ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ዓለም አቀፍ ውድድር የማዘጋጀት ዕድል ተሰጣት

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በአውሮፓውያኑ 2022 በዩክሬን ላይ ሙሉ ወረራ ከከፈተች አንስቶ በየትኛውም የኦሊምፒክ ፌዴሬሽን ዓለም አቀፍ ውድድር እንድታዘጋጅ ዕድል ተሰጥቷት የማታውቀው ሩሲያ፣ የ2030ውን የዓለም የክብደት ማንሳት ሻምፒዮናን እንድታስናግድ ተመረጠች።

ዓለም አቀፉ የክብደት ማንሳት ፌዴሬሽን ይህንን ውሳኔውን ትናንት እሁድ ይፋ አድርጓል። ፌዴሬሽኑ ይህንን ውሳኔ ያስተላለፈው ታግደው የነበሩት ሩሲያውያን አትሌቶች በሚያዘጋጃቸው የክብደት ማንሳት ውድድሮች ላይ በድጋሚ መሳተፍ እንደሚችሉ ካሳወቀ ከአራት ወራት በኋላ ነው።

ዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ሐምሌ ላይ በሩሲያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ላይ ጥሎት የነበረውን እገዳ ለጊዜው ማንሳቱ ይታወሳል። ይህ እገዳ የተጣለው አገሪቱ በዩክሬን ላይ ወረራ መፈጸሟን ተከትሎ ነበር።

ይህ የዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ውሳኔ ሩሲያውያን አትሌቶች በ2028 በሎስ አንጀለስ በሚካሄደው የኦሊምፒክ ውድድር ላይ አገራቸውን ወክለው እንዲወዳደሩ ዕድል ሊከፍት ይችላል።

ዓለም አቀፉ የክብደት ማንሳት ፌዴሬሽን እሁድ ዕለት በታዳጊዎች፣ በወጣቶች እና በከፍተኛ ደረጃዎች የሚካሄዱ የአራት የዓለም ሻምፒዮናዎችን አስተናጋጅ ከተሞች ይፋ አድርጓል። በ2029 የሚካሄደውን ከፍተኛ ውድድር የማዘጋጀት ዕድል ለሕንዷ አህመዳባድ ከተማ ተሰጥቷል።

የፌዴሬሽኑ ዋና ፀሐፊ ሆሴ ኩይኖኔስ "የቀረቡልን የእናዘጋጅ ጥያቄዎች በሙሉ እጅግ ጥሩ ነበሩ፤ በተመረጣችሁት አገራት የሚካሄዱት ውድድሮች ከፍተኛ ስኬት እንደሚያስገኙ እርግጠኞች ነን" ብለዋል።

በዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ አንድም የበጋም ሆነ የክረምት የኦሊምፒክ ስፖርት ዓለም አቀፍ ሻምፒዮና ሩሲያ ውስጥ አልተካሄደም።

የሩሲያዋ ካዛን ከተማ እንድታዘጋጅ ተሰጥቶ የነበረው የ2025 የዓለም የውሃ ስፖርቶች ሻምፒዮና የጦርነቱን መጀመር ተከትሎ ወደ ሲንጋፖር ተዘዋውሮ ነበር።

ሞስኮ የዓለም የክብደት ማንሳት ሻምፒዮናን የማስተናገድ ዕድል ስታገኝ ከአውሮፓውያኑ 1983 ወዲህ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

የሩሲያ የክብደት ማንሳት ፌዴሬሽን "ከበርካታ ዓመታት በኋላ ከፍተኛ ደረጃ ያለውን ውድድር ወደ አገር ውስጥ መመለስ የቻልን የመጀመሪያው የኦሊምፒክ ስፖርት ፌዴሬሽን [ነን]" ብሏል።

የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ቪኖኩሮቭ በበኩቸላቸው ዓለም አቀፉ የክብደት ማንሳት ፌዴሬሽን "ዕምነት ስለጣለባቸው" አመስግነዋል።

በሩሲያ የሚደረገው ይህ ውድድር በአውስትራሊያ ብሪዝበን ለሚካሄደው የ2032 የኦሊምፒክ ውድድር ማጣሪያ ሆኖ ያገለግላል።

የሩሲያ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት "ሩሲያ ከፍተኛ ደረጃ ያላቸውን ውድድሮች ለማስተናገድ የሚያስፈልገው በቂ ልምድ እና አቅም አላት" ብለዋል።

ዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ሐምሌ ላይ ሩሲያ ላይ የተጣለውን እገዳ በጊዜያዊነት ለማንሳት መወሰኑን ቢያሳውቅም፣ አገሪቱ በኦሊምፒክ ውድድሮች ላይ ሰንደቅ ዓላማዋን፣ ቀለሞቿን እና ብሔራዊ መዝሙሯን ማሳየት ይፈቀድላት እንደሆነ ውሳኔ እንዳልተሰጠ በወቅቱ ገልጾ ነበር።

ኮሚቴው "በሩሲያ ውስጥ የኦሊምፒክ ዝግጅቶችን አለማዘጋጀቱን እንዲሁም የሩሲያ መንግሥት ባለሥልጣናትን ወደ ዝግጅቶቹ አለመጋበዙን" እንደሚቀጥል አስታውቆ ነበር።

ሞስኮ ላይ የተጣለውን እገዳ ተከትሎ አንዳንድ ሩሲያውያን አትሌቶች በ2024ቱ የፓሪስ ኦሊምፒክ እና በ2026 በሚላን በተካሄደው የክረምት ኦሊምፒክ ላይ የተሳተፉት ገለልተኛ ተወዳዳሪዎች ሆነው ነው።

ዩክሬን የሩሲያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ላይ የተጣለው እገዳ እንዲነሳ የተለላፈው ውሳኔ ውድቅ እንዲደረግ ለስፖርት ጉዳዮች የግልግል ፍርድ ቤት ይግባኝ አቅርባለች።