በፖላንድ በተፈጸመ ጥቃት 6 ሰዎች ሲገደሉ በአጥቂው ቤት 3 ተጨማሪ አስከሬኖች ተገኙ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በፖላንድ ሁለተኛዋ ትልቅ ከተማ ክራኮው ጽንፈኛ የፖለቲካ አመለካከት እንዳለው በሚጠረጠር አንድ ግለሰብ በተፈጸመ ጥቃት 6 ሰዎችን ሲገደሉ 16 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸው ተገለጸ።

ጥቃቱ የተፈጸመው ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ በክራኮው ታሪካዊ የገበያ ሥፍራ ውስጥ ነው።

የጸረ ሽብር ፖሊስ የተጠርጣሪውን ቤት ሲፈትሽ ተጨማሪ ሦስት አስከሬኖች ማግኘቱን አስታውቋል።

ፖሊስ እንደገለጸው ተጠርጣሪው በመኪና ወደ ተጨናነቀው አካባቢ በመግባት በዘፈቀደ በሰዎች ላይ ተኩስ ከፍቷል።

ከተገደሉት መካከል አራት ሴቶች እና ሁለት ወንዶች ይገኙበታል። ሦስቱ የፖላንድ ዜጎች ሲሆኑ፣ አንዱ የብሪታንያ ዜጋ ነው ተብሏል። የቀሩት ሁለቱ ተጎጂዎች ማንነት ግን እስካሁን አልታወቀም።

ከ16ቱ ቁስለኞች መካከል ሁለት ፖሊሶች እና ከኦስትሪያ፣ ጀርመን፣ ፖርቹጋል፣ ሩሲያ እና ብሪታንያ የመጡ የውጭ ዜጎች ይገኙበታል። ከፖሊሶቹ አንዱ ከባድ ጉዳት እንደደረሰበት ተገልጿል።

የ25 ዓመት ዕድሜ ያለው ፖላንዳዊው ተጠርጣሪ ከፖሊስ ጋር የተኩስ ልውውጥ ካደረገ በኋላ ተይዟል። እሱም በተኩስ ልውውጡ ወቅት ተጎድቶ ወደ ሆስፒታል የተወሰደ ሲሆን፣ የቀዶ ሕክምና ተደርጎለታል።

የፖላንድ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ማርሲን ኪየርቪንስኪ እስካሁን ድረስ የተሰበሰቡት ማስረጃዎች ጥቃት ፈጻሚው በቀኝ ጽንፈኛ አስተሳሰብ ተጽዕኖ ሥር እንደነበረ እና እጅግ የተጋነነ ብሔርተኛ አመለካከት እንደነበረው እንደሚያሳዩ ተናግረዋል። ፖሊስም ተጠርጣሪው ብቻውን ወንጀሉን ስለመፈጸሙ የመጀመርያ ደረጃ የምርመራ ውጤቱ እንደሚያሳይ ገልጿል።

በሌላ በኩል ከክራኮው 200 ኪሎሜትር ያህል ርቀት ላይ በምትገኘው ኦስትሮቪየች ሽቪየንቶክሺስኪ ውስጥ በተጠርጣሪው መኖሪያ ቤት ሦስት ተጨማሪ አስከሬኖች ተገኝተዋል።

የፖላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ቱስክ እንደተናገሩት፣ ሁለት ሴቶችና አንድ ወንድ ተጎጂዎች የተጠርጣሪው የቅርብ ቤተሰብ አባላት እንደሆኑ ይታመናል። የሞታቸው ሁኔታ በዝርዝር ለማጣራት ምርመራ ቀጥሏል።

ከጥቃቱ በኋላ የፖላንድ ባለሥልጣናት የጸጥታ ጥበቃን አጠናክረዋል። የክራኮው ከተማም ለተጎጂዎች የሐዘን ጊዜ ማወጇ ተገልጿል።

የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር አንዲ በርንሃም በክራኮው ከተማ በተፈጸመው አሰቃቂ ጥቃት መደንገጣቸውንና ጥልቅ ሐዘን እንደተሰማቸው ገልጸዋል።

"ሕይወታቸውን ላጡት ሰዎች ቤተሰቦች፣ ለተጎዱት ሁሉ እና በዚህ ኢ ሰብዓዊ ጥቃት ስለተጎዱ ሁሉ አስባለሁ። ዩናይትድ ኪንግደም ከፖላንድ ሕዝብ ጎን ትቆማለች" ሲሉም አክለዋል።

ስሙ ይፋ ያልሆነው አጥቂ፣ ጥቃቱን በፈጸመበት ወቅት ሙሉ ወታደራዊ የውጊያ ትጥቅ ለብሶ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፣ በእጁም ወታደሮች የሚጠቀሙበት መሣሪያ እንደነበረ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል። ሆኖም መንግሥት ተጠርጣሪው የፖላንድ የጦር ኃይል አባል እንዳልነበረ ገልጿል።

ተጠርጣሪው በሚጠቀምበት መኪና ውስጥም ተጨማሪ መሣሪያዎችና ጥይቶች መገኘታቸው ተገልጿል።

የፖላንድ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ማርሲን ኪየርቪንስኪ "ሁሉም ማስረጃዎች ተጠርጣሪው በቀኝ ጽንፈኛ አስተሳሰቦች ተማርኮ እንደነበር" በማለት ተጠርጣሪው "እጅግ የተጋነነ ብሔርተኛ አመለካከት" እንደነበረውም ገልጸዋል።

የፖላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ቱስክ በበኩላቸው፣ የጥቃቱን ፈጻሚ ሊደግፉ የሚችሉ ማናቸውም ግለሰቦች እንደሚታሰሩ ተናግረው፣ ስለ ጉዳዩ ጠቃሚ መረጃ ያለው ሰው ለባለሥልጣናት እንዲያሳውቅ ጥሪ አቅርበዋል።

የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ፖሊሲ ኃላፊ ካያ ካላስ፣ በፖላንድ ክራኮው ከተማ የተፈጸመውን ጥቃት "ከፖላንድ ድንበር አልፎ የሚሰማ አሳዛኝ አደጋ" ሲሉ ገልጸውታል።

የብሪታንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኤድ ሚሊባንድ በበኩላቸው፣ የዩኬ መንግሥት በዚህ "አሰቃቂ ጥቃት" ሕይወታቸውን ላጡ ሰዎች "ጥልቅ ሐዘን" እንደተሰማው በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ገልጸዋል።

"ለተጎጂዎቹ ቤተሰቦች ሁሉ ከልብ የመነጨ ሐዘኔን እገልጻለሁ" ሲሉም አክለዋል።