ሃሪ ኬን የእንግሊዝን የ25 ዓመታት የባላንዶር ሽልማት ጥበቃ ቀለበሰ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ሃሪ ኬን በለንደን በተካሄደ መርሃ ግብር ከማይክል ኦወን በኋላ የባላንዶርን ሽልማት ያሸነፈ የመጀመሪያው እንግሊዛዊ ሆነ።

ማይክል ኦወን እ.አ.አ በ2001 ባላንዶርን ካሸነፈ በኋላ ሃሪ ኬን ትናንት ምሽት የዓለም ምርጡ እግር ኳስ ተጨዋች ተብሏል።

የ33 ዓመቱ የባየር ሙኒክ ተጨዋች የባላንዶርን ሽልማት ያሸነፈ አምስተኛው እንግሊዛዊ ሆኗል።

ስታንሊ ማቲዊስ (በ1956)፣ ቦቢ ቻርልተን (በ1966) እና ኬቨን ኪገን (በ1978 እና 1979) ይህን ሽልማት ያሸነፉ እንግሊዛዊያን ናቸው።

ከዩናይትድ ኪንግደም ደግሞ ዴነስ ሎው (ስኮትላንዳዊ) እና ጆርጅ ቤስት (ሰሜን አየርላንዳዊ) እንዲሁ አሸናፊ ለመሆን በቅተዋል።

የሪያል ማድሪድ እና ፈረንሳይ ተጨዋች የሆነው ኪሊያን ምባፔ ሁለተኛ ምርጥ ተጨዋች ሲባል፤ የባርሴሎና እና ስፔን አጥቂ የሆነው ላሚን ያማል ደግሞ ሦስተኛ በመሆን አሸንፈዋል።

"ብዙ ሰዎች ላያስቡት ይችላሉ፤ እና ምንአልባትም እኔም እዚህ እደርሳለሁ ብዬ አላስብም ነበር" ሲል ሃሪ ኬን ለዳዘን መገናኛ ብዙኃን ተናግሯል።

"በመውደቅ እና መነሳት ማለፍ ነበረብኝ፤ በተለይም ገና በጅማሮዬ ወቅት። ሰዎች እንደሌሎች ተጨዋቾች ኮከብ ይሆናል ብለው የሚያስቡኝ ሰው አልነበርኩም።

"ጊዜዬን መጠበቅ እና ጠንክሬ መሥራት ነበረብኝ፤ ብዙ ጊዜ እኔ ከራሴ አእምሮ ጋር ነበር የምጋፈጠው እና ይህን ማለፍ ነበረብኝ፤ በራሴ ማመን፣ ቁርጠኛ መሆኔን ማሳየት ነበረብኝ።

"ይህም ከፍተኛ ደረጃ ላይ ብደርስም እንኳን መሻሻል እንድቀጥል እና እንዳድግ መስመር ያስያዘኝ ይመስለኛል" በማለት የዛሬ ድሉ የዘመናት ሥራ መሆኑን ገልጿል።

የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ቶማስ ቱሆል የተጫዋቹን ውጤት በማሞካሸት ይህን በማየታቸው "ደስተኛ" እንደሆኑ እና የባላንዶር ሽልማት ለሃሪ "ትልቅ ክብር" እንደሆነ ተናግረዋል።

ባለፈው የውድድር ዘመን ሃሪ ኬን በ51 ጨዋታዎች 61 ግቦችን አስቆጥሯል። ይህም በባየር ሙኒክ ታሪክ በአንድ የውድድር ዘመን ከፍታኛ ግብ ያስቆጠረ ተጫዋች ያደርገዋል።

የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎችን ጨምሮ ደግሞ ሃሪ ኬን በ63 ጨዋታዎች 73 ግቦችን ሲያስቆጥር፣ ለስምንት ግቦች ደግሞ ኳስ አቀብሏል።

በአውሮፓ ዋነኛ ከሆኑ አምስት ሊጎች ውስጥ በአንድ የውድድር ዘመን አንድ ተጨዋች ብቻ ከዚህ በላይ ግብ አስቆጥሯል።

ሃሪ ኬን ባለፈው ዓመት ምንም እንኳን በዓለም ዋንጫ እና ቻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎ አሸናፊ ሳይሆን ቢቀርም ባላንዶርን ማሸነፉ ድሉን ልዩ ያደርገዋል።

የሦስት አናብስቶች አንበል የሆነው ሃሪ እ.አ.አ ከ1981 ካርል-ሄንዝ ሩመንግ በኋላ ባላንዶርን ያሸነፈ የመጀመሪያው የባየር ሙኒክ ተጨዋችም ሆኗል።

የሃሪን ድል በማስመልከት ሰኞ ምሽት የዌምብሌይ ስታዲየም ቀስቶች ወርቅ መብራት አብርተዋል።