የብራዚል ፕሬዝዳንት ሉላ ተፎካካሪያቸው የሆኑትን የቀድሞው መሪ ልጅ አሸንፈው ለአራተኛ ጊዜ ተመረጡ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ብራዚላዊው አንጋፋ የግራ ዘመም ፖለቲከኛ ሉዊዝ ኢናሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ ከፍተኛ ፉክክር የነበረበትን ምርጫ በማሸነፍ በድጋሚ በፕሬዝዳንትነት ተመረጡ።

ሆኖም ተቀናቃኛቸው የቀኝ ዘመም ፖለቲከኛው ፍላቪዮ ቦልሶናሮ ሽንፈታቸውን አልተቀበሉም። ፍላቪዮ ቦልሶናሮ አሁን በቤት ውስጥ እስር ላይ ያሉት የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ዣየር ቦልሶናሮ ልጅ ናቸው።

የምርጫው ሁሉም ድምፆች ተቆጥረው ያለቁ ሲሆን ሉላ 51.79 በመቶ ድምፅ አግኝተዋል። ቦልሶናሮ 48.21 ደግሞ በመቶ ማግኘታቸውን የብራዚል ከፍተኛ የምርጫ ፍርድ ቤት አስታውቋል።

የምርጫ ጣቢያዎች ለሁለት ተጨማሪ ሰዓት ክፍት ሆነው መቆየታቸውን "ምክንያቱ የማይታወቅ" ሲሉ የተቹት ቦልሶናሮ ውጤቱን ለመቀበል አሻፈረኝ ብለዋል። ይሁን እንጂ የእሳቸውም ሆነ የተቀናቃኛቸው የምርጫ ዘመቻ ቡድኖች ጣቢያዎቹ ለተጨማሪ ጊዜ ክፍት ሆነው እንዲቆዩ ጠይቀው እንደነበር ታውቋል።

ቦልሶናሮ በዋና ከተማዋ ብራዚሊያ ለደጋፊዎቻቸው ሲናገሩ ምርጫው እንዲሰረዝ ጥያቄ እንደሚያቀርቡ አመልክተዋል።

ይህ አቤቱታቸው ግን ውጤቱን "ታሪካዊ ድል" እና ያልተጠበቀ የድምፅ ለውጥ የታየበት ሲሉ የገለፁትን ሉላ እና ደጋፊዎቻቸው ደስታቸውን ከመግለፅ አላገዳቸውም።

ሉላ በፕሬዚደንታዊ ምርጫ ሲያሸንፉ የአሁኑ አራተኛቸው ነው። እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከአውሮፓውያኑ ጥር 2003 እስከ ታኅሣሥ 2010 ድረስ ለሁለት የሥልጣን ዘመናት አገልግለዋል። ከዚያም በጥር 2023 እንደገና ወደ መሪነት ተመልሰዋል።

ሆኖም እሁድ በተካሄደው የመጨረሻ ዙር ምርጫ ለድል የበቁት አልጋ በአልጋ በሆነ መንገድ ተጉዘው አይደለም።

እአአ ጥቅምት 4 በተካሄደው የመጀመሪያ ዙር ምርጫ ቦልሶናሮ ሉላን መርታታቸውን ተከትሎ ብዙዎች ሉላ በሦስት ሳምንታት ውስጥ ውጤቱን ቀልብሰው ማሸነፍ ይችላሉ የሚል እምነት አልነበራቸውም።

የሉላ በድጋሚ ማሸነፍ፣ መራጮች በሥልጣን ላይ የነበሩ መሪዎችን እየቀጡ ወደ ቀኝ ዘመም መሪዎች ፊታቸውን ያዞሩበትን የላቲን አሜሪካ አገራት አዝማሚያም የተቃረነ ሆኗል። እንደ አርጀንቲና፣ ቺሊ እና ኮሎምቢያ ያሉ የአህጉሪቱ ትልልቅ አገሮች አሁን ላይ በወግ አጥባቂ መሪዎች እየተመሩ ነው።

የግራ ዘመሙ የሉላ የምርጫ ዘመቻ ግን፣ በጎዳና ላይ ሰልፎች እና በማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻዎች ተፅዕኖ በመጀመሪያው ዙር ከተሸነፉ በኋላ፣ ዳግም ሕይወት ዘርቶ ተቀስቅሷል።

የቀድሞው የብረታ ብረት ሠራተኛ ሉላ፣ እአአ በ1989 ጀምሮ ለፕሬዚደንትነት ከተወዳደሩበት ጊዜ ጀምሮ በብራዚል ግራ ፖለቲካ ዋነኛ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰው ሆነው ቆይተዋል። ሆኖም በ2003 ለመጀመሪያ ጊዜ ሥልጣን ከያዙ በኋላ ከገጠሟቸው ፈተናዎች ሁሉ ከባድ የሆነ የፖለቲካ ሁኔታ ከፊታቸው ይጠብቃቸዋል።

