለእድገቷ እና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦቷ መሠረታዊ መሆኑን ትገልጻለች። ለታችኛው ተፋሰስ አገራት ስጋት እንዳልሆነም አስታውቃለች።
አብዱራሕማን እንደሚሉት ግድቡን የተመለከተውን ውዝግብ ጨምሮ ሌሎችም ሰፊ ቀጣናዊ ውጥረቶች በቀጣይ የቀጣናው ተዋናዮች የሚወስዱትን ስትራቴጂካዊ ስሌት ይወስናል።
"ከግድቡ እና ከግብፅ ጋር በተያያዘ ግብፅ ኢትዮጵያ ላይ በአየር ወይም በሌላ መንገድ ጥቃት እንዳትፈጽም የኢትዮጵያ መንግሥት በሱዳን ውስጥ ማንኛውንም ጥቃት ያከሽፋል" ይላሉ።
"ሱዳንም በይፋ ኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ሳታውጅ ተመሳሳይ እርምጃ ልትወስድ ትችላለች። ይህም እንደ ህወሓት ያሉ ከኢትዮጵያ ጋር የሚዋጉ ታጣቂ ቡድኖችን በመደገፍ ነው" ሲሉም ያክላሉ።
የአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካ ተንታኝ አብዲ ካይዲ ቡራልም በዚህ ይስማማሉ።
"ውጥረቱ ከቀጥተኛ ወታደራዊ ግጭት ይልቅ ወደ ውክልና ግጭት እና የፖለቲካ ጫና ለመፍጠር ወደ ሚደረጉ ኦፕሬሽኖች ይሸጋገራል ብዬ አምናለሁ" ይላሉ።
አብዲ-ካይድ ቡራሌም ቀጥተኛ ጦርነት የሚነሳበት ዕድል ውስን ነው ይላሉ።
"የሱዳን መንግሥት የእርስ በርስ ጦርነት እና ውስጣዊ ፈተና ውስጥ ነው። በታሪክ በኢትዮጵያ እና ሱዳን መካከል ያለው ውጥረት ከቀጥተኛ ግጭት ይልቅ በውክልና ፉክክር የሚታይ ነው" ይላሉ።
የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት የፖለቲካ እና የውጭ ጉዳይ አማካሪ አምጃድ ፋራድ ለሮይተርስ እንደተናገሩት፤ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ቀጥተኛ ግጭት ውስጥ ላለመግባት ብትሞክርም ግዛቷን ለመከላከል ቁርጠኛ ናት።
አል ፋሽጋን በተመለከተ ለረዥም ጊዜ የዘለቀ አለመግባባት ነበር። አሁን ያለው ዲፕሎማሲያዊ ቁርሾ ግን ከድንበር ግጭት ይልቅ ድንበር ተሻጋሪ የድሮን ጥቃቶችን ይመለከታል።
የድንበር አካባቢውን የሚቆጣጠረውስ ማን ነው?
በአፍሪካ ቀንድ የድንበር ጉዳይ ለረዥም ጊዜ የዘለቀ የግጭት መነሻ ነው።
በኦጋዴን ጉዳይ ኢትዮጵያ በ1977 ከሶማሊያ ጋር ተዋግታለች። ከኤርትራ ጋርም በባድመ ምክንያት ጦርነት ገብታለች።
በትግራይ ጦርነት ወቅት አካባቢው በኤርትራ ሠራዊት ሥር እንደነበር ተገልጿል።
ከ1988ቱ ጦርነት በኋላ ኢትዮጵያ እና ሱዳን ለረዥም ጊዜ ተቋርጦ የነበረውን ድንበርን የተመለከተ ውይይት መልሰው ጀምረዋል። 744 ኪሎሜትር የሚረዝመውን ድንበር በትክክል ማካለል ላይ ያተኮረም ነው።
በቀላሉ ሊፈታ ያልቻለው የአል ፋሽጋ ጉዳይ ነው።
ለዚህም መነሻው በቅኝ ግዛት ዘመን በ1902 እና 1907 የተደረሱ ስምምነቶች ናቸው።
ሱዳን እና ኢትዮጵያ ከተከዜ ወንዝ አንስቶ ድንበር ይጋራሉ። ይህም ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ኤርትራ የሚገናኙበት ሥፍራ ነው።
ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን እና ኢትዮጵያ ወደ ደቡባዊ አቅጣጫ ድንበራቸው ይካለላል።
አሁን በሱዳን ያለው ግጭት በምዕራብ እና ማዕከላዊ ክፍል የተወሰነ ነው። ይህም ዳርፉር እና ኮርዶፋንን ይሸፍናል።
ሆኖም ግን ስትራቲጂክ ሚና ያላቸው በርካታ ከተሞች በኢትዮጵያ ድንበር አቅራቢያ ይገኛሉ።
ከኢትዮጵያ 120 ኪሎሜትር የሚርቀው ጋዳሪፍ በሱዳን ጦር ሥር ይገኛል። ወደ ደቡብ አቅጣጫ የብሉ ናይል መዲና ዳማዚንም በሱዳን ጦር ሥር ናት።
ዓባይ ወንዝ የሚያልፍበት ይህ አካባቢ በውሃ ኃይል የሚሠራው ዋነኛ ግድብ መገኛ ሲሆን ከድንበር 80 ኪሎሜትር ገደማ ይርቃል።
በብሉ ናይል ግዛት የሚገኘው ኩርሙክ በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል አጋሮች (ሱዳን ሊበሬሽን ሙቭመንት ኖርዝ) እጅ እንደነበር ተገልጿል።
ከነሐሴ 2026 ጀምሮ የዚህ ቡድን መሪ አብዱልአዚዝ አል-ሂሉ ነው።
ይህ ስትራቴጂክ ከተማ በጦርነቱ ውስጥ በተለያዩ ኃይሎች እጅ ወድቋል።
በስተደቡብ የሚገኘው ያቡስ ከ2011 ጀምሮ በሱዳን ሊበሬሸን ሙቭመንት ኖርዝ ሥር ይገኛል።
የሱዳን ጦር በአካባቢው በርካታ ኦፕሬሽኖች አካሂዷል።
አብዱራሕማን እንደሚሉት፤ ከኢትዮጵያ ጋር ሱዳን በምትጋራው ድንበር አካባቢ የሚገኙ ግዛቶች በሱዳን ጦር ሥር ይገኛሉ።
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል በምዕራባዊ የአገሪቱ ክፍል እንደሚገኝም ያክላሉ።
"ስለዚህም በምሥራቃዊ አካባቢ የሎጅስቲክስ ችግር አለ። ቡድኑ በዚያ አካባቢ እምብዛም የሕዝብ ድጋፍም የለውም" ይላሉ።
ተንታኞች እንደሚሉት አሁን ላይ በኢትዮጵያ እና ሱዳን ጉዳይ ያለው ስጋት ቀጥተኛ ወታደራዊ ግጭት ይከሰታል የሚለው አይደለም።
ሆኖም ግን በውክልና በቀጣናው ፉክክሮች ይኖራሉ። ድንበር ተሻጋሪው አለመተማመን መረጋጋት የራቀውን ቀጣናውን ወደተባባሰ ውጥረት ሊያስገባውም ይችላል።