ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፈረንሳይ በመላው አገሪቱ የሚገኙ ሱፐርማርኬቶች ማቀዝቀዣ ላይ ለተፈጸመው የሳይበር ጥቃት ኢራንን ከሰሰች
ፈረንሳይ ባለፈው ወር በመላው አገሪቱ በሚገኙ ሱፐርማርኬቶች የማቀዝቀዣዎች (ፍሪጅ) የሙቀት መጠንን ከፍ በማድረግ ምግብ እንዲበላሽ ላደረገው የሳይበር ጥቃት፣ የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብን ተጠያቂ አደረገች።
የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዦን ኖኤል ባሮ፣ ጥቃቱ "በመጠኑም ሆነ ባደረሰው የጥቃት ደረጃ ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ" መሆኑን ገልጸዋል። ለድርጊቱ ተጠያቂ የሆኑት አካላት ማዕቀብ እንደሚጣልባቸውም ተናግረዋል።
ኢራን እስካሁን ስለቀረበባት ክስ ይፋዊ ምላሽ ባትሰጥም፣ አንዳንድ የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ውንጀላውን መሠረተ የለሽ ሲሉ ውድቅ አድርገውታል።
በፈረንሳይ በሺህዎች ቶን የሚቆጠሩ የቀዘቀዙ እና ትኩስ ምግቦች እንዲበላሹ ምክንያት ከሆነው ከዚህ የሳይበር ጥቃት በኋላ ሌሎች የአውሮፓ አገራት ሱፐርማርኬቶች ላይም ተመሳሳይ ጥቃት ደርሷል። ክስተቶቹ ተያያዥነት ያላቸው እንደሆን ግን አልታወቀም።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ባሮ፣ በፈረንሳይ ሱፐርማርኬቶች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት፣ "የሀገራችን ግዛት ላይ ጥፋት ለማድረስ ያለመ የመጀመሪያው መጠነ ሰፊ የሳይበር ጥቃት" ሲሉ ገልጸውታል።
"በብሔራዊ ጥቅማችን እና በፈረንሳይ ሕዝብ ደኅንነት ላይ የተቃጣ ከባድ ጥቃት ነው" ሲሉም መንግሥታቸው እንዴት እንደሚመለከተው አስረድተዋል።
የአገሪቱ መንግሥት "ይህንን ከባድ ድርጊት በተመለከተ እጅግ ጠንካራ ተቃውሞውን ለመግለጽ" በፓሪስ የሚገኙትን የኢራን አምባሳደር መጥራቱን ተናግረዋል።
ፈረንሳይ ለዚህ ጥቃት ምላሽ ለመስጠት እና "ድርጊቱን ለመድገም የሚያስብ ማንኛውንም አካል ለመከላከል ስትል የትኛውንም አስፈላጊ እና ተመጣጣኝ እርምጃ" እንደምትወስድ አክለዋል።
የፓሪስ አቃቤ ሕግ በበኩላቸው ከኢራን አብዮታዊ ዘብ ጋር ግንኙነት ባለቸው የሳይበር ጥቃት ክፍል ኃላፊ እና በሁለት ምክትሎቻቸው ላይ ምርመራ መከፈቱን አስታውቀዋል።
የሳይበር ጥቃት ክፍሉን 'ሻሂድ ካቬህ' ሲሉ የጠሩት አቃቤ ሕጉ ላውር ቤኩዋው፣ ክፍሉ ከኢራን አብዮታዊ ዘብ የኤሌክትሮኒክስ እና የሳይበር ማዕከል ጋር ግንኙነት እንዳለው አብራርተዋል።
'ሻሂድ ካቬህ' በኢራን መንግሥት በቀጥታ ተቀጥረዋል ተብለው ለሚታመኑ የጠላፊዎች ስብስብ የተሰጠ ስም ነው።
ባለፉት ሳምንታት በኢራን የሚገኙ በርካታ ተንታኞች እንዲሁም ፖለቲከኞች አሜሪካ እና እስራኤል ባለፈው የካቲት ላይ የጀመሩትን ጦርነት እንደገና የሚጀምሩ ከሆነ፣ ቴህራን የምትወስደው ማንኛውንም የአጸፋ እርምጃ ከመካከለኛው ምሥራቅ የሚሻገር መሆን እንዳለበት ሲከራከሩ ነበር።
የኢራን አብዮታዊ ዘብ ይህንን ጥቃት ስለማድረሱ እንዲሁም የሳይበር ጥቃት የኢራን የመከላከል ስትራቴጂ አካል ስለመሆኑ እስካሁን ግልጽ አይደለም።
ጠላፊዎች በጥቅምት መጀመሪያ በበርካታ የፈረንሳይ ሱፐርማርኬቶች ውስጥ የሚገኙ የማቀዝቀዣ ክፍሎችን የሙቀት መጠን የሚቆጣጠረውን ሶፍትዌር ተቆጣጥረው ነበር።
በዚህ ጠለፋ ከ100 በላይ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ሱፐርማርኬቶች እንዲሁም 180 የኢንተርማርሼ እና የኔቶ ብራንድ መደብሮችም ተጠቅተዋል።
በአንዳንድ መደብሮች ውስጥ የማቀዝቀዣዎች የሙቀት መጠን በአንድ ሌሊት ወደ 50 ዲግሪ ሴልሺየስ ከፍ ማለቱ ተዘግቧል።
ካርፉር፣ ሞኖፕሪክስ እና ኤል.ኤክሌርክ ጨምሮ ሌሎች ዋነኛ የምግብ ችርቻሮ ሽያጭ ተቋማትም በዴንማርኩ የምህንድስና ኩባንያ 'ዳንፎስ' በሚቀርበው ሶፍትዌር ላይ የተቃጣው ጥቃት ደርሶባቸዋል።
ይህ ሶፍትዌር ግዙፍ የችርቻሮ ንግድ ተቋማት የማቀዝቀዣ ክፍሎቻቸውን ከሩቁ እንዲቆጣጠሩ የሚያስችል ነው።
ባለፈው ሳምንት በተከሰተው ሁለተኛ ዙር ጠለፋ ደግሞ በመላው አውሮፓ ከ100 በላይ መደብሮችን ተጠቅተዋል።
በዚህ ጥቃት ቤልጂየም እና ሉክሰምበርግ ውስጥ የሚገኙ ሱፐርማርኬቶች የተጎዱ ሲሆን ስዊድን፣ አየርላንድ፣ ኔዘርላንድስ፣ ኢስቶኒያ እና ፊንላንድን ጨምሮ በሌሎች አገራት ያሉ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ሱቆችም ጥቃቱ ደርሶባቸዋል።