አዲሱ የስልጣን ዘመናቸው በአውሮፓውያኑ ጥር 5/2027 የሚጀምር ሲሆን፣ ከአሜሪካ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ የሚገጥማቸውን ጨምሮ በበርካታ የአገር ውስጥ እና የውጭ ጫናዎች ታጅቦ እንደሚቀጥል ይታመናል።

በምርጫው ትራምፕ የሉላን ተቀናቃኝ ፍላቪዮ ቦልሶናሮን በቀጥታ ባይደግፉም፣ በኮሎምቢያና በሆንዱራስ በተካሄዱ ፕሬዚደንታዊ ምርጫዎች ያሸነፉ የቀኝ ዘመም እጩዎችን ግን ሲደግፉ ነበር።

ይሁን እንጂ አስተዳደራቸው፣ 213 ሚሊዮን ሕዝብ ባላት ብራዚል ውስጥ ወግ አጥባቂ መሪ ሥልጣን ይዞ ማየትን እንደሚመርጥ ብዙም ጥርጥር የለውም።

ዋይት ሐውስ ላቲን አሜሪካን በአሜሪካ ተጽዕኖ ሥር ያለ ቀጣና አድርጎ የሚመለከት ሲሆን፣ የትራምፕ አስተዳደርም በመከላከያ፣ በደኅንነት እና በንግድ ጉዳዮች የአሜሪካ ፖሊሲዎችን የሚደግፉ መሪዎች ሥልጣን እንዲይዙ ፍላጎት አለው።

ይህ ለአሜሪካ ከሚኖረው ፋይዳ በተጨማሪ ቻይና በምዕራባዊ ንፍቀ ክበብ ያላትን ተፅዕኖ ለመቀነስ እንደሚረዳም አሜሪካ ታምናለች።

በነዳጅ ሀብት የበለጸገችው እና ውድና አነስተኛ መጠን ያላቸው ንጥረ-ነገሮች ስብስብ በሆኑ ብርቅዬ ማዕድናት ክምችት በዓለም ሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ብራዚል፣ በደቡብ አሜሪካ ከሚገኙ ትልልቅ ሀገራት መካከል በቀኝ ዘመም መሪ የማትተዳደር ብቸኛዋ ሀገር ናት።

ግራ ዘመሙ ፕሬዚደንት ሉላ በአንጻራዊነት ለቻይና ወዳጅነት ያላቸው መሪ ተደርገው ይወሰዳሉ።

ፍላቪዮ ቦልሶናሮ ብራዚል ከዋሽንግተን ጋር የበለጠ መቀራረብ እንዲኖራት እንደሚሰሩ ቃል ገብተው የነበረ ሲሆን ሉላ ደግሞ አሜሪካ በምርጫው ጣልቃ እንዳትገባ አስጠንቅቀዋል።

የሉላ ማሸነፍ ዋይት ሐውስን ቅር ሊያሰኝ ቢችልም፣ ቦልሶናሮ ቢያሸንፉ ኖሮ የብራዚል እርሻ እና የማዕድን ዘርፎች በከባቢ አየር ላይ ተፅዕኖ ሊፈጥሩ በሚችሉ መንገዶች ይቀጥላሉ የሚል ስጋት ያላቸው የከባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች ግን በደስታ የሚቀበሉት ነው።

በቦልሶናሮ አባት ዣይር ቦልሶናሮ የፕሬዚዳንትነት ዘመን በአማዞን ደን ውስጥ የተመዘገቡትን ከፍተኛ የደን ጭፍጨፋና የደን ቃጠሎ መጠኖች በማሳያነት የሚጠቅሱ የከባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች፣ በወጣቱ ቦልሶናሮ አመራር ስር ይህ ሁኔታ ተባብሶ ይቀጥላል የሚል ፍርሃት እንደነበራቸው ገልፀዋል።

የሉላ ደጋፊዎች በድሉ ደስታቸውን እየገለፁ ቢሆኑም፣ በሌላ በኩል ተቀናቃኛቸው ቦልሶናሮ ከ48 በመቶ በላይ ድምፅ ማግኘታቸው በአገሪቱ ስር የሰደደ ልዩነት መኖሩን እንደሚያመለክት ተገልጿል። ይህም የቀኝ ዘመሞች የበላይነት ካለው የአገሪቱ ፓርላማ ጋር ተዳምሮ ለሉላ ቀጣይ ፈተና ይደቅንባቸዋል ተብሏል